ባላንጣዎቹ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የፍልሚያ ሜዳ ያደረጉት የአፍሪካ ቀንድ

የሳዑዲው እና የኤምሬቶች መሪዎች፣ የሱዳን ጄነራሎች እና የአፍሪካ ቀንድ ካርታ
የንባብ ጊዜ: 8 ደቂቃ

በባላንጣነት የሚታየዩት የመካከለኛው ምሥራቅ ኃይሎች የገቡበት ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር፤ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ለውጦች እንዲታዩ ምክንያት ሆኗል። በዚህ መሃል የተገኙት የቀንዱ አገራት በበኩላቸው የእነዚህ ኃይሎች ሽኩቻ እና ተያያዥ ለውጦችን እንዴት እንደሚያስተናግዱት በማጤን ላይ ናቸው።

በሳዑዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል የቀጠለው ውጥረት እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ያሉ አገራት አጋጣሚውን ለመጠቀም ወይም ሁኔታው የሚያመጣውን ለውጥ ለመቋቋም እየሞከሩ ነው።

እስራኤል፤ ነጻ አገርነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ የሰጠችውን ድንገተኛ የአገርነት እውቅና እንዲሁም በቀጣናው ያላትን ተጽእኖ እያሰፋች የምትገኘው ቱርክ ጉዳይም አገራቱን አማራጫቸውን እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።

ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸው የሚታሰቡት ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ እና ግብፅ አካሄዳቸው ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከእስራኤል ግቦች ጋር የሚጣረስ ተደርጎ ይቆጠራል።

አንዳንድ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ለየትኛው አካል እንደሚወግኑ በግልጽ አሳይተዋል። ሌሎች ደግሞ ምንም እንኳ ወደ አንዱ ቢያዘነብሉም አካሄዳቸውን ጥንቃቄ የተሞላበት አድርገዋል።

ቢቢሲ ሞኒተሪንግ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን እንቅስቃሴ፣ ይፋዊ አስተያየቶች እና ከውጭ ኃይሎች ጋር የተደረጉ ግንኙነቶችን ተከታትሎ ባጠናቀረው በዚህ ትንታኔ፤ የቀጣናው አገራት በአሁኑ ሰዓት ምን አቋም እንደያዙ ዳስሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼኽ ሞሐሙድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

ወደ ኤምሬቶች ያዘነበለችው ኢትዮጵያ

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በሳዑዲ አረቢያ ፍትጊያ ውስጥ ይፋዊ አቋም ላለማሳየት ብትጠነቀቅም፤ የአቡ ዳቢ የቅርብ አጋር መሆኗን ቀጥላለች።

የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ ላለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሣሪያ ለማስተላለፍ ትጠቀምባቸው የነበሩት የሶማሊያ እና የምሥራቃዊ ሊቢያ መስመሮች ተስተጓጉለውባታል።

ይህንንም ተከትሎ ለአማጺው ኃይል መሣሪያ ለማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ጥገኝነት እየጨመረ መምጣቱን ዘገባዎች ያሳያሉ።

የዜና ወኪሉ ሮይተርስ፤ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሥልጠና የሚሰጥበት ምሥጢራዊ ካምፕ ኢትዮጵያ ውስጥ መቋቋሙን የሚያትት የምርመራ ዘገባ ባለፈው ሳምንት አውጥቷል።

ይህ ዘገባ ከወጣ ከቀናት በኋላ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን ሊዘግቡ የነበሩ የሮይተርስ ጋዜጠኞችን ፈቃድ እንደሰረዘ እንዲሁም የዜና ወኪሉን ሌሎች ዘጋቢዎች ፈቃድ ሳያድስ እንደቀረ ተገልጿል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ካምፕ በገንዘብ መደገፏን እንዲሁም በሱዳን ጦርነት መሳተፏን በተመለከተ የቀረቡ ክሶችን ውድቅ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ፤ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድጋፍ እያደረገች ነው የሚለው ውንጀላ በሱዳን ባለሥልጣናት በኩልም ቀርቦ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች እና አጋሮቻቸው ከአገሪቱ ተነስተው ብሉ ናይል ግዛት ውስጥ የሚገኙ የሱዳን ኃይሎች ላይ ጥቃት እንዲከፍቱ እንደፈቀደ በመግለጽ ከስሰዋል።

ለኢትዮጵያ ድንበር ቅርብ በሆኑ ሱዳን አካባቢዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ይህንን ክስ ለማጠናከር የሚጠቀሙበትም አልጠፉም።

ሳዑዲ አረቢያም ግን ኢትዮጵያን ከጎኗ ለማሰለፍ የምታደርገውን ጥረት አላቋረጠችም። ባለፈው ሳምንት የካቲት 4/2018 ዓ.ም. ላይ የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሃን ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድን ሲያነጋግሩ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድ ጋር የነበራቸው ውይይት "በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች" ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ውጤታማ" ተብሎ የተገለጸው ይህ ውይይት የተካሄደው፤ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሪያድ ከተገናኙ በኋላ ነበር።

በዚህ ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 10 ቀን ደግሞ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ መጥተው ነበር። የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ኢትዮጵያ ይበልጥ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና እስራኤል እንዳትሳብ የተደረገ ሙከራ ተደርጎ ታይቷል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና በተመለከተ ግልጽ የሆነ አቋም አላሳየችም። ለሶማሊላንድ እውቅና እንደሚያሰጥ የተገለጸውን ስምምነት ከሐርጌሳ ጋር ተፈራርማ እንደነበር ከግምት ውስጥ ሲገባ ግን ወደ እስራኤል እና ሶማሊላንድ የማዘንበል ዕድሏ ከፍተኛ እንደሆነ ይገመታል።

ባለፉት ዓመታት የባሕር በር አልባ የመሆኗን ጉዳይ ለመቀየር እየጣረች ያለችው ኢትዮጵያ፤ በአሰብ ወደብ ጉዳይ ከኤርትራ ጋር የገባችበትን ፍጥጫ አካርሮታል።

ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው ስምምነት ያስከተለው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ኢትዮጵያ ጉዳዩን እንዳትገፋበት አስገድዷታል።

በስምምነቱ ምክንያት የተቃቃሩት ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ወደ ቱርክ ተጉዘው ስምምነት ሲፈጽሙ ግን ሞቃዲሾ እና አዲስ አበባ የባሕር በርን በተመለከተ ድርድር ውስጥ የመግባታቸው ጉዳይ በቅድመ ሁኔታነት ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ያደራደሩት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በአዲስ አበባ ጉብኝታው ወቅት፤ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና "ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም" አይኖረውም ሲሉ ተደምጠዋል።

እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅን ለመስጠት ውሳኔዋን ይፋ ያደረገችው ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በደረሱት ስምምነት መሠረት የባሕር በርን በተመለከተ የሚያደርጉት ንግግር በተጓተተበት ወቅት ነው።

ይህ የእስራኤል ድንገተኛ እርምጃ ኢትዮጵያ ተጨማሪ አማራጮች እንዲኖራት አድርጓል።

አሁን ኢትዮጵያ አጓጊ የሆነ የባሕር በር አማራጭ ከሶማሊያ ይቀርብላታል፤ አልያም ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት በድጋሚ ታነሳለች።

አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ የሶማሊላንድን ጉዳይ የምታነሳ ከሆነ ምናልባትም የሚደረስባት ጫና ካለፈው ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል።

እስካሁን ድረስ ግን ኢትዮጵያ አማራጮቿን ክፍት ማድረግን መርጣለች።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሳዑዲ አረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel

ወደ ሳዑዲ እና ግብፅ የተጠጋችው ኤርትራ

ከኤርትራ ጋር የገባችበት ውጥረት እየተካረረ የመጣው ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላት ግንኙነት መጠናከሩ አሥመራ ሌላኛውን ጽንፍ እንድትይዝ አድርጓል።

ኤርትራ ይህንን አካሄድ መከተል የጀመረችው የመካከለኛው ምሥራቆቹ አገራት ባላንጣዎች ከመሆናቸው አስቀድሞ ነበር።

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጥር ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በርን በተመለከተ ከያዘችው ፈርጣማ አቋም እና በአሰብ ወደብ ላይ ከምታነሳው የሉዓላዊነት ጥያቄ ጀርባ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደምትገኝ በመጥቀስ ከስሰዋል።

በተጨማሪም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያን እና ሌሎች ጎረቤት አገራትን በመጠቀም ሱዳንን የመውረር ፍላጎት አላት ሲሉ ወንጅለዋል።

ኤርትራ የሳዑዲ አጋር ከሆነችው ግብፅ ጋር ያላት ግንኙነር ከሪያድ ጋር ትስስሯን እንድታጠናክር አግዟታል። ባለፉት ቅርብ ወራትም የሦስቱ አገራት መሪዎች እና ባለሥልጣናት ሪያድ፣ ካይሮ እና አሥመራ ውስጥ ተገኝተው ስለ ቀይ ባሕር ደኅንነት ተከታታይ ውይይቶችን አድርገዋል።

ጂቡቲም እንደ ኤርትራ ሁሉ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላት ግንኙነት ባለፉት ዓመታት እየሻከረ፤ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ደግሞ ይበልጥ እየተወዳጀች መጥታለች። በዚህም የተነሳ የሁለቱ አገራት የቅርብ ጊዜያት ሁኔታዎች በጂቡቲ አቋም ላይ እምብዛም ለውጥ አላመጡም።

ከዚህ በበለጠ ለጂቡቲ አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው ዕውቅና ነው። የጂቡቲ ወደብ ዋነኛ ተጠቃሚ የሆነችው ኢትዮጵያም ቴል አቪቭን ተከትላ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ልትሰጥ ትችላለች የሚል ስጋት ጭሮባታል።

አዲስ አበባ እና ሐርጌሳ የወደብ ስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ፤ 95 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን የባሕር ላይ ገቢ እና ወጪ ንግድ በምታስተናግደው ጂቡቲ ላይ ከፍተኛ የንግድ ኪሳራን ያመጣል።

በዚህም ምክንያት ጂቡቲ፤ ሶማሊያ የሶማሊላንድ ዕውቅናን በመጻረር የከፈተችውን ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ በማገዝ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ነው።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ

የፎቶው ባለመብት, Hassan Sheikh Mohamud

ከኤምሬቶች ጋር ያላትን ግንኙነት የበጠሰችው ሶማሊያ

ሶማሊያ ምናልባትም የመካከለኛው ምሥራቅ ኃይሎች ፉክክር አንዲት ትንሽ አገር ቅድሚያ የምትሰጣቸውን አጀንዳዎች እንዴት በአንድ ጀምበር ሊቀይር እንደሚችል ለመረዳት የምታግዝ ግልጽ ማሳያ ነች።

ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ ስትፈራው የነበረው ተገንጣይ ግዛቷ እጅግ ጉልበታም በሆነ የውጭ አገር ሲደገፍ የመመልከት ስጋት ዕውን ሆኖ ፊት ለፊቷ ተደቅኗል።

እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና የመጀመሪያ በትሩን ያሳረፈው የሶማሊያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግንኙነት ላይ ነው። ለረጅም ጊዜ የሶማሊያ አጋር ሆና የቆየችው አቡ ዳቢ አሁን የእስራኤልን እርምጃ አቀነባብራለች የሚል ክስ ቀርቦባታል።

ለሶማሊላድ ዕውቅና በተሰጠ በቀናት ልዩነት ሶማሊያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የፈጸመቻቸውን ስምምነቶች ሰርዛለች። የአቡ ዳቢ የጭነት እና ወታደራዊ አውሮፕላኖች አየር ክልሏ ውስጥ እንዳይበሩም አግዳለች።

ሞቃዲሾ ይህንን እርምጃ የወሰደችው የሳዑዲ እና የኤምሬቶች መካረር እያየለ በመጣበት በዚህ ወቅት ነው። እርምጃው የተወሰደበት ጊዜ የሶማሊያ ውሳኔ በሳዑዲ ትዕዛዝ የተፈጸመ ነው የሚል ግምት እንዲነሳም ምክንያት ሆኗል።

ከተሰረዙት ስምምነቶች መካከል አቡ ዳቢ በሶማሊያ ውስጥ ዋና ዋና ወደቦችን ለማስተዳደር ፈቃድ ያገኘችበት ውል ይገኝበታል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሶማሊያ ወታደራዊ እና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና ከፍ እንዲል ያደረገው የአውሮፓውያኑ 2023 የመከላከያ ስምምነትም ከተሰረዙት ውሎች መካከል ነው።

የሶማሊላንድን ባንዲራ ያዙ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ለ30 ዓመታት ነጻ አገርነቷን አውጃ የኖረችው ሶማሊላንድ፤ ባለፈው ታህሳስ ላይ የመጀመሪያውን የአገርነት እውቅና ከእስራኤል አግኝታለች

ኤምሬቶች ከሶማሊያ ጋር የገባችበት መቃቃር በቀጣናው ተጽእኖዋን ለማስፋት ለወጠነችው ዕቅድ ትልቅ እንቅፋት ነው። አሁንም ቢሆን ግን አቡ ዳቢ በተበታተነው የሶማሊያ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ምኅዳር ውስጥ አጋሮች አሏት።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንድትሰጥ የሚጠይቁ ተደጋጋሚ ድምጾች በዝተዋል። የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ኤምሬቶችን ሚደግፉ ሠልፎችን አካሂደዋል። ጥር መጨረሻ ላይም የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አቡ ዳቢን ጎብኝተዋል።

የኤምሬቶች የወደብ አስተዳደር ኩባንያ የሆነው 'ዲፒ ወርልድ' አሁንም ሶማሊላንድ ውስጥ የሚገኘውን የበርበራ ወደብ እና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ያለውን የቦሳሶ ወደብ ያንቀሳቅሳል።

ሶማሊላንድ፣ ፑንትላንድ እና ጁባላንድ የሶማሊያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተገቡ ስምምነቶች ለመሰረዝ ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ አድርገዋል።

በእነዚህ ሦስት ግዛቶች ውስጥ ቁጥጥር የሌላት ሶማሊያ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንቅስቃሴዋን እንድታቆም የምታስገድድበት እምብዛም መንገድ የላትም።

የተጠናከረው ሶማሊያ እና ቱርክ ወዳጅነት

ሶማሊያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የገባቻቸውን ስምምነቶች ለመሰረዝ ያስተላለፈችውን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ የመቻሏ ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬን ጭሯል።

ሶማሊያ በአንጻሩ አዳዲስ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥምረቶችን መፍጠር እንዲሁም ከነባር ወዳጆቿ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ትብብር የማጠናከር ዘመቻን ተያይዛዋለች።

ባለፈው ሳምንት የባሕር ኃይል አሃዶችን፣ ከ10 በላይ ዘመናዊ ታንኮችን እና ሌሎች ከባድ የጦር መሣሪያዎችን የጫነው የቱርክ 'ሳንካክታር' የጦር መርከብ ሞቃዲሾ ደርሷል። ከቀናት አስቀድሞ ደግሞ የቱርክ ኤፍ-16 የጦር አውሮፕላኖች በሞቃዲሾ ሰማይ ላይ ዝቅ ብለው በመብረር ትርዒት ሲያሳዩ ነበር።

የነዳጅ ፍለጋ እና የደኅንነት መርከቦችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የቱርክ መርከቦችም ወደ ሶማሊያ ተጉዘዋል።

'ቻግሪ ቤይ' የተሰኘው የቱርክ የነዳጅ ፍለጋ እና ቁፋሮ መርከብ ባለፈው ሳምንት እሁድ ወደ ሶማሊያ መቅዘፍ ጀምሯል። ይህ የነዳጅ ፍለጋ መርከብ ከጥቂት ወራት በኋላ በሶማሊያ ውሃ ውስጥ ጥልቅ ቁፋሮ እንደሚጀምር ይጠበቃል።

በተጨማሪም በሶማሊያ ሰሜን ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኘው ላስቆራይ ከተማ ውስጥ አዲስ የቱርክ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር የማቋቋም ዕቅድ እንዳለ የሶማሊያ እና የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን

የፎቶው ባለመብት, AK Party

የጦር ሰፈሩ ይገነባበታል የተባለው ቦታ እስራኤል የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ለመመሥረት ካቀደችበት የሶማሊላንዱ በርበራ ወደብ እምብዛም የማይርቅ ስትራቴጂካዊ የባሕር ጠረፍ ነው።

እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷ ቱርክ እነዚህን እርምጃዎቿን እንድታፋጥን ያደረጋት ይመስላል። አሁንም ቢሆን የቱርክን ወታደራዊ ጦር ሰፈር በምታስተናግደው ሶማሊያ ውስጥ እየታየ ያለው የአንካራ እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም በዚህ መጠን አልታየም።

ሶማሊያ፤ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ያጣችውን ድጋፍ ለማካካስ እንዲሁም በግዛት አንድነቷን ላይ ተጨማሪ ስጋት እንዳይጋረጥባት ለመከላከል ስትል ከሳዑዲ አረቢያ፣ከ ግብፅ እና ከኳታር ጋር የመከላከያ እና የደኅንነት ስምምነቶችን ተፈራርማለች።

