ኢራን እና እስራኤል ለምን ደመኛ ጠላቶች ሆኑ?

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ
የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ

ወትሮም በጠላትነት በዓይነ ቁራኛ የሚጠባበቁት ሲበረታም በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የሚፋለሙት እስራኤል እና ኢራን ካለፈው ሐሙስ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም. ሌሊት አንስቶ እስራኤል በከፈተችው ጥቃት ወደ ለየለት ጦርነት ውስጥ በመግባታቸው ዓለም ጭንቀት ውስጥ ገብቷል።

እስራኤል በኢራን ዋና ከተማ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በፈጸመችው ከባድ ጥቃት በርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ሲገደሉ፣የኒውክሌር ተቋማት እና ወታደራዊ መሠረተልማቶቿ ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።

ይህንን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በበኩሏ የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ በርካታ የእስራኤል ከተሞችን በሚሳዔሎች እና በድሮኖች አጥቅታለች። ከዚያ ዕለት በኋላ የእስራኤል ጥቃት የቀጠለ ሲሆን፣ የኢራንም የአጸፋ ምላሽ እንደቀጠለ ነው።

እስራኤል ኢራን አውዳሚውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ከጫፍ ደርሳለች ይህም በኅልውናዬ ላይ የተጋረጠ ስጋት ነው ስትል የምትከስ ሲሆን፣ ኢራንም በበኩሏ እስራኤል ሉአላዊነቷን እየተገፋች በመሆኗ እራሷን ከመከላከል ወደ ኋላ እንደማትል አሳውቃለች።

በዚህም ምክንያት የሁለቱ አገራት ድንበር ዘለል መጠቃቃት ወደ አውዳሚው የኒውክሌር ጦርነት እንዳያመራ ዓለም ስጋት ውስጥ ገብቷል። የመንግሥታቱ ድርጅት እና በርካታ አገራት እስራኤል እና ኢራን ወደተባባሰ ሁኔታ ከመግባት እንዲቆጠቡ ጥሪ ሲያርቡ፤ አንዳንድ አገራት ከእስራኤል መቆማቸውን ሲያመለክቱ ሌሎች ደግሞ የእስራኤልን ጥቃት አውግዘዋል።

እስራኤል እና ኢራን ለዘመናት የዘለቀ ባላንጦች ናቸው። በሁለቱ አገራት መካከል የቆየው ከፍተኛ የጠላትነት ስሜት በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲርቅ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

ቴህራን ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ የምትሻትን እስራኤልን “ትንሿ ሰይጣን” ስትላት፣ አሜሪካንን ደግሞ “ትልቋ ሰይጣን” በማለት ለሁለቱም ያላትን ተመሳሳይ አመለካከት ስታንጸባርቅ ቆይታለች።

ኢራን እስራኤል ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ከመፈጸም ይልቅ በገንዘብ እና በትጥቅ የምትደግፋቸውን ቡድኖች በመጠቀም በእጅ አዙር ጥቃት እንደምታስፈጽም ይነገራል።

አያቶላ ኾሜኒ እና የኢራን እስላማዊ አብዮት መሪዎች ፀረ አስራኤል አቋም በመያዝ የፍልስጤማውያንን ትግል ይደግፋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አያቶላ ኾሜኒ እና የኢራን እስላማዊ አብዮት መሪዎች ፀረ አስራኤል አቋም በመያዝ የፍልስጤማውያንን ትግል ይደግፋሉ

የቴህራን እና የቴል አቪቭ ጠላትን ምንጭ ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስከ አውሮፓውያኑ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የነበረው ግንኙነት ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ እና የባሕረ ሰላጤው አገራት በተለየ መልካም የሚባል ነበር።

እስራኤል በ1948 ላይ ከተመሠረተች በኋላ ከግብፅ በመቀጠል ለአይሁዳዊቷ አገር እውቅና በመስጠት ሁለተኛዋ እስላማዊት አገር የነበረችው ኢራን ናት።

በወቅቱ ኢራን ትመራ የነበው በመካከለኛው ምሥራቅ ጠንካራ የአሜሪካ አጋር በነበረው የሻህ ፓህላቪ ሥርወ መንግሥት ነበር።

እአአ 1979 ላይ የኢራን እስላማዊ አብዮትን ተከትሎ መንግሥታዊ ለውጥ ሲደረግ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ልዩነት መልኩን ቀየረ።

የአያቶላህ ኾሜኒ እስላማዊ አብዮት የሻህ መንግሥትን ገርስሶ እራሱን የጭቁኖች መሪ አድርጎ ብቅ ሲል፣ የመንግሥታቸው ዋነኛ መለያም የአሜሪካን እና የአጋሮቿን “ኢምፔሪያሊዝም” መቃወም ሆነ።

