ጃፓን ከታይዋን አቅራቢያ በሚገኘው ደሴቷ ሚሳዔሎችን ልታሰፍር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቻይና ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገባችው ጃፓን፤ ከአምስት ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2031 ከታይዋን አቅራቢያ በሚገኘው ራቅ ያለ ምዕራባዊ ደሴት ላይ ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፍ ሚሳዔል ለማስፈር ማቀዷን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጃፓን፤ ዮናጉኒ በተባለው ደሴት ላይ ሚሳዔሎቿን እንደምታሰማራ ይፋ ካደረገችበት አውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ይህንን ዕቅዷን መቼ እንደምትፈጽም የተቆረጠ ቀን ስታስቀምጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ራስ ገዟን ታይዋን እንደ ግዛት አካሏ አድርጋ የምትቆጥረው ቻይና፤ ደሴቷን "መልሳ ለማዋሃድ" ኃይል የመጠቀም ሐሳብን ከጠረጴዛው ውጪ አላደረገችም።
ዮናጉኒ የተባለው የጃፓን ደሴት ከታይዋን የባሕር ዳርቻዎች ያለው ርቀት የ110 ኪሎ ሜትር ሲሆን ጥርት ባለ ቀንም ከደሴቱ ቆሞ ታይዋንን መመልከት ይቻላል።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ፤ ታይዋን ላይ ጥቃት የሚከፈት ከሆነ አገራቸው ራስን የመከላከል ኃይሏን እንደምታንቀሳቅስ ባለፈው ኅዳር ላይ ከተናገሩ ወዲህ የቶኪዮ እና ቤጂንግ ፍጥጫ እየተካረረ ይገኛል።
የአሜሪካ አጋር ተደርጋ በምትቆጠረው ታይዋን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት በዋሽግተን እና ቤጂንግ መካከል ቀጥተኛ የሆነ ግጭትን ይፈጥራል የሚለው ስጋት ለረዥም ጊዜ የቆየ ነው። በዚህ አካሄድ ውጊያ የሚከፈት ከሆነ እንደ ጃፓን ያሉ በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ አጋሮችም እንደሚሳተፉበት ይገመታል።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ያደረገው ይህ ንግግር የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለዓመታት ባልታየ ደረጃ የተቃረነ እንዲሆን አድርጎታል።
ቻይናም በተለያዩ መንገዶች በጃፓን ላይ ግፊት ማሳደሯን ጠይቃለች። የጦር መርከቦችን መላክ፣ የብርቅዬ የምድር ማዕድናት ማሰናከል፣ የቻይናውያን የሚያደርጉትን ጉብኝት መገደቡ፣ ኮንሰርቶችን መሰረዝ እንዲሁም ፓንዳዎችን ማስመለስ ጭምር በቻይና የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው።
የጃፓን መከላከያ ሚኒስትር ሺንጂሮ ኮይዙሚ ሚሳዔሎቹን ለማጓጓዝ የተያዘውን ቀነ ገደብ ማክሰኞ ዕለት ይፋ ያደረጉት ቻይና የብሔራዊ ደኅንነት ስጋትን በማንሳት በጃፓን 20 ኩባንያዎች እና ተቋማት ላይ የኤክስፖርት ገደብ በጣለች በማግሥቱ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ፤ በዮናጉኒ ደሴት ላይ የሚገኘው የጦር ክፍል ከመሬት ወደ አየር በመካከለኛ ርቀት የሚወነጨፉ እንዲሁም የሚመጡ የጦር አውሮፕላን እና ሚሳዔሎችን ማክሸፍ የሚችሉ ሚሳዔሎችን እንደሚታጠቅ ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ ቻይና የጃፓንን ውሳኔ በተመለከተ አስተያየት አልሰጠችም። ባለፈው ኅዳር ላይ የመከላከያ ሚኒስትሯ ደሴቷን በጎበኙበት ወቅት ግን ቻይና "ቀጣናዊ ውጥረትን ለመፍጠር እና ወታደራዊ ግጭትን ለመተንኮስ" እየተንቀሳቀሰች ነው ስትል ጃፓንን ከስሳ ነበር።
ከቀናት በኋላም ወደ ደሴቷ ድሮን በመላክ ንዴቷን ገልጻለች። ጃፓን ደግሞ በምላሹ የጦር ጄቶችን አንቀሳቅሳ ነበር።















