ኤርትራ እና ህወሓት "ጦርነት ለማወጅ" በጥምረት እየሰሩ ነው ስትል ኢትዮጵያ ከሰሰች

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመንግሥታቱ ድርጅት በፃፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሰሩ ነው ሲል ከሰሰ።
ሚኒስቴሩ በፃፈው በዚህ ደብዳቤ፣ ሁለቱ አካላት በቅርቡ የፋኖ ታጣቂዎች የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ወልዲያን ለመቆጣጣር ባደረጉት ሙከራ ውስጥ ተሳትፈዋል ሲል ወንጅሏቸዋል።
መስከረም 22/2018 ዓ.ም. ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ "በኤርትራ መንግሥት እና በህወሓት አክራሪ አንጃ መካከል ያለው ጥምረት ባለፉት ጥቂት ወራት ግልጽ እየሆነ መጥቷል" ብሏል።
በተጨማሪም ሁለቱም ተዋናዮች "በገንዘብ፣ በማደራጀት እና እንደ ፋኖ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን የግጭት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ በመምራት" ተሳትፎ አድርገዋል ሲል ይከስሳል።
በደብዳቤው መሠረት የኤርትራ መንግሥት እና ህወሓት በቅርቡ የፋኖ ታጣቂዎች በሰሜን ወሎ ወልዲያ ከተማን ለመያዝ ባደረጉት ጥቃት ላይ ተሳታፊ ናቸው።
ሚኒስቴሩ የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች እና ተዋጊዎች በቀጥታ በወልዲያን የማጥቃት ዘመቻ እንዲሁም በራያ እና ወልቃይት አካባቢ በነበሩ አለመረጋጋቶች ላይ መሳተፋቸውን ያትታል።
ቢቢሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ደብዳቤውን በሚመለከት ለማናገር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካም።
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ አስተዳደር ዙርያ ባሉ አከባቢዎች ከመስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ውጊያ ያካሄዱ ሲሆን በዚህም የተነሳ መንገዶች ተዘግተው ነበር።
ለቀናት በዘለቀው በዚህ ግጭት የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ወሎ ጉባ ላፍቶ ወረዳ ሳንቃ ከተማ ጤና ጣቢያ ላይ በፈጸመው የድሮን ጥቃት የአራት ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤው ላይ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ስምምነት መጣሱን ገልጿል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች "የመከላከል አቋም" መያዙን እና "ከፍተኛ ተዓቅቦ" ማድረጉን ገልጾ ነገር ግን " ይህ ፖሊሲያችን ገደብ የሌለው አይደለም" ሲል አስጠንቅቋል።
ደብዳቤው ኤርትራን "የዚህ ወንጀል ተግባር ዋነኛ አንቀሳቃሽ" ሲል የገለጻት ሲሆን ግጭቶችን "በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ" በመስጠት ታግዛለች ሲል ከስሷል።
የኤርትራ መንግሥትም ሆነ ህወሓት ኢትዮጵያ ስላቀረበችው ክስ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ በጻፈው በዚህ ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ "የባሕር በር ለማግኘት በምታደርገውን ጥረት" የተነሳ ኤርትራ ስጋት እንደገባት በመጥቀስ ኢትዮጵያን "የማተራመስ እና የመከፋፈል" ዓላማ አላት ሲል ይከስሳል።
ሚኒስቴሩ "ኤርትራ ይህንን ፀብ አጫሪ ተግባሯን እንደ አስቀድሞ የመከላከል መንገድ" ተጠቅማለች በማለት ይህ ዓይነቱ ሙከራ "ኤርትራ ለዓመታት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የምታደርገውን ጥረት ለመሸፈን የምታቀርበው ሰበብ ነው" ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ደብዳቤው ላይ ኢትዮጵያ "በሰላማዊ መንገድ" የባሕር በር የማግኘት ጥረቷን እንደምትቀጥል በመግለጽ መንግሥት "ለኤርትራም ለኢትዮጵያም ጠቃሚ የሆኑ ተቋማዊ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስሮችን" እንደሚፈልግ አስታውቋል።
አክሎም የኢትዮጵያ ራዕይ " የሁለቱንም አገራት የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት በሚያስጠብቅ ትስስር አማካኝነት የጋራ ብልጽግና" መሆኑን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ "ለመደራደር ዝግጁ ነች" ያለው ደብዳቤው ዓለም አቀፉ አካላት ኤርትራ "በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የምታደርገውን የማወክ ተግባር" እንድታቆም እንዲሁም "የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንድታከብር" ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ደብዳቤያው አክሎም የዓለም አቀፍ አጋር አካላት በባሕር በር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ ሰላም አና መረጋጋትን በሚመለከቱ በሰፊ የቀጠናዊ ጉዳዮች "ገንቢ የሆነ ውይይት እና ትብብር" እንዲደረግ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ ጠይቋል።
ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ በ1990 ዓ.ም ግንቦት ወር ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ይገባኛል የተነሳ ጦርነት ውስጥ ገብታ የነበረ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግንኙነታቸው መሻሻል አሳይቶ ቆይቷል።
የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ ጎን በማሰለፍ በትግራይ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ላይ የተሳተፈ ሲሆን ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ግንኙነታቸው ዳግም ሻክሯል።
ኢትዮጵያ 'የባሕር በር የኅልውና ጉዳይ ነው' ማለቷን ተከትሎም ከኤርትራ ባለሥልጣናት ዘንድ አሉታዊ ምላሾች ሲሰጡ ቆይተዋል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርትራ ከህወሓት አንጃ እና ሌሎች ታጣቂ አካላት ጋር በክረምቱ ወራት ጥቃት ለመሰንዘር "እየተባበሩ እና ቅንጅት" እየፈጠሩ ነው የሚል ክስ ማቅረቡ ተዘግቦ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ኤርትራ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጦርነት አጀንዳው ድጋፍ ለማሰባሰብ፤ የከፈተውን ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አጠናክሮብኛል ስትል መክሰሷ ይታወሳል።
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን የሚከስሱ ደብዳቤዎችን ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ እና የሀገራት መሪዎች ልኳል በማለትም ወቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ደብዳቤውን ስለመጻፉ በይፋ ያለው ነገር አልነበረም።
በሐምሌ ወር ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው የኤርትራ ጦር አባላት በኢትዮጵያ ድንበር ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ እና የከፉ ጥሰቶች መፈጸም መቀጠላቸውን ሪፖርቶች እየወጡ እንደሆነ ለመንግሥታቱ ድርጅት አቅርበዋል።
ኤርትራ በበኩሏ ዓለም አቀፉ በሚያውቀው ድንበር ተወስና እንዳለች ገልጻ ይህንን የአምባሳደሩን ወቀሳ አጣጥላለች።