የአያቶላ አስተዳደር ኢራን ከእስራኤል ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠ። ለእስራኤል ፓስፖርትም እውቅና ነስቶ በቴህራን የነበረውን የእስራኤል ኤምባሲን፣ የእስራኤል መንግሥትን ሲዋጋ ለነበረው ለፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) አሳልፎ ሰጠ።

በመላው ዓለም የሚካሄዱ ግጭቶችን የሚያጠናው ኢንተርናሽል ክራይሲስ ግሩፕ ዳይሬክተር የሆኑት አሊ ቫኤዝ የኢራን መሪዎች ጥላቻ የጀመረው ገና ከጠዋቱ ነው ይላሉ።

“በእስራኤል ላይ የመረረ ጥላቻ የአዲሱ የኢራን መንግሥት መገለጫ የሆነው፤ አብዛኞቹ የኢራን አመራሮች እንደ ሊባኖስ ባሉ አካባቢዎች ከፍልስጤም ተዋጊዎች ጋር ወታደራዊ ልምምድ እና የሽምቅ ውጊያ ሲያደርጉ ቅርበት ስለፈጠሩ ነው” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አዲስቷ ኢራን እራሷን የፍልስጤማውያን ጉዳይን በማጉላት የሙስሊሞች ተቆርቋሪ አገር ሆና ለመታየት ስለምትሻ ፀረ እስራኤል ሆና ብቃ ብላለች።

እንደ ቫኤዝ ገለጸ ቀደም ባሉት ዓመታት ለእስራኤል ትልቋ ስጋት ኢራቅ በነበረችበት ዘመን፣ እስራኤል ኢራን ያመረረች ጠላት ትሆንብኛለች የሚል ጥርጣሬ አልነበራትም ይላሉ።

ነገር ግን እስራኤል እና ኢራን በዓይነ ቁራኛ እየተጠባበቁ ቆይተው ከሳዳም ሁሴን መንግሥት መውደቅ በኋላ እስራኤል በቀጠናው ለደኅንነቷ አደገኛዋ አገር ኢራን መሆኗን በማመን የዘወትር ስጋቷ ሆነች። በተለይም ኢራን ለሰላማዊ አገለግሎ ነው የምትለው የኒውክሌር አቅም ግንባታዋ የበለጠ እንቅልፍ ነሳት።

ከ1979 (እአአ) እስላማዊ አብዮት በኋላ የኢራን እና የእስራኤል ግንኙነት ተበላሽቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከ1979 (እአአ) እስላማዊ አብዮት በኋላ የኢራን እና የእስራኤል ግንኙነት ተበላሽቷል

የእስራኤል እና ኢራን የእጅ አዙር ጦርነት

ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ እና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ከእስራኤል ውጪ በቀጠናው ጠንካራ አገር የሆነችውን ሳዑዲ አረቢያን በጥርጣሬ ነው የምትመለከታት።

በአብዛኛው ሱኒ ሙስሊሞች በሚኖሩበት ቀጠና፣ የብዙኃን ሺዓ ሙስሊሞች መገኛ የሆነችው ኢራን ወደፊት ሊቃጣባት ከሚችል ጥቃት እራሷን ለመጠቅ ስትል በመረጠችው ስትራቴጂ ከተቀረው ዓለም ልትነጠል መቻሏን ቫዬዝ ይገልጻሉ።

በዚህም የኢራን መንግሥት ከአገራት ይልቅ በአካባቢው የተለያዩ ዓላማዎችን አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር በማበር ፍላጎቱን ለማስጠበቅ ሲጥር ቆይቷል።

ኢራን 'አክሲስ ኦፍ ሬዚዝታንስ' ስትል የምትጠራው ስብስብ በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በየመን የተንሰራ ሲሆን በዋናነት በአገራቱ ውስጥ ያሉ እና ፀረ እስራኤል የሆኑ ታጣቂ ቡድኖችን ያቀፈ ነው።

ቴህራን በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን እና መቀመጫውን በሊባኖስ ያደረገውን ሔዝቦላህን ታስጣጥቃለች።

ጋዛን ለሚያስተዳድረው ሐማስ፣ በየመን ለሚንቀሳቀሱት ሁቲ አማጺያን ኢራን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በአካባቢው ተጽእኖ ስትፈጥር ቆይታለች።

እስራኤል ደግሞ ኢራን በዙሪያዋ ይህ ሁሉ ስታከናወን ዝም ባላ አልተመለከተችም። ኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉ አገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በቴህራን የሚደገፉ ቡድኖች ላይ እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች።

ባለፉት ዓመታት በኢራን እና በእስራኤል መካከል የነበረው ጦርነት “ከመጋረጃ ጀርባ” ያለ ጦርነት ተብሎ ሲገለጽ ኖሯል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሁለቱ አገራት በሌሎች አገራት ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ኃላፊነት ሲወስዱ አይታይም።

