ሜታ "በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆችን" ሱስ አስይዟል በሚል የቀረበበት ክስ መታየት ጀመረ

ማርክ ዛከርበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የፌስ ቡክ፣ የኢንስታግራም እና የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ ሆን ብሎ ልጆችን በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ሱስ እንዲጠመዱ አድርጓል የሚሉ ክሶችን የአሜሪካ ፍርድ ቤት መመልከት ጀመረ። ይህም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ያጋጠመው ትልቁ የሕግ ፈተና ነው ተብሏል።

በኦክላንድ ካሊፎርኒያ የሚገኝ አንድ የዳኞች ቡድን፣ በሚቀጥሉትን ስድስት ሳምንታት ውስጥ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በተውጣጡ ከፍተኛ ዐቃቤያን ሕጎች የሚያቀርቧቸውን ክሶች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያው ጠበቆች የሚሰጡትን ምላሾች ማዳመጡን እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ማክሰኞ ዕለት ችሎቱ ሲከፈት፣ ሜታ "በሚሊዮኖች" የሚቆጠሩ የ11 እና 12 ዓመት ሕጻናት ኢንስታግራም ላይ እንደሚያሳልፉ ደርሶበታል፤ ነገር ግን "እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ብዙም ጥረት አላደረገም" ሲሉ አንድ የካሊፎርኒያ ጠበቃ ተናግረዋል።

የሜታ ተወካይ በበኩላቸው፣ በግኝታቸው መሠረት እንደዚህ ያሉ ተጠቃሚ ሕጻናት 100,000 ገደማ ብቻ መሆናቸውን ገልፀው፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ሊባል የሚችል ነገር የለም የሚል ክርክር አቅርበዋል።

የካሊፎርኒያው ጠበቃ ሜታ መድረኮቹ የታዳጊዎችን የአእምሮ ጤና እንደሚጎዱ እያወቀ ነው ዝምታን የመረጠው ሲሉ፣ ሜታ በበኩሉ የተሻለ ልምድ እያገኙ ያሉ ምን ያህል ታዳጊዎች እንዳሉ ችላ እየተባለ መሆኑን ተናግሯል።

ችሎቱ የተከፈተው እአአ በ2023 ካሊፎርኒያ እና ኒውዮርክን ጨምሮ በ29 የአሜሪካ ግዛቶች በቀረበ ክስ መነሻነት ነው። ግዛቶቹ፣ ልጆችን የተመለከቱ የፌዴራል እና በግዛት ደረጃ የተዘጋጁ ሕጎች ላይ በርካታ ጥሰቶች ተፈጽመዋል ሲሉ ይከራከራሉ።

ግዛቶቹ ከሜታ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እየጠየቁ ሲሆን፤ የ"ላይክ" ብዛት ቁጥርን ማቆም እና ያለማቋረጥ አማራጮችን እየከፈቱ መመልከትን ጨምሮ በኢንስታግራም እና ፌስቡክ ላይ ለውጦች እንዲደረጉም ይፈልጋሉ።

የካሊፎርኒያ ዋና ጠበቃ ሜጋን ኦኔል በመክፈቻ ክርክራቸው፣ ከሜታ በተሰጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰነዶች ውስጥ የተገኙ መረጃዎችን በማሳያነት ተጠቅመዋል። እነዚህም የኩባንያውን የምርምር ውጤቶች፣ የሠራተኞችን ኢሜይሎች እና እስከ ዙከርበርግ ድረስ የደረሱ የውይይት መዝገቦችን ያካትታሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስለ ኢንስታግራም ከተደረጉ የውስጥ ጥናቶች አንዱ "ታዳጊዎች አጠቃቀማቸውን በተመለከተ በሱስ ስለመያዛቸው የሚገልጽ ታሪክ አለ" ይላል።

ኦኔል ለዳኞች ካቀረቧቸው ሌሎች መረጃዎች መካከል፣ "የዕይታ ጊዜን ለመጨመር የተነደፉ የይዘት ገጽታዎች ከጤናማ ሕይወት ጋር ፈጽሞ የሚጣረሱ እና ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ዋጋ የሚጨምሩላቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ የሚያደርጉ" መሆናቸውን ሜታ ደርሶበታል የሚለው ይገኝበታል።

ምንም እንኳን ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊ ተጽዕኖዎች ቢያውቅም፣ ሜታ ወጣቶችን የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዒላማ አድርጓል ሲሉ ኦኔል ተከራክረዋል። አክለውም፣ መድረኮቹ ለሕጻናት ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆናቸውን "ለሕዝቡ ለማረጋገጥ" የማይገባ ጥረት ሲያደርግ እንደነበረ ገልፀዋል።

ኦኔል የሜታን የንግድ ሞዴል በተመለከተ ለዳኞች ጠቅለል አድርገው ሲያስረዱ "ተጠቃሚዎችን ሱስ አስይዟቸው፤ እስከቻሉት ድረስ አቆዩዋቸው፤ መረጃቸውን ሰብሰቡ፤ ሕዝባዊ መግለጫዎች ሲሰጡ እውነቱን ከህዝብ ደብቁ" የሚል ይዘት ያለው ነው ብለዋል።

ጠበቃዋ፣ ሜታ ስለ መድረኮቹ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርገው ነገር እና የውስጥ የጥናት ውጤቶቹ የሚያሳዩት እውነታ እጅግ የተራራቁ መሆናቸው በችሎቱ ሂደት ግልጽ እንደሚሆን ተናግረዋል።

"ሜታ በበኩሉ ከትርፍ በፊት ደህንነትን እንደሚያስቀድም ተናግሯል፤ ነገር ግን ወደ ተግባር ሲመጣ ትርፍን የማስቀደሙን እውነታ ደጋግሞ ደብቋል" ሲሉም አክለዋል።

የሜታ ዋና ጠበቃ የሆኑት ፖል ሽሚት፣ ኦኔል በመክፈቻ ክርክራቸው ላይ የተጠቀሙበትን የኩባንያውን የምርምር ሪፖርት በመጠቀም ምላሽ ሰጥተዋል።

ሜታ በመድረኩ ላይ የእያንዳንዱን ተጠቃሚ ዕድሜ ማረጋገጥ ቢችልም፣ ሜታ ጥሷቸዋል ተብለው የተከሰሰባቸው ሕጎች ራሳቸው ኩባንያው ዕድሜያቸው ያልደረሰ ተጠቃሚዎችን በሚገባ ለመከታተል የሚያስፈልገውን መረጃ እንዳይጠቀም ማድረጋቸውን በመጥቀስ ጠበቃው ተከራክረዋል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ እና የኢንስታግራም ኃላፊ አዳም ሞሴሪ፣ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ሱስ የሚያስይዙ ሆነው እንዳልተዘጋጁ የገለጹባቸውን ያለፉ መግለጫዎችም ጠቁመዋል። በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ መያዝ እንደሚቻል የሚያሳይ ምንም ዓይነት ጥናት የለም ሲሉም አክለዋል።