ከኢትዮጵያ እስከ ኢራን - የእስራኤሉ የስለላ መሥሪያ ቤት ሞሳድ ‘ኦፕሬሽኖች’

ኻሊድ ሜሻል [ግራ]፣ ያህያ አያሽ [መሐል] እና ጭምብል ያጠለቀ የእስራኤል ሰላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኻሊድ ሜሻል [ግራ]፣ ያህያ አያሽ [መሐል] እና ጭምብል ያጠለቀ የእስራኤል ሰላይ

እስራኤል በባለፉት ስድስት ቀናት በኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች፣ ወታደራዊ ተቋማት እንዲሁም የመኖሪያ ስፍራዎች ላይ ያልተቋረጠ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች።

አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል እንዲሁም በመዲናዋ ቴህራን ውስጥ ነው።

በኢራን ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች የአየር ላይ ቢሆኑም የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ ዒላማዎችን በማመላከት እንዲሁም ጥቃቶችን ከመሬት ላይ ሆኖ በመምራት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ተብሎ ይጠረጠራል።

የሞሳድ ወኪሎች የኢራንን የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን ለማጥቃት ወደ ኢራን በድብቅ የገቡ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ተጠቅመዋል ተብሎ ይታመናል።

ከዚህ ቀደም የኢራን ባለሥልጣናትም ቢሆኑ የፀጥታ ኃይላቸው የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሠራተኞች ሰርገው ገብተውበታል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረው ነበር።

እስራኤል ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በፈጸመችው ጥቃት ቁልፍ የሚባሉ የኢራን የጦር አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸው እስራኤል ያሉበትን ትክክለኛ ቦታ በተመለከተ መረጃ እንዳላት የሚያሳይ ነው።

ሞሳድ በእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ ያለውን ሚና እስራኤል ስለስለላ ድርጅቱ እንቅስቃሴ ምንም አስተያየት ስለማትሰጥ መገምገሙ ቀላል አይሆንም።

ሆኖም የደኅንነት ተቋሙ ከዚህ ቀደም ያቀነባበራቸው ግድያዎች እንዲሁም የፈጸማቸው 'ኦፕሬሽኖች' የሚከተሉት ናቸው።

የሐማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒያ ግድያ

እስማኤል ሃኒያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሐማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒያ ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም. በኢራኗ መዲና ቴህራን በአንድ የእንግዳ ማረፊያ ቤት ውስጥ ሳሉ ተገድለዋል። እስማኤል የተገደሉት ከአንድ ጠባቂያቸው ጋር ነበር።

እስራኤል መጀመሪያ ላይ ለመሪው ግድያ ኃላፊነቱን አልወሰደችም ነበር። ነገር ግን ከወራት በኋላ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ከሃኒያ ግድያ ጀርባ አገራቸው እንዳለች አምነዋል።

ሆኖም በሐማስ መሪ እስማኤል ሃኒያ ግድያ ዙሪያ በርካታ ያልጠሩ ነገሮች አሉ።

የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኻሊል አል ሃያ አብረዋቸው የነበሩ የዓይን እማኞችን ዋቢ አደርገው እንደተናገሩት እስማኤል ሃኒያ በቀጥታ በተነጣጠረባቸው ሚሳዔል እንደተመቱ ነው።

በሌላ በኩል ኒውዮርክ ታይምስ ሰባት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የሐማሱ የፖለቲካ መሪ የተገደሉት ከሁለት ወራት በፊት በድብቅ ወደሚኖሩበት ሕንጻ ውስጥ በገባ ቦምብ ነው።

ቢቢሲ የሐማሱ መሪ ግድያን በተመለከተ የሚባሉ ጉዳዮችን ማረጋገጥ አልቻለም።

አልጀዚራን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ የእስራኤል ዘመናትን ያስቆጠረ ወረራ፣ መዋቅራዊ ጭቆና፣ የፍልስጤምን የነጻነት እንቅስቃሴን በተመለከተ በመናገር የሚታወቁት እና የሐማስ መለያ የነበሩት የ62 ዓመቱ ኢስማኤል ሃኒያ ወደ ኢራን ያቀኑት በአዲሱ ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ላይ ለመታደም ነበር።

እስራኤል ለመግደል ስታድናቸው የነበረው ሃኒያን ብቻ ሳይሆን ቤተሰባቸውንም ጭምር ነው። ከዚህ ቀደም በሰሜን ጋዛ ሻቲ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አስር ቤተሰቦቻቸውን ገድላለች።

በዚያን ወቅትም የጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት ከመስከረም 2016 ዓ.ም. መጨረሻ በኋላ 60 የሚሆኑ የቤተሰብ አባሎቻቸው ተገድለውብኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በሚያዝያ ወር ሦስቱ ልጆቻቸው እና አራት የልጅ ልጆቻቸውም በጋዛ ሻቲ ካምፕ መኪና ውስጥ ሳሉ በእስራኤል ቦምብ ጥቃት ተገድለዋል።

እስራኤል ሐማስን እንዲሁም የሐማስን አመራሮች ለማጥፋት በተደጋጋሚ ስትዝት ቆይታለች።

ሃኒያ እንዲሁም የሐማስ መሥራች እና መንፈሳዊ መሪ የሆኑትን ሼክ አህመድ ያሲን በአውሮፓውያኑ 2003 ከእስራኤል የግድያ ሙከራ ተርፈዋል።

ሐማስ ከዓመት በፊት መስከረም መጨረሻ ላይ በእስራኤል ላይ ከፈጸመው ጥቃት በኋላ እስራኤል በጋዛ የሚገኘው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር፣ ወንድሙ መሀመድ ሲንዋር፣ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ኃላፊ መሐመድ ዴይፍ እና ምክትሉ ማርዋን ኢሳን ገድላለች።

የሔዝቦላህ አባላት 'ፔጀሮች' ፍንዳታ

በፔጀር ፍንዳታ ምክንያት የሞተው የሄዝቦላህ ታጣቂ የሆነው ሁሴን አምሀዝ የቀብር ሥነ-ሥርዓት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፔጀር ፍንዳታ ምክንያት የሞተው የሄዝቦላህ ታጣቂ የሆነው ሁሴን አምሀዝ የቀብር ሥነ-ሥርዓት

በዚህ ዓመት መጀመሪያ መስከረም ላይ የሔዝቦላህ አባላት መረጃ ለመለዋወጥ የሚጠቀሙባቸው በእጅ የሚያዙ ፔጀሮች በአብዛኛው ጠንካራ የሔዝቦላህ ይዞታ የሚባሉ ስፍራዎችን ጨምሮ በመላው ሊባኖስ ፈነዱ።

ፍንዳታዎቹ የያዟቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያቸው ያሉ ሌሎች ሰዎችንም ገድለው፣ እንዲሁም አቁስለው ግራ መጋባት እና ሽብርን ፈጥረዋል።

በቀጣዩ ዕለትም ዋኪ ቶኪ የሚባሉ ገመድ አልባ ስልኮች ፈንድተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ ጎድተዋል።

ትላልቅ የመገበያያ መደብሮችን ጨምሮ በየስፍራው የፈነዱት ፔጀሮች እና ዋኪ ቶኪዎች በመላው ሊባኖስ ከፍተኛ ድንጋጤን እና ሽብር የፈጠሩ ናቸው።

ሆስፒታሎች በተጎጂዎች የተጨናነቁ ሲሆን፣ በርካቶቹ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ቱርክ ይህንን የእስራኤልን ጥቃት የጦር ወንጀል ሲሉ ጠርተውታል።

በጋዛ የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ ፍልስጤማውያንን የሚደግፈው ሔዝቦላህ እና እስራኤል ግጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ሔዝቦላህ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሁለት ወራት በኋላ አገራቸው ለእነዚህ ፍንዳታዎች ተጠያቂ መሆኗን አምነዋል ሲሉ የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ሁለት የቀድሞ የሞሳድ ወኪሎች የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር አጋር ከሆነው ሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሞሳድ በእነዚህ ዋኪ ቶኪዎች ውስጥ የሚፈነዱ መሳሪያዎችን መቅበራቸውን አረጋግጠዋል።

ሔዝቦላህ ከ10 ዓመት በፊት ከ16 ሺህ በላይ ዋኪ ቶኪዎችን ከሐሰተኛ ድርጅት ሳያውቅ እንደገዛ ወኪሎቹ ገልጸው 5 ሺህ ፔጀሮችንም እንዲሁ ገዝተዋል።

የታዋቂው ኢራናዊ ኒውክሌር ሳይንቲስት ግድያ

በጥይት የተበሳሳ የመኪና መስታወት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከአራት ዓመት በፊት ታዋቂውን የኢራን የኒውክሌር ሳይንቲስት ሞህሸን ፋክሪዛዴህን የጫነ ተሽከርካሪ ከዋና ከተማይቱ ቴህራን በስተምሥራቅ በምትገኘው አብሳርድ ከተማ ተኩስ ተከፈተበት።