በተለይ ኢራን እስራኤልን በቀጥታ ከመተንኮስ ይልቅ በምትደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖች በኩል በእጅ አዙር ስታጠቃት ኖራለች።

እአአ 1992 የወቅቱ የሔዝቦላህ መሪ የነበሩት አባስ አል-ሙሳዊ ግድያን ተከትሎ ለኢራን ቅርበት ያለው እስላማዊ ጂሃድ ቡድን ደቡብ አሜሪካ አርጀንቲና ውስጥ የሚገኘውን የእስራኤል ኤምባሲን በቦምብ አጋይቶ 29 ሰዎችን ገድሎ ነበር።

እስራኤል ለሔዝቦላህ መሪ ግድያ ኃላፊነት ባትወስድም የቴል አቪቭ የደኅንነት ተቋም የሆነው ሞሳድ ግድያውን መፈጸሙ ይታመናል።

እስላማዊው የጂሃድ ቡድንም ቢሆን የእስራኤልን ኤምባሲ ያጋየው ያለ ኢራን እውቅና እንደማይሆን በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።

እስራኤል የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም ለማደናቀፍ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም ለማደናቀፍ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች

የኢራን ኑክሌር እና የእስራኤል ስጋት

እስራኤል የኢራን ጉዳይ አንገብጋቢ የሚሆንባት የአያቶላህ ቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራም ነው። ለዚህም ኢራን የቦምቡ ባለቤት እንዳትሆን እስራኤል የተቻላትን ስታደርግ ቆይታለች።

ኢራን ግን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ብቸኛው ዓላማ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚውል ሰላማዊ ዓላማ ያለው ነው ስትል ቆይታለች።

ይህን ምክንያት ጨርሶ የማትቀበለው እስራኤል በዲፕሎማሲ በኩል ኢራን ላይ ማዕቀብ ከማስጣል አልፋ ከአሜሪካ ጋር አብራ የኢራንን የኑክሌር ማብላያ ጣቢያን ‘ስቱአኔት’ በሚባል ኮምፒዩተር ቫይረስ አውካ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳ ነበር።

እስራኤል የኢራን ኮምፒዩተሮችን ብቻ ሳይሆን ሳይንቲስቶቿንም ዒላማ እያደረገች በቴህራን ጎዳናዎች ላይ ገድላለች።

በአውሮፓውያኑ 2020 በጉምቱው የኑክሌር ሳይንስ ተመራማው ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ላይ የተፈጸመው ግድያም ብዙ ያነጋገረ ነበር።

የእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ እኒህን ተመራማሪ ለመግደል ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች ሳይሳካሉት ቆይተው ነበር፣ ከአምስት ዓመታት በፊት ከኢራን መዲና ቴህራን ወጣ ብሎ ከሚገኝ ስፍራ ፋክሪዛሄድን የመግደል ውጥኑ ሰምሮለታል።

ኢራንም ብትሆን በእስራኤል ላይ ድሮኖችን እና ሮኬቶችን ስታስወነጭፍ እንዲሁም የእስራኤል ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

የአረብ አብዮትን ተከትሎ እአአ 2011 በሶሪያ የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ሌላኛው የእስራኤል እና የኢራን የቅራኔ ምንጭ ነው።

ምዕራባውያን እንደሚሉት ከሆነ አመጽ የተነሳባቸውን ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድን በሥልጣን ለማቆየት ኢራን ጦር መሳሪያ፣ ገንዘብ እና ሥልጠና የሚሰጡ የጦር መኮንኖችን ልካለች።

እስራኤል ደግሞ ጠንካራው የሊባኖስ ሔዝቦላህ ቡድን ከኢራን የሚያገኛቸው ድጋፎች በሶሪያ በኩል የሚያልፉ ስለነበሩ የባሻር አል-አሳድ መንግሥት መወገድን አጥብቃ ትሻ ነበር።

እስራኤል እና ኢራን በየብስ ላይ “ከመጋረጃ ጀርባ” የሚያካሂዱት ጦርነት ወደ ባሕር ላይም ተሸጋግሮ በተለያዩ ጊዜያት በመርከብ የጉዞ መስመሮችም ላይ ስጋትን ሲደቅን ቆይቷል።

እአአ 2021 ላይ እስራኤል ዕቃ ጫኝ መርከቦቿ ላይ በኦማን ባሕረ ሰላጤ በኩል ሲያልፉ በኢራን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ከሳለች። ኢራን ደግሞ ቀይ ባሕር ላይ ሲጓዝ በነበረው መርከቧ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች።

እንዲሁም እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የየመን ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ የእስራኤል እና የወዳጆቿ ምዕራባውያን መርከቦችን ዒላማ አድርገው ሲያጠቁ ቆይተዋል።

