ህወሓት በትግራይ ክልል እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለውን ጉዳይ ለመፍታት "ለንግግር ዝግጁ ነኝ" አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት የፈጠረውን በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት " ለንግግር ዝግጁ መሆኑን" ገለጸ።
ህወሓት ትናንት ጥር 23/2018 ዓ.ም በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራውና ለአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ ላይ "ለሰላም እና መረጋጋት" ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቆ "እንደ ሁልጊዜው ለንግግር ዝግጁ ነኝ" ብሏል።
ሕጋዊነቱ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት በዚህ ደብዳቤው ኮሚሽኑ ባለፉት ቀናት በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት እንዲረግብ ሁሉም ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መጠየቁን አወድሷል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ አርብ ዕለት ባወጡት መግለጫ የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት በክልሉ ያለውን ሁኔታ ላለማባባስ "በከፍተኛ ሁኔታ እንዲታቀቡ" መጠየቃቸው ይታወሳል።
በትግራይ ክልል አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉት "ሰሞነኛ ክስተቶች እጅግ እንዳሳሰቧቸው" ኮሚሽነሩ አክለው ገልጸዋል።
የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በደብዳቤያቸው ድርጅታቸው በትግራይ እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለውን ጉዳይ ለመፍታት "ንግግር ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ" ያምናል ብለዋል።
ህወሓት ለኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ "ሀቀኛ፣ አካታች እና ውጤት ተኮር ውይይት ለማካሔድ ቁርጠኛ መሆኑን" ገልፆ፣ የአፍሪካ ኅብረት ይህን እንደሚያደርግ እምነት እንዳለው አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ህወሓት "ገንቢ በሆነ መንገድ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውይይት ለማድረግ" ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ባለፉት ቀናት የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡበት ጸለምት አካባቢ በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ግጭት መከሰቱ ተዘግቧል።
የዜና ወኪሎቹ ኤኤፍፒ እና ሮይተርስ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ጸለምት አካባቢ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት መካሄዱን የደኅንነት እና የዲፕሎማቲክ ምንጮችን በመጥቀስ ዘግበዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) ካለፈው ሳምንት እሁድ ዕለት ጀምሮ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች መካከል በሚገኙ "አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች" ግጭቶች መቀስቀሳቸውን አረጋግጧል።
ኮሚሽኑ በተለይም በጸለምት፣ መጋሌ እና አብአላ አካባቢዎች የተነሱት ግጭቶች "የሰዎችን የሕይወት እና የአካል ደኅንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ" እንደሆኑ አስታውቋል።
ህወሓት በመግለጫው በጸለምት ስተለነሳው ግጭት ያለው ነገር የለም። በተመሳሳይ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ስለተነሳው ግጭት እስካሁን መግለጫ አልሰጠም።
በጸለምት ከተነሳው ግጭት በተጨማሪ አርብ ጥር 22/2018 በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሁለት ከተሞች እና አንድ ወረዳ ውስጥ አርብ ሌሊት እና ቅዳሜ ንጋት ላይ የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቢቢሲ ያገኛቸው መረጃዎች አመልክተዋል።
እንትጮ በተባለችው ከተማ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ደግሞ መቁሰሉን የከተማዋ ፖሊስ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
በተያያዘም የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጌታቸው ረዳ የሚመራው ተቃዋሚው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት)፤ "ኋላ ቀር ቡድን" ሲል የጠራው አካል "የአፋር ክልል እና ጎንደርን የሚያካልል መጠነ-ሰፊ ጥቃት" ለማካሄድ የሚያደርገውን "ዝግጅት ጨርሶ ተኩስ" ከፍቷል ሲል ወንጅሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት የአቶ ጌታቸው ፓርቲ፣ ቡድኑ "ከባድ መሳሪያዎችን ከቀበረበት እና ከደበቀበት በማውጣት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች እያስጠጋ" ነው ብሏል።
ይህንን ውጥረት ተከትሎም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች አየር ማረፊያዎች የሚያደርጋቸውን በረራዎች ከጥር 21/2018 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡ ይታወሳል።













