በጃፓን በርካታ ሴቶች ከ100 ዓመት በላይ የሚኖሩበት ምሥጢር ምንድን ነው?

የ100 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት የሥነ ውበት አማካሪ ቶሞኮ ሆሪኖ፣ ፉኩሺማ ከተማ ወደሚገኘው ቢሯቸው ከመሄዳቸው በፊት ሲኳኳሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ100 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት የሥነ ውበት አማካሪ ቶሞኮ ሆሪኖ፣ ፉኩሺማ ከተማ ወደሚገኘው ቢሯቸው ከመሄዳቸው በፊት ሲኳኳሉ

የጃፓን መንግሥት ዕድሜያቸው 100 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ዜጎቼ ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ መድረሱን አስታውቋል።

ይህ ቁጥር በአገሪቱ ታይቶ የማያውቅ እና እንደ ክብረ ወሰን የተመዘገበ ነው።

ለ55 ዓመታት በተከታታይ አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘግቡ የመጡት የጃፓን የዕድሜ ባለጸጎች እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ 99,763 እንደነበሩ አርብ ዕለት የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር አስታውቋል።

ከእነዚህ የዕድሜ ባለጸጎች መካከል ደግሞ 88 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

የጤና ሚኒስትር የሆኑት ታካማሮ ፉኮካ ረዥም ዓመት የኖሩትን 87,784 ሴቶች እና 11,979 ወንዶች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

"ለረዥም ዓመት ለማኅበረሰብ ዕድገት ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ነበር ያሉት።

ጃፓን ረዥም ዕድሜ በሚኖሩ ሰዎች ቁጥር የምትታወቅ ሲሆን፣ ምንም እንኳ አንዳንድድ ጥናቶች ይህንን ቢቃረኑም በዓለም ላይም ረዥም ዕድሜ የመኖር ምጣኔው ከፍተኛ ከሆነባቸው አገራትም ቀዳሚዋ ናት።

ይህ ብቻም ሳይሆን በዓለም ላይ በፍጥነት እያረጁ ከሚገኙ ማኅበረሰቦች ከሚገኙባቸው አገራት መካከልም አንዷ ናት።

ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ያላት ግን ዝቅተኛ የውልደት ምጣኔ ያለባት አገርም ናት ጃፓን።

በጃፓን ረዥም ዕድሜ የኖሩት ሴት የ114 የዕድሜ ባለጸጋዋ ሺጌኮ ካጋዋ ሲሆኑ፣ 111 ዓመት በመኖር ደግሞ ክብረ ወሰኑን የያዙት ወንድ ኪዮታካ ሚዙኖ ናቸው።

ይህ ቁጥር ይፋ የሆነው መስከረም 5 ከተከበረው የጃፓን በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቀን ቀደም ብሎ ነው።

ይህ ዕለት ብሔራዊ በዓል ሲሆን በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የእንኳን ደስ አላችሁ ደብዳቤ እና ብርማ ኩባያ በስጦታ ተልኮላቸዋል።

በዚህ ዓመት 52,310 አዛውንቶች ለዚህ ስጦታ ብቁ ሆነው የተመረጡ መሆናቸውን የጃፓን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በዕድሜየገፉ ሰዎች በመናፈሻዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይሰራሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጃፓናውያን ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ያላቸው ሲሆን፣ የተለመዱ በሽታዎች ቁጥር ዝቅተኛ የሆነባት እና በቡድን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት የተለመደባት አገር ናት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ከቡድን ሰባት አገራት ጋር ስትነጻጸር ጃፓን ዕድሜያቸው ከ100 ባለፈ ዜጎች ቁጥር ዝቅተኛው ምጣኔ የነበራት አገር ነች።

ነገር ግን ቀጥሎ በመጡት አስርታት ይህ ቁጥር በፍጥነት መቀየር ጀምሯል።

መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1963 በዕድሜ የገፉ ሰዎችን መቁጠር ሲጀምር ዕድሜያቸው መቶን የተሻገረ ሰዎች 153 ብቻ ነበሩ።

በ1981 ግን ይህ ቁጥር አንድ ሺህን ሲያልፍ በ1998 ደግሞ 10,000 ደርሷል።

ረዥም ዕድሜ የሚኖሩ ሰዎች መብዛታቸው የሚያሳየው በልብ ሕመም እና እንደ ካንሰር ባሉ የተለመዱ በሽታዎች በተለይ ደግሞ በጡት እና ፕሮስቴት ካንሰር የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ነው።

የጃፓን ሴት አዛውንቶች ዝቅተኛ ቀይ ሥጋ መመገባቸው እና አሳ እና አትክልት ማዘውተራቸው ዝቅ ያለ የሰውነት ክብደት እንዲኖራቸው እና ጤናቸውን እንዲጠብቁ ረድቷቸዋል።

የሰውነት ክብደት መጨመር በሴቶች ላይ ዝቅተኛ ሲሆን፣ ይህም ለምን ጃፓናውያን ሴቶች ከወንዶች አቻዎቻቸው በተሻለ ረዥም ዓመት ለመኖር እንደቻሉ በቂ ማስረጃ ነው።

በሌላው ዓለም በምግቦች ላይ የሚጨመረው ስኳር እና ጨው እየጨመረ ሲመጣ ጃፓን ግን ዜጎቿ የሚጠቀሙትን ጨው መጠን እንዲቀንሱ በማስተማር ውጤት አምጥታለች።

ረዥም ዕድሜ ለመኖር ግን አመጋገብ ብቻውን የሚጠቀስ አይደለም።

ጃፓናውያን ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ቤት ከመቀመጥ ይልቅ በእግራቸው መንሸራሸር ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አዛውንቶች በተሻለ በሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎቶች መጠቀም ያዘወትራሉ።

ከአውሮፓውያኑ 1928 ጀምሮ በቡድን በመሆን የአካል ብቃት አንቅስቃሴ ማድረግ የተለመደ ነው።

ይህ ደግሞ ከሕብረተሰብ ጤና ባሻገር የማኅበረሰቡን ቅርርብም ያጠናክራል።

የሦስት ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ሲሆን በመላ አገሪቱ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሰብሰብ እያሉ እንቅስቃሴ ይሠራሉ።

ይሁን እንጂ በዓለም ላይ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር ላይ በርካታ ጥናቶች ጥያቄ ያነሳሉ።

የመረጃ ግድፈት፣ አስተማማኝ ያልሆነ የሰነድ አያያዝ እንዲሁም የልደት ምስክር ወረቀት መጥፋት ለቁጥሩ ከፍ ማለት ይጠቀሳል ሲሉ ይሞግታሉ።

የጃፓን መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2010 የቤተሰብ ምዝገባውን በፈተሸበት ወቅት ከ230 ሺህ በላይ ዕድሜያቸው 100 እና ከዚያ በላይ መሙላቱ ከተመዘገቡት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ከአስር ዓመት በፊት በመሞታቸው ጭምር ሊገኙ አልቻሉም።

ይህ መዛባት የተከሰተው በሰነድ አያያዝ ላይ በተፈጠረ ስህተት እንዲሁም አንዳንድ ቤተሰቦች የሞቱ በዕድሜ የገፉ ዘመዶቻቸውን ጡረታቸውን ለመቀበል በማሰብ ሳያሳውቁ በመቅረታቸው ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ጃፓን በአገር አቀፍ ደረጃ የቤተሰብ ምዝገባዋን የፈተሸችው በቶኪዮ ይኖሩ የነበሩት እና 111 ዓመት ይሆናቸዋል የተባሉት ሶጌን ኮቶ ከሞቱ ከ32 ዓመት በኋላ በቤተሰቦቻቸው ቤት ውስጥ አስከሬናቸው በመገኘቱ ነው።