በጃፓን በዘንድሮው ዓመት 40 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ብቻቸውን ቤት ውስጥ ሞተው መገኘታቸውን ሪፖርት አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጃፓን በአውሮፓውያኑ 2024 የመጀመሪያው አጋማሽ 40 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ቤት ውስጥ ብቻቸውን ሞተው መገኘታቸውን የአገሪቷ ፖሊስ መረጃ አመለከተ።
ከእነዚህ መካከል አራት ሺህ የሚሆኑት ሕይወታቸው ካለፈ ከአንድ ወር በላይ በኋላ አስክሬናቸው መገኘቱን እና የ130 ሰዎች አስክሬኖች ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ ማንም ሳያያቸው መቆየታቸውን የብሔራዊ ፖሊስ ኤጀንሲ ገልጿል።
ኤጄንሲው ጨምሮም ሪፖርቱ በአገሪቱ ብቻቸውን ኖረው ብቻቸውን የሚሞቱ ሕዝቦቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ከፍተኛ የአረጋውያን ቁጥር ችግር ፍንትው አድርጎ ያሳያል ብሏል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ጃፓን በዓለማችን በርካታ በእድሜ የገፉ ዜጎች ያሏት አገር ናት።
የአገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስ ኤጀንሲ መረጃ እንዳሳየው በ2024 የመጀመሪያው አጋማሽ በአጠቃላይ ብቻቸውን ይኖሩ የነበሩ 37 ሺህ 227 ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል።ከእነዚህ መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ናቸው።
ከእነዚህ መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት አስክሬናቸው የተገኘው በአንድ ቀን ውስጥ ሲሆን ወደ 3 ሺህ 939 ሰዎች ደግሞ አስክሬናቸው የተገኘው ከሞቱ ከአንድ ወር በኋላ መሆኑን የፖሊስ ሪፖርት አመልክቷል።
130 የሚሆኑ አስክሬኖች ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ማንም ሳያያቸው ቆይተዋል።
7 ሺህ 498 የሚሆኑት አስክሬኖች 85 ዓመት እና ከዚያ በላይ እድሜ የሆናቸው ሰዎች ሲሆኑ፣5 ሺህ 920 የሚሆኑት ደግሞ እድሜያቸው ከ75 እስከ 79 የሚሆን ነው ።
እድሜያቸው በ70 እና 74 መካከል የሚገኙት ደግሞ 5 ሺህ 635 መሆናቸው ተገልጿል።
ፖሊስ ያገኘውን ይህንን መረጃ ያልታወቁ ሞቶችን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ሪፖርት ማድረጉን የጃፓን የሕዝብ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ኤንኤችኬ ዘግቧል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የጃፓን ብሔራዊ የሕዝብ ደኅንነት የጥናት ተቋም እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆናቸውና ብቻቸውን የሚኖሩ አረጋውያን ዜጎች ቁጥር በ2050 10.8 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል።
የጃፓን መንግሥትም በአገሪቷ ለዘመናት የተንሰራፋውንና በከፊል በአገሪቷ ባለው የአረጋውያን ቁጥር መበራከት የመጣውን የብቸኝነት እና የመገለል ችግር ለመፍታት የሚያስችል ሕግ ሚያዝያ ወር ላይ አስተዋውቆ ነበር።
አገሪቷ እየቀነሰ የመጣውን የሕዝብ ቁጥሯን እና የአረጋውያን መበራከት ችግር ለመፍታት ለረዥም ጊዜ ጥረት ስታደርግ ብትቆይም ይህንን ለማሳካት ግን ከባድ ሆኖባታል።
ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ በአገራቸው የውልደት መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ እንደ ማኅብረሰብ መቀጥል የማንችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ጫፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል።
አንዳንድ ጎረቤት አገራትም ተመሳሳይ የሥነ ሕዝብ ተግዳሮቶች እየገጠሟቸው ነው።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ቻይና ከ1960ዎቹ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ የሕዝብ ቁጥሯ ቀንሷል።
በተመሳሳይ ደቡብ ኮሪያም አነስተኛ የውልደት መጠን መዝግባለች።












