የዓለም መንግሥታት በኢራን ላይ ስለደረሰው ጥቃት ምን አሉ?

በኢራን ላይ የተፈጸመው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የተቀናጀ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ መንግሥት እጅ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

ኢራናውያን "ለመንግሥት ለውጥ እንዲዘጋጁ" ትራምፕ ከጠየቁ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸው ተገልጿል።

እስራኤል፤ በኢራን ጥቃት እንዳይፈጸምባት በሚል "የቅድመ ጥንቃቄ ጥቃት" ማድረሷን ገልጻለች።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ኢራን እና አሜሪካ ለሳምንታት ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ትናንት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ "ዓለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት ተናግቷል" ብለዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል ያደረሱት ጥቃት እንዲሁም የኢራን የአጸፋ ምላሽ ቀጣናውን እንዳወከው ገልጸው "ወደተባባሰ ቀጣናዊ ግጭት ከመገባቱ እና ንጹኃን ከመጎዳታቸው በፊት በአፋጣኝ ግጭቱ መቆም አለበት" በማለት አሳስበዋል።

ተመድ በኒው ዮርክ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ላይ በድርጅቱ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልክ "ጥቃቱ ስትራቴጂያዊ ቦታዎችን ብቻ ዒላማ ያደረገ ነው" ብለዋል።

"ግባችን የሚሳዔል ግንባታን ማስቆም ነው። በዓለም አቀፉ የውሃ አካል ዙሪያ ያሉ አገራት እንዳይረበሹ፣ ኢራንን የሚደግፉ ታጣቂዎች እንዲወገዱ እና አገሪቱ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳትታጠቅ እንፈልጋለን" ሲሉም ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን በበኩላቸው "እስራኤል እና አሜሪካ በመተባበር በእስራኤል፣ በአጋሮቻችን እንዲሁም በዓለም ደኅንነት ላይ የተቃጣውን ስጋት ለመቀልበስ እየሠሩ ነው" ብለዋል።

"አንድ መንግሥት 'ሞት ለእስራኤል' እና 'ሞት ለአሜሪካ' ሲል እንደ ቀልድ አንወስደውም" በማለትም በጉባዔው ላይ ተናግረዋል።

የኢራን አጋር ሩሲያ ጥቃቱን አውግዛለች። የተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫስሊ ናብኒዛ "ኢራን ላይ የተፈጸመው ጥቃት መላው ቀጣናውን የሚያናውጥ ነው" ሲሉ ኮንነዋል።

ከዚህ ቀደም "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የመካከለኛው ምሥራቅን ሰላም እና መረጋጋት የሚያውክ ድርጊትን ይቆጣጠር" ስትል ሞስኮ ጥሪ አቅርባለች።

ባለፉት ሳምንታት ኢራን እና አሜሪካን ሲያደራድሩ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳዲ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ "በጣም ደንግጫለሁ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

ሚኒስትሩ፤ የኢራን እና አሜሪካ ንግግር ላይ ጉልህ መሻሻል መታየቱን በገለጹ በሰዓታት ውስጥ ነው ጥቃት የተፈጸመው።

ሚኒስትሩ "የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርበናል። እዚያ ነጥብ ላይ ለመድረስ ለዲፕሎማሲ ዕድል መስጠት አለብን" ሲሉ ለቢቢኢ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረው ነበር።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ "ጥሩ እየሄደ የነበረው ድርድር ከስሟል። በዚህ ጥቃት አሜሪካም ዓለምም አይጠቀምም። በጥቃቱ ለሚጎዱ ንጹኃን እፀልያለሁ። አሜሪካ ከዚህ በላይ በጥቃቱ መቀጠል የለባትም። ጦርነቱ የአሜሪካ አይደለም" ብለዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ እና እስራኤል "ማንም ሳይነካቸው ትንኮሳ ፈጽመዋል" በማለት ጥቃቱን አውግዘዋል።

"ሕገ ወጥ" ሲሉ ጥቃቱን የኮነኑን ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ "ትራምፕ 'ቅድሚያ ለአሜሪካ' ከሚለው ፖሊሲ ወደ 'ቅድሚያ ለእስራኤል' ተሻግረዋል። ስለዚህ አሜሪካ የመጨረሻ ምርጫቸው ናት" ብለዋል።

