እስራኤል በኢራን ላይ የከፈተችው ዘመቻ መቋጫው ምን ይሆን?

- ፀሐፊ, ሊዝ ዱሴት
- የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ዘጋቢ
ባለፈው አርብ እስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት በኢራን ከከፈተች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ለኢራናዊያን በቀጥታ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት "ጨካኝ እና ጨቋኝ የሆነውን አገዛዝ" ለመቃወም ጊዜው እንደደረሰ ተናግረዋል። የእስራኤል ወታደራዊ ተልዕኮ "ነፃነታችሁን እንድትቀናጁ መስመር መጥረግ" ነውም ብለዋል።
የእስራኤል እና ኢራን ወታደራዊ ፍጥጫ እየተጋጋለ እና የጥቃቱ መጠን እየሰፋ ባለበት በዚህ ሰዓት ብዙዎች የእስራኤል እውነተኛ የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው? ብለው እየጠየቁ ነው።
በመጀመሪያው የጥቃት ቀን ኔታኒያሁ እንዳሉት "እስላማዊ አገዛዙን የኒውክሌር እና የባላስቲክ ሚሳኤል ስጋት" በቀላሉ መቋጨት ብቻ ነው?
ወይስ የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር መቆጣጠር የሚያስችለውን የቴህራን እና የዋሽንግተንን ንግግር ማደናቀፍ? አሊያ ደግሞ ለኢራናዊያን የነፃነትን መንገድ በመጥረግ የኢራንን ሃይማኖታዊ አገዛዝ እስከ ወዲያኛው የማሰናበትን ግብ ያደረገ ነው?
ጄነራሎችን ወይስ ትራምፕን፡ እነ ማንን ይሰማሉ?
የእስራኤል የረጅም ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር በፖለቲካ ሕይወታቸው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በዓለም ላይ የደቀነውን አደጋ ማስጠንቀቅ የግላቸው ተልዕኮ በማድረግ ይታወቃሉ።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች እና የኔታኒያሁ ጄነራሎች ባለፉት ዓመታት ከአንድ ጊዜ በላይ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዳይፈጸሙ ስለመከልከላቸው ይነገራል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ለተጀመረው ጥቃት ፈቃድ አለመስጠታቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኔታኒያሁ የተሰጣቸው የተጠንቀቅ ቢጫ መብራት ጥቃቱን ለመፈፀም በቂ ሆኖ አግኝተውታል።
አንድ የምዕራባዊያን ባለሥልጣን የእስራኤል ዋነኛ ግብ የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር መስበር እንደሆነ አስምረዋል።
ይህ ውሳኔ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲን ጨምሮ በቀጣናው ባሉ አገራት ሰፊ ውግዘት ገጥሞታል።
የኤጀንሲው ዳይሬክተር ራፋይል ግሮሲ "ዓውዱ ወይም ሁኔታው ምንም ይሁን ምን የኒውክሌር ጣቢያዎች መጠቃት እንደሌለባቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ተናግሪያለሁ" ብለዋል።
ከዚህ ባሻገርም ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ጥቃቱ በዓለም አቀፍ ሕግ ሕገ-ወጥ ነው በሚልም እያወገዙ ነው።
ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ግብ እና የከፍተኛ አማካሪዎቻቸው እና አጋሮቻቸው ግብ አንድ መሆኑን ይጠይቃሉ።
በቻተም ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሳናም ቫኪል "ኔታኒያሁ የአግዛዝ ለውጥ ለማምጣት የግል ፍላጎታቸው ላይ ቢያተኩሩም፤ የእስራኤል የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተቋማት ግን የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር ለመቀልበስ በእጅጉ ቁርጠኛ ናቸው" ይላሉ።
"ሁለተኛው ግብ [የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር ለመቀነስ] ለማሳካት ከባድ ቢሆንም፤ በተወሰነ ደረጃ ሊሳካ ይችላል" የሚሉት ባለሙያዋ፤ "የመጀመሪያው ግን [የአገዛዝ ለውጥ] በአጭር እና በተጋጋለ ግጭት ለማሳካት ፈታኝ ነው" ሲሉ አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር ማውደም
ኔታኒያሁ የእስራኤልን ጥቃት የኅልውና ስጋትን ለመደምሰስ ቅድመ እርምጃ አድርገው ይመለከታሉ። ኒውክሌር ቦምብ ለማበልፀግ የኢራን መገስገስ በእሳቸው አገላለፅ "90ኛ ደቂቃ" ላይ ነው።
ቴህራን መስመሯን እንድታልፍ አይፈቀድላትም የሚለው አቋማቸውን የምዕራባዊያን አጋሮቻቸውም ይደግፉታል። ይሁን እንጂ የኔታኒያሁ ሰዓት በሰፊው ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።
ኢራን በተደጋጋሚ የኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት መወሰኗን አስተባብላለች። ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ዳይሬክተር ቱልሲ ጋባርድ የደኅንነት ባለሟሎች "ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እየገነባች አለመሆኑን ይከታተላሉ" ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ በቅርቡ ባወጣው የሩብ ዓመት ሪፖርቱ ኢራን በቀላሉ ጦር መሳሪያ የሚያሠራ 60 በመቶ የተጣራ የዩራኒየም ክምችት ላይ መድረሷን ወይም ዘጠኝ የኒውክሌር ቦምብ መሥራት የሚያስችል አቅም አላት ብሏል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የኢራን ሰፊ የኒውክሌር መርሐ ግብር ሦስት ቁልፍ ጣቢያዎች ዒላማ ተደርገዋል። እነዚህም ናታንዝ፣ ኢስፋሃን እና ፎርዶው ጣቢያዎች ናቸው።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጄንሲ በናታንዝ ጣቢያ ከመሬት በላይ ያለው የነዳጅ ማቀነባበሪያ መውደሙን ገልጿል።
ኤጀንሲው በኢስፋሃን አራት "ወሳኝ ሕንፃዎች" እንደተጎዱም አስታውቋል።
እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያደረሰችውን ጉዳት "ግዙፍ" ስትል፤ ኢራን በአንፃሩ የተወሰነ ነው ብላለች።
በተጨማሪም እስራኤል "የእውቀት ምንጭ" ያለቻቸውን የኢራን ባለሙያዎች እየገደለች ሲሆን፤ እስካሁን ዘጠኝ የኒውክሌር ተመራማሪዎችን እና በርካታ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችንን ገድላለች።
ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችን፣ የሚሳኤል ማስወንጨፊያ እና ማምረቻዎችን የሚያካትተው የጥቃት ዝርዝር አሁን ወደ ምጣኔ ሀብታዊ እና የነዳጅ ጣቢያዎች ሰፋ ብሏል።
ኢራንም በበኩላ አፃፋዊ እርምጃ እየወሰደች ሲሆን፣ በሁለቱም ወገን የንፁሃን ተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን በኢራን ሰፊ የኒውክሌር መርሐ ግብር ላይ እስራኤል ወሳኝ ጉዳት ለማድረስ ሁለተኛ ግዙፍ እና በእጅጉ ጥበቃ የሚደረግለትን ፎርዶው ጣቢያን መምታት አለባት።
አንዳንድ ባለሙያዎች በተራሮች ሥር በጥልቅ የተገነባው ውስብስብ ጣቢያ፣ ኢራን የጦር መሳሪያ ለመሆን የተቃረበውን አብዛኛውን ዩራኒየም ያከማቸችበት ስፍራ ነው ብለው ያምናሉ።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የወቅቱ ግብ ወደዚህ ጣቢያ የሚወስዱ መንገዶችን መዝጋት ለመሆኑን እየዘገቡ ነው።
እስራኤል ተራሮችን መናድ የሚያስችል መሳሪያ የላትም። ነገር ግን የአሜሪካ አየር ኃይል ይህ መሳሪያ አለው።
'ኤምኦፒ' በመባል የሚታወቀው ይህ መሳሪያ ዒላማዎችን ሰርስሮ መግባት የሚችል ቢሆንም ግዙፍ ጉዳት ለማድረስ ግን ለበርካታ ቀናት ድብደባ ማድረግ አለበት።
የቀድሞ የአሜሪካ ባለሥልጣን እና በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ማዕከል የዓለም አቀፍ ኢነርጂ ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ሪቸርድ ነፊው "ሊከሰት ይችላል ብዬ የማስበው ኔታኒያሁ ወደ ትራምፕ ስልክ ደውለው 'ይህን ሁሉ ሥራ ሠርቻለሁ፤ ቢ-2 ቦምቦች ስጋት እንዳይሆኑ አድርጊያለሁ። ነገር ግን የኒውክሌር መሳሪያ መርሐ ግብሩን ልገታው አልችልም' ይላሉ" ሲሉ ለቢቢቢ ተናግረዋል።
አንድ የምዕራባዊ ባለሥልጣን "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምን እንደሚወስኑ እስካሁን ግልፅ አይደለም" ብለዋል።
የሰላም ንግግርን ለማደናቀፍ ሁነኛ ሰዓት?
ትራምፕ ወዲህ እና ወዲያ ማለታቸውን ቀጥለዋል።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የኒውክሌር ንግግሩን ጥቃት እንዳያደናቅፈው እስራኤል ኢራን ላይ መዛት እንድታቆም ጥሪ አቅርበው ነበር።
የእስራኤል ጥቃት ከጀመረ በኋላ ደግሞ ጥቃቱን በማሞካሸት ከዚህ የከፋ እንደሚመጣ አስጠንቅቀዋል። ጥቃቱ ኢራን እጇ ተጠምዝዞ ወደ ስምምነት ሊያመጣት ይችላል የሚል እምነትም አላቸው።
እሁድ እለት ትሩዝ በተባለው ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው "በቅርቡ በእስራኤል እና ኢራን መካከል ሰላም ይወርዳል። ብዙ የስልክ ልውውጥ እና ስብሰባዎች እየተካሄዱ ነው" ብለዋል።
የኢራን ተደራዳሪዎች በኦማን መዲና መስካት እሁድ ዕለት ሊደረግ ታስቦ የነበረው ንግግር እስራኤል ጥቃት እንደማትፈፅም ቴህራን እንድታምን የተደረገ ማጭበርበሪያ ነው ብለው ይጠረጥራሉ።
አርብ ዕለት በእስራኤል የዘነበባት እሳት ቴህራን ያልጠበቀችው ነው።
ለአንዳንዶችም የጥቃቱ ጊዜ ወሳኝ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓ ምክር ቤት የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ምክትል ኃላፊ የሆኑት ኤሊ ጀርማያ "የእስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር ለመቆጣጠር ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስምምነት የመድረስ ዕድል የገደለ ነው" ይላሉ።
"ምንም እንኳ አንዳንድ የእስራኤል ባለሥልጣናት የጥቃቶቹ አላማ የአሜሪካን የዲፕሎማቲክ ጥረት ለማጠናከር ነው ቢሉም፤ የጥቃቱ ቅፅበት እና ስፋት ሙሉ ለሙሉ ንግግሩን ለማደናቀፍ ያለመ ነው" ሲሉ ያክላሉ።
ስለ ንግግሩ እውቅና ያላቸው ውስጠ አዋቂዎች "ስምምነት ሊደረስ ይችል ነበር" ብለዋል። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ቴህራን "ቀይ መስመር" ካለችው አሜሪካ ከምታቀርበው የኒውክሌር ማበልፀጊያ ከፍተኛ መጠን መቀነስ ላይ የተወሰነ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ከአውሮፓውያኑ 2015 ታሪካዊ ከተባለው ስምምነት መውጣታቸውን ተከትሎ ኢራን ከተቀመጠላት የኒውክሌር ነዳጅ ማምረቻ የ3.67 በመቶ ገደብ አልፋለች።
ሁለተኛ በሆነው በዚህ ሙከራ የአሜሪካ መሪዎች ስምምነት ላይ ለመድረስ ለኢራን በዘርፉ ባለሙያዎች የተገደበ መስኮት የተባለ "የ60 ቀናት" ቀነ ገደብ ሰጥተዋል።
እስራኤል በ61ኛው ቀን ጥቃት ፈፅማለች።
"አሁን ላይ የኦማን መስመር ሞቷል" የሚሉት ዶ/ር ቫኪል፤ "ነገር ግን ውጥረቱን ለማርገብ እና መውጫ መንገድ ለመፈለግ ቀጣናዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ነው" ብለዋል።
የኔታኒያሁ 'ጥቁር ስሜት'
አሁናዊ ውጥረቱ የመሳሪያ ክምችት፣ የዩራኒየም ማጣሪያ እና ሱፐርሶኒክ ሚሳዔል ብቻ አይደለም የሚል ዕይታ በቴህራን በኩል አለ።
በጆን ሆፕኪንስ ትምህርት ቤት ዓለም አቀፍ ጥናት የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሮፌሰር የሆኑት ቫሊ ናስር "እስራኤል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ኢራንን እንደ አገር አቅሟን ለመጣል፣ የወታደራዊ ተቋሞቿን እና በእስራኤል እና ኢራን መካከል ያለውን የኃይል ሚዛን ወሳኝ በሆነ መንገድ ለመቀየር፤ ምናልባትም እስላማዊ ሪፐብሊኩን ሙሉ ለሙሉ ለመጣል ነው" ብለው ይሞግታሉ።
የኢራን ሕዝብ ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጥ ግልፅ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጠንካራ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እና ሥርዓታዊ በሆነ ጥብቅ ቁጥጥር ሥር የተያዘው የኢራን 90 ሚሊዮን ሕዝብ ባለፉት ዓመታት መከራ አሳልፏል።
በዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ እጥረት በመሰሉ ጉዳዮች እና በሥነ-ምግባር ፖሊስ ሴቶች ላይ በሚጣሉ ገደቦች ምክንያት በየዓመቱ ተቃውሞዎች ይቀሰቀሳሉ።
በ2002 የነበረው ማዕበላዊ ተቃውሞ ታላቅ ነፃነት የተጠየቀበት ቢሆንም፤ ከባድ የእስር ምላሽ ነበር የተሰጠው።
የሕዝቡን አቀባበል ግምገማቸውን የሚያጋሩት ፕሮፌሰር ናስር "ምናልባትም መጀመሪያ ላይ ተወዳጅ ያልሆኑ አራት፤ አምስት ጄነራሎች ሲገደሉ [ሕዝቡ] እፎይታ ተሰምቶት ይሆናል። ነገር ግን አሁን መኖሪያ ሕንፃዎቻቸው ሲመቱ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ የአገሪቱ የኃይል እና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች እየተጠቁ ነው" ብለዋል።
"አብዛኛው ኢራናዊያን አገሩ በቦምብ እየተደበደበች ከአጥቂ ጋር የሚወግንበት እና እንደ ነፃነት የሚያይበት ሁኔታ አይታየኝም"።
ነገር ግን የኔታኒያሁ መግለጫ ሰፊ ጥቃት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ፍንጭ ሰጪ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቅዳሜ ዕለት "በአያቶላህ አገዛዝ እያንዳንዱን ስፍራ እና ዒላማን" አገራቸው እንደምትደበድብ አስጠንቅቀዋል።
ኔታኒያሁ እሁድ ዕለት በፎክስ ኒውስ የአገዛዝ ለውጥ የእስራኤል ጦር ጥረት አካል እንደሆነ በግልፅ ተጠይቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በእርግጠኝነት ውጤቱ ይህ ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱም የኢራን አገዛዝ በጣም ደካማ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
እሁድ ምሽት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ምንጮቻቸውን በመጥቀስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል የኢራንን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ለመግደል የያዘውን ዕቅድ እንደሻሩት ዘግበዋል።
ይህን ተከትሎ የእስራኤል ሹማምንት ትኩረታቸው የኢራን የፖለቲካ አመራሮች ላይ አለመሆኑን ወትውተዋል።
በስተመጨረሻም የግጭቱ ፍፃሜ የሚወሰነው በአደገኛ እና ባልተገመተው ፍጥጫ እና አቋማቸው ባልታወቀው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነው።
የቀድሞ የእስራኤል መንግሥት አማካሪ እና የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሮጀክት ፕሬዝዳንት ዳንኤል ሌቪ "በቅርብ ጊዜ ውጤቱን የሚወስን መጨረሻ የሚገኘው በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ነው" ይላሉ።















