ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ጦርነት የኤርትራ ወታደሮችን የተለያዩ ጥፋቶች በመፈጸም ከሰሱ

ጠ/ሚ ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, HoPR

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ትግራይ ውስጥ በኤርትራ ወታደሮች የተለያዩ ጥፋቶች መፈጸማቸውን እና በአገራቱ መካከል አሁን ለተባባሰው ችግር መነሻ መሆኑን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 26/2018 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በኤትርትራ ወታደሮች ተፈጸሙ ስላሏቸው ውድመቶች ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ጉዳይን ስታነሳ ነው የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን በማንሳት ይህ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል አለመግባባት የተጀመረው በትግራይ ጦርነት ወቅት መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥፋቶች በኤርትራ ወታደሮች መፈጸማችን ተናግረዋል።

"ኤርትራ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ችግር ነበረ። እኛ ከመጣን በኋላ አያስፈልገንም ይቅርብን ብለን ለምነናል" ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

"ፀቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባሕር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ወጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ የአንዳንድ ግለሰቦችን ቤት፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ፀብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም አንጂ።

"አክሱምን ይዘን ስናልፍ፤ አክሱም ገብቶ ወጣቶችን በጅምላ ሲረሽን ፀብ ተፋገፍሟል። አድዋን ይዘን ስናልፍ፣ አድዋ ሄዶ ፋብሪካዎችን ሲፈታታ፣ ሲሰርቅ ፀብ ተጋግሏል።

"አዲግራት ደርሰን የመድኃኒት ፋብሪካውን የሚነቀለውን ነቅሎ የማይነቀለውን ሲያፈራርስ ፀቡ ጫፍ ደርሷል።ግን ያኔ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህም በዚያም ለመዋጋት አቅም አልነበረውም።"

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውን እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ደመቀን ወደ ኤርትራ መላካቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ጦር ወደ መቀሌ ሲጠጋ የኤርትራ ጦር ልክ በሌሎች ከተሞች እንዳደረገው ሁሉ በመቀለም ተመሳሳይ ጥፋቶችን ሊፈጽም ይችላልበሚል ስጋት ከውቅሮ እንዳያልፉ መነጋገራቸውን እና የሚያልፉ ከሆነ ግን "ወደ እናንተ ነው የምንዞረው" በማለት በአካባቢው "የሚጠብቅ ኃይል አስቀምጠን ነው መቀለ የገባነው" ብለዋል።

ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም "እንዴት ህወሓት ሳይጠፋ እንዴት ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል በሚል ነው ፀቡ ጫፍ የደረሰው" ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም ኢትዮጵያን መጉዳት የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን ተናግረው "ገንዘብ ፋይናንስ ያደርጋሉ እመኑኝ ግን ኢትዮጵያን ግን አይችሏትም። ገንዘባቸውን ያፈሳሉ፤ ይከስራሉ እኛ ጉዟችንን እንቀጥላለን።"

ለሕዳሴ ግድብ ብድር እና እርዳታ አልተወሰደም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት አንድም ብድር እና እርዳታ ከየትኛውም ወገን አለመውሰዷን ተናግረዋል።

"በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኛ አቋም፤ በአገርም ውስጥ ከአገር ውጪም ባሉ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ጨክነው በጋራ ቆመው ስለሠሩ የተከወነ ፕሮጀክት ነው" ሲሉ ለግድቡ ግንባታ ብድርም ሆነ እርዳታ እንዳልወሰደች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው የታላቁ ሕዳሴ ግደብን ግንባታን በገንዘብ መደገፏን በቅርቡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆየ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምላሽ በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ የተሰጠ ይፋዊ መልስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ገንብታ ብቻ እንዳልቆመች በመግለጽ "ከአፍሪካ ሦስተኛ የሆነውን ኮይሻን እየሠራች ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ሥራ አለመቆሙን ለምክር ቤት አባላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአፍሪካ አንደኛው ኤርፖርት ግንባታም ተጀምሯል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ጋር

የፎቶው ባለመብት, PM Office

'ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ኮሜርሻል ብድር አልተበደረችም'

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያ እርሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት "ኮሜርሻል ብድር" እንዳልተበደረች ተናግረዋል።

ከለወጡ በፊት ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ብድር እንደነበረባት እና አበዳሪ አገራት ኢትዮጵያ መክፈል አትችልም አናበድርም ያሉበት ሁኔታ እንደነበረም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ዓመታት ለፕሮጀክቶች በሚል ሰበብ ጤነኛ ያልሆነ የብድር ስምምነት ወይንም 'ኮሜርሻል ሎን' ከአንዳንድ አገራት በመበደር ለመክፈል ሳትችል መቅረቷን ተናግረዋል።

"ኢትዯጵያ ብድር መበደር የማትችል የሚል ታርጋ" ተሰጥቷት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተካሄደው የኢኮኖሚክ ሪፎርም ይህንን አሻሽሏል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት 2025 አስር ፈጣን ዕድገት የተመዘገበባቸው የዓለም አገራት መካከል አምስቱ አፍሪካውያን ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ናት" ብለዋል።

የኢኮኖሚክ ሪፎርሙ "እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ ታሪክ አመርቂ ውጤት የመጣበት ዘመን ነው"

አሁን ያለው የኢትዯጵያ የኢኮኖሚክ ዕድገት በማንም ዐይን በማንም መመዘኛ ምንም የሚያከራክር ሁኔታ ውስጥ ያለ አይደለም።

በሪፎርሙ ውስጥ ቴክኖሎጂ ቀዳሚ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ታሳቢ በማድረግ መንግሥታቸው የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ አንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከጥቂት ወራት በኋላ ሰባት ወራት ግንባታው የሚጠናቀቀው "የኤአይ ዩኒቨርስቲ በዓለም ሁለተኛው ነው" ነው ብለዋል።

በዓለም እስካሁን አንድ ብቻ ነው የኤአይ ዩኒቨርስቲ መኖሩን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ "ሥራ ይጀምራል" ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ ክምችት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኑሮ ውድነቱ በዜጎች ላይ የፈጠረው ጫና እንዳለ ሆኖ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚው መስክ አስገራሚ መነቃቃት እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በቢሊየኖች የሚቆጠር ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰው፣ አገሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት በታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ አግኝታለች ብለዋል።

በዚህም መሠረት ከሸቀጦች ንግድ 4.5 ቢሊየን ዶላር፣ ከአገልግሎት ዘርፍ 4.6 ቢሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ሃዋላ 2.3 ቢሊየን ዶላር፣ እንዲሁም ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል።

በአጠቃላይ በስድስት ወራት ውስጥ 11.3 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ቤት የገባ ሲሆን፤ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ነው ብለዋል።

በዚህም የተነሳ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ ወደማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነት እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ እየፈተነ ስላለው የዋጋ ንረት ሲናገሩ፤ ችግሩ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣም እንዲሁም የገቢ መጠን ማነስ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።

መንግሥት ይህንን ጫና ለማቅለል በነዳጅ፣ በማዳበሪያ እና በመድኃኒት ላይ በቢሊየኖች የሚቆጠር ድጎማ እያደረገ መሆኑን፣ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን እና የገበያ ሥርዓቱን ለማዘመን አማራጮችን በማስፋት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዘንድሮው ምርጫ "ሰላማዊ"፣ "ፍትሃዊ"፣ "አካታች" ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከተካሄዱት ምርጫዎች የተሻለ እንዲሆን "አበክረን ነው እየሰራን ያለነው" ሲሉም አክለዋል።

የመንግሥት ኃላፊዎች በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አሁን እኔ የተሻለ ምርጫ ይኖራል እያልኩ ነው፤ አንዳንዶች ሰግታችኋል ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልሱ በውጤት እንየው ነው" ብለዋል።

ምርጫው ባለፈው ከነበረው ምርጫ አሳታፊ እንዲሆን ይሰራል በማለት "የአንድ ፓርቲ ድምጽ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም" ብለዋል።

አክለውም የኔ እምነት ይህ ፓርላማ አሁን ካለው አምስት እና የአስር ሰዎች ድምጽ፣ በአምስት እና አስር እጥፍ ያድጋል የሚል እንደሆነ ተናግረዋል።