በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ጦርነት ከተጀመረ ሁለቱንም የሚያወድም ይሆናል - አምባሳደር ኃይሌ መንቆሪዎስ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ አምባሳደር ኃይሌ መንቆሪዎስ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት ከገቡ ሁለቱንም አገራት የሚያወድም እንደሚሆን አስጠነቀቁ።
አምባሳደር ኃይሌ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ጦርነቱ አይመጣም ብሎ ማሰብ አትችልም" ያሉ ሲሆን፣ "ነገር ግን ምን ዓይነት ጦርነት እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ሁለቱም የጠብ አጫሪነት ባህሪ አላቸው፣ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ ራስን እና ሥልጣንን ማጠናከርን ያስቀድማሉ" ሲሉ የሁለቱን አገራት መሪዎች ተችተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት በዓለም ዙሪያ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን የመሩት አምባሳደር ኃይሌ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር በር ለማግኘት ኃይል የሚጠቀሙ ከሆነ "የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው የሚሆነው" ብለዋል።
"ለባሕር በር ብሎ ኤርትራን የሚወር ከሆነ፣ ኤርትራ የአፍሪካ ዩክሬን ትሆናለች ማለት ነው። ይህ ደግሞ ግጭቱን የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ቀጠናዊ ያደረገዋል" ብለዋል።
የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ሻዕቢያ) ከፍተኛ አመራር የነበሩት አምባሳደር ኃይሌ፣ ቡድን 15 በመባል የሚታወቁት የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሕገ መንግሥቱን እንዲተገብሩ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ከጠየቁት መካከል አንዱ ነበር።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት የሚገቡ ከሆኑ ሌሎች አገራት ጣልቃ ሊገቡ እንደሚችሉ የሚናገሩት አምባሳደር ኃይሌ፣ "ሳዑዲ አረቢያ አፍንጫችን ስር ነች ያለቸው። ግብፅ እዚያ አለች...፣ ለማንኛውም ኤርትራ 'ተወረርኩኝ፤ እርዳታ እሻለሁ' ካለች፣ ወረራውን ለመቀልበስ ከየትኛውም አገር ድጋፍ የመጠየቅ መብት አላት" ብለዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት የምትሆን ከሆነ በቀይ ባሕር ቀጣና የሚመጣውን የኃይል ሚዛን ለውጥ ሳዑዲ አረቢያ ጠንቅቃ ታውቃለች ሲሉ ተናግረዋል።
"ይህ ለእሷ እና ለፍላጎቷ ጎጂ ይሆናል፤ ስለዚህ ኤርትራን የመደገፍ ፍላጎት አይኖራትም አይባልም" ብለዋል።
አምባሳደር ኃይሌ እንደ ኤርትራ ያለች ትንሽ አገር የአቅም ውስንነት እና አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ስላላት ነገሮች በሰላም እንዲያልቁ መግፋት ነበረባት ይላሉ።
"እኔ እንደማስበው ሁለቱም የየራሳቸውን 'ኅልውና' እየገፉ ነው። ችግር አያስከትልም ብለን ራስን መሸንገል አያስፈልግም። ነገር ግን መጨረሻው ወዴት እንደሚወስድ ሲታሰብ፣ ሁለቱንም ወደ ግባቸው የሚያደርስ መንገድ አይደለም" ብለዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል መቃቃር የመጣው የትግራዩን ደምአፋሳሽ ጦርነት ካስቆመው ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር በር ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ ነው ማለታቸውን ተከትሎ አለመግባባቱ እየተካረረ መጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀደሙ መሪዎች ማድረግ ያልቻሉትን "ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት አደርጋታለሁ የሚል ህልም አለው፤ የሕዳሴ ግድብ እንደራሱ ሌጋሲ [ውርስ] አይቆጥረውም፤ የመለስ ነው ብሎ የሚያምነው፤ እሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ውርስ እተውለታለሁ ብሎ የሚያስበው፤ የባሕር በር ማስገኘትን ነው። ይሄንን ደግሞ በማንኛውም መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋል።"
አምባሳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር ባር ጥያቄያቸውን ካቀረቡ በኋላ በኤርትራ የተነሳውን ስጋት ዘርዝረው "ይህን ሲባል፤ ኤርትራም እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ እንደሆነ መረጃ አለኝ። በከፊል በትግራይ ግንኙነት እየፈጠሩ ነው፤. . . በአማራም ከፋኖዎች ጋር እንዲሁ ግንኙነት አላቸው" ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሊተማመነባቸው የሚችሉ የአገር ውስጥ ኃይሎች ተከፋፍለዋል ብለው ያምናሉ።
"ኢሳይያስ በህወሓት እና በአማራ አማካኝነት በሁሉም በኩል ዐቢይን ለመክበብ እየሞከረ አይደለም ማለት አይቻልም።"
አምባሳደሩ አሁን የሚታየውን የኃይል አሰላለፍ በመተቸት በሁለቱም በኩል ያለው እንቅስቃሴ "የጋራ ጥፋት እንደሚያመጣ ማወቅ አለባቸው፤ ጦርነት ከመጣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንጠቀማለን ቢሉም፤ በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ ለሁለቱም ድል ይመጣል ብሎ ማመን አይቻልም" ብለዋል።
ግጭት ከተነሳ ቀድሞው የሚጐዱት የሁለቱ አገራት ሕዝቦች መሆናቸውን የተናገሩት አምባሳደር ኃይሌ፣ "አሁን ሁሉም በየፊናው እያጨበጨበ የራሱ መንግሥት ጠበቃ ከመሆን ይልቅ፣ ጦርነቱን ለማስቀረት መሥራት ነው የሚጠቀመው።
"ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጉዳቱ ለሁሉም ነው፤ አፍራሽ ነው የሚሆነው፤ ከተቻለ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች እንደ አውሮፓ ወደ አንድ አቅጣጫ ለመጓዝ መሞከር ነው ያለባቸው፤ እንጂ ሌላ ጦርነት መሆን የለበትም።"
ጦርነት ለሁሉም ጥፋት የሚያመጣ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ኃይሌ የሁለቱ አገራት ሕዝብ ምሁራን፣ ፓርቲዎች እና ሌሎችም ይህንን ጦርነት ለማስቀረት ጥረት ማድረግ አለባቸው በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
"ሕዝቡን ከዚህ ጥፋት ለማዳን የሚፈልግ ካለ ጊዜው አሁን ነው፤ ከቀውሱ በፊት እንጂ ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ አይደለም። ስለዚህ ይህን ጦርነት ለማስቀረት ሁላችንም ድምጻችንን በማሰማት ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን" ብለዋል።
ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክት ሲያስተላልፉም "ለሰላማዊ መፍትሄ፣ ለውይይት ዕድል ስጡ" በማለት ያንዣበበውን የጦርነት ደመና እንዲያስወግዱ ጠይቀዋል።
"በተለይ ለኢሳያስ መልዕክት ብልክ በኤርትራ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የታቀደው ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ፣ ፓርላማ ቢኖረን ኖሮ፣ በኤርትራ ውስጥ ውይይት እንዲደረግ የሚያስችል ዕድል ቢፈጠር፣ ውይይት የሚፈቅድበት ዕድል ቢፈጠር፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እንወያይ ነበር። እና መፍትሄ እናገኝ ነበር" ብለዋል።
ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት የሚገቡ ከሆነ "ሁለቱንም ያጠፋል፣ አቅማቸውን ያዳክማል እና የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን ያጠባል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ይህንን ለመከላከል ለሁለቱ አገራት ሕዝብ ጥቅም የሚያስቡ በሙሉ "ይህንን ጦርነት በምንም መልኩ እንዲቃወሙት እመክራለሁ" ብለዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በድንበር ይገባኛል ምክንያት ደም አፋሳሽ ጦርነት ያደረጉት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጠላትነት ሲተያዩ ቆይተው ግንኙነታቸው የተሻሻለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነበረ።
ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸው ተሻሽሎ በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ በጋራ የትግራይ ኃይሎችን እስከ ደርሰው የነበረ ቢሆንም ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ አለመግባባቶች ተከስተው ግንኙነታቸው ቀስበቅስ ተቀዛቅዞ ወደ ፍጥጫ እያመራ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን በይፋ ካሳወቀች በኋላ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ የያዟቸው ግዛቶች አሉ በማለት እየከሰሱ ሲሆን፣ በሁለቱም በኩል ወታደራዊ ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ይነገራል።















