ዩናይትድ ኪንግደም ለአሜሪካ ታሪፍ አጸፋ ለመስጠት ወደ ኋላ አልልም አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፤ አሜሪካ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የደረሰችውን የታሪፍ ስምምነትን የማታከብር ከሆነ አገሪቱ አጸፋ ለመስጠት ወደ ኋላ እንደማትል አስታወቀ።
ሆኖም ቢሮው "ማንም የንግድ ጦርነት አይፈልግም" ብሏል።
ዩኬ ይህንን ያለችው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ ገቢራዊ የሚሆን የ15 በመቶ ታሪፍ በሁሉም አገራት ላይ ከጣሉ በኋላ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቃል አቀባይ አብዛኛው የዩኬ እና የአሜሪካ ስምምነት ለአብነትም በተሽከርካሪዎች፣ ብረት እና መድኃኒቶች ላይ የተጣለው ታሪፍ ይቀየራል ተብሎ እንደማይጠበቅ ገልጸዋል።
ሆኖም ሁኔታውን "እየተቀያየረ ያለ" ሲሉ የገለፁት ቃል አቀባዩ፤ በዩኬ እና አሜሪካ መካከል ንግግሮች እንደቀጠሉ ናቸው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትራምፕ አዲሱን የ15 በመቶ ታሪፍ በማይቀበሉ አገራት ላይ ታሪፉ ከፍ ይላል ማለታቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ከአሜሪካ ጋር የደረሰው የታሪፍ ስምምነት ገታ ማድረጉን ሰኞ ዕለት አስታውቋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ ባለፈው ዓመት የጣሉትን ዓለም አቀፍ ታሪፍ ከፕሬዝዳንቱ ሥልጣን በላይ ነው በሚል ውሳኔውን ሽሯል።
ውሳኔው ትራምፕ የአደጋ ጊዜ የኢኮኖሚ ሕግን ተጠቅመው የጣሉትን ሁሉንም ታሪፍ የሚመለከት ነው።
ውሳኔውን ተከትሎ ትራምፕ ሌላ ሕግ ተጠቅመው መጀመሪያ ላይ የ10 በመቶ ዓለም አቀፍ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ እሑድ ዕለት ወደ 15 በመቶ አሻሽለውታል።
የብሪታኒያ የንግድ ሚኒስትር ፒተር ካይል ለአሜሪካ አቻቸው ጄመሰን ግሪር የትራምፕ ታሪፍ እንዳሳሰባቸው ገልጫለሁ ብለዋል።
ብሪታኒያዊያን ለመጠበቅ ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሁለቱ አገራት መካከል አስቀድሞ የተደረሰውን የታሪፍ ስምምነት ማክበር አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የጣለው አዲሱ የ15 በመቶ ታሪፍ በ1974 የወጣውን የአገሪቱን ንግድ ሕግ መስረት መሠረት በማድረግ በጊዜያዊ መፍትሔነት የቀረበ ነው።
እንደ መሰረታዊ ማዕድናት፣ ብረት እና መድኃኒቶች ያሉ አንዳንድ ምርቶች ከታሪፍ ነፃ እንደሚደረጉ ተነግሯል።
ዓለም አቀፍ የንግድ ተንታኞች በአዲሱ ታሪፍ ክፉኛ ከሚመቱ አገራት መካከል ከአሜሪካ ጋር የ10 በመቶ የታሪፍ ስምምነት ያላት ዩኬ አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።
ከአዲሱ ታሪፍ በላይ ተጥሎባቸው የነበሩት ቻይና እና ብራዚል ደግሞ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
የብሪታኒያ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዝዳንት አንዲ ሀልዳን የትራምፕ የ15 በመቶ ታሪፍ ገቢራዊ ከሆነ ዩኬ ከሁሉም የንግድ አጋሮች ግርጌ ስር ትቀመጣለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
"በሳምንቱ መገባደጃ የሆነው ነገር ጥሩ የንግድ ስምምነት ያላቸው አጋራት ከሁሉም በላይ ተጎጂ እንደሚሆኑ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።