ሳዑዲ እና ሶማሊያ ጥር 1 ቀን የተፈራረሙት የመከላከያ ትብብር ስምምነት፤ ሪያድ የሞቃዲሾ ኃይሎችን እንድታሰለጥን እንዲሁም ሁለቱ አገራት በቀይ ባሕር የደኅንነት ትብብር እንዲኖራቸው ያደርጋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ ወይም እና የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ ወይም እና የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን

በሳዑዲ ቁጣ የተጠቀመው የሱዳን ጦር

ወታደራዊው ሱዳን መንግሥት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የምትሰጠውን ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ለዓመታት ሲቃወም ቆይቷል፤ ፍሬ ባያፈራለትም።

በዚህም የተነሳ የሳዑዲ እና ኤምሬቶች መቃቃር ለሱዳን ጦር ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሮለታል። ላለፉት በርካታ ወራት ሱዳን፤ ሳዑዲ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላይ ያላትን ንዴት በዝምታ ስትጠቀምበት ቆይታለች።

የሱዳን ጦር ከፓኪስታን ጋር ለተፈራረመው የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ግዢ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገችው ሳዑዲ እንደሆነች በሰፊው ይታመናል።

ይህ የግዢ ስምምነት የሱዳን ጦር ዘመናዊ ድሮኖችን እና ፀረ አውሮፕላን ሚሳዔሎችን ታጥቆ አቅሙን እንዲያጠናክር የሚያደርግ ነው። በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላይ ብልጫ እንዲኖረውም ያስችለዋል።

የሱዳን ጦር ከጥር መጨረሻ አንስቶ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር በሚያደርገው ጦርነት ድልን እየተቀናጀ ነው። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ካዱግሊ ላይ ለሁለት ዓመት አድርጎት የነበረውን ከበባ ሰብሯል።

በዚያው ግዛት ውስጥ የምትገኘው ዴሊንግ ከተማ ገብታበት የነበረው ከባብም እንዲሁ አብቅቷል። የሀቢላ ከተማንም በእጁ አስገብቷል።

ጦሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን አውድሟል። በዳርፉር እና በኮርዶፋን ግዛቶች የሚገኙ ወሳኝ ይዞታዎቹ ላይም ጥቃት ፈጽሟል።

ከሁሉም በላይ የሳዑዲ ተጽእኖ ፈጣሪነት ምስጋና ይግባውና የአሜሪካ መንግሥት በጦርነቱ ላይ ለሱዳን ጦር የተመቸ አቋም ይዟል።

ሳዑዲም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ላይ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለቡድኑ የምታደርገውን ድጋፍ በተመለከተ የምታሰማው ተቃውሞ እየጨመረ መጥቷል።

በጥንቃቄ የምትጓዘው ኬንያ

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና እስራኤል ሌላኛዋ አጋር የሆነቸው ኬንያ፤ የሳዑዲ እና የኤምሬቶችን መቃቃር በተመለከተም ሆነ በሶማሊላንድ ዕውቅና ጉዳይ እስካሁን ዝምታን መርጣለች።

ከሶማሊያ እስከ እስራኤል ካሉት ሁሉም ወገኖች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላት የምትመስለው ኬንያ፤ የደፈረሰው እስከሚጠራ ድረስ በጥንቃቄ መጓዝን የመረጠች መስላለች።

ይሄ ዝምታ መቀጠሉ ግን ሶማሊያ እንዳታልፈው አድርጓታል። በተለይም ኬንያ በሱዳን ጦርነት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ትተባበራለች መባሉ ይህንን ስሜት አጋግሎታል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አንዳንድ ጎረቤት አገራት "ለአጭር ጊዜ ፍላጎቶቻቸው" ሲሉ ለሶማሊላንድ የተሰጠውን ዕውቅና "መጠቀም" ይፈልጋሉ ሲሉ ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ክስ ሲያቀርቡ የየቱንም አገር ስም ያልጠቀሱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እና ኬንያ የእስራኤልን እርምጃ እንዲያወግዙ ለማሳመን ወደ ሁለቱ አገራት ያደረጓቸው ጉዞዎችም ውጤት አላስገኙላቸውም።