ለቁማር፣ ለወሲብ እና ለሌሎች ሱሶች የሚያጋልጠው መድኃኒት ያስከተለው ቀውስ

ኤማ በቅርቡ የቢቢሲን ዜና እስክታነብ ድረስ በድንገት የቁማር ሱስ ውስጥ ለምን እንደገባች መረዳት አልቻለችም ነበር።
ባለፈው ዓመት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ አጥታለች፤ ነገር ግን የምትወስደው ሕክምና ለዚህ ሱሷ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል አስባ አታውቅም።
ኤማ አሁን ለእንቅስቃሴ ችግር በታዘዘ መድኃኒት ምክንያት ለቁማር፣ ለወሲብ እና ለሸመታ ሱሶች መጋለጣቸውን በሚመለከት ለቢቢሲ እማኝነታቸውን ከሰጡ ከ250 በላይ ሰዎች አንዷ ነች።
ቢቢሲ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል የፖሊስ መኮንን፣ ነርሶች፣ ዶክተሮች እና የባንክ ዳይሬክተር ይገኙበታል።
ቢቢሲ ለእንቅስቃሴ ችግር የሚታዘዘው መድኃኒት የሚያስከትለውን አስከፊ የጎንዮሽ ጉዳት በተመለከተ ዘገባውን ካቀረበ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላም ብዙ ታካሚዎች ዶክተሮች አሁንም ስለ ዶፓሚን አግኖስቲክ መድኃኒቶች በተገቢው መንገድ ማስጠንቀቅ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
ምንም እንኳን መድኃኒቶቹ በቅርቡ ለእረፍት አልባ የእግር እንቅስቃሴ (Restless Legs Syndrome) ከሚሰጡት ውስጥ ደረጃቸው ዝቅ ተደርጎ ቢቀመጡም፣ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ በጠቅላላ ሐኪም የሚታዘዘው የመድኃኒት መጠን ላይ ምንም ተጽእኖ አላሳደረም።
ባለፈው ሳምንት በፓርላማው ውስጥ የጤና ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት እንደራሴ የዩኬ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ስለእነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች እንዲገመግም ጠይቀዋል።
'ሕይወቴን አመሰቃቅሎታል'
እንደ ብዙ ሴቶች ሁሉ፣ ኤማ ለመጀመሪያ ጊዜ በእርግዝና ወቅት የጤና ችግር አጋጥሟታል። ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ከአይረን መጠን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይታሰባል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የሕመሟ ምልክቶች እየተባባሱ ከሄዱ በኋላ፣ በብሪታንያ የመድኃኒት ኩባንያ ጂኤስኬ የሚመረተውን ሮፒኒሮል (Ropinirole) የተባለውን መድኃኒት ታዘዘላት።
ኤማ "የሆነ የሚቆጣጠረኝ" ነገር እንዳለ ይሰማኛል በማለት ቁማር መጫወት እና አላስፈላጊ ነገሮችን መግዛት እንደጀመረች ትናገራለች።
ከመድኃኒቷ ጋር ያለውን ግንኙነት የተገነዘበችው ባለቤቷ መድኃኒቶቿን ሲመረምር እና ቢቢሲ ካወጣቸው ታሪኮች አንዱን ሲያገኝ ብቻ እንደሆነ ታስታውሳለች።
"አነበብኩትና 'ፈጣሪ ሆይ፤ ይህማ እኔ ነኝ' አልኩ" ትላለች።
ኤማ በአካባቢዋ በሚገኝ የጠቅላላ ሐኪም ክሊኒክ ቀጠሮ ስትይዝ፣ የምትወስደውን ማንኛውንም መድኃኒት መዘርዘር እንዳለባት የሚገልጽ የኦንላይን ቅጽ መሙላት እንዳለባት ተነገራት።
ነገር ግን የቁማር ሱስ እንደያዛት እና ሮፒኒሮል እየወሰደች እንደሆነ ብትናገርም ኤማ ዶክተሯ ባህሪዋን ከመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ጋር ፈጽሞ አላገናኘውም ትላለች።
በምትኩ ኤማ መቆመሯን ቀጠለች እና በኋላም የቢቢሲን ዘገባዎች ካነበበች በኋላ መድኃኒቷ እንዲቀየርላት ጠየቀች። ቢያንስ 30 ሺህ ፓውንድ እንዳጣች ተናግራለች።
"ሕይወቴን አመሰቃቅሎታል፤ የገባንበትን ዕዳ ለምን ያህል ጊዜ ከፍለን አንደምንጨርሰው ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው" ትላለች።
መድኃኒቱ የዶፓሚን እንቅስቃሴን ከፍ በማድረግ ነው የሚሠራው። ዶፓሚን እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የሚረዳ ኬሚካል ሲሆን፣ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።
በመላው ዩኬ መድኃኒቱ ባስከተለባቸው የባህሪ የጎንዮሽ ጉዳቶች የተነሳ ለከፍተኛ ዕዳ፣ ለትዳር መፍረስ፣ ወደ ወንጀል እና ራስን ወደ ማጥፋት እንዳመሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ታካሚዎች ከመጠን በላይ እንደሚበሉ፣ ከፆታቸው የተለየ አለባበስ እንደሚከተሉ እና በግድየለሽነት ገንዘብ እንደሚያወጡ እና አንዳንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነቶችን እንደጀመሩ ይናገራሉ።
ሌላው በተደጋጋሚ ከሚሰሙ ታሪኮች መካከል ደግሞ ለብዙ አስርት ዓመታት በትዳር አብረውት የኖሩት ሰው ፆታዊ ፍላጎቱ አይሎ ማግኘታቸውን የሚገልጹ አረጋውያን ሴቶች ናቸው።
ተጠቃሚዎች ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ባህሪያት አልነበራቸውም። እነሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው፣ እነዚህ ባህሪያት በመድኃኒታቸው ምክንያት ሊከሰቱ እንደሚችሉ አልተገነዘቡም።
መድኃኒቱን ከሚወስዱ ከስድስት የፓርኪንሰን ታካሚዎች መካከል አንዱ በመድኃኒት የሚከሰት የጎንዮሽ ጉዳቶች ይታይበታል።
ነገር ግን ይህ ጉዳት ከመድኃኒቱ ጋር በሚሰጡ በራሪ ወረቀቶች ላይ አልተገለጸም። ከመድኃኒቱ ጋር በሚሰጡት በራሪ ወረቀቶች ላይ ከተዘረዘሩት የጎንዮሽ ጉዳዮች መካከል የልቅ ወሲብ ምሥሎች ሱስ ውስጥ እንደሚከት አልተጠቀሰም በሚል ትችት ቀርቧል።
ቢቢሲ አባት እና ልጅ ከመድኃኒቱ ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የሚገልጽ ታሪክ አውጥቶ ነበር።
ይህ የሆነው አባትየው በቸልተኝነት ከደንበኞቹ 600 ሺህ ፓውንድ በመስረቅ ለወሲብ እና ለጥንታዊ ቅርሶች ግዢ እንዲከፍል ካደረገው በኋላ ነው።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብዙ ወንዶች ይህን ዓይነት ባህሪ እንደሚታይባቸው እና በአሁኑ ጊዜ ከመጠን በላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፍላጎት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Family handout
ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረው ሚካኤል፣ በቅርቡ ለገጠመው የጤና ችግር መድኃኒቱ ከታዘዘለት በኋላ በተደጋጋሚ በወሲብ ንግድ ወደ ሚተዳደሩ ሰዎች መሄድ ጀምሯል።
"በወሲብ ሱስ ተጠምጄያለሁ ብዬ አስባለሁ" ይላል፤ ምንም እንኳን ትዳር ቢኖረውም. . . ከበርካታ ሴቶች ጋር እንደተኛ አክሎ ተናግሯል። ከዚህ በፊት ሚስቱ ላይ ወስልቶ ወይም ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነት ፈጽሞ አያውቅም።
እንደሌሎች ሰዎች ሁሉ፣ መጀመሪያ ላይ ስሜቱን እንደወደደው ይናገራል፣ አሁን ግን ወጥመድ ውስጥ እንደገባ ይሰማዋል። ይህን ለሐኪሙ ወይም ዘወትር ወደ ሕክምና ክተትል አብራው ለምትሄደው ለባለቤቱ መንገር አልቻለም።
"እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ አውቃለሁ፤ ግን ሊረዱኝ ከሚችሉ ሰዎች ጋር መነጋገር አልችልም" ይላል። "ወደፊት የምሄድበት ቦታ የለኝም" ሲልም አክሏል።
ቢቢሲ ጂኤስኬ እአአ በ2000 መድኃኒቱ በወሲባዊ ፍላጎት ላይ ስለሚያስከትለው ተጽእኖ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ከመስጠቱ ከሰባት ዓመታት በፊት፣ ከመድኃኒቱ ጋር የተያያዘ የሕፃናት ወሲባዊ ጥቃት መፈጸሙን እንዳወቀ አረጋግጧል።
በሮፒኒሮል የሚኖር አንድ የ63 ዓመት አዛውንት የሰባት ዓመት ልጅ ላይ ፆታዊ ጥቃት ፈጽሞ ታስሯል።
ይህ ጉዳይ በኋላ ላይ የመድኃኒት አምራቹ ኩባንያ በ2003 በመድኃኒቱ "ወጣ ያለ" የወሲብ ባህሪ መካከል ያለውን ግንኙነት ባወጣው ሪፖርት ላይ አካትቶታል።
ጂኤስኬ ሪፖርቱን በቀጣዩ ዓመት ለዩኬ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ጋር እንዳጋራ እና በቀናት ውስጥ ስለ ወሲባዊ ጥቃት ወንጀል መናገሩን ገልጿል።
ነገር ግን ስለ "ወጣ ያለ" ባህሪ ከመድኃኒቱ ጋር በሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ውስጥ ታይቶ አያውቅም። ይልቁንም "የሚጨምረ የወሲብ ፍላጎት"፣ "ጎጂ ባህሪ" እና "የተለወጠ የወሲብ ፍላጎት" ሊኖር የሚችልበትን ዕድል ይዘረዝራል።
በአውሮፓውያኑ 2005 ደግሞ መድኃኒቱ ለፆታዊ ችግር ሕክምና ውጤታማ መሆኑን ለማየት በአሜሪካ ውስጥ ካለ የግል ሆስፒታል ጋር በትብብር መሥራት ጀምሯል።
ጂኤስኬ ለቢቢሲ እንደተናገረው መድኃኒቱ በስፋት ሙከራ ተደርጎበታል። በዓለም ዙሪያ ባሉ ተቆጣጣሪዎች ተቀባይነት አግኝቷል። የጎንዮሽ ጉዳቶቹም በግልጽ ተገልጸዋል።
የመድኃኒት እና የጤና እንክብካቤ ምርቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ (ኤምኤችአርኤ) ባወጣው መግለጫ ደግሞ በ2007 ማስጠንቀቂያዎች እስኪያካትት ድረስ ዓመታት እንደፈጀበት ገልጿል።
ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ሁሉንም የሚገኙ ማስረጃዎች ግምት ውስጥ ማስገባትን ስለሚጠይቅ እና ከመድኃኒቱ ጋር የሚሰራጩ በራሪ ወረቀቶች "ሙሉ" የሆኑ የባህሪያት ዝርዝር ሊያካትቱ አለመቻላቸው ነው። ለዚህም የመድኃኒቱ ተጽእኖ ከግለሰብ ግለሰብ መለያየቱ አንዱ ነው።
ቢቢሲን ያነጋገራቸው ብዙዎቹ ሰዎችም በአግባቡ ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው የተናገሩ ሲሆን፣ የጎንዮሽ ጉዳቶች በተመለከተ ፍትሕ ማግኘት እንደማይችሉ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ፣ ከዩኬ ውጭ ከመድኃኒቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ክሶች ተመሥርተዋል። የካሳ ጥያቄዎችም ቀርበዋል፤ ተከሳሾች በነፃነት የተለቀቁባቸው የወንጀል ጉዳዮችም ተስተውለዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት የቤልጂየም ፍርድ ቤት የሮፒኒሮል መድኃኒቱ የአራት ዓመት የልጅ ልጁን ላይ የወሲብ ጥቃት እንዲፈጽም ማድረጉን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ ግለሰብን ነፃ አውጥቷል።
በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው እነዚህን የጎንዮሽ ጉዳቶች ታካሚዎችን በበቂ ሁኔታ ማስጠንቀቅ ባለመቻሉ ጂኤስኬን ከሷል፤ በመጪው መጋቢት በፈረንሳይ ፍርድ ቤት ፍርድ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ሰውየው መድኃኒቱ ከባልደረባው ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳበላሸው እና በቁማር 90 ሺህ ዩሮ እንዲያጣ እንዳደረገው ተናግሯል። ለደረሰበት ኪሳራም ካሳ ጠይቋል።















