ሜክሲኮ ውስጥ የእፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ መገደሉን ተከትሎ በተነሳ አመጽ ቢያንስ 25 ወታደሮች ተገደሉ

ከተቃጠለ ባስ ፊት መሳሪያ ይዞ የቆመ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሜክሲኮ ውስጥ ዋነኛ የእፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ የሆነው ኤል ሜንቾ በመንግሥት ኃይሎች መገደሉን ተከትሎ በተነሳ አመጽ ቢያንስ 25 የአገሪቱ ብሔራዊ ዘብ ወታደሮች መገደላቸው ተገለጸ።

የሜክሶኮ መንግሥት ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ የተቀሰቀሰውን አመጽ ለመቆጣጠር በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ማሰማራቱን አስታውቋል።

"ኤል ሜንቾ" በሚል ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው ኔሜሲዮ ኦሴጉኤራ ሰርቫንቴስ የተባለው የእፅ ዝውውር ቡድን መሪ፤ እሁድ ዕለት በሜክሲኮ ልዩ ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

የሜክሲኮ መከላከያ ሚኒስተር ሪካርዶ ትሬቪላ እንደገለጹት ኤል ሜንቾ በቁጥጥር ስር የዋለው የጸጥታ ኃይሎች ሊያገኛት ቀጠሮ የያዘላትን ፍቅረኛውን ተከታትለው ካገኙ በኋላ ነው።

ግለሰቡ ሊያዝ ሲል በጠባቂዎቹ እና በመግሥት ኃይሎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በጥይት የተመታ ሲሆን ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ዋና ከተማ ታፓላፓ እየተወሰደ እያለም ሕይወቱ አልፏል።

ኤልሜንቾ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ መንግሥት ኤል ሜንቾ እንዲያዝ የሚያደርግ መረጃ ለሚሰጡ ሰዎች የ15 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቅርቦ ነበር

እርሱን ለመያዝ በተደረገው ኦፕሬሽን ቢያንስ ስድስት ጠባቂዎቹ እንደተገደሉ ተገልጿል። ከመንግሥት ኃይሎች መካከል ደግሞ ሶስት ወታደሮች እንደቆሰሉ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

'ኻሊስኮ ኔው ጄኔሬሽን ካርቴል' የተባለውን በሜክሲኮ እጅግ የሚፈራ የወንጀል ቡድን ይመራ የነበረው ኤል ሜንቾ፤ በአገሪቱ ዋነኛ ተፈላጊ ሰው ነበር። የአሜሪካ መንግሥትም እርሱን እንዲያዝ የሚያደርግ መረጃ ለሚያቀርቡ ሰዎች የ15 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቅርቦ ነበር።

የእርሱን ሞት ተከትሎ የእፅ ዝውውር ቡድን አባላት ቢያንስ በ20 ግዛቶች ውስጥ አመጽ አስነስተዋል። አባላቱ መኪናዎችን እና ነዳጅ ማደያዎችን በእሳት ሲያያይዙ እንዲሁም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ሲታኮሱ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

በአንዳንድ ከተሞች በመንገድ ላይ ሹል ብረቶች እና ሚስማሮችን በመበተን መንገዶችን የዘጉ ሲሆን በሌሎች ቦታዎች ደግሞ አውቶቡሶችን እና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን በመቀማት መንገድ መሃል አቃጥለዋል። በርካታ ባንኮች እና ንግድ ተቋማትንም በእሳት አያይዘዋል።

በእሳት የተያያዘ አውቶብስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አመጹ ከተቀሰቀሰ በኋላ በኻሊስኮ ግዛት ውስጥ ቢያንስ 25 የሜክሲኮ ብሔራዊ ዘብ አባላት መሞታቸውን የአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስትር ተናግረዋል። አንድ የእስር ቤት ጠባቂ እንዲሁም አንድ የዐቃቤ ሕግ ቢሮ አባልም ተገድለዋል።

የኤል ሜንቾ የወንጀል ቡድን አባላት የሆኑ 30 ሰዎችም መገደላቸውን የአገሪቱ የደህንነት ሚኒስትር ኦማር ጋርሲያ ሃርፉች መናገራቸውን የዜና ወኪሉ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሼንባውም፤ ኤል ሜንቾ የተገደለበትን የሠራዊቱን ዘመቻ ያደነቁ ሲሆን በመላ አገሪቱ ሠላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጡት ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአገሪቱ መንግሥት ከእሁድ ዕለት አንስቶ በመላ አገሪቱ 9,500 ገደማ ወታደሮችን ማሰማራቱን አስታውቆ ነበር። አሁን ደግሞ ተጨማሪ 2,500 ወታደሮች አመጽ ወደተነሳባቸው አካባቢዎች እንደሚላኩ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።