የኒውክሌር ሳይንቲስቱ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሚታገዝ የርቀት መቆጣጠሪያ ጠመንጃ ነበር የተገደሉት።

"በሚንቀሳቀስ ዒላማ ላይ ምንም ዓይነት የሰላማዊ ሰዎች ጉዳት ሳይደርስ በዚህ መንገድ ግድያ መፈጸም መሬት ላይ የስለላ መረጃዎችን በጥንቃቄ ማሰባሰብ ይጠይቃል" ሲል የቢቢሲ የፐርሺያ [ፋርስ] ዘጋቢ ጂያር ጎል ጽፏል።

ከዚያ ቀደም ብሎ በአውሮፓውያኑ 2018 ሞሳድ ከወራት በፊት የሰረቃቸው የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን የሚመለከቱ በርካታ ሰነዶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አሳይተው ነበር።

ሞሳድ እነዚህን ሰነዶች ከቴህራን 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ የእቃ ማከማቻ መጋዘን መስረቁ የተገለጸ ሲሆን፣ በኋላም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሩሃኒ ይህንኑ አረጋግጠዋል።

ኔታንያሁ እነዚህን ሰነዶች ባቀረቡበት ጋዜጣዊ መግለጫ "ያልተገለጸ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ፕሮግራም ነው" ካሉ በኋላ አገራቸው የገደለቻቸው የኒውክሌር ሳይንቲስት ሚና ነበራቸው ብለዋል።

ኢራን ከዚያ ቀደም ብላ በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2012 አራት የኒውክሌር ሳይንቲስቶቿን እስራኤል መግደሏን ገልጻለች።

የናዚው አዶልፍ ኤክማን

የናዚ ጀርመን መኮንን የነበረው አዶልፍ ኢኽማን በእስራኤል የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዶልፍ ኢክማን (መነጽር ያደረገው) በእስራኤል የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል

ሞሳድ ከሚታወቅባቸው የስለላ ሥራዎች አንዱ በአውሮፓውያኑ 1960 የናዚ ጀርመን የጦር መኮንን የሆነው አዶልፍ ኢክማንን ከአርጀንቲና አፍኖ ያመጣበት ሴራው አንዱ ነው።

ሆሎኮስት ተብሎ የሚጠራው የአይሁዶች ጭፍጨፋን ካቀናበሩ የናዚ መኮንኖች መካከል አንዱ የሆነው ኢክማን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ማጎሪያዎች አይሁዶች እንዲገደሉ አድርጓል።

በወቅቱ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች በናዚ ጀርመን ተገድለዋል።

ኢክማን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተገባደደ በኋላ በተለያዩ አገራት ሲደበቅ ቆይቶ በስተመጨረሻም መኖሪያውን አርጀንቲና አደረገ።

14 ሰላዮች ያሉት የሞሳድ ቡድን ኢክማንን አፈላልጎ፣ ከደቡብ አሜሪካዊቷ አገር አርጀንቲና አፍኖ ወደ እስራኤል በማምጣት ለፍርድ በማቅረብ በሞት ተቀጥቷል።

የኢንቴቤው ኦፕሬሽን

የኢንቴቤ አውሮፕላን ታጋቾች ከተለቀቁ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢንቴቤ አውሮፕላን ታጋቾች ከሳምንት በኋላ ነው የተለቀቁት

በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ ውስጥ በእስራኤል የስለላ ድርጅት የተካሄደው የኢንቴቤ ኦፕሬሽን ሞሳድ ካከናወናቸው አንዱ ነው።

ሞሳድ የደኅንነት መረጃዎችን ሲያቀርብ የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ደግሞ እጅግ ውስብስቦቹን ተልዕኮ አጠናቅቋል።

ከእስራኤል ቴል አቪቭ በግሪክ አቴንስ በኩል ወደ ፓሪስ እያቀና የነበረው አውሮፕላን ተጠልፎ ነበር ወደ ኡጋንዳ የመጣው።

አውሮፕላኑ 250 መንገደኞች አሳፍሮ የነበረ ሲሆን፣ 103 የሚሆኑት እስራኤላውያን ናቸው።

ሁለት የፍልስጤም ሕዝባዊ ነፃነት ግንባር አባላት እና ሁለት ጀርመናውያን ጠላፊዎቹ አውሮፕላኑ አስገድደው ወደ ኡጋንዳ እንዲያበር አስገደዱት።

አገራትን አቋርጠው የዜጎቻቸውን ሕይወት ለመታደግ የተሰማሩት የእስራኤል ኮማንዶዎች በሞሳድ ድጋፍ ታጋቾቹን ማስለቀቅ ችለዋል።

ይህን የአውሮፕላን ጠለፋ ለማክሸፍ በተወሰደ እርምጃ ሦስት ታጋቾች፣ ጠላፊዎቹ፣ በርካታ የኡጋንዳ ወታደሮች እና የአሁኑ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ወንድም ዮናታን ኔታኒያሁ ተገድለዋል።

ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ መውሰድ

የሞሳድ መኮንን ከሱዳን ወደ እስራኤል ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች የተጫኑበት ክፍት መኪና አጠገብ ቆሞ

የፎቶው ባለመብት, Raffi Berg

የምስሉ መግለጫ, የሞሳድ መኮንን ከሱዳን ወደ እስራኤል ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ጋር

ሌላው ሞሳድ ካከናወናቸው ኦፕሬሽኖች መካከል አንዱ 7 ሺህ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን ከኢትዮጵያ በምሥጢር በማስወጣት በሱዳን በኩል ወደ እስራኤል ለመውሰድ የተደረገው ነው።

ይህ የሆነው በ1980ዎቹ ሲሆን ሞሳድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኼም ቤጊን በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሐሰተኛ ‘የዳይቪንግ ሪዞርት’ (የመዝናኛ ስፍራ) ሽፋንን ተጠቅሞ ቤተ-እስራኤላውያኑን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ማጓጓዝ ችሏል።

ሱዳን በወቅቱ እስራኤል ጠላቴ ነው የምትለው የአረብ ሊግ አባል ነበረች።

የሞሳድ አባላት በሱዳን የቀይ ባሕር ወደብ አካባቢ ሪዞርት አቋቁመው ነበር። ይህ ሪዞርት ለሰላዮቹ እንደ ካምፕ ሆኖ ነበር የሚያገለግለው።

ሰላዮቹ ቀን ቀን የሆቴል ሠራተኛ ሆነው ያገለግላሉ። ማታ ማታ ደግሞ ከኢትዮጵያ በእግራቸው የመጡ አይሁዶችን በድብቅ በአውሮፕላን እና በባሕር ያጓጉዛሉ።

ይህ ኦፕሬሽን ቢያንስ ለአምስት ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ የሰላዮቹ እንቅስቃሴ በተጋለጠበት ወቅት የሞሳድ ቡድን አባላት ሱዳንን ለቅቀው ወጥተው ነበር።

የሙኒክ ኦሊምፒክ አፀፋ

በሙኒክ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሄደው ታግተው የተገደሉ የእስራኤል አትሌቶችና አሰልጣኞች ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሙኒክ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሄደው ታግተው የተገደሉ የእስራኤል አትሌቶችና አሠልጣኞች

በአውሮፓውያኑ 1972 የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ‘ብላክ ሴፕተምበር’ በሙኒክ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ የሄዱ ሁለት የእስራኤል ኦሊምፒክ ቡድን አባላትን ገድሎ ዘጠኙን ደግሞ አገታቸው።

በወቅቱ የምዕራብ ጀርመን ፖሊስ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረት ቢያደርግም ባለመሳካቱ ዘጠኙም ታጋቾች ተገደሉ።

በዚህ ጥቃት ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉትን ለመበቀል ዓላማ የያዘውው ሞሳድ፣ ሞሐመድ ሀምሻሪን ጨምሮ በርካታ የፍልስጤም ነፃ አውጭ ቡድን አባላትን ዒላማ ማድረግ ጀመረ።

ሞሐመድ ሀምሻሪ ፓሪስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ስልክ ላይ በተጠመደ ፈንጂ አማካይነት ተገደለ።

ሀምሻሪ በፍንዳታው አንድ እግሩን ካጣ በኋላ ነው ከቀናት በኋላ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ለሞት የበቃው።

ያህያ አያሽ እና የሚፈነዱት ስልኮች

የያህያ አያሽ ፎቶ ቢልቦርድ ላይ ተሰቅሎ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ያህያ አያሽ የፍልስጤም ነፃነት አርማ ተደርጎ ይቆጠራል

በተመሳሳይ በ1996 በተካሄደ ኦፕሬሽን ያህያ አያሽ የተባለው ለሐማስ ቦምብ የሚሠራው ግለሰብ ሞቶሮላ አልፋ የተሰኘው የግንኙነት ሬዲዮው ላይ በተጠመደ 50 ግራም በሚመዝን ፈንጂ አማካይነት ተገደለ።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪ የነበረው አያሽ ቦምብ በመሥራት ጥበቡ እና የእስራኤል መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ውስብስብ ጥቃቶች አቀነባብሯል ተብሏል።

በዚህ ድርጊቱ ምክንያት ነው በእስራኤል የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ዘንድ እጅግ ተፈላጊው ሰው የሚል መዝገብ ላይ አስፍረውት ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2019 እስራኤል ግድያውን በተመለከተ ደብቃው የነበረውን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ ቻነል 13 የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ አያሽ ከመሞቱ በፊት ከአባቱ ጋር ያደረገውን የስልክ ልውውጥ አስደምጧል።

የአያሽ እና የሀምሻሪ ግድያ የረቀቀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈፀም ግድያ ምሳሌዎች ናቸው።

ታንቆ የተገደለው የሐማሱ ወታደራዊ መሪ

ማሕሙድ አል-ማብሁህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2010 የሐማስ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ የነበረው ማህሙድ አል ማብሁህ በዱባይ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ተገደለ።

መጀመሪያ ላይ ሞቱ ተፈጥሯዊ ቢመስልም ነገር ግን የዱባይ ፖሊሶች የጸጥታ ቪዲዮዎችን ከመረመረ በኋላ በሰዎች መገደሉን ለመለየት ቻለ።

ፖሊስ ቆየት አል ማብሁህ በኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲሁም ከዚያ ታንቆ መገደሉን አጋለጠ።

ግድያው በሞሳድ የተቀነባበረ ነው ተብሎ መጠርጠሩም ጋር ተያይዞ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዘንድ ዲፕሎማሲያዊ ቁጣ ቀስቅሶ ከእስራኤል ጋር ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

የእስራኤል ዲፕሎማቶች በበኩላቸው ሞሳድን ከጥቃቱ ጋር የሚያገናኘው ምንም አይነት ማስረጃ የለም ሲሉ አስተባብለዋል።

ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎች

ምንም እንኳ ሞሳድ በርካታ ኦፕሬሽኖች ቢፈጽምም ታዋቂ የሆኑ ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎችን አካሂዷል።

በአውሮፓውያኑ 1997 እስራኤል የሐማስ ፖለቲካዊ ቢሮ ኃላፊ ኸሊድ ሜሻል ዮርዳኖስ እያሉ በመርዝ ለመግደል ያደረገችው ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ተከስቷል።

የሞሳድ ሰላዮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ እስራኤል ለሜሻል የተሰጠውን መርዝ የሚያረክስ መድኃኒት ለመስጠት ተገዳለች።

በዚህ ሙከራ ሳቢያ በዮርዳኖስ እና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ነበር።

በ2003 እስራኤል በጋዛ ከተማ የሚገኘውን የሐማሱ መሪ ማህሙድ አል-ዛሃርን ቤት በአየር ጥቃት አወደመች። ምንም እንኳ አል-ዛሃር ከጥቃቱ ቢተርፍም ሚስቱ እና ወንድ ልጁ እንዲሁም በርካታ ሰዎች በጥቃቱ ተገደሉ።

ኻሊድ ሜሻል ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኻሊድ ሜሻል በአውሮፓውያኑ ከ1996 እና 2017 የሐማስ መሪ ሆኖ አገልግሏል

የሐማስ ጥቃት

አውሮፓውያኑ ጥቅምት 1973 ግብፅ እና ሶሪያ በሶቪየት ኅብረት ታግዘው እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈታቸው ይታወሳል።

ከ50 ዓመታት በኋላ እስራኤል ድጋሚ ድንገተኛ ጥቃት ተከፈተባት። መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ተነስተው ወደ እስራኤል በመግባት ያልተጠበቀ ጥቃት ፈፀሙ።

ሞሳድ ይህ ከባድ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል ቀድሞ ሊደርስበት አለመቻሉ በአንዳንዶች ዘንድ ወቀሳ እንዲሰነዘርበት እያደረገ ነው።

የእስራኤል ባለሥልጣናት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ባደረሰው ጥቃት1200 ሰዎች ገድሎ ከ250 በላይ የሚሆኑት ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል ይላሉ።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ53 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።

በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ በተደረገው ግምገማ መሰረት በጋዛ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል።

እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ከሶስት ወር እገዳ በኋላ የተወሰነ እርዳታ ጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን በሚባል ድርጅት አማካኝነት እንዲሰራጭ ፈቅዳ ነበር።

ድርጅቱ በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፍ ሲሆን በቅርቡም እርዳታ ሊቀበሉ ወደ ማዕከሉ በተሰባሰቡ ፍልስጤማውያን ላይ የእስራኤል ጦር ተኩስ ተከፍቶ በርካቶች ተገድለዋል።