ኢራን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ የአሜሪካ እና አጋሮቿ የጦር መቀመጫዎች ላይ የአጸፋ ምላሽ ሰንዝራለች።

ጥቃት ከተሰነዘረባቸው መካከል፤ ዱባይ፣ ዶሃ፣ ባሕሬን እና ኩዌት ይገኙበታል። ሳዑዲ አረቢያ "የኢራን ከፍተኛ የነውጥ ጥቃቶች ናቸው" ስትል አውግዛለች።

ሳዑዲ ባወጣችው መግለጫ "ከወንድም አገሮች ጎን እንቆማለን። የሚወስዱትን እርምጃም ባለን አቅም ሁሉ እንደግፋለን" ብላለች።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በጋራ ባወጡት መግለጫ "በድርድር መፍትሔ መገኘት አለበት" በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል።

ሦስቱ አገራት ኢራን ላይ በተወሰደው እርምጃ ውስጥ ተሳታፊ እንዳልሆኑ ገልጸዋል። ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማኅበሰረብ ጋር ተቀራርበው እየሠሩ መሆኑንም አመልክተዋል።

"የኢራን መንግሥት ወደ ድርድር እንዲሄድ እንጠይቃለን። ኢራናውያን እጣ ፈንታቸውን የመሰን ዕድልም ይሰጣቸው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ "የዩኬ ፍላጎቶች እና አጋሮችን ለማስጠበቅ የእንግሊዝ አውሮፕላኖች ተሰማርተዋል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ማክሮን በበኩላቸው አሁን ያለው ሁኔታ "መላው ቀጣናውን የሚያሰጋ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ፈረንሳይ የቅርብ አጋሮቿን ለመጠበቅ "አስፈላጊውን ኃይል እንደምታሰማራም" አመልክተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ካጃ ካሊስ "ኢራን ላይ ጠንካራ ማዕቀቦች ጥለናል። ኒውክሌርን በተመለከተ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲገኝ ድጋፍም አድርገናል" በማለት በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

ንጹኃንን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግን መጠበቅ ቅድሚያ እንዲሰጠው አሳስበዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፤ ውጥረቱን ለማርገብ በቀጣው ከሚገኙ አጋሮቻቸው ጋር እየተወያዩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የብራዚል መንግሥት በበኩሉ አሜሪካ እና እስራኤል ያደረሱት ጥቃት "እጅግ አሳሳቢ ነው" ብሏል።

የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳትታጠቅ በማድረግ ረገድ አሜሪካን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ዋና ኃላፊ ቮልከር ቱርክ "ሁሉም ወገኖች ምክንያታዊ ይሁኑ፤ ግጭት አቁመው ወደ ድርድር ይመለሱ" ብለዋል።

"ሁሌም ቢሆን በወታደራዊ ግጭት የሚጎዱት እና ዋጋ የሚከፍሉት ንጹኃን ናቸው። ንጹኃንን መጠበቅ በዓለም አቀፍ ሕግ ቅድሚያ ይሰጠዋል" ሲሉም አሳስበዋል።

ትራምፕ ግባቸው "ኢራን አሜሪካውያን ላይ የደቀነችውን አደጋ መቀልበስ" መሆኑን በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ተናግረዋል።

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንድትታጠቅ እንደማይፈቅዱም ገልጸዋል።

"እኛ ስንጨርስ መንግሥታችሁን አቋቁሙ። መንግሥታችሁን ለመቀየር በዚህ ትውልድ አንዴ ብቻ የሚመጣ ዕድል አላችሁ" ብለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም በተመሳሳይ ኢራናውያን "አምባገነን መንግሥትን አውርደው ሰላማዊ ኢራን እንዲገነቡ" መልዕክት አስተላልፈዋል።

"ጥምር እርምጃችን ጀግና ኢራናውያን የአገራቸውን የወደፊት እጣ ፈንታ እንዲወስኑ ይረዳል" ብለዋል።