ኤርትራ እና ህወሓት "ጦርነት ለማወጅ" በጥምረት እየሠሩ ነው መባሉን አስተባበሉ

ኤርትራ እና ህወሓት "ጦርነት ለማወጅ" በጥምረት እየሠሩ ነው የሚለውን ክስ አስተባበሉ።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሠሩ ነው ብሎ መክሰሱን ተከትሎ ህወሓት እና ኤርትራ ምላሽ ሰጥተዋል።
ህወሓት ትናንት ለመንግሥታቱ ድርጅት በላከው ደብዳቤ ላይ "በህወሓት እና በትግራይ ሕዝብ ላይ የተሳሳተ እና የፖለቲካ ዓላማ ያዘለ ክስ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰንዝሯል" ብሏል።
"እንደዚህ ያለ የሐሰት ውንጀላ የፌደራል መንግሥት የፕሪቶርያ ስምምነትን በተደጋጋሚ እየጣሰ መሆኑ ትኩረት እንዲነፈገው የሚያደርግ ማዘናጊያ ነው" ሲል ህወሓት በደብዳቤል ገልጿል።
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ለተመድ የላከችው ደብዳቤ "ድፍረት የተሞላውና እጅግ አሳሳች ነው። 'ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል' እንዲሉ " ሲሉ ተችተዋል።
"ላለፉት ሁለት ዓመታት ብልፅግና 'ከተቻለ በሕጋዊ መንገድ ካልተቻለ በወታደራዊ ኃይል ሉዓላዊ የባሕር በር ማግኘት' የሚለውን ደጋግሞ ሲያስተጋባ ቆይቷል" ብለዋል።
"ግዛት ማስፋፋትን ዒላማ ያደረገው ይህ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በግድየለሽ እና ተንኳሽ ዛቻም የታጀበ ነው" ሲሉም አክለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ. ም. በጻፈው ደብዳቤ፤ ኤርትራ እና ህወሓት "በቅርቡ የፋኖ ታጣቂዎች የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ወልዲያን ለመቆጣጣር ባደረጉት ሙከራ ውስጥ ተሳትፈዋል" ሲል ወንጅሏቸዋል።
በምላሹ በህወሓት ለተመድ የተላከው ደብባቤ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "ሐሰተኛ ክሶችን ህወሓት ላይ በማቅረብ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለማስለወጥ እየሞከረ ነው" ይላል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ ለተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተጻፈው ደብዳቤ "በኤርትራ መንግሥት እና በህወሓት አክራሪ አንጃ መካከል ያለው ጥምረት ባለፉት ጥቂት ወራት ግልጽ እየሆነ መጥቷል" ብሏል።
ህወሓት ትናንት መስከረም 28/ 2018 ዓ. ም. ለጉተሬዝ በላከው ደብዳቤ ላይ "ማተኮር ያለብዎት የሰላም ሒደቱ የገጠመው መሰናክል እንዲሁም እየተባባሰ የመጣው ስጋት ላይ ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ክስ "መሠረት አልባ" ነው ያለው ህወሓት፤ "በትግራይ እና በኤርትራ ሕዝብ መካከል ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ሰላምና ቀጣናዊ ዕርቅን የሚያረጋግጥ ሆኖ ሳለ መሠረት አልባ ክሶች ሌላ ጦርነት በቀጣናው ያስነሳሉ" ሲል ከሷል።
"የፌደራል መንግሥት በመሠረት አልባ ክሶች አመካኝቶ ሌላ ጦርነት በክልሉ ሊከፍት ይመስላል" ሲልም በደብዳቤው ወንጅሏል።
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የላከው ደብዳቤ "አሳሳች፣ የኢትዮጵያን እንዲሁም የዓለም ሕዝብ የናቀ ነው" ሲሉ አጣጥለዋል።
አያይዘውም ኤርትራ ከዚህ ቀደምም እንዳስታወቀችው "እንዲህ ወዳለው ነገር ተጎትታ አትገባም" ብለዋል።አቶ የማነ "የሚመለከታቸው አካላትም በዚህ ድርጊት እንዳይናወጡ" አሳስበዋል።
ህወሓት ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶርያ ስምምነት የጣለበትን ግዴታዎች አክብሮ ቢቀጥልም፤ የፌደራል መንግሥቱ በስምምነቱ ማግስት ከተወጣቸው ኃላፊነቶች በዘዘለ ተፈናቃዮችን በማስመለስ እና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ግዴታዎቹን አለመወጣቱን ገልጿል።
"በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። መጠለያ፣ ምግብና ሕክምና አያገኙም። አብዛኛው የትግራይ ክፍል የኢትዮያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ባልሆኑ ኃይሎች ይዞታ ሥር ነው" ሲል ህወሓት ለተመድ ቅሬታውን ገልጿል።
"እነዚህ በአብዛኛው በመከላከያ ሠራዊት የሚደገፉ ኃይሎች የትግራይ ሕዝብን መሬት ይዘዋል። የትግራይን ሥነ ሕዝብ አወቃቀር ለመለመጥ የተደረገም ነው። የፌደራል መንግሥቱ ተቋማት በይፋ ምዕራብ ትግራይ የአማራ ክልል አካል ነው የሚል ትርክትን በመግፋት የፕሪቶርያ ስምምነትን ጥሰዋል" ሲልም ከሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለተመድ በላከው ደብዳቤ ላይ ህወሓት እና ኤርትራ "በገንዘብ፣ በማደራጀት እና እንደ ፋኖ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን የግጭት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ በመምራት" ተሳትፎ አድርገዋል ሲል ይከሳል።
የኤርትራ መንግሥት እና ህወሓት በቅርቡ የፋኖ ታጣቂዎች በሰሜን ወሎ ወልዲያ ከተማን ለመያዝ ባደረጉት ጥቃት ላይ ተሳታፊ ናቸው ሲልም ወንጅሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ፤ የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች እና ተዋጊዎች በቀጥታ ወልዲያን በማጥቃት ዘመቻ እንዲሁም በራያ እና ወልቃይት አካባቢ በነበሩ አለመረጋጋቶች ላይ መሳተፋቸውን ያትታል።
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ አስተዳደር ዙርያ ባሉ አከባቢዎች ከመስከረም 16 ቀን 2018 ዓ. ም ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ውጊያ ያካሄዱ ሲሆን በዚህም የተነሳ መንገዶች ተዘግተው ነበር።
ለቀናት በዘለቀው በዚህ ግጭት የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ወሎ ጉባ ላፍቶ ወረዳ ሳንቃ ከተማ ጤና ጣቢያ ላይ በፈጸመው የድሮን ጥቃት የአራት ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በደብዳቤው ህወሓት የፕሪቶርያ ስምምነትን ጥሷል ሲል ቢከስም፤ ህወሓት በምላሹ በላከው ደብዳቤ የፌደራል መንግሥቱ ስምምነቱን እንደጣሰ ወንጅሏል።
በህወሓት በተጻፈው ደብዳቤ ላይ፤ በፕሪቶርያ ስምምነት እንደተቀመጠው "የመከላከያ ሠራዊት አባል ያልሆኑ ኃይሎች ትግራይን ለቀው አለመውጣታቸውን" ጨምሮ ሌሎችም የስምምነቱ ጥሰቶች "የሰላም ሒደቱን አሰናክለዋል፤ አለመረጋጋት እንዲሰፍንም ምክንያት ሆነዋል" ብሏል።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር በሚጻረር ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት ሕጋዊ ዕውቅና መንፈጉ "ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ነው" ሲል የከሰሰው ህወሓት "በትግራይ እና በአካባቢው እየጨመረ የመጣው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ያሰጋል" ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ሠራዊት የተገነጠሉ ወታደሮችን "ማሠልጠን እና ማስታጠቅ ቀጥሏል" የሚል ክስም ሰንዝሯል።
ይህም "ዳግመኛ ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል" ገልጿል።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር በበኩላቸው በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባደረጉት ቃለ ምልልስ "የጦርነት ፍላጎት እንዲሁም የጎረቤቶቻችንን ግዛት የመውሰድ ዓላም የለንም። ሆኖም ታሪክም እንደሚመሰክረው ከተተነኮስን እንዴት አገራችንን መከላከት እንደምንችል እናውቃለን" ማለታቸውን ጠቅሰዋል።
አክለውም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ "ብልፅግና ስለገዛቸው ድሮኖች፣ የረዥም ርቀት ሚሳዔሎች፣ ታንኮች ወዘተ ያወራል። ኤርትራ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩም ይዝታሉ። ይሄ ከሕሊና በላይ ነው። ታሪክን የማያውቁ ብቻ ናቸው የሚያደምጡት" ማለታቸውን ገልጸዋል።
አቶ የማነ "መልሳችን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለትርጉም አልባ ጦርነት አትማግዱት ነው። ትክክለኛ ችግራችሁን ፍቱ። አድቡ!" ሲሉም የፕሬዝዳንት ኢሳያስን ንግግር አጣቅሰዋል።
ህወሓት በበኩሉ አንቶኒዮ ጉተሬዝን በመጥቀስ በጻፈው ደብዳቤ "ያልተተገበሩ የፕሪቶርያ ስምምነቶችን በተመለከተ የአፍሪካ ኅብረት ግምገማ እንዲያደርግ ጠይቀናል። እርስዎም የፖለቲካ ውይይት ማድረግን እንዲደግፉ እንጠይቃለን" ብሏል።
"የፖለቲካ ውይይት የፕሪቶርያ ስምምነት ፈራሚዎች አንዳቸው በሌላቸው ያላቸውን እምነት ያድሳል፤ የስምምነቱን ትግበራም ያረጋግጣል" ሲልም አክሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ "የባሕር በር ለማግኘት በምታደርገውን ጥረት" የተነሳ ኤርትራ ስጋት እንደገባት በመጥቀስ ኢትዮጵያን "የማተራመስ እና የመከፋፈል" ዓላማ አላት ሲል ይከስሳል።
ሚኒስቴሩ "ኤርትራ ይህንን ፀብ አጫሪ ተግባሯን እንደ አስቀድሞ የመከላከል መንገድ" ተጠቅማለች በማለት ይህ ዓይነቱ ሙከራ "ኤርትራ ለዓመታት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የምታደርገውን ጥረት ለመሸፈን የምታቀርበው ሰበብ ነው" ሲል ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓት እና ኤርትራ "ጦርነት ለማወጅ" በጥምረት እየሠሩ ነው ሲል ለከሰሰበት ደብዳቤ ህወሓት በሰጠው ምላሽ "የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአደገኛ ሁኔታ እውነታን እያዛባ፤ ወራሪውን እንደ ተጎጂ፣ተጎጂውን እንደ ወራሪ አቅርቧል" ብሏል።
የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ ጎን በማሰለፍ በትግራይ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ላይ የተሳተፈ ሲሆን፤ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ግንኙነታቸው ዳግም ሻክሯል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ኤርትራ ከህወሓት አንጃ እና ሌሎች ታጣቂ አካላት ጋር በክረምቱ ወራት ጥቃት ለመሰንዘር "እየተባበሩ እና ቅንጅት" እየፈጠሩ ብላ መክሰሷ ተዘግቦ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ኤርትራ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጦርነት አጀንዳው ድጋፍ ለማሰባሰብ፤ የከፈተውን ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አጠናክሮብኛል ስትል መክሰሷ ይታወሳል።
በሐምሌ ወር ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው የኤርትራ ጦር አባላት በኢትዮጵያ ድንበር ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ እና የከፉ ጥሰቶች መፈጸም መቀጠላቸውን ሪፖርቶች እየወጡ እንደሆነ ለመንግሥታቱ ድርጅት ገልጸዋል
ኤርትራ በበኩሏ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚያውቀው ድንበር ተወስና እንዳለች ገልጻ ይህንን የአምባሳደሩን ወቀሳ አጣጥላለች።















