በፍቅር ውስጥ አብሮ ማደግ፡ ትክክለኛ የሕይወት ዘመን ውሃ አጣጭን የማግኛ ሳይንስ

ሁለት የልብ ቅርጽ የተቀመጠበት ጠርሙስ
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

የፍቅረኞች ቀን በሚከበርበት ዕለት ለእኔ የሚሆን ውሃ አጣጭ፣ የግራ ጎን የሆነ ስፍራ አለ ብሎ የሚያምን ሊኖር ይችላል።

በታሪክ ውስጥ የሰው ልጅ ፍቅር የአጋጣሚ ጉዳይ ይሆናል ብለው እንደማያምን ታይቷል። "የተጻፈልኝ አለ" ብሎ ማመን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ አለ።

በጥንት ግሪክ ፕሌቶ እያንዳንዳችን አራት እጅ፣ አራት እግር እና ሁለት ፊት እንደነበረን ይጠቅሳል።

ከዚያ ዜዮስ ሁለት አድርጎ ከፈለን። ይኸው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እያንደንዳችን በምድር ላይ የጠፋውን ግማሽ አካላችንን ኀሰሳ ላይ ነን የሚል አፈ ታሪክ አለ።

እናም ለዘመነኛ ሰው ውሃ አጣጭ ፍለጋ የሚደረገው ኀሰሳ ተሳክቶ አጣማሪውን ሲያገኝ የልቡ መሻት ይሞላል ማለት ነው።

ይህን ዓይነት 'ወንድ ያለ ሴት ባዶ ነው. . . " ዓይነት አመለካከት በፈረንሳይ እና በብሪታኒያ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ በሚነገሩ ተረቶች፣ አፈ ታሪኮች እና ተረኮች ውስጥ ይገኛል።

ለሚወዱት ሲሉ ራስን መስዋዕት ማድረግ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሌላው የሚቱ አካል ነው።

ታላቁ የእንግሊዝ ደራሲ ዊሊያም ሼክስፔርም በኃያል ፍቅር የተሳሰሩ ነገር ግን በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ወይም በዕጣ ፈንታ ስለሚነጣጠሉ ጥንዶች ጽፏል።

ሼክስፔር በብዕሩ ዓለም የጥንዶቹን የፍቅር ታሪክ ጽፋ እስከ መጨረሻው ደስታ ጨልጠው እንዳይሰክሩ እንደምታለያያቸው የሚያሳዩ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎቹ ተመድርከዋል፤ ተነብበዋል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የሆሊውድ ፊልሞች፣ የሮማንስ ዘውግ ያላቸው ልብ ወለዶች የቀባቧቸው የፍቅር ታሪኮች የብዙ ተመልካች እና አንባቢ ቀልብ ገዝተዋል።

ነገር ግን ሳይንስ ስለ የፍቅር አጋር ምን ይላል? በእርግጥ ውሃ አጣጫቸውን ለሚፈልጉ ከሰፊው ዓለም አንድ ጥግ ተቀምጦ ይገኛል?

 የፕሌቶ እና ዜዮስ ምሥሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሌቶ (በስተግራ) እና ዜዮስ (በስተቀኝ)

'የሕይወቴ ሕይወት' የሚየስብል ፍቅር እንዴት?

በአንጅሊያ ሩስኪን ዩኒቨርስቲ የሶሻል ሳይኮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ቫይረን ስዋሚ በአውሮፓ ታሪኮች፣ ልብ ወለዶች፣ ተረቶች ውስጥ ያሉትን የአውሮፓውያን ዘመናዊ የፍቅር አስተሳሰብ ለመረዳት ፍተሻ አካሂደዋል።

"እነዚህ ታሪኮች መጀመሪያ አንድን ግለሰብ እንደ ጓደኛ፣ እንደ ሕይወት አጋር መምረጥ እንዳለብን ይገፉ ነበር" ይላሉ።

"ከዚያ በፊት በአብዛኞቹ አውሮፓ ውስጥ፣ የፈለጋችትን ያህል ሰዎች መውደድ ይቻል ነበር። እና ፍቅር ተለዋዋጭ ነበር፤ ብዙውን ጊዜ ስለ ወሲብ አልነበረም።"

በጊዜ ሂደት ሰው ልጅ ከግብርና ሥራ ራሱን እያራቀ ሲመጣ እና በኢንዱስትሪ ላይ ጥገኛ ሲሆን፣ ሰዎች ያላቸው የእርስ በርስ ግንኙነት ስንጥቃት እየገባው መጣ።

