እስራኤል በኢራን በፈጸመችው ጥቃት የተገደሉ የጦር አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty
እስራኤል ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በመላው ኢራን ባሉ የኒውክሌር ይዞታዎች፣ ወታደራዊ ስፍራዎች እና የመኖሪያ ስፍራዎች ላይ በፈጸመቻቸው በርካታ ጥቃቶች ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና ዘጠኝ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ተገድለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው አርብ ማለዳ የፈጸመችው ጥቃት የኢራን የኒውክሌር መሰረተ ልማት እና የባለስቲክ ሚሳኤል ፋብሪካዎችን ለመጉዳት ያለመ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራይዚንግ ላየን ኦፐሬሽን' [ የሚያንሰራራ አንበሳ ዘመቻ] ሲሉ በጠሩት ጥቃት ከተገደሉት መካከል የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ እና የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ይገኙበታል።
ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
መሐመድ ባግሄሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መካከል የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሆኑት መሐመድ ባግሔሪ አንዱ ናቸው።
መሐመድ በጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነታቸው የአገሪቱን ጦር እንዲሁም የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋነኛ መሪ ናቸው።
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ አብዮታዊ ዘቡን የተቀላቀሉት በአውሮፓውያኑ 1980 ገና በ20 ዓመታቸው ነበር።
መሐመድ ከወንድማቸው ጋር በመሆን በኢራን- ኢራቅ ጦርነት ወቅት የአብዮት ዘቡ የስለላ ክፍል እንዲቋቋም ረድተዋል። መሐመድ በኢራን ካሉ የጦር አዛዦች መካከል አክራሪ ባለመሆን ይታወቃሉ።
በቅርቡ በጥንታዊው የፐርሴፖሊስ ፍርስራሽ ፊት ለፊት ሰላም እንዲሰፍን እና ጦርነት እንዲወገድ ባደረጉት ንግግር ከፍተኛ ትችት ገጥሟቸው ነበር።
ግድያቸውን ተከትሎ አብዶልራሂም ሙሳቪ የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው መተካታቸውን የኢራን መንግሥታዊ የዜና ወኪል ኢርና ገልጿል።
ሆሴይን ሳላሚ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሆሴን ሳላሚ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ነበሩ።
ሆሴይን የአብዮታዊ ዘብን የተቀላቀሉት የኢራን ኢራቅ ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 1980 ነው።
በወታደራዊ ማዕረግ ከፍ እያሉ ሲመጡም በአሜሪካ እና በምዕራባውያን አጋሮቿ ላይ በሚናገሩት ጠንካራ ትርክቶች እና በንግግር አዋቂነታቸው ዝናን አተረፉ።የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ የሆኑትም በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር።
ባለፈው ወር ኢራን በእስራኤልም ሆነ በአሜሪካ ጥቃት ከደረሰባት "የገሃነም በሮችን ትከፍታለች" ብለዋል።
በኢራን ኒውክሌር እና ወታደራዊ ፕሮግራሞች ተሳትፏቸው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እና አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ በኃላፊው ላይ ማዕቀብ ጥለውባቸዋል።
ኢራን 300 ድሮኖች እና ሚሳኤሎችን ያሳተፈ የመጀመሪያውን የቀጥታ ጥቃት በእስራኤል ላይ ስትፈጽም እሳቸው የአብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ነበሩ።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከእስራኤል ጋር ያለው ውጥረት መጋጋሉን ተከትሎ ሆሴይን አገራቸው "ለማንኛውም ሁኔታ፣ ክስተት እና አጋጣሚዎች" ዝግጁ መሆኗን ሐሙስ ዕለት ተናግረው ነበር።
የአገሪቱን እስላማዊ ሥርዓት ለመጠበቅ እንዲሁም መደበኛ ጦር ሠራዊቱን ለመደገፍ በሚል ከ40 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብም ዘወትር በምዕራባውያን ስሙ የሚነሳው የአገሪቱ የጦር ክፍልም ተጠቃሽ ነው።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከ190 ሺህ በላይ ወታደሮች እንደሚኖረው የሚገመት ሲሆን፤ የራሱን የምድር፣ የባሕር እና የአየር ኃይል አጠናክሯል። የኢራንን ስልታዊ የጦር መሣሪያዎችንም የሚቆጣጠረው ይኸው ኃይል ነው።
መሐመድ ፓክፑት የአብዮታዊ ዘቡ ዋና አዛዥ ሆነው መሾማቸውን የኢራን የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።
ጎላማሊ ራሺድ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጎላሚሊ ራሺድ የኢራን ጥምር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተባብረው የአብዮታዊ ዘቡ ካህታም አል አንቢያ የተሰኘው ማዕከላዊ ዋና መስሪያ ቤት ኃላፊ ነበሩ።
ጎላሚሊ በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ከኢራቅ ጋር በተደረገው ጦርነት የተዋጉ ሲሆን ቀደም ብሎ የኢራን ጦር ኃይሎች ምክትል ዋና አዛዥ ነበሩ።
ግድያቸውን ተከትሎ አሊ ሻድሚኒ የአደጋ ጊዜ ዕዝ መሪ ሆነው መሾማቸውን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል።
አሚር አሊ ሃጂዛዴህ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአብዮታዊ ዘቡ የኤሮስፔስ ኃይል አዛዥ የነበሩት አሚር አሊ ሃጂዛዴህ የሃገሪቱን የሚሳኤል ፕሮግራም በመምራት ታዋቂ ሰው ነበሩ።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት አዛዡ በእስራኤል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከበርካታ የአየር ኃይል አዛዦች ጋር በመሬት ስር ውስጥ በሚገኝ የእዝ ማእከል ውስጥ ተሰብስበው ነበር ብሏል።
አዛዡን ጨምሮ ቡድኑ የተገደሉትም በህንፃው ላይ ባነጣጠረ ጥቃት ነው ብሏል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት እና ሚያዝያ ወራት ላይ በእስራኤል ላይ የተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶችን ያዘዙትም ሃጂዛዴህ መሆናቸውን መከላከያው አስታውቋል።
ሃጂዛዴህ በአውሮፓውያኑ 2020 ከቴህራን ተነስቶ ይበር የነበረ የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን በመጣል ኃላፊነት ከወሰዱ በኋላ በኢራን ህዝብ ዘንድ ተቀባይነታቸው ቀንሶ ነበር።
በዚህ አደጋ 176 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ፍሬይዱን አባሲ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ፍሬይዱን አባሲ በአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2013 ድረስ የአገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ ነበሩ።
ፍሬይዱን አባሲ ለኢራን የኒውክሌር ማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2020 እስከ 2024 የአገሪቱ የፓርላማ አባል ነበሩ።
ሳይንቲስቱ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2010 በቴህራን ጎዳና ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር።
ከኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ጠንካራ አቋም እንዳላቸውም ይነገራል።
በቅርቡ ኤስኤንኤን አይ አር ከተባለ የኢራን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መገንባት እንደሚቻል ተናግረው ነበር።
የተገደሉ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች
እስራኤል በዚህ ጥቃት የገደለቻቸው ዘጠኝ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መሆናቸውን ጦሯ አስታውቋል።
- መህዲ ቴህራንቺ፦ በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት
- አብዶልሃሚድ ሚኖሸር፦በሻሂድ በህሽቲ ዩኒቨርስቲ የኒውክሌር ኢንጂነሪንግ ኃላፊ
- አህመድ ረዛ ዞልፋጋሪ፦ በሻሂድ በህሽቲ ዩኒቨርስቲ የኒውክሌር ኢንጂነርግ ፕሮፌሰር
- አሚርሆሴን ፈቂ ፦ በሻሂድ በህሽቲ ዩኒቨርስቲ የኒውክሌር ፕሮፌሰር
በተጨማሪም ሞታልቢዛዴህ የተሰኘ የኒውክሌር ሳይንቲስት መገደሉ ተገልጿል።
የኢራኑ ታላቁ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አማካሪ አሊ ኻምካኒ የከፋ ጉዳት እንደደረሰባቸው የኢራን ዘገባዎች አመልክተዋል።
እስራኤል ኢላማ ያደረግኩት ወታደራዊ ይዞታዎችን ነው ብትልም፤ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው በቴህራን የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና ከተገደሉትም መካከል ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ዘግቧል።
እስራኤል በኢራን ጥቃት ያደረሰችባቸው ስፍራዎች የትኞቹ ናቸው?
እስራኤል በዚህ ጥቃት ከመታቻቸው መካከል በናታንዝ በተሰኘችውና ከተማ የሚገኘው የኢራን ዋነኛ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ማዕከል አንዱ ነው።
ማዕከሉ በተደጋጋሚ እንደተመታ የኢራን መንግሥታዊው ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ማዕከሉ ከመሬት ስር በሜትሮች ርቀት የሚገኝ ሲሆን የእስራኤል ጥቃት ምን ያህል ጥልቀት እንደነበረው እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ከዚህም በተጨማሪ ቴህራን እና በአካባቢው ያሉ ወታደራዊ ስፍራዎች፣ ታብሪዝ በተሰኘችው ከተማ የሚገኝ የኒውክሌር የምርምር ማዕከል እና በሁለት የጦር ሰፈሮች ፍንዳታ ተሰምቷል።
ከቴህራን በስተደቡብ የምትገኘው የኢስፋሃን ከተማ፣ በስተደቡብ ምዕራብ የምትገኘው የአራክ ከተማ እንዲሁም በስተምዕራብ የምትገኘው የከርማንሻህ ከተማ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
የኢራን ታላቁ መንፈሳዊ መሪ አሊ ኻሜኒ ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል "መራራ እና የከፋ ህመም " እጣ እንደሚገጥማት አስጠንቅቀዋል።
"በአምላክ ፈቃድ እንዲሁም በእስላሚክ ሪፐብሊክ ጦር ኃይሎች ኃያል እጅ እስራኤል ቅጣት ሳይፈጸምባት አይቀርም" ብለዋል።















