ከፍተኛ ውዝግብ ስላስነሳው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ማን ምን አለ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካካል "አከራካሪ ሆነው የቆዩ" የተባሉትን አምስት የምርጫ ክልሎች በተመለከተ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ደርሶኛል ያለውን ውሳኔ ይፋ ካደረገ በኋላ የሁለቱ ክልሎች የፖለቲካ ተዋንያን በየፊናቸው መግለጫዎችን አውጥተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) እና ሌሎችም ፓርቲዎች ውሳኔውን በብርቱ ተቃውመውታል።
በአፋር ክልል እና በደቡባዊ የትግራይ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት እና ከትግራይ ኃይሎች በወጡ ወታደራዊ አዛዦች የሚመራው የትግራይ የሰላም ኃይልም በተመሳሳይ ተቃውሞውን አሰምቷል።
በአማራ ክልል በኩል ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አካላት በበኩላቸው "አከራካሪ" ስለተባሉት አካባቢዎች የተላለፈውን ውሳኔ በበጎ ተመልክተውታል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በመግለጫቸው ይህንን አመልክተዋል።
በኮለኔል ደመቀ ዘውዱ የሚመራው በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴም ለውሳኔው ድጋፉን ሰጥቷል።
ከትግራይ ክልል በኩል የተነሳው ጠንካራ ተቃውሞ
ምርጫ ቦርድ በአማራ እና ትግራይ መካካል "አከራካሪ ሆነው የቆዩ" የተባሉትን አምስት የምርጫ ክልሎች "ከትግራይ ውጪ ሆነው" ድምጽ እንዲሰጥባቸው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መተላለፉን ያስታወቀው ሰኞ የካቲት 16/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነበር።
መግለጫው ላይ "አከራካሪ" ተብለው የተጠቀሱት "የሁመራ፣ የአዲረመፅ፣ የኮረም ኦፍላ፣ የጠለምት እና የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች" ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች የተነሳው "የይገባኛል ጥያቄ እስከሚፈታ ድረስ"፤ "ከትግራይ ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ" እንዲካሄድባቸው እንደተወሰነ ተገልጿል።
"የክልል ምክር ቤት ምርጫው በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ መንግሥት ውሳኔ ሲፈታ አመቺ ሁኔታ ተመርጦ ወደፊት እንዲካሄድ" ፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዳስተላለፈ ቦርዱ አስታውቋል።
የምክር ቤቱን ውሳኔ በመቃወም የመጀመሪያውን መግለጫ ያወጣው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ነው። በሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ውሳኔውን "ሕገ መንግሥቱን እና የፕሪቶሪያን ስምምነት በግልጽ የሚቃረን" ሲል ገልጾታል።
"ይህ ውሳኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን የትግራይ ሕገ መንግሥታዊ ወሰኖች በቀጥታ አደጋ ላይ ይጥላል" ብሏል።
ውሳኔው የተላለፈው "የትግራይ ሕዝብ ውክልና እና ድምፅ በሌለበት" የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሆነ የጠቀሰው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ እርምጃውን "በጽኑ" አውግዟል።
"ይህ እርምጃ ሊያስከትል የሚችለው ከባድና ሰፊ መዘዝ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ይህ አደገኛ መንገድ በአስቸኳይ እንደገና እንዲጤን እና እንዲታረም እንጠይቃለን" ብሏል።
ህወሓትም በበኩሉ ባወጣው መግለጫ "የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልጽ የሚጥስ እና በትግራይ ሕዝብ ሕልውና ላይ አደገኛ አደጋ የሚደቅን ነው" ሲል ተቃውሟል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ "ወደ ቀያቸው መመለስ የነበረባቸውን ወገኖቻችንን ተስፋ የሚያጨልም" እንዲሁም "አሁንም በወራሪዎች ሥር ሆነው ግፍና ስቃይ እየደረሰባቸው ያሉ ወገኖቻችንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል የጄኖሳይድ አዋጅ ነው" ሲልም በጠንካራ ቃላት ተቃውሟል።
"ከዚህም ባለፈ በትግራይ እና በአማራ ሕዝቦች መካከል አዲስ ግጭት ለመፍጠር የታለመ ሴራ ነው" ሲል ከስሷል።
የፌደራል መንግሥት "ሕገ መንግሥታዊ ሉዓላዊ የትግራይ መሬትን ለወራሪዎች አሳልፎ ለመስጠት እየሠራ ነው" ሲል የወነጀለው ህወሓት፤ "የትግራይ ሉዓላዊ መሬት እና የሕዝብ ሕልውና ጉዳይ የማይታለፍ ቀይ መስመር" እንደሆነ በአጽንኦት አንስቷል።

የፎቶው ባለመብት, weyn
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ተቃዋሚው ስምረት ውሳኔውን "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝትን የሚያውጅ" ሲል ጠርቶታል።
ፌዴሬሽን ምክር ቤት "ክልሎችን ከነባር አስተዳደራዊ መዋቅራቸው ውጪ በፌደራል መንግሥት ስር እንዲሆኑ የመወሰን ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ውክልና የለውም" ሲል የሕጋዊነት ጥያቄ አንስቷል።
በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የተነሳው ውዝግብ መፈታት ያለበት በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው የክልሎች ወሰን አከላለል ለውጥ ድንጋጌ መሠረት እንደሆነ ጠቀሰው ስምረት፤ ይህ ሂደት አለመጠነቀቁን አስታውሷል።
"ይህ ሕጋዊ ሂደት ሳይጠናቀቅ እና በሕዝበ ውሳኔ ይፋዊ ለውጥ ሳይደረግ" ይህ ውሳኔ መተላለፉ "የክልል አስተዳደረን በጉልበት የመንጠቅ ሙከራ ነው" ብሏል። ውሳኔው በሕግ ፊት "ውድቅና የማይጸና" ነው የሚል አቋሙን ገልጿል።
ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህንን እርምጃ "በአስቸኳይ እንዲያቆም እና ለሕገ መንግሥቱ የበላይነት እንዲገዛ" ያሳሰበው ስምረት፤ "የማስተካከያ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ በምርጫም ሆነ በመሰል ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ እንደማይሳተፍ" አስታውቋል።
ከትግራይ ኃይሎች ተነጥለው በወጡ ወታደራዊ አዛዦች የሚመራው የትግራይ ሰላም ኃይል የተባለው ታጣቂ ቡድንም ውሳኔውን "አጥብቆ እንደሚቃወም" ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የታጣቂ ቡድኑ ወታደራዊ ምክር ቤት ያወጣው ይህ መግለጫ፤ "እንድንታገል ምክንያት ከሆኑን ወሳኝና ከምንም በላይ ቦታ የምንሰጠው ጉዳያችን አንዱ የተጋሩ ህልውና ነው" ብሏል።
የህልውና ጉዳይ "ያለ ርስት ባለቤትነት እና ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በፍጹም ሊረጋገጥ አይችልም" የሚል እምነት እንዳለውም አክሏል። ቡድኑ የትግራይ "ርስት እና ሉዓላዊ ሕገ መንግሥታዊ ግዛቶች" ሲል በጠራቸው በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ውሳኔ የተላለፈው "የተጋሩ ውክልና በሌላው የፌዴሬሽን ምክር ቤት" ነው ሲልም በመግለጫው አስፍሯል።
"ይህ ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን እና የፕሪቶሪያውን ውል በመጣስ ፌዴሬሽኑንም ሆነ ቀጣናውን ወደ ፍፁም አደጋ እንደሚያስገባው" አስገንዝቧል። ይህንን በመገንዘብ "በአፋጣኝ እርምት ከማድረግ ባሻገር ሕገ መንግሥቱን እና የፕሪቶሪያውን ውል የጣሰ ውሳኔ ያሳለፉ አካላትን የፌደራል መንግሥት በሕገ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ" ጠይቋል።

የፎቶው ባለመብት, AWRA
"የሉዓላዊ ግዛታዊ አንድት" ጉዳይ "ቀይ መስመር" መሆኑን ገለጸው ቡድኑ፤ "ተጋሩ የትም ብንሆን በኅልውናችን እና በርስታችን ፍፁም ልዩነት ሊኖረን [አይገባም]" ብሏል።
ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይም በተመሳሳይ ውሳኔውን "የትግራይን ሕልውና እና ግዛታዊ አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል"፣ ሕገ መንግሥቱን እና የፕሪቶሪያ ስምምነትን "የሚጥስ" እንዲሁም "ወረራን የሚያበረታታ" በማለት ተቃውሞታል።
ፓርቲው "የትግራይ ሕዝብ በተጨባጭ በማይወከልባቸው ፌደራል ተቋማት የመነጨ" ሲል የጠራው ይህ ውሳኔ፤ "ምንም ዓይነት ሕጋዊም ሆነ የሞራል ተቀባይነት" እንደሌለው በመግለጫው አስፍሯል። ውሳኔው "በአስቸኳይ እንዲሻር" እና አምስቱ የምርጫ ክልሎች "በትግራይ ሕገ መንግሥታዊ ግዛት ውስጥ" እንዲደረጉ አሳስቧል።
ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ደግሞ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ፤ ውሳኔው "የፌደራል እና ክልሎች ግንኙነትን እንዲሁም የአስተዳደር ሥልጣንን በተመለከተ ከተቀመጡት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር ያልተጣጣመ" ነው ብሏል።
"ውጥረትን መቀነስ እና ሁሉን አቀፍ ውይይት በአስቸኳይ በሚያስፈልግበት በዚህ ጊዜ" ይህ ውሳኔ መተላለፉ፤ "ለወታደራዊ እንቅስቃሴ መጨመር እና ለፖለቲካዊ ውጥረት መባባስ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል" ሲል አስጠንቅቋል።
ውድብ ናፅነት ትግራይ፣ ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት፣ ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ እንዲሁም ውድብ ወለዶ ትግራይ ውሳኔውን በመቃወም መግለጫ ያወጡ ሌሎች የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።
የአማራ ክልል ፓርቲዎች ድጋፍ
ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያስተናገደው ተቃውሞ ብቻ አይደለም። ተቃዋሚው ፓርቲ አብን ባወጣው "አስቸኳይ የአስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ" ውሳኔውን "እንደሚያከብር" አስታውቋል።
ፓርቲው የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ የሚያከብረው "ከፕሪቶሪያ ስምምነት መንፈስ አንጻር" እንደሆነ እንዲሁም "መንግሥት ከአገራዊ ሁኔታዎች አንጻር" የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችን "ሙሉ በሙሉ እንደማይመቹት" በመግለጫው ጠቅሷል።
"ችግር ፈጣሪዎች የሚደመጡበት፣ የሕዝብ ድምጽ ግን የሚታነቅበት ሁኔታ ከእንግዲህ እንዲቀጥል አንፈቅድም" ሲል አቋሙን ገልጿል።
የይገባኛል ጥያቄዎች በሚነሳባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ "ለክልሉ ምክር ቤት ጭምር ምርጫ መካሄድ እንዳለበት" አሳስቧል።
ይህንን በማድረግ "በባህል፣ በሥነ ልቦና እና በማንነት ከሚመስለው እና በአለበት አስተዳደር ወሰን ማለትም በአማራ ክልል ምክር ቤት ጭምር ተሳትፎ እንዲኖረው" ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል።
እንደ አብን ገለጻ፤ አካባቢዎቹ በአማራ ክልል ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲባል የሚነሳው የይገባኝ ጥያቄ "ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ ሕገ መንግሥታዊ ገደብ-ዘለል እና ልዩ ፖለቲካዊ ውሳኔ" መተላለፍ አለበት።
"የሕዝባችን ጥያቄ የጥፋት ኃይሎችን 'ለማባበል' ወይም ለሽንገላ ሊውል እንደማይገባ በጥብቅ እናሳስባለን" ሲልም ፓርቲው አቋሙን ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of innovation and technology
ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በበከሉ "የሕዝባችንን የማንነት ትግል ዕውቅና የሰጠ" ሲል ውሳኔውን አድንቋል። "የዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ማሳያ አድርጎ" እንደሚወስደውም በመግለጫው አስታውቋል።
"ይህ ውሳኔ ለብዙ ዓመታት በግፍ እና በጭቆና ተረግጦ የቆየውን የአማራ ማንነት ጥያቄ በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው" ሲልም አሞካሽቷል።
በእነዚህ አካባቢዎች "የሚገኙ ማኅበረሰቦች በመጪው ምርጫ ራሳቸውን ችለው እንዲወዳደሩ መወሰኑ"፤ "በትግላችን የመሠረትነውን የአስተዳደር መዋቅር ወደ ተሟላ ሕጋዊና ሕዝባዊ መሠረት ይለውጠዋል" ብሏል።
የአካባቢዎቹ ሕዝብ "በምርጫው በመሳተፍ በንቃት እንዲመዘገብ እና በድምፁ ተወካዮችን እንዲመርጥም" ጥሪ አቅርቧል።
በአማራ ክልል ሥር የተመሠረተው የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት፣ ሁመራ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ በሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሰብሳቢነት የሚመራው የማንነት አስመላሽ ኮሚቴም በተመሳሳይ ለውሳኔው ድጋፉን ገልጿል።
ኮሚቴው ለምርጫ ቦርድ እና ለፌደሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ ውሳኔውን "ለዓመታት የፖለቲካ መብታቸው ተገፍፎ ለኖሩ ዜጎች የዲሞክራሲ ጭላንጭል የፈነጠቀ ታሪካዊ እርምጃ" መሆኑን ገልጿል። ኮሚቴው የሚያቀነቅነውን የማንነት ጥያቄ "ለመፍታት እንደ አንድ እርምጃ" እንደሚቆጥረውም አስታውቋል።
ይሁን እንጂ ይህን ምርጫ ለማስፈጸም "የመንግሥት ጥበቃ እና የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አፈጻጸም" አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሷል።
ምርጫ ቦርድ "ከምክር ቤቱ የተላለፈለትን ተግባራዊ" እንዲያደርግ እንዲሁም ከዚህ ቀደም "ህወሓት በወሰነው ሕገ ወጥ አከላለል ተፅዕኖ ስር" እንዳይወድቅ አሳስቧል።
"የወልቃይት ጠገዴ እና አካባቢው ሕዝብ ያለ ማንም ስጋት እና ጫና የራሱን ተወካዮች እንዲመርጥ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩም" ጠይቋል።
በተጨማሪም ኮሚቴው ተቃዋሚው ፓርቲ ስምረት ውሳኔውን "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነት" እንዲሁም "የአስተዳደር ነጠቃ" በማለት ያሰማውን ተቃውሞ ተችቷል። ስምረት፤ "እውነተኛውን እና ፍትሐዊውን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጥያቄ ለመደፍጠጥ እና ለማፈን" ሞክሯል ሲልም ተቃውሟል።