ግለሰቦች "እየተነጠሉ" በመምጣት "አንድ ሌላ ሰው፣ ድብታ ከተጫነው፣ የሐዘን ጥቁር ደመና ከከበበው ሕይወት እንዲታደጋቸው መፈለግ ጀመሩ።"

ያለንበት ዘመን ደግሞ የፍቅር መተጫጨትን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ እና መተግበሪያዎች በመውሰድ ጉዳዩን የአልጎሪዝም ጣጣ አድርጎታል።

ስዋሚ ይህንን "ወዳጅነትን መገበያየት" ሲሉ ይገልጹታል። የነፍስን አጋር የመፈለግ ጣጣ በተቃራኒው የምፈልገውን የሚያሟላልኝ ማነው ወደሚል ሃሳብ ዞረ።

"ለበርካታ ሰዎች ይህ ያለ እስትንፋስ በድኑን የቆመ ሃሳብ ነው፤ አጋርን እየተገበያየን ነው።. . . በበርካታ መተግበሪያዎች ላይ ይሆነኛል የምንለውን እያሰስን. . .አሁን ታከተኝ ፍለጋዬን ማቆም አለብኝ" የሚል ስሜት ላይ እስክንደርስ የሚሆነንን በዙሪያችን ካሉት መካከል እንፈልጋለን ሲሉ ይተቻሉ።

የላንሴሎት እና ጉዌንቬር ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቫይረን ስዋሚ የዛሬዎቹ ስለ ፍቅር ያሉ ሀሳቦች እንደ ላንሴሎት እና ጉዌንቬር ካሉ የመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ ታሪኮች ሊገኙ እንደሚችሉ ያምናሉ

ውሃ አጣጭ

ጄሰን ካሮል በአሜሪካ ብሪግሃም ያንግ ዩኒቨርስቲ የትዳር እና የቤተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር ናቸው።

እርሳቸው "ውሃ አጣጭ" ለሚለው የሰው ልጅ ሃሳብ 'ስሱ' ናቸው።

"የሰው ልጅ ከፍጥረቱ አጋር ፈላጊ ነው" በማለት ብቻችንን እንሆን ዘንድ አልተመረጥንም" ይላሉ።

"ከአጋራችን ጋር መሆን እንፈልጋለን" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ለተማሪዎቻቸው አጋራቸውን መፈለግ ሳያቆሙ የግራ ጎን የሚለውን ሃሳብ እንዲተዉት ይመክራሉ።

የፕሮፌሰሩ ሃሳብ እርስ በርሱ የሚጣረስ ቢመስልም ለካሮል ግን በዕጣ ፈንታ እና በመጣመር መካከል ያለ ልዩነት ነው።

"ውሃ አጣጭ በቀላሉ ይገኛል። ነገር ግን አንድ የእኔ የሚሉት ሰው ግን ሁለት ሰዎች መካከል ውስጥ ያለ መሳሳብ፣ በዓመታት ውስጥ የሚዳብር፣ በይቅርታ እና አንዳንዴ በመጋጨት ውስጥ ጸንቶ የሚቆም ነው" ይላሉ።

'ለእኔ የተጻፈ' የሚሉት ወጥመድ

ካሮል የሚያቀርቡት ማብራሪያ መነሻውን ያደረገው ለአስርት ዓመታት ካደረጉት ጥናት ነው።

ለእኔ የተጻፈ የሚሉት ወጥመድ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች "በዕጣ ፈንታ ማመን" ወይንም "አብሮ ማደግ" ከሚሉት የባለሙያዎች ሃሳብ ጋር የተገናኘ ነው።።

በ1990ዎቹ እና 2000ዎቹ በፕሮፌሰር ሲ ሬይመንድ እና ባልደረቦቻቸው የተሠሩት እና በሰፊው የሚጠቀሱት ጥናቶች አንዳችን ለሌላኛችን የተፈጠርን ነን ብለው የሚያምኑ ጥንዶች ከግጭት በኋላ ፍቅራቸውን መጠየቅ ይጀምራሉ ይላሉ።

ነገር ግን አብሮ ማደግ የሚለው ላይ የተመሠረቱ ጥንዶች በመካከላቸው አለመግባባት ቢከሰትም አብረው ይቆያሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

ካሮል አብሮ ማደግ ላይ የሚያተኩሩ አመለካከቶች በፍቅር ግንኙነታቸው ውስጥ የሆነ የተለየ ነገር መፈለጋቸው አይቀርም ይላሉ። መንገዱ ውጣ ውረድ የበዛበት፣ ወጀብ የማያጣው መሆኑን ግን ከግምት ውስጥ አስገብተዋል።

"ይጠይቃሉ. . .ግንኙነታቸውን የተሻለ፣ ለውጥ የሚያሳይ እድገት ያለው እንዲሆን ምን የተሻለ ማድረግ እንዳለባቸው ይጠይቃሉ።"

 በፍቅር ውስጥ ያሉ ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተመራማሪዎች በፍቅር ውስጥ አብሮ ማደግ አለ ብለው የሚያምኑ ጥንዶች ከግንኙነታቸው የተለየ ነገር ይጠብቃሉ፤ ነገር ግን በሂደቱ ውስጥ ተግዳሮት መኖሩን አይክዱም ይላሉ

በእርሳቸው አመለካከት ለእኔ የተጻፈ ነው የሚሉት ወጥመድ፣ ፍቅሩ ብቻ ሳይሆን፣ ፍቅር ፈተናዎች ሊኖሩት አይገባም የሚለው አመለካከት ራሱ ችግር አለበት።

ረዥም ጊዜ በሚቆዩ ጥንዶች መካከል የሚታየው ጠንካራ ነገር፣ ሁሉ ነገር በአበባ ምንጣፍ ላይ መጓዝ አለመሆኑን ይረዳሉ።

በጥንካሬ ወቅት ብቻ ሳይሆን በድካም እና በተግዳሮት ውስጥም እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመሄድ ቁርጠኛ መሆናቸው ላይ ነው።

ጥንዶቹ በድካማቸው ወቅት እንዴት አብረው እንደቆሙ ለማወቅ ግን እነርሱ እንስካልነገሩን ድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ካሮል የፍቅር አጋር ዕድል ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች ለግንኙነታቸው እስትንፋስ የሚሰጥ ነገር ለማድረግ ተነሳሽነት ሲያጡ ይስተዋላል ይላሉ።

አክለውም ለእኔ የተጻፈችው እርሷ ነች ወይም እርሱ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች ግንኙነታቸው መንገራገጭ ሲጀምር አብሮ ለመቀጠል ሲቸገሩ ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።

"ችግር በገጠመ የመጀመሪያው ሰዓት ለእኔ የተጻፍክ መስሎኝ ነበር። ምናልባት ግን አይደለህም ማለት ነው። ምክንያቱም የነፍስ አጋሮች እንዲህ መሆን የለባቸውም" ሲሉ ያስረዳሉ።

"ግን ግንኙነቱ ጸንቶ የሚቀጥል ከሆነ ግን የቁልቁለት ጉዞ አይገጥመውም።"

እውነተኛ ፍቅር ወይስ ትራውማ?

ቪኪ ፓቪት በለንደን የምትኖር የፍቅር አማካሪ ነች።

'ለእኔ የተጻፈ' የሚሉ ጥንዶች ስሜታቸውን ከሚያማልሉ አገላለጾች የተነሳ መሆኑን፣ በቀላሉ የሚሸነገሉ መሆናቸው እና የማያቋርጥ የጭንቀት ስሜት ጋር የሚከሰት መሆኑን ታስረዳለች።

"ብዙ በአፍላ ፍቅር እፍ ማለት ሲኖር፣ አንዳንድ ጊዜ የከረሙ ጤናማ ያልሆኑ ባህሪያቶችን መቀስቀስ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ" ትላለች።

"ወጥነት የጎደለው ወይም ትንሽ ሞቅ እና ቀዝቀዝ በሚል የሚዋልል ስሜት የሚገለጽ ሰው 'እንደገና እስካየው ድረስ እጓጓለሁ' የሚል ስሜት እንዲሰማዎት ሊያደርግ ይችላል፤ ነገር ግን እውነቱ በጣም ብዙ ጭንቀት እየሰጧችሁ እና የበለጠ እንድትፈልጓቸው እያደረጉ ነው።"

ፓቪት ዕጣ ፈንታ እንደሆነ የምናስበው ስሜት ከዚህ ቀደም የጎዳንን እና ለማከም የምንፈልገውን ችግር ከነርቭ ሥርዓታችን ላይ እየጠራን ሊሆን ይችላል ስትል ቴራፒስቶች 'ትራውማ ቦንድ' ሲሉ እንሚጠሩት ትናገራለች።

እንዲህ ዓይነት ጥምረት ፍቅር ቢመስልም ሰዎች ከዚህ ቀደም ወደሚያውቁት ዓይነት ጤናማ ወዳልሆነ ግንኙነት እንዲሳቡ ያደርጋል ብላለች።

ቪኪ ፓቪት

የፎቶው ባለመብት, Vicki Pavitt

የምስሉ መግለጫ, የፍቅር አማካሪዋ ቪኪ ለእኔ የተጻፈ ነው የሚሉት የፍቅር አጋር ብዙ ጊዜ የጭንቀት ምንጭ ይሆናል ትላለች

የፍቅር ስሜት

የነፍሴ አጋር የሚሉት ነገር አይኖርም ብሎ ማሰብ ትንሽ ከፍቅር ማፈንገጥ ይመስላል። ሥነ ሕይወት በዚህኛው መንገድ ላይ የሚገለጽ ፍቅር መኖሩን ያመለክታል።

ከሆርሞን ጋር የተያያዘ የወሊድ መቆጣጠሪያ ጥንዶች አንዳቸው ስለሌላኛቸው የሚሰማቸውን ሊቀይረው ይችላል።

ጥናቶች እርግዝናን የሚያስቀሩ መድኃኒቶች በወር አበባ ዑደት ወቅት ለፍቅር አጋር የሚኖርን ስሜት እንደሚቀንሱ ይጠቁማሉ። ይህም የመጀመሪያ የትዳር ጓደኛ ምርጫን ሊለውጥ ይችላል።

አንዱ ግን ብቸኛው ያልሆነ

ሥነ ልቡና እና ባዮሎጂ "እርሱ/እርሷ ብቻ" የሚለውን የምናስብበትን መንገድ ቢያስቀምጡም ሒሳብ ደግሞ ሌላ መንገድ ያመላክታል።

በናሽቪል፣ ቴኒሲ በሚገኘው የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሑር የሆኑት ዶ/ር ግሬግ ሊዮ የመጣጣም ስልተ ቀመር (ፎርሙላ) አዘጋጅተዋል። ይህ ስልተ ቀመር "አንድ" ብቻ ሳይሆን ብዙ "አንዶች" ሊኖርዎት እንደሚችል ይጠቁማል።

በፐብሊክ ኢኮኖሚ ቲዎሪ ጆርናል ላይ በታተመው ጥናታቸው ከነፍስ አጋር ጋር የሚኖር ጥምረት ውስጥ ሁሉም ሰው በኮምፒውተር በተደራጀ የፍቅር ጓደኝነት ቋት ውስጥ ይገኛል።

በሺዎች የሚቆጠሩ በዲጂታል የተፈጠሩ የፍቅር ጓደኝነት ፈላጊዎች እርስ በርስ ነጥብ ይሰጣጣሉ። ስልተ ቀመሩ "የመጀመሪያ ደረጃ የነፍስ አጋሮች" የሚለውን እርስ በርስ በማዛመድ ይመርጣል።

ከዚያም እነርሱን በማስወገድ የቀሩትን ያስመርጣል እና ሁለተኛ ደረጃ የነፍስ ተጣማሪ ያገኛሉ። እንዲዚያ እያለ ይቀጥላል።

በፕሮፌሰሩ በኮምፒውተር የታገዘ አጋርን የመምረጥ ጥናት አንድ ሰው የሚሆነውን በመጀመሪያ ምርጫ የማግኘት ዕድሉ አናሳ ነው። ነገር ግን ሰዎች ከሁለተኛ ወይንም ከሦስተኛ ምርጫቸው አጋራቸውን ሊያገኙ ይችላሉ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ፣ ጥንዶች አንዳቸው የሌላኛው ቀዳሚ ምርጫ ባይሆኑም ደስተኛ እንደሆኑ ይቆጠራሉ።

በእርግጥ ይህ የሂሳብ ባለሙያው የቁጥር ጨዋታ ቢሆንም የሚነግረን ነገር ግን የፍቅር ቀመሩ በርካታ ጥሩ ዕጩ ሊሆኑ የሚችሉ መኖራቸውን እና "አንድ ብቻ" አለመሆኑን ነው።

በቀይ ጨርቅ ጣቶቻቸው የተሳሰረ ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፓቪት ዕጣ ፈንታ የሚመስለን ነገር ከትራውማ ጥምረት ጋር የጠያያዘ ሊሆን ይችላል ትላለች

ትንሽ ግን አስደሳች ነገር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ታዲያ ጥንዶች አንዳቸው የሌላኛቸው ብቸኛ ምርጫ መሆናቸውን እንዴት ማረጋገጥ ይችላሉ?

በዘ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዣኪ ጋብ ይህንን በ2015 በሶሲዮሎጂ መጽሔት ላይ በታተመው 'Enduring Love' ጥናታቸው ላይ አብራርተዋል።

በጥናቱ ወደ 5,000 የሚጠጉ ሰዎች እና 50 ጥንዶችን ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል። የግል ማስታወሻቸው ተፈትሿል። በቤታቸው ውስጥ የተከሰቱ ጉዳዮች ተመዝነዋል።

ሰዎችን ምን እንዳስደሰታቸው ሲጠየቁ ፀሐይ እየጠለቀች የተደረገላቸው የቃልኪዳን ቀለበት ወይም የሄዱባቸው ድንቅ ስፍራዎች አይደሉም።

"ያልተጠበቀ፣ እንደሚያስቧቸው የሚያሳዩ ስጦታዎች እና ፍቅርን የሚገልፁት በምሽት ወደ አልጋ ከመሄዳቸው በፊት የጠጡት ሻይ፣ አበባ መግዛት፣ በግብዣ መካከል የተለዋወጧቸው ፈገግታዎች እንዲሀም በቀዝቃዛ ማለዳ ተነስተው የሠሩላቸው እነርሱን የሚያስብ ቁርስ ሊሆን ይችላል።"

እነዚህ "በየዕለቱ ትኩረት የሚስቡ ድርጊቶች" ከታላላቅ የፍቅር ምልክቶች የበለጠ አቅም ኖሯቸው ተገኝተዋል።

በጥናቷ ላይ 22 በመቶ የሚሆኑ እናቶች እና 20 በመቶ የሚሆኑት ልጅ የሌላቸው ሴቶች ዋጋ እንዲሰማቸው ከሚያደርጓቸው ሁለት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ የሆነውን፣ ከትላልቅ ምሽቶች ወይም ውድ ስጦታዎች የበለጠ፣ ትናንሽ አካላዊ መግለጫዎችን መርጠዋል።

በመረጃው ውስጥ ያለው የግንኙነት እርካታ በዋናነት ስለ ገንዘብ ወይም ስለ ሮማንስ አልነበረም፤ ይልቁንም ስለ "የጥንዶች በቅርበት መተዋወቅ" እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ስላለው አገላለጽ ነበር።

በአጋር የሚደረግ ማቀፍ፣ ማዕድ አብሮ መጋራት፣ በቤታቸው ውስጥ አብረው የደነሱት ዳንስ፣ የትዳር አጋር በስልክ ላይ የሚያስቀምጡት የሚወዱት ምሥላቸው የበለጠ ስሜት ይሰጣል።

"እዚህ ላይ የነፍስ አጋሮች ስሜት ከሕይወት በላይ አይንሳፈፍም፤ ጥንዶቹ የኑሮን የዕለት ተዕለት ጫናዎች የሚቋቋሙት ስንዝር በስንዝር እየተጓዙ ነው" ይላሉ።

የቫላንታይን ምሽት የእራት ግብዣ

ሳይንስ ፍቅርን አይነጥቅም፤ ከዚያም ይልቅ በደስታም ሆነ በሐዘን ወቅት ፍቅር እንዲያብብ በማድረግ ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ካሮል ይናገራሉ።

"ልዩ በሆነ ግንኙነት ውስጥ ለመኖር ያለን ምኞት በጣም ያስደስተኛል" ይላሉ።

ፓቪት "ከእርስዎ ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት መፍጠር የሚችሉ እና ማንም ሰው ፍጹም እንዲሆን መጠበቅ ማቆም የሚችሉ ከሆነ፣ የእርስዎ ሰው አንድ ሰው እንዳለ ማመን ጥሩ ነው፣ ጠቃሚ ነው" ብለዋል።

የነፍስ አጋሮችን በተመለከተ ሳይንስ የተለየ መንገድን ነው የሚያመለክተው።

የእኔ ብቻ ነው ከሚሉት ሰው ጋር ግንኙነት የሚመሠርቱ ሰዎች፣ ዕጣ ፈንታን እና አጋጣሚን መጠበቅ ያቆሙ ከፊታቸው ወደሚገኝ ጉድለት ወዳለው ሰው መመልከት የቻሉ እና በተግባር "ከዚህ ሰው ጋር እንሞክር?" የሚሉ ናቸው ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናቅቃሉ።