አደገኛ የሆነውን የብልት ማወፈሪያ ሕክምና የሚወስዱ ወንዶች ቁጥር ለምን ጨመረ?

አልጋ ጫፍ ላይ የተቀመጠ ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ጄሰን የብልቱ ቅርፅ "የኮካ ኮላ ቆርቆሮ" እንዲመስል አልፈለገም ነበር። ይህ አገላለጽ፣ በሕክምና በእጅጉ እንዲወፍር የተደረገ ብልት ቅርፁ አጭር እና ወፍራም ከሆነው የኮካ ኮላ ጣሳ ጋር ስለሚመሳሰል የተሰጠ ነው።

ጄሰን ባደረገው ሕክምና የብልቱ ውፍረት በ16 በመቶ ጨምሯል። የብልቱ መጠን መጨመር "በራስ መተማመኑ እንዲጨምር" ማድረጉን ይናገራል።

ብልቱ ላይ "ተጨማሪ ትንሽ ውፍረት" ከመኖሩ በስተቀር፣ "ሁሉም ነገር እንደ ነበረ ነው" ይላል።

በዓለም ላይ ምን ያህል ሰዎች እንደ ጄሰን በሙሌት (filler) የሚደረግ የብልት ማወፈሪያ ሕክምና እንደተሰጣቸው ግልጽ አይደለም። ይህ ጉዳይ፣ ከንፈርን ለማተለቅ የሚደረግ ሙሌት ምን ያህል ተወዳጅ እየሆነ እንደመጣ በግልጽ መታዘብ እንደሚቻለው አይደለም።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የትኛውም ሰው ሕክምናውን መስጠት ስለሚችል፣ ዘርፉ ላይ እምብዛም ቁጥጥር አይደረግም። ምን ያህል ሰዎች እንደሚጠቀሙትም የሚያሳይ ይፋዊ መዝገብም የለም።

ይሁን እንጂ የብልታቸው ቀለም ወደ ጥሩ የተቀየረባቸው እና ቆዳው "የተላጠባቸው" አንዳንድ ወንዶች፤ ወደ ደንገተኛ ሕክምና ክፍል መወሰዳቸው አልቀረም። የብሪታንያ የዩሮሎጂካል ቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ማኅበርም ይህንን ሕክምና ለሚወስዱ ወንዶች ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

እንዲህ ከሆነ ታዲያ ለምን ወንዶች ሕክምናውን ይወስዳሉ? ምን ዓይነት አደጋዎችንስ ያስከትላል?

ጄሰን የብልቱ መጠን በመጨመሩ ደስተኛ ቢሆንም፣ የውፍረቱ ቅርጽ "የተመጣጠነ" እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የሆነ ነገር እንደጎደለ ከተሰማህ፣ ለምን አታደርገውም" ይላል እዚህ ውሳኔ ላይ ደረሰበትን ምክንያት ሲያስረዳ።