"በይገባኛል ውዝግብ፣ በአስተዳደር ለውጦች እና በሰላም እጦት" እየተፈተኑ ያሉ የራያ አካባቢ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Alamata Comm.
በትግራይ እና በአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የራያ አካባቢ ነዋሪዎች በየጊዜው በሚለዋወጥ አስተዳደር እና በሚከሰት ግጭት ምክንያት ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሕይወት ከራቃቸው ዓመታት ተቆጥረዋል።
የሰሜኑን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ሥር የገባው አካባቢው ከዚያ በኋላ አንዴ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሌላ ጊዜ በአማራ ክልል ከዚያም በፌደራል ኮማንድ ፖስት ሥር ሲተዳደር ነበር።
በዚህም ምክንያት የትራንስፖርት፣ የትምህርት እና ሌሎች መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ወጥነት በሌለው እና በተቆራረጠ መልኩ ሲሰጡ ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት ጥር 22/ 2018 ዓ.ም በአካባቢው ተሰማርቶ የፀጥታ ሁኔታን ሲያስከብር የነበረው መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ለቅቆ ከወጣ በኋላ አካባቢው በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የፌደራል መንግሥቱ ጋር ሲዋጉ በነበሩት የትግራይ ኃይሎች ሥር ገብቷል።
በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በተለይ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች አካባቢዎች መፈናቀላቸውን ተፈናቃዮች እና ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በተፈጠሩ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ከአራት ጊዜ በላይ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
ሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. የትግራይ ታጣቂዎች ወደ ራያ አላማጣ አካባቢዎች ከገቡ በኋላ ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው ነበር።
በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተፈናቅለው በቆቦ የተጠለሉ ሰዎች 42 ሺህ ገደማ እንደሚደርሱ በሪፖርቱ ገልጿል።
ከዚያም የአካባቢውን ፀጥታ ከሚያስከብረው የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመነጋገር ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።
ሆኖም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ ያሉ "ትምህርት ቤቶች ተዘግተው መቆየታቸውን እና አንዳንዶቹም የተዋጊዎች ማረፊያ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር" ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
በአላማጣ ከተማ ስምንት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የጠቀሱት ወላጁ፣ ሁሉም በመዘጋታቸው ልጆች ለሥነ ልቦና ችግር እንዲሁም ለስደት እየተዳረጉ ነው ብለዋል።
የአሁኑ መፈናቀል እና ውጥረት የመጣውም አካባቢው በዚህ ያልተረጋጋ ሁኔታ ባለበት ወቅት ነው።
"ከ60 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል"
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ "ብዙ ሕዝብ ነው የተፈናቀለው። ይህን ለማወቅ ከተማው ላይ ያለውን ሁኔታ ማየት በቂ ነው። ከተማው ባዶ ነው። የተፈናቀሉ ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ ግን አላውቅም" ብለዋል።
እነዚህ የተፈናቀሉ ሰዎች መደበኛ የሆነ መጠለያ ተዘጋጅቶላቸው ያረፉበት ቦታ እንደሌለ የገለጹት ነዋሪው፣ በሆቴል አልጋ ይዘው እና ለሦስት ለአራት ቤት ተከራይተው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
"ለዚህም በአንድ ቀን ለአልጋ ብቻ በትንሹ 400 ብር አካባቢ ለመክፈል ተገደዋል" ብለዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በአማራ ክልል የተሾሙ የቀድሞ የአካባቢው ባለሥልጣን በበኩላቸው ከ60 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።
"የተፈናቀሉት ሰዎች ከ60 ሺህ በላይ ይሆናሉ። ከራያ አካባቢ ከሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ነው የተፈናቀሉት። ወደ ቆቦ፣ ወልዲያ፣ ሰቆጣ ፣ ደሴ እንዲሁም ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሄዱ አሉ" ብለዋል።
ቢቢሲ የቀድሞ ባለሥልጣኑ የጠቀሱትን ቁጥር ከገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።
የቆቦ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ኃይለአብ ወንድምአገኝ በከተማዋ በተለያየ ቦታ የተፈናቀሉ ሰዎች እንደሚገኙ ፤ ነገር ግን የተፈናቃዮችን ቁጥር እና ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ አመራሮች መረጃዎችን እያሰባሰቡ እንደሆነ እና ሲደርሳቸው እንደሚገልጹ ተናግረዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አለሙ ይመር በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ እየተነጋገሩ እንደሆነ ገልጸው፤ ቆይተን እንድንደውል ከነገሩ በኋላ ስልካቸው ሳይነሳ ቀርቷል።
ከአካባቢው ከተፈናቀሉት በተጨማሪ እዚያው ያሉ ነዋሪዎችም በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል
አላማጣ ከተማ የሚኖሩ አንዲት እናት "ሰዎች ተፈናቅለው እንደወጡ እና እርሳቸው ግን ከቤተሰባቸው ጋር ተደብቀው እንደሚገኙ" ተናግረዋል።
"ልጆቼን ይዤ ብወጣ ምን አበላቸዋለሁ፣ የትስ አርፋለሁ? ብዬ አልወጣሁም፤ ግን ስጋት ውስጥ ነው ያለሁት" ብለዋል።
አካባቢውን የተቆጣጠሩት የትግራይ ኃይሎች ፖሊስ ጣቢያዎችን ጨምሮ ቢሮዎችን መክፈታቸውን የገለጹት ነዋሪዋ፣ "የሃይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎችን ጨምሮ. . .ሰዎች ታፍነው እንደሚወስዱ፣ እንደሚታሰሩ እና በከተማዋ ከፍተኛ ዘረፋ እንደሚፈጸም " ታፍነው ተወስደዋል ያሏቸውን ሰዎች በስም ጠቅሰው ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች ቀደም ብሎ አንድ ሺህ ብር ማውጣት እንደሚፈቅዱላቸው፤ ነገር ግን አሁን ላይ ይህ እንደሌለ በመግለጽም "እናቶች የዕለት ፍጆታ ለመግዛት እና ልጆቻችንን ለመመገብ ተቸግረናል" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በተዘረጉ ኬላዎች ፍተሻ እንደሚያደርጉ እና "ማንነት በመለየት የአማራ ሰዎች ዒላማ ይደረጋሉ፤ የፋይዳ መታወቂያ ካገኙም ይሰባብራሉ" ሲሉም ከስሰዋል።
በምርጫ ቦርድ ሕጋዊነቱ የተሰረዘው ህወሓትም ሆነ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአካባቢው ስላለው ሁኔታ እና ስለሚቀርቡ ክሶች ያሉት ነገር የለም።
ቢቢሲ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ሥር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ የሆኑትን ምሆስ ሺፈራውን እንዲሁም ደቡባዊ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዝናቡ ገብረመድኅንን ለማነጋጋር ያደረገው ሙከራም ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።
ትጥቅ ያልፈቱ የትግራይ ኃይሎች እና የዳግም ግጭት ስጋት
የሰሜኑን ጦርነት ከቋጨው የፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የትግራይ ኃይሎች እና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አዛዦች፤ የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለማሰናበት እና መልሶ ለማቋቋም በናይሮቢ የመግባቢያ ሰነድ ቢፈራረሙም አሁንም ድረስ ትጥቅ ያልፈቱ በርካታ ተዋጊዎች አሉ።
ግንቦት ወር 2016 ዓ.ም. የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተስፋዓለም ይሕደጎ በስምምነቱ መሰረት 274 ሺህ 800 የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንደሚፈቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ሆኖም ይህ በተባለ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ትጥቅ ፈትተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት የተቀላቀሉት 63 ሺህ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ከአንድ ወር በፊት ኮሚሽኑ ገልጿል።
የስምምነቶች አፈፃፀም መጓተት እና መጣስ በተደጋጋሚ ለሚነሱ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች አንዱ ምክንያት ሆኗል።
ባለፈው ሳምንትም የትግራይ ኃይሎች እና የአገር መከላከያ ሠራዊት በጸለምት አካባቢ ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።
የትግራይ እና አማራ ክልሎች በሚወዛገቡበት ጸለምት በሚገኙት ማይ-ዳጉሻ፣ ማንጫራ እና ሌሎች ሥፍራዎች በከባድ መሳሪያ የታጀበ ውጊያ መታየቱን ሪፖርቶች አመልክተዋል።
አሁንም ሌላ ዙር ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት በነዋሪዎች ዘንድ ነግሷል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ሐሙስ ጥር 28/2018 ዓ.ም. በኤምባሲው የማኅበራዊ ሚዲያ ገፅ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፤ ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ ያጋጠሙ ክስተቶችን በመጥቀስ፣ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስታውሰዋል።
ማሲንጋ "ዘላቂ ሰላም ከባድ ሥራ፣ ምክንያታዊነት እና ስክነትን" የሚጠይቅ ቢሆንም የተሻለው መንገድ ይህ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, North Wollo Communication
በትግራይ በኩል ደቡብ ትግራይ በሚል ስያሜ የሚጠራው የራያ አካባቢ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ኦፍላ እና ዛታ ወረዳዎች፣ ኮረም ከተማ፣ አላማጣ ከተማ፣ ራያ አላማጣ ወረዳ እና ራያ ባላ ወረዳ ናቸው።
የፌደራል መንግሥቱ አወዛጋቢ ቦታዎች በዘላቂነት ለመፍታት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ከሁለቱ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ከዚህ ቀደም መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ እነዚህ አካባቢዎች ሕዝቡ በሚመርጠው አስተዳደር እንደሚተዳደሩ በተደጋጋሚ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥር 26/2018 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ውስጥ በሰጡት ማብራሪያ ወቅት አወዛጋቢ የሆኑ አካባቢዎችን ጉዳይ አንስተዋል።
በዚህ ማብራሪያቸው ወልቃይትን ብቻ በስም ጠቅሰው ያነሱ ሲሆን፣ ውዝግቦች በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈቱ የፌደራል መንግሥት ፍላጎት እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል።















