የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የፓርላማ ንግግር አስተባበሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ሠራዊት የሚፈጽማቸውን ግፎች እንዲያቆም የሚጠይቅ መልዕክት ወደ አሥመራ እንደላኩ የገለጹበትን የፓርላማ ንግግር የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አስተባበሉ።
በወቅቱ ወደ ኤርትራ ተልከው እንደነበር ያመኑት ገዱ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጣቸው መልዕክት "ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዘ የስም ማጥፋት ዘመቻ" ላይ "የጋራ ጥንቃቄ" እንዲደረግ የሚጠይቅ እንደነበር ተናግረዋል።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ጦር "አንድ አገር ሠራዊት በሚመስል ሁኔታ" ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር "አብሮ ሲሠራ" እንዲሁም "እስከ ደብረ ታቦር ድረስ መጥቶ" ሲዋጋ ነበር ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት የጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ መንግሥት ተቃዋሚ የሆኑት ገዱ፤ ይህንን ምላሽ የሰጡት ረቡዕ ጥር 27/2018 ዓ.ም. እንደተጻፈ በተገለጸ ደብዳቤ ነው።
አሁን በአሜሪካን አገር የሚገኙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሠራጨው ይህ ደብዳቤ የእሳቸው መሆኑን እና ትክክለኛነቱን በቢቢሲ ተጠይቀው አረጋግጠዋል።
የቀድሞው ባለሥልጣን ይህንን ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሰኞ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር እርሳቸውን "በእማኝነት ቆጥረው" ማብራሪያ በስጠታቸው እንደሆነ በደብዳቤያቸው ላይ ጽፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጉዳይ አንስተው ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር በሁለቱ አገራት መካከል "ጸብ የተጀመረው" በትግራይ ጦርነት ወቅት እንደሆነ ገልጸው ነበር።
በወቅቱ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ የነበረው የኤርትራ ወታደሮች አክሱም ከተማ ውስጥ "ወጣቶችን በጅምላ መረሸናቸውን" ተናግረዋል። ሽረ፣ አድዋ እና አዲግራት ከተሞች ውስጥ ፋብሪካዎች እንዲሁም ፎቆዎችን እንዳወደሙም በማንሳት ከስሰዋል።
እነዚህ ግፎች መፈጸማቸውን ተከትሎ "በርካታ መልዕክተኞች ወደ ኤርትራ" መላካቸውን የገለጹት ዐቢይ፤ ከእነዚህ ልዑካን አንዱም የቀድሞው የካቢኔ አባል ገዱ መሆናቸውን አንስተዋል።
ዐቢይ "ክቡር አቶ ገዱ ያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። ከአንዴም ሁለቴ ኤርትራ ልኬያቸዋለሁ። የላኩዋቸው 'የትግራይን ሕዝቤን አታጎሳቁሉ፣ ሀብቱን አትዝረፉ፣ ጸቡ ከህወሓት እንጂ ከትግራይ ሕዝብ አይደለም' የሚል ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
"አቶ ገዱ አሁን እኛ ጋር የሉም፤ ግን ክር አላቸው፣ ሕሊና አላቸው። ዛሬ ቢደብቁ በታሪክ ውስጥ ይወጣል። ለምን ጉዳይ ሄደው እንደተነጋገሩ እሳቸውም ያውቃሉ፣ ሻዕቢያም ያውቃል፣ እኛም እናውቃለን" ሲሉም የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እማኝነታቸውን ሊሰጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ከአቶ ገዱ በተጨማሪ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር "ደመቀ መኮንን" እና "አሁን ሲስተሙ ውስጥ ያሉ ሁለት ሦስት ሰዎችም" ተመሳሳይም መልዕክት ይዘው ወደ ኤርትራ መጓዛቸውን አንስተዋል።
ለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ምላሽ የሰጡት ገዱ፤ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደበሩ መገለጹን አስተባብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia
በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ገዱ፤ በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ የቆዩት እስከ የትግራይ ጦርነት መጀመር ድረስ ነበር። ጦርነቱ ከተጀመረ አንድ ቀን በኋላ በጥቅምት 25/2013 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚንስትር ሆነው እንደተሾሙ ተገልጾ ነበር።
ገዱ በደብዳቤያቸው፤ በጥር 2013 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለማድረስ "ከአንድ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን" ጋር ወደ አሥመራ ተጉዘው እንደነበር አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ በወቅቱ ወደ አሥመራ የወሰዱት መልዕክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተገለጸው እንዳልሆነ በማንሳት አስተባብለዋል።
"ሕዝቤን አታጎሳቅሉ የሚል መልዕክት አስይዘው እኔን ወደ ኤርትራ የላኩኝ መሆኑን እንዳረጋግጥ ምስክርነት ጠርተውኛል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ ላይም ትልቅ ስህተት ፈጽመዋል" ብለዋል።
እንደ አቶ ገዱ ገለጻ ወደ ኤርትራ የተላከው መልዕክት "ሦስት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ" ነበር። በቀዳሚነት የጠቀሱት የመልዕክት ጭብጥ የደስታ መግለጫን የሚመለከት ነው።
"በወያኔ ላይ በጋራ በወሰድነው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለድል በመብቃታችን የእንኳን ደስ አለህ የደስታ መግለጫ ለፕሬዚደንት ኢሳያስ ማስተላለፍ [የሚል ነበር]" ሲሉ የመጀመሪያ ያሉትን መልዕክት ይዘት ገልጸዋል።
ሁለተኛው መልዕክት "ለኤርትራ መንግሥት እና ሕዝብ ምስጋና መቅረብን" የሚመለከት ነበር ብለዋል። ምስጋናው የቀረበው ኤርትራው ፕሬዝዳንት መንግሥት "የሰሜን ዕዝ ጥቃት በደረሰበት ወቅት ሠራዊቱን ተቀብለው ላደረጉት እንክብካቤ" እንዲሁም "ኋላም ለመልሶ ማጥቃት እንዲዘጋጅ ላደረጉት ወንድማዊ ድጋፍ" እንደሆነም ገዱ ገልጸዋል።
በቀድሞው ከፍተኛ ባለሥልጣን ገለጻ መሠረት "ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ" ተከፍቷል የተባለ "ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ" ጉዳይ ደግሞ ሦስተኛው የመልዕክት ይዘት ነው።
ይህ ዘመቻ "አንዳንድ ወያኔ ደጋፊዎች እና ኢትዮጵያን እና የኤርትራን መልካም ግንኙነት የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሚዲያዎች አማካኝነት" የከፈቱት እንደሆነ በመልዕክቱን ላይ መካተቱን ጠቅሰዋል።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ "ይህ ነገር ውሎ አድሮ በሁለታችንም ላይ ጣጣ ሊያመጣብን ስለሚችል የጋራ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል" የሚል መልዕክት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
እነዚህ መልዕክቶች ከተሰጧቸው በኋላ "ለምን የኤርትራ መንግሥት ሠራዊቱን እንዲያስወጣ በግልጽ አንነግራቸውም" የሚል ሀሳብ በተጨማሪነት እንዳነሱ ጠቅሰዋል።
"እርስዎ ግን ሠራዊታችሁን አስወጡ ብለህ በፍጹም እንዳትጠይቅ ብለው አስጠነቀቁኝ። ከዚያም የሰጡኝን ተልዕኮ ተብዬ ተለያየን" ሲሉም ተሰጠኝ ያሉትን ምላሽ ገልጸዋል።
አክለውም "ከዚህ ውጪ የትግራይን ሕዝብ በተመለከተ ያነሱልኝም ሆነ የሰጡኝ ምን[ም] ዓይነት መልዕክት አልነበረም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ ያደረጉን ንግግር አስተባብለዋል።
"በወቅቱ የእርስዎ ጭንቀት የተከፈተበብን የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ ሊያስከትልብን የሚችለው ጣጣ ነው እንጅ የትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰሰው መከራ በፍጹም አጀንዳዎት አልነበረም" ሲሉ ከስሰዋል።
ገዱ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጣቸውን መልዕክት ይዘው ወደ ኤርትራ እንደተጓዙ እንዲሁም ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል። ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ሲያቀርቡ "በያዝነው መልዕክት ላይ ምንም ያወዛገበን ነገር አልነበረም" ብለዋል።
ተከፍቷል የተባለውን "የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘመቻ" በተመለከተ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት የተሰጣቸው ምላሽ "የሚቻለው ጥንቃቄ እንዲደረግ እኛም እናንተም ለበታች መዋቅሮቻችን መመሪያ እናስተላልፍ፣ በተረፈ እኔና ዐቢይ በተስማማነው መሠረት ገና ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች አሉን የሚል ነበር" ብለዋል።
ይህንንም ምላሽ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማድረሳቸውን ጠቅሰዋል። ገዱ በዚህ ደብዳቤያቸው የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ጦርነት ስለነበረው ተሳትፎም አንስተዋል።
"የትግራይ ጦርነት ተጀምሮ በፕሪቶሪያ ስምምነት እስኪቆም ድረሰ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን ሳይሰለፍ የቀረበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም" ብለዋል።
"ሌላው ቀርቶ በ2013 ክረምት ላይ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል አልፈው በገቡበት ወቅት የኤርትራ ሠራዊት እስከ ደብረ ታቦር አካባቢ ድረስ መጥቶ እናስታውሳለን" በማለት ጽፈዋል።
መከላከያ ሠራዊት እና የኤርትራ ጦር "በአንድ ላይ ወታደራዊ ኦፕሬሽን መሥራት ያቆሙት" የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈጸመ በኋላ ነው ብለዋል። "እስከዚያው ድረስ ግን የአንድ አገር ሠራዊት በሚመስል ሁኔታ አብረው ነበሩ" ሲሉ በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።















