በረመዳን ጾም ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው ቴምር ለጤና ያለው ጥቅም

ቴምር
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች በጾም ወቅት ፀሐይ ስትጠልቅ አንድ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። እርሱም በቴምር ጾማቸውን መፍታት ነው።

በዚህ ረጅም የጾም ጊዜ ጤናማ ሙስሊሞች ከአምስቱ የእስልምና ምሰሶዎች አንዱ የሆነውን ረመዳን ለማሰብ ከጀንበር መውጣት እስከ መጥለቅ ድረስ ከምግብ እና ከመጠጦች ይታቀባሉ።

ቴምር በነብዩ መሐመድ ጾምን ለመፍታት ሁነኛ ስለመሆኑ ምክር የተሰጠበት ነው። በቅዱስ ቁራንም በርካታ ጊዜ የቴምር ስም ተጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም ቴምር ለማንኛውም ጾመኛ ለሰውነት እና ለጤና በርካታ ጠቀሜታዎች ይዟል።

'ልዩ' የምግብነት ይዘት

ቴምር በውስጡ በያዛቸው የንጥረ ምግብ ይዘቶች ስብስብ ምክንያት ለረጅም ሰዓት ለሚጾሙ ሰዎች ዓይነተኛ የጾም መፍቻ ነው።

ረመዳንን የሚጾሙት የሥነ ምግብ ባለሙያ ሸናዝ በሽር "ጾማችሁን ስትፈቱ ሰውነታችሁ ግሉኮስ ለማምረት ይሞክራል። ምክንያቱም ኃይል ለማግኘት ስለሚያስፈልገው" ይላሉ።

በቴምር ውስጥ ያለው ከፍተኛ የስኳር መጠን የደም የስኳር መጠንን ከፍ በማድረግ ከየትኛውም ምግብ በላይ በጣም ፈጣን ነው። ሌሎች ምግቦችን ሰውነት እስኪሰባብራቸው ድረስ ጊዜ ይወስዳሉ።

"ቴምር ቀላል ስኳር ስላለው በጣም ልዩ ነው። ነገር ግን የተወሳሰበ ካርቦሃይድሬትም አለው" ሲሉ ያክላሉ።

ይህም ማለት ፍሬው ቀኑን ሙሉ ቀስ እያለ ኃይል ይለቃል። ለዚህም ነው ቀኑን ሙሉ ላልተመገበ ሰው ሁነኛ አማራጭ የሚሆነው።

ቫይታሚን ቢ6፣ ኤ እና ኬ እንዲሁም በአይረን የተሞላ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰውነት የሚያስፈልገውን ንጥረ ምግብ የሚሰጥ ይሆናል።

ሂጃብ የለበሱ ሁለት ሴቶች ቴምር እየተመገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቴምር ለጾመኞች በርካታ የኒውትሬሽን ዓይነቶችን የያዘ ነው

ፈሳሽ መስጠት

ምንም እንኳ ቴምር ደረቅ ፍራፍሬ ቢሆንም ፈሳሽ በመስጠትም ይጠቅማል።

በተፈጥሮ የያዘው 'ኤሌክትሮላይት ፖታሲየም' የተባለ ንጥረ ነገር ውሃን አምቆ መያዝ እና ወደ ሕዋስ መሳብ ይችላል።

"በርካታ ሰዎች ጾማቸውን በቴምር እና በውሃ አንድ ላይ ይፈታሉ። ይህም ኃይል እና ፈሳሽ ለማግኘት በጣም ጥሩ ነው" ይላሉ።

"ስለዚህ ከዚህ በላይ ተጨማሪ 'ኤሌክትሮላይት' አያስፈልግም" ሲሉ ያክላሉ።

ከመጠን በላይ መመገብ

አንዳንድ ሰዎች በረመዳን ወቅት ክብደታቸው ይቀንሳል። ነገር ግን የሚጾሙ ሰዎች በአፍጥር ወቅት ከመጠን በላይ ከተመገቡ ክብደታቸው ይጨምራል።

በተለምዶ ሙስሊሞች ቴምር ከተመገቡ በኋላ የአፍጥር ምግባቸውን ሳይመገቡ ወዲያው ወደ ጸሎት ይገባሉ።

ሰውነት ከቴምር ያገኘውን ኃይል እስኪሰባብር ድረስ ከመጠን በላይ የመመገብ ፍላጎት ረገብ ይላል።

"ሰውነታችሁ በእርግጥም የተወሰነ ምግብ እንዳገኘ ለማሰብ የምግብ መፈጨቱን ሂደት ዕድል ይሰጠዋል" ይላሉ በሽር።

የስነ ምግብ ባለሙያ ሸሀንዝ በሽር

የፎቶው ባለመብት, Shehnaz Bashir

የምስሉ መግለጫ, ቴምር በአፍጥር ከአቅም በላይ እንዳንመገብን ይረዳናል ይላሉ የስነ ምግብ ባለሙያዋ

የምግብ መፈጨት

የሆድ ድርቀት እና መነፋት በሚጾሙ ሙስሊሞች ዘንድ የተለመዱ ችግሮች ናቸው። ይህም ምክንያቱ በቀን ውስጥ መመገብ እና መጠጣት በተለምዶ ለሆድ ዕቃ ጤናማ እንቅስቃሴ የሚረዳ ሲሆን፤ ይህ ሁኔታ ግን በጾም ወቅት ለረጅም ሰዓታት የሚስተጓጎል ይሆናል።

ቴምር ከፍተኛ የፋይበር ምንጭ ያለው ሲሆን፤ ይህም ዐይነ ምድር በአንጀት ውስጥ በቀላሉ እንዲዘዋወር ያደርጋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት በቀን 30 ግራም ፋይበር መመገብን ይመክራል።

በሽር "አንዳንድ ጊዜ በረመዳን ቀላል የካርቦሃይድሬት ምግቦች ሊያምረን ይችላል። ነገር ገን ቀደም ብለን ምግብ ካዘጋጀን ምግባችን ውስጥ ፋይበር መኖሩን ማረጋገጥ እንችላለን" ይላሉ።

ምግባችሁ ላይ ጥራጥሬዎችን ጣል ማድረግ ፋይበር ለማግኘት ሌላኛው ቀላል መንገድ ሊሆን ይችላል።

ቴምር ባንመገብስ?

ከረመዳን ጾም ውጪ ከሃይማኖታዊ ምክንያቶች ባሻገር ለጤና ብለው በሚጾሙ ሰዎች ዘንድ ቴምር ተወዳጅ እየሆነ ነው።

ቴምር የማይወዱ ከሆነ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝርያዎች አሉ። ስለዚህም እነዚህን ሞክሩ።

"ሁሉም የተለያየ መልክ አላቸው። አንዳንዶች ይታኘካሉ፣ አንዳንዶች ለስላሳ ናቸው፣ አንዳንዶች ጠንካራ ቆዳ አላቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ ትንሽ ቆዳ አላቸው" ይላሉ በሽር።

ይህንም ሞክረው ቴምርን የማይወዱ ከሆነ፤ ከጁሶች ጋር አብሮ በመፍጨት መጠቀም ይቻላል።

"ቴምርን ከወተት ጋር መቀላቀል፤ ምንአልባት ከትንሽ እርጎ እና የለውዝ ፍሬ ጋር ፈጭቶ በዚህ መንገድም መጠቀም ይቻላል" ይላሉ።

የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ቴምር ሰውነት ማግኘት የሚያስፈልገውን አብዛኛውን ንጥረ ነገር በመያዝ ቆንጆ ምግብ ነው ይላሉ።