ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር እንዲቆራረጡ የሚያደርጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
ሳራ ከእናቷ ጋር መነጋገር ያቆመችው ከ21ኛ ዓመት ልደቷ በኋላ ነበር። ከእናቷ ጋር በቁጣ የተሞላ የስልክ ንግግር ካደረጉ በኋላ ማውራት አቆሙ።
ቤተሰቦቿ ልደቷን ለማክበር ጊዜ ማጣታቸው አንደኛው ምክንያት ነበር። ሳራ እንደምትለው፣ እናቷ ፍቅር አታሳያትም፤ ትኩረቷን ያደረገችውም በራሷ ሕይወት ላይ ብቻ ነው።
የሳራ እናት ሳራ የተማረችውን ትምህርት በማጣጣል ቤተሰቡን በግብርና ሥራ እንድታግዝ ትወተውታለች።
የሳራ አባት ቁጥጥር የሚያበዛ እና በዝባዥ ነው። ሳራ እናቷ ከአባቷ ከለላ እንድትሰጣት ትፈልግ ነበር። እናቷ ግን እሷን አለመጠበቋ ያሳዝናታል።
ሳራ እና እናቷ ለሦስት ዓመታት አላወሩም። ሳራም ነጻነት እንዳገኘች ትናገራለች።
ሳራ ከቤተሰቦቿ ጋር ያወራችው አገር ጥላ መውጣት ስታስብ ነው። ቤተሰቦቿ ምንም እንዳልተፈጠረ ሆነው አነጋገሯት።
ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ግንኙነታቸው ሻክሮ ቀጥሏል።
ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚቆራረጡ ልጆች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ቢታመንም በመረጃ የተደገፈ ነው ለማለት ያስቸግራል።
ከቤተሰብ ጋር መቆራረጥ ልክ ነው? የሚለው አከራካሪ ነገር ነው።
በቤተሰባዊ ግንኙት ዙሪያ መጽሐፍ ያሳተመችው እና በዩኒቨርስቲ ኦፍ ዌስት ኢንግላንድ የሥነ ልቦና መምህርት የሆነችው ሉዚ ብሌክ እንደምትለው በጉዳዩ ላይ እምብዛም ጥናት አልተሠራም።
"ከቤተሰብ ጋር ስለመቆራረጥ ማውራት ያሳፍራል። እንደ ነውርም ይታያል። እኔ ላይ ሊደርስ ይችላል ብሎ ማንም አያስብም" ትላለች።
በአውሮፓውያን 2022 በአሜሪካ በተሠራ ጥናት መሠረት፣ ከ8,500 ሰዎች መካከል 26 በመቶ የሚሆኑት በ24 ዓመታት ውስጥ ከአባታቸው ጋር ለተወሰነ ጊዜ ተቆራርጠው ነበር። ስድስት በመቶው ደግሞ ከእናታቸው ጋር ለተወሰነ ጊዜ ተቆራርጠዋል።
በጀርመን 10 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ዘጠኝ በመቶ ከእናቶቻቸው፣ 20 በመቶ ከአባቶቻቸው ጋር ለ13 ዓመታት ገደማ ተቆራርጠዋል።
አንዳዶቹ ልጆች ለተወሰነ ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ሲቆራረጡ፣ ሌሎች ደግሞ አልፎ አልፎ ቤተሰቦቻቸውን ያገኛሉ። ከነጭራሹ ከወላጆቻቸው ጋር ግንኙነታቸውን ያቋረጡም አሉ።
የሥነ ማኅበረሰብ አጥኚ ካርል ፒልመር እንደሚለው፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ትውልድ በጠንካራ የቤተሰብ ትስስር አይደራደርም።
ከቤተሰብ ጋር መለያየት የሚባል ነገርም የሚታሰብ አልነበረም። አሁን ላይ ይህ አመለካከት ተሸርሽሯል።
ከወላጆች ጋር መቆራረጥ ዛሬ ዛሬ እየተለመደ መጥቷል።
የሥነ ልቦና ባለሙያው ጆሽዋ ኮልማን በዋናነት የሚሠራው ከተቆራረጡ ቤተሰቦች ጋር ነው።
ግለኛነት እየበረታ መምጣቱ አንዱ ቤተሰብን እየለያየ ያለ ምክንያት ነው ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
"ብዙዎች በግል ሕይወታቸው እየተጠመዱ ነው። ማንነታቸው እና ደስታቸው የሚመነጨው ከራሳቸው ኑሮ ነው። ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጡታል" ይላል።
በዕድሜ የገፉ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የመራራቅ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን የአሜሪካ ጥናት ያመለከታል።
ግለኛነት እምብዛም በማይታይባቸው አገራት ቁጥሩ ዝቅ ይላል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሰዎች መሰሎቻቸውን በቀላሉ ያገኛሉ። ቡድን መሥርተው "መርዛማ" ሰዎችን ከሕይወታቸው ለማስወጣት ይደጋገፋሉ።
ይሄ የማኅበራዊ ሚዲያ አብዮት ለቤተሰብ መቆራረጥ አንድ መነሻ እንደሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ።
ቤተሰቦች ሲለያዩ የአንዱን ወገን ትርክት ብቻ ሰምቶ መፍረድ ተገቢ እንዳልሆነ የሥነ ልቦና ባሙያዎች ይናገራሉ።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ከቤተሰብ ጋር መቆራረጥ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
የሥነ ማኅበረሰብ አጥኚ ካርል ፒልመር እንደሚለው፣ 300 ግንኙነታቸውን ያቋረጡ ቤተሰቦችን አነጋግሮ በሠራው ጥናት መሠረት፣ ከአማቾች ጋር መጣላትን ጨምሮ ብዙ ምክንያቶች ቤተሰብን ይለያያሉ።
ፍቺ፣ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ልጆችን ለመቀበል አለመፍቀድ እና ሌሎችም ምክንያቶች ቤተሰብን ያቆራርጣሉ።
የሥነ ልቦና መምህርት ሉዚ ብሌክ እንደምትለው፣ በዩናይትድ ኪንግደም 800 ሰዎች ላይ በሠራው ጥናት መሠረት፣ በቤተሰብ መካከል በሚፈጠር መቋሰል ምክንያት መለያየት ይከሰታል።
"ስሜትን የሚጎዱ ንግግሮች እና ከመጠን ያለፈ ቁጥጥር መቆራረጥን ያስከትላሉ" ትላለች።
"ማንም ሰው የሚጎዳው ግንኙነት ውስጥ መቀጠል አይፈልግም። ብዙውን ጊዜ የምናወራው ስለ አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ነው። ሆኖም ግን ስሜታዊ ብዝበዛንም መዘንጋት የለብንም" ስትልም ታክላለች።
ሁለቱ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነጥብ አንድ ሰው እንደ ስሜታዊ ጥቃት የሚወስደው ነገር ለሌላው ሰው የተለየ ትርጉም መስጠቱ ነው።
ለምሳሌ በሱስ የሚሰቃዩ ልጆች ወላጆቻቸው ከሱስ ሊያላቅቋቸው ሲሞክሩ ነገሩን የሚያዩት እንደ እርዳታ ሳይሆን እንደ ቁጥጥር ይሆናል።
ጤናማ ወላጆች የትኞቹ ናቸው? የሚለው በየጊዜው ትርጓሜው እንደሚለዋወጥ ባለሙያዎቹ ያሰምሩበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
ቀድሞ እንደ ስሜት ብዝበዛ የማይወሰድ ነገር አሁን ትክክለኛ ስም ተሰጥቶት መወያያ ነጥብ ይሆናል።
ማኅበረሰቡ ስለ አእምሮ ጤና ያለው ግንዛቤም እየተለወጠ ነው የመጣው።
የፍልስፍና ምሁር ክሪስቶፈር ካውል በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ደብሊን ይሠራል። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር እስከ ወዲያኛው አብረው መዝለቅ አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ እንዲህ ይመልሳል።
"በአንድ በኩል ወላጆቻችን የመኖራችን ምክንያት ናቸው። ሆኖም ግን ወላጆች በዝባዥ ከሆኑ አብረናቸው የመቀጠል ግዴታ የለብንም።"
ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንደ ጓደኞች መሆን ቢችሉ ግንኙነታቸው ጤናማ እንደሚሆን ያምናል።
ወላጆች ለልጆቻቸው ሙሉ ኃላፊነት ያላቸው በለጋ ዕድሜ ሲሆን፣ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ግን ግንኙነቱ መልኩን ይለውጣል።
"ትልቅ ሰው ከሆኑ በኋላ ለሕይወት ችግር በአጠቃላይ ወላጆችን መውቀስ ትርጉም አይሰጥም" ይላል ባለሙያው።
በሕይወት ለሚከሰቱ ስህተቶች ወይም ውድቀቶች ራስን ተጠያቂ ከማድረግ ወይም ኃላፊነት ከመውሰድ ይልቅ ወላጆችን መውቀስ ይቀላል። ይሄ አካሄድ ግን ለሁሉም ዓይነት ቤተሰብ ላይሠራ ይችላል።
ከልጇ ጋር ለ25 ዓመት ያላወራች እናትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ባለቤቷ ጥሏት ከሄደ በኋላ ሌላ ባል አገባች።
ያገባቸው ሰው ጥቃት አድራሽ ነበር። ልጇም በዚህ ምክንያት ተጣላት። ለእናትየው ግን አዲስ ባል ማግባት ለልጆቿ ከለላ መስጫ መንገድ ሆኖ ነበር የታያት።
የፍልስፍና ምሁር ክሪስቶፈር እንደሚለው፣ አንዳንድ ልጆች ራሳቸውን እንደ ወላጅ ሆነው ያሳድጋሉ።
ወላጆቻቸው ስላላሳደጓቸውም ይወቅሷቸዋል። ወላጆች በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ለልጆቻቸው ሐዘኔታን ማሳየት እንዳለባቸው ይናገራል።
"የወላጆችን ባህሪ መረዳት ሰላም ይሰጣል። ሁሉም የሚያደርጉት ነገር የታሰበበት እና የታቀደ ነው ማለት አይደለም" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
ወላጆች ስሜታዊ ብዝበዛ አድርሰው ከሆነ ተቆራርጦ ከመቅረት ወይም ለክስተቱ ዕውቅና ሳይሰጡ ይቅር ተባብሎ ግንኙነትን ከመቀጠል ይልቅ በግልጽ መነጋገርን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
ሰዎችን ከሕይወት እስከ ወዲያኛው ማስወጣት የሚኖረውን የሥነ ልቦና ጫና ከግምት ውስጥ ማስገባት ያሻል።
ሰዎች ለእኛ እንዲያደርጉ የምንፈለግውን ለሰዎች ማድረግ እንዳለብን በሃይማኖትም በፍልስፍናም ይነገራል።
በቤተሰብ ግንኙነትም ይሄንን መርኅ መከተል የተሻለ አማራጭ ይሆናል።
አንዳንዴ ስለ ልጅነት ያለን ትውስታ የተዛባ ይሆናል። ከወላጆቻቸው ጋር በመቆራረጣቸው የተሻለ ሕይወት እንደሚመሩ የሚናገሩም አልታጡም።
ወላጆች ግን ከዚህ በተቃራኒው ሐዘን እና የልብ ስብራት ይገጥማቸዋል።
እንደ ዓመት በዓል ባሉ ወቅቶት ከቤተሰብ ጋር መቆራረጥ ጥልቅ ሐዘን ሊፈጥር ይችላል።
ለተወሰነ ጊዜ ከቤተሰብ ራቅ ብሎ ማሰብ እና ማሰላሰል ከዚያም ውሳኔ ላይ መድረስን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ዕርቅ ማውረድ ሌላው ጤናማ መንገድ ነው። በአሜሪካ በተሠራ ጥናት ከ8500 ሰዎች መካከል 62 በመቶ ከእናቶቻቸው ጋር የተቆራረጡ ልጆች ዳግመኛ ግንኙነታቸውን ሲያድሱ 44 በመቶው ደግሞ ከአባቶቻቸው ጋር ሰላም አውርደዋል።
በዘገባው መነሻ ላይ ታሪኳን የጠቀስነው ሳራ እንደምትለው እናቷ በዕድሜ እየገፋች ስትመጣ እያዘነችላት ነው።
"እያረጀች ነው። ሕይወት ለእሷ ቀላል አልነበረም። የአእምሮ ጤና መታወክም ገጥሟት ነበር። ታሳዝነኛለች" ትላለች ሳራ።
ወላጆች ለልጆቻቸው ፍጹም ደስተኛ ሕይወት የመስጠት ሙሉ ግዴታ የለባቸውም ይሆናል። ልጆችም ለወላጆቻቸው ፍጹም ታማኝነት የማሳየት ግዴታ ላይ ጣልባቸው ይችላል።
በባለሙያዎቹ ዕይታ፣ በመካከላቸው መተሳሰብ እና መተዛዘን እንዲሁም መደማመጥ ካለ ግን አማካዩን መንገድ ይዘው በተሻለ ሁኔታ ግንኙነታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ።















