ትራምፕ ከቻይናው መሪ ጋር ከተገናኙ በኋላ ታይዋን ነጻነቷን እንዳታውጅ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ታይዋን ከቻይና የተነጠለች ነጻ አገር መሆኗን እንዳታውጅ አስጠነቀቁ።
ትራምፕ አርብ ዕለት በቻይና ቤይጂንግ የሁለት ቀን ይፋዊ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ወቅት "አንድ አካል ነፃ እንዲሆን አልፈልግም" ብለዋል።
ቀደም ሲል የታይዋን ፕሬዝዳንት ላይ ቺንግ-ቴ፣ ታይዋን ራሷን የምትመለከተው እንደ ሉዓላዊ አገር በመሆኑ ነፃነቷን ማወጅ አያስፈልጋትም ብለው ነበር።
አሜሪካ ለበርካታ ዓመታት ታይዋንን ስትደግፍ የቆየች ሲሆን በሕጓም ውስጥ ራሷን መከላከል እንድትችል ድጋፍ ማድረግ እንዳለባት ተቀምጧል።
ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር ያላትን መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጠብቆ መቆየትም ትፈልጋለች።
ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ቻይና የግዛቴ አካል ናት ስለምትላት ስለ ራስ ገዟ ደሴት "በምንም ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጥም" ብለው ነበር።
ዋሺንግተን በይፋ ታይዋን ነጻ አገር መሆኗን እንደማትደግፍ አስታውቃለች። ዩናይትድ ስቴትስ አንድ የቻይና መንግሥት የሚለውን ሃሳብ በመቀበል ከአገሪቱ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማስቀጠል ትፈልጋለች።
ቤይዢንግ ለታይዋኑ ፕሬዚዳንት ያላትን ጥላቻ በግልጽ የምትናገር ሲሆን ከዚህ ቀደም "በጥባጭ" እንዲሁም "በሁለቱ ወገን ያለውን ሰላም አደፍራሽ" ስትል ገልጻዋለች።
በርካታ ታይዋናውያን ነጻ አገር እንደሆኑ ቢያስቡም አብዛኛዎቹ ነጻ አገር መሆናቸውን ሳያውጁ፣ ከቻይና ጋር ሳይዋሃዱም ያላቸውን ግንኙነት ግን አስጠብቀው መቀጠል ይፈልጋሉ።
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት በዚህ ጉዳይ የአሜሪካ አቋም አለመቀየሩን ተናግረዋል።
"ታውቃለሁ ጦርነትም ለመዋጋት 15,289 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንዳለብን። ያንን አልፈልግም። እንዲረጋጉ ነው የምፈልገው። ቻይና እንድትረጋጋ ነው የምፈልገው።"
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በቻእና የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቅቀው ሲመለሱ ለጋዜጠኞች ከፕሬዚዳንት ዢ ጋር በደሴቲቱ ዙሪኣ "ብዙ" መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን አሜሪካ ትከላከላት አንደሆነ ግን ለመነጋገር አለመፈለጋቸውን አስታውቀዋል።
ዢ ስለደሴቲቱ "በጣም ይጨነቃል" እንዲሁም "የነጻነት አንቅስቃሴ ማየት አይፈልግም" ብለዋል።
የቻይና መገናኛ ብዙኃን "የታይዋን ጥያቄ በቻይና እና አሜሪካ ግንኙነት ውስጥ በጣም አስፈላጊው ጥያቄ ነው" ሲሉ ዢ አስጠንቅቀዋል። አክለውም "በተገቢው መንግድ ካልተያዘ ሁለቱ አገራት ሊጋጩ ወይም ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ" ማለታቸውን ጠቅሰዋል።
ትራምፕ በታይዋን ጉዳይ ከቻይና ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል ብለው ያስቡ እንደሆን ተጠይቀው "አይመስለኝም። ነገሮች ጥሩ የሚሆኑ ይመስለኛል። [ዢ] ጦርነት ማየት አይፈልግም" ሲሉ መልሰዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቻይና በደሴቲቱ ዙሪያ ወታደራዊ ልምምዶችን ያደረገች ሲሆን ይህም በቀጣናው ውጥረትን ከመፍጠር ባሻገር የዋሺንግተንን አቋም ፈትኗል።
ባለፈው ዓመት የትራምፕ አስተዳደር ለታይዋን የተሻሻሉ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና የተለያዩ ሚሳዔሎችን ያካተተ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ሊሸጥ መሆኑን ሲያስታውቅ ቤይጂንግ ተቃውማለች።
ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ከቻይናው አቻቸው ጋር "በዝርዝር" መወያየታቸውን ጠቅሰው በቅርቡ ሽያጩ ላይ ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
አክለውም "ማለት የምችለው አሁን በቀጥታ አነጋግረዋለሁ፤ ታውቃለህ፣ ታይዋንን እያስተዳደረ ያለው ማን እንደሆነ ታውቃለህ" በማለት የፕሬዚዳንቱን ስም ሳይጠሩ ተናግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ከታይዋን ጋር መደበኛ የሆነ ግንኙነት የሌላት ቢሆንም ይፋዊ ያልሆኑ ግንኙነቶችን ግን ስታካሄድ ቆይታለች።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በቀጥታ የታይዋንን ፕሬዚዳንት የማያነጋግሩ ሲሆን ይህንን ቢያደርጉ ግን ከቤይጂንግ ጋር ውጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል።
ቻይና የታይዋኑን ፕሬዚዳንት ላይ ቺንግ-ቴን ተገንጣይ ስትል ነው የምትጠራቸው።
የታይዋን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቼን ሚንግ-ቺ ቅዳሜ ዕለት ታይዋን ትራምፕ ምን ማለታቸው እንደሆነ ማብራሪያ ትፈልጋለች ብለዋል።
ቼን አክለውም አሜሪካ ለታይዋን የምትሸጠው የጦር መሣሪያ በአሜሪካ ሕግ ድጋፍ ያለው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "የታይዋን እና አሜሪካ የመሣሪያ ሽያጭ ሁልጊዜ የቀጣናው ሰላምና መረጋጋት መሠረት ነበር" ብለዋል።
ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ "ጦርነት ማየት አንፈልግም፤ አሁን ባለው መልኩ ከቀጠልን ቻይና የሚስማማት ይመስለኛል። ነገር ግን የሆነ አካል ተነስቶ 'አሜሪካ ስለምትደግፈን ነጻ አገር እንሁን' እንዲል አንፈልግም" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አሜሪካ በታይዋን ነጻነት ላይ ባላት አቋም መለሳለስ አሳይታ ቻይናን አስቆትታ ነበር።
እአአ በየካቲት 2025 የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድረገጹ ላይ የታይዋንን ነጻ አገርነት እንደሚቃወም የሚገልጸውን ሐረግ በማንሳቱ ቤይጂንግ "ለተገንጣይ ኃይሎች ያልተገባ መልዕክት ያስተላልፋል" ስትል ተቃውማው ነበር።
በወቅቱ በታይዋን የሚገኙ የአሜሪካ ባለሥልጣናት "ከሁለቱም ወገን ያለውን ሁኔታ ለመቀየር በተናጠል የሚደረግ እርምጃን አንደምንቃወም ለረዥም ጊዜ ስንነናገር ነበር" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።