ኢራን በእስራኤል ተገደሉ ያለቻቸውን የኑክሌር ፕሮግራሟ ዋነኛ ሳይንቲስት የቀብር ሥነ ሥርዓት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢራን በእስራኤል ተገደሉ ያለቻቸውን የኑክሌር ፕሮግራሟ ዋነኛ ሳይንቲስት የቀብር ሥነ ሥርዓት

የሐማስ ጥቃት እና የሁለቱ አገራት ፍጥጫ

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የተጀመረው የጋዛው ጦርነት መካከለኛው ምሥራቅን ብሎም መላው ዓለምን ከማሳሰቡ ባሻገር፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለውን ጠላትነት ወደ ከፍ ደረጃ አድርሶታል።

በኢራን የሚደገፈው ፍልስጤማዊው ቡድን ሐማስ የእስራኤልን ድንበር ተሻግሮ ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ክስተቱ ኢራን እና እስራኤልን ወደ ለየለት ጦርነት ያስገባል ሲሉ በርካቶች ገና ከመነሻው ስጋታቸውን ሲያስቀምጡ ነበር።

በአካባቢው የሚገኙ እና በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖችም እስራኤልን ዒላማ ያደረጉ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ሲያስወነጭፉ ቆይተዋል።

እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት እና የታገቱባትን ዜች ለማስለቀቅ ጋዛ ላይ የከፈተችው ዘመቻ ወደ ሁለተኛ ዓመቱ በተቃረበበት ጊዜ ከኢራን ጋር ወደ ለየለት ጦርነት ገብታለች። ቀደም ሲልም በኢራን የሚደገፉትን ሐማስን፣ ሔዝቦላህን እና ሁቲዎችን ዒላማ ጥቃቶችን ስትፈጽም ቆይታለች።

በዚህም የቡድኖቹን ወሳኝ መሪዎች ኢራን እና ሊባኖስ ውስጥ ጭምር አድና በመግደል ከባድ ጉዳት አድርሳባቸዋለች። በተጨማሪም ሶሪያ ውስጥ ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸመ ጠላቶቼ የምትላቸውን ኃይሎች አቅም ማዳከም ችላለች።

በዚህ መካከል የኢራን ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን እና የኑክሌር ሳይንቲስቶችን እያደነ የሚያጠፋው የእስራኤል የስለላ ተቋም፣ ሶሪያ ውስጥ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጸመ።

በዚህ ጥቃትም ዒላማ ሆነው የተገደሉት ቀላል የሚባሉ የኢራን ባለሥልጣናት አልነበሩም። ሁለት ጄኔራሎች እና በርካታ የጦር መኮንኖች ደማስቆ ውስጥ እንደወጡ ቀርተዋል።

ነገር ግን እስራኤል በኢራን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት በይፋ ኃላፊነቱን ባትወስድም ዓለም ግን ከእሷ ውጪ ይህንን ጥቃት ሊፈጽም የሚችል ኃይል እንደሌለ ይስማማል።

ኢራንም በጄነራሎቿ ላይ ለተፈጸመው ግድያ አጸፋ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ እስራኤልን ዒላማ በማድረግ ከ300 በላይ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን አስወንጭፋ በሁለቱ አገራት መካከል የኖረው ውጥረት መልኩን እንዲቀይር አድርጋለች።

አሁን ደግሞ እስራኤል በኢራን ላይ ለቀናት የዘለቀ መጠነ ሰፊ ጥቃት መክቷን ተከትሎ ኢራንም ተከታታይ የአጸፋ ጥቃቶችን በእስራኤል ላይ መፈጸሟ አስፈሪው የሁለቱ አገራት ቀጥተኛ ግልጽ ጦርነት ጅማሬ ሆኗል።

እስራኤል የኢራንን ወታደራዊ ኃይል ለማንኮታኮች ኢራን ደግሞ ለተፈጸመባት ጥቃት አጸፋ ለመመለስ ያላቸውን አቅም ሁሉ እየተጠቀሙ ነው።

ይህ ጦርነት ወደ አውዳሚው የኒውክሌር ጦርነት እዳያመራ ዓለም ስጋት ውስጥ ጥሏል። እስራኤል ኢራንን ለማንበርከክ የጀመረችውን ዘመቻ ከቀጠለች ኢራን ያሏትን አማራጮች ከመጠቀም ወደኋላ ላትል ትችላለች። ለዚህም ነው የዓለም አገራት መጠቃቃቱ በቶሎ እንዲቆም እየወተወቱ ያሉት።

ኢራን ውስጥ ፀረ እስራኤል ሰልፎች በተደጋጋሚ ይደረጋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢራን ውስጥ ፀረ እስራኤል ሰልፎች በተደጋጋሚ ይደረጋሉ