ኤምሬቶች፣ ቱርክ እና ሳዑዲ ከኢትዮጵያ የሚፈልጉት ምንድን ነው?

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ ሁሌም ባላንጣ አልነበሩም። በግብፅ አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ሥልጣን እንዲጨብጡ በማገዝ አብረው ተሰልፈዋል።
እንደ ዛሬው ሆድ እና ጀርባ ሳይሆኑ በፊት በሊቢያ እና በየመን ጉዳይ ተቀራራቢ አቋም ነበራቸው። በእስራኤል እና በፍልስጤም ጉዳይም ከአረብ ሊግ አገራት መካከል የሚቀራረብ አቋም አራምደዋል።
ለቁርሿቸው ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ጸባቸው ድንበር ተሻግሮ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ዋና ዋናዎቹን ምክንያቶች በዚህ ዘገባ እንዳስሳለን።
የኢትዮጵያ ስም ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ተያይዞ መነሳት ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። ከንግድ እና ኢንቨስትመንት ጀርባ ያሉ ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸው ምንድን ናቸው? የሚለውንም እንመለከታለን።
በሌላኛው ጽንፍ ያለችው አገር ደግሞ ቱርክ ናት። እንደ ሁለቱ የባሕረ ሰላጤው አገራት ሳይሆን ኢትዮጵያ እና ቱርክ ዘመናት ያስቆጠረ ትስስር አላቸው። ጥያቄው በአሁናዊ ግንኙነታቸው ምን ተለወጠ? የሚለው ነው።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የፖሊሲ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሙከረም ሚፍታህ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያን ፉክክር የሚመለከቱት በዋናነት ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ፍላጎት አንጻር ነው።
የሴንተር ፎር ናሽናል ኤንድ ሪጅናል ኢንተግሬሽን ስተዲስ ቲንክታንክ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት የታሪክ ባለሙያው ዶ/ር ኢብራሒም ሙሉሸዋ፤ ቱርክ በኤርዶዋን ሥር ለአፍሪካ ልዩ ትኩረት የሰጠ ፖሊሲ እያራመደች መሆኑን ያስረዳሉ።
ሦስቱ አገራት ከኢትዮጵያ ምን ይፈልጋሉ? የሚለውን ለመረዳት ከታሪካዊ ዳራው እናንሳ።
የአረቡ ዓለም መሪ የመሆን ፉክክር
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ የሚያሳድሩት ጫና እየበረታ መምጣቱ ሲገለጽ ቆይቷል። ለመሆኑ ለዚህ ምክንያት የሆነው የሁለቱ አገራት ፉክክር መነሻው ምንድን ነው?
ሁለቱም ሙስሊም የአረብ አገራት ናቸው። ነገር ግን የአረቡ እና የሙስሊሙ ዓለም መሪ ሆኖ ለመውጣት ይገዳደራሉ።
ዶ/ር ሙከሪም እንደሚናገሩት፤ በተለይም ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ከመጡ በኋላ የመሪነት ሚናን ለመውሰድ ፉክክሩ በርትቷል።
ሳዑዲ በእስልምና ቅዱስ ሥፍራ የሆኑት የመካ እና መዲና መገኛ እንደመሆኗ የሙስሊሙን ዓለም የምወክለው እኔ ነኝ የሚል እምነት አላት።
ኤምሬቶች ይሄንን ለመገዳደር በቂ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ መነሻ ስለሌላቸው ፊታቸውን ጠንካራ የንግድ ማዕከል ወደመሆን አዙረዋል።
በዋነኛነት በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ ቀዳሚ ተወዳዳሪ አገር እየሆነች ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይና እና ከሕንድ ትልልቅ ኩባንያዎችን በመሳብ ራሷን ስታሳድግ፤ በአንጻሩ ሳዑዲ አረቢያ ይሄንን ማሳካት እንዳልቻለች ዶ/ር ሙከሪም ይናገራሉ።
ሃይማኖት ላይ ከተመረኮዘ የመሪነት ጥያቄ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሃብት ጉዳዮች እንዳሉ መረሳት የለበትም።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ምጣኔ ሃብት እየገነባች ነው። ጠንካራ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ዱባይ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናት።
ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ የነዳጅ ሃብት የፈጠረላት አቅም አለ። ከነዳጅ ሽያጭ በሚገኘው ሃብት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ በመግዛት ራሷን እያጠናከረች እንደሆነ ባለሙያው ይገልጻሉ። ከዚህ አንጻር የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እምብዛም ጠንካራ አይደሉም።
"የውድድር መንፈስ በጊዜ ሒደት እየተጠናከረ ወደ ባላንጣነት መጣ" የሚሉት ዶ/ር ሙከረም፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ ፉክክር ከመሪዎቻቸው እንደሚጀምር ይገልጻሉ።

'የሁለቱ መሐመዶች የለውጥ ተምሳሌት የመሆን ፉክክር'
የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼኽ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን 'ሪፎርሚስት' ሆነው መታየት ይፈልጋሉ።
ሁለቱም አገራት በንጉሣዊ ቤተሰብ ነው የሚተዳደሩት። 'ከወግ አጥባቂነት' በመውጣት ረገድ ሁለቱም መሪዎች የአረቡ ዓለም 'ተምሳሌት' መሆን እንደሚፈልጉ ዶ/ር ሙከረም ይናገራሉ።
ለምሳሌ፤ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ በመፍቀድ እንዲሁም የምዕራቡን ዓለም ድምጻውያን በመጋበዝ መሐመድ ቢን ሰልማን ለለውጥ ዝግጁ መሆናቸውን ለማሳየት ይሞክራሉ።
ሼኽ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በዚህ ውድድር መበለጥ አይፈልጉም። በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለው የግል ፉክክር ላይ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ታክለውበታል።
"ሪፎርሚስት ነን የሚሉት ሁለቱ መሪዎች፤ ልዩነታቸው ተቋማዊ እና አገራዊ ቅርጽ ወይም መልክ እየያዘ መጥቷል። ሁለቱ መሐመዶች ከፍተኛ የሆነ መናናቅ እና ጥላቻ አላቸው። ግላዊ ጠባቸውን ተቋማዊ አድርገውታል" ይላሉ ዶ/ር ሙከሪም።
ከግለሰብ ፉክክር ተነስቶ አገራዊ መልክ የያዘውን ልዩነት ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ አፍሪካ ቀንድ እንውሰደው።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ፍላጎት በዐቢይ ዘመን
የአረብ አገራት ሚና ጎልቶ መታየት የጀመረው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ነው።
ኤምሬቶች እና ሳዑዲ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ኢንቨስትመንት አላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በኢትዮጵያ ላይ አውጥታለች።
ዶ/ር ሙከሪም የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ግንኙነት በሁለት ምዕራፍ ይከፍሉታል። ከአውሮፓውያኑ 2018 በፊት እና በኋላ በሚል።
በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በልማት ድጋፍ፣ በግንባታ፣ በኢነርጂ፣ በሰብአዊ ድጋፍ እና ሌሎችም ዘርፎች ከ2018 በፊት የነበራቸው ሚና ውስን ነበር።
በአገራት መካከል የሚፈጠር የፖለቲካም ይሁን የምጣኔ ሃብት ትስስር ከትንሽ ተነስቶ እንደሚያድግ በመጥቀስ፤ የኢትዮጵያ እና የኤምሬቶች ግንኙነት ግን "ለውጡ ድንገቴ መሆኑ ጥርጥር የለውም። የዕድገት ደረጃውን አላሳየም" ሲሉ ባለሙያው ይገልጹታል።
ለማነጻጸሪያነት ቱርክን ብንወስድ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የምጣኔ ሃብት እና የፖለቲካ ግንኙነት ዕድገት ወይም ለውጥ "ሊተነበይ የሚችል" እንደሆነ ያስረዳሉ።
ቱርክን ካነሳን አይቀር ከባሕረ ሰላጤው አገራት በተለየ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትስስር እንመልከት።
የቱርክ 'ፀረ ቅኝ ግዛት' ፍላጎት
የቱርክ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦቶማን መንግሥት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ከመምጣቱ ጋር ይያያዛል።
ቱርኮች ለዘመናት በቀይ ባሕር አካባቢ ነበሩ። ዘመናዊት ኢትዮጵያ ከተመሠረተች በኋላ ቱርክ በአፍሪካ ከሰሃራ በታች የመጀመሪያውን ኤምባሲ በአዲስ አበባ (በአውሮፓውያኑ በ1926) መክፈቷ የግንኙነታቸውን ጥንካሬ ያሳያል።
በሶሻሊዝም መሩ ደርግ የተቀዛቀዘው ግንኙነት በኢሕአዴግ ዘመን ዳግመኛ አንሰራርቷል። ዶ/ር ኢብራሒም እንደሚሉት፤ በቱርክ ገዢው ፓርቲ ኤኬ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ለአገሪቱ ዕድገት ሲባል በሌሎች አገራት ኢንቨስት ወደማድረግ ተገብቷል።
ከእነዚህ አገራት አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። ቱርክ በኢትዮጵያ ያላት ኢንቨስትመንት ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይገመታል። ከ200 በላይ በሚደርሱ የቱርክ ፋብሪካዎች ውስጥ ወደ 20 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተቀጥረው ይሠራሉ።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ግን ከንግድ እና ኢንቨስትመንት ባሻገር ወታደራዊ ትብብርንም ያካትታል። ዶ/ር ኢብራሒም የሚጠቅሱት በትግራይ ጦርነት ወቅት ቱርክ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮኖች) ለፌደራል መንግሥቱ መስጠቷን ነው።
ቱርኮች ራሳቸውን "የአውሮፓ አካል እንዳልሆኑ" ከመቁጠራቸው በተጨማሪ "ፀረ ቅኝ ግዛት" እንቅስቃሴ እንደሚያራምዱ መግለጻቸውን ይጠቅሳሉ።
"ይህም ቢያንስ በሐሳብ ደረጃ ቱርክ እና ኢትዮጵያ በእኩልነት ላይ የተመሠረት አጋርነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው" ይላሉ።
ቱርክ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ወዳላቸው ፍላጎት እንሻገር።

'የአሜሪካ እና እስራኤልን ፍላጎት ማስጠበቅ'
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የሳዑዲ አረቢያን ፍላጎት ስንመለከት አንደኛው ትንታኔ፤ መረጋጋት በራቀው የአፍሪካ ቀንድ ፓለቲካ ምክንያት የደኅንነት ስጋት ውስጥ ላለመግባት እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ፍላጎትን ለማስጠበቅ ይሻሉ የሚለው ይሆናል።
በእርግጥ አገራቱ በአፍሪካ ቀንድ የጦር ማዕከል ማስፋፋት ይፈልጋሉ። ቀጣናው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት መሆኑም እሙን ነው። አገራቱ በምሥራቅ አፍሪካ ኢንቨስትመንቶቻቸውን ማስጠበቅ ይሻሉ።
ከትግራይ ጦርነት እና በአማራ ክልል ካለው ግጭት እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሰላም እና ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ ቢገባም፤ በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ ከሚባሉት አንዷ እንደመሆኗ አገራት ትስስራቸውን ማጠናከር ይፈልጋሉ።
በዶ/ር ሙከረም አስተያየት ግን ዋነኛው ማጠንጠኛ የአሜሪካ እና እስራኤልን ፍላጎት ነው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የአሜሪካ እና የአፍሪካ ትስስር እየላላ መጥቷል። ስለዚህም የአሜሪካን ፍላጎት በሌሎች አገራት በኩል የማስፈጸም ሙከራዎች ይስተዋላሉ።
የአፍሪካ ቀንድ ሥነ ምድራዊ አቀማመጥ ቀጣናውን ለመቃኘት እንዲሁም ራስን ከአደጋ ለመከላከል ሁነኛ በመሆኑ የአረቡ አገራት ፍላጎት ማሳደራቸው ምክንያታዊ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሜሪካ እና እስራኤል በአፍሪካ ቀንድ ያላቸው ፍላጎት "እስራኤል የአገረ መንግሥት ጥያቄዋን ለመመለስ" ከምታራምደው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር እንደሚተሳሰር ዶ/ር ሙከረም ይናገራሉ።
በእስራኤል እና በፍልስጤም ጉዳይ ተጽዕኖ ማሳደር ከሚችሉ አገራት መካከል ግብፅን ጨምሮ የአረብ ሊግ አባላት ተጠቃሽ ናቸው።
"በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በሚደረግ ማንኛውም ነገር ተጽዕኖ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ። ስለዚህ አሜሪካ እና እስራኤል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ይደግፋሉ" በማለት ያስረዳሉ።
ሳዑዲ አረቢያ በአንጻሩ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት መቀዛቀዝ እየታየበት ነው። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን "የእስራኤል መንግሥት ተላላኪ" ስትልም ትነቅፋለች።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ በምሥራቅ አፍሪካ በተቃርኖ ከመቆማቸው ጀርባ የአሜሪካ እና የእስራኤልን ፍላጎት መመልከት ይቻላል።
"በኢትዮጵያም ይሁን በአፍሪካ ቀንድ በአጠቃላይ ያላቸው ሚና ለእነሱም ጭምር ጠቃሚ ነው ብዬ አልወስድም። ሊለካ የሚችል ምን ጥቅም አግኝተዋል? በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ምን አግኝተዋል?" በማለት ዶ/ር ሙከረም ይጠይቃሉ።
የኢትዮ-ኤርትራ እና ቀጣናዊ ጉዳይ
ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።
መቋጫ ካላገኘው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ጀርባ ኢትዮጵያም የባሕረ ሰላጤው አገራትም ስማቸው ሲነሳ ቆይቷል። ተገዳዳሪዎቹን የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚደግፉ አካሎች "የእጅ አዙር ጦርነት" እያካሄዱ መሆኑን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሌላ በቀጣናው ውጥረት የጫረ ክስተት ነው። እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና መስጠቷ ያስቆጣት ሶማሊያም ተቃውሞ ማስተጋባቷን ቀጥላለች። በዚሁ ምክንያት ከኤምሬቶች ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣለች።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚወዛገቡት ኢትዮጵያ እና ግብፅ፤ በሶማሊያ እንዲሁም በሱዳን አማካኝነት ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ ይሞክራሉ።
ቀጣናዊ አሰላለፉ ከቀንዱ አገራት ፍላጎት በተጨማሪ በውጭ አገራት ጣልቃ ገብነትም የሚወሰን ነው።
ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጀርባ "የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አለች" ብለው የሚወነጅሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የቅርብ አጋራቸው አድርገው የወሰዱት ሳዑዲ አረቢያን ነው።
ዶ/ር ሙከረም፤ በባሕር በር ጥያቄ ምክንያት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደማይችሉ ጽኑ እምነት አላቸው። ነገር ግን በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ቢነሳስ?
"ከሳዑዲ ጋር ሲነጻጸር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው። ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት አላቸው። ያንን ለመጠበቅ ሲሉ ከኢትዮጵያ ጎን ሊሆኑ ይችላሉ" ሲሉ ይመልሳሉ።
ጦርነት የሚያስከትለውን ውድመት እና ዲፕሎማሲያዊ ውግዘት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄዋን በሰላማዊ መንገድ በሶማሊላንድ አማካኝነት ልታሳካ እንደምትችል ያምናሉ።
በእርግጥ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ አገርነት ዕውቅና ብትሰጥ ከሶማሊያ እና ከቱርክ ጋር ውዝግብ መፈጠሩ አይቀሬ ነው።
ቱርክ ለአፍሪካ የተለየ ትኩረት መስጠት በመጀመሯ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ መቀጠሏን የሚያነሱት ዶ/ር ኢብራሒም በበኩላቸው፤ ቱርክ በቀጣናው ያላት ፖሊሲ ከሁሉም አገራት "እኩል ተጠቃሚ" የሚያደርጋት እንደሆነ ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ እና የቱርክ ግንኙነት በጎመራበት የኤርዶዋን አስተዳደር ውስጥ አገሪቱ "አንዱን ጥላ አንዱን መያዝ እንደማትፈልግ" ይገልጻሉ።
ቱርክ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በአንካራ ስምምነት ያሸማገለችውም ከሁለቱ አገራት አንዱን ላለመምረጥ ነው።
ቱርክ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት "ኢትዮጵያን በቀላሉ አንለቅም። የኢትዮጵያ ፍላጎት የኛም ፍላጎት ነው" የሚል እንደሆነ ይናገራሉ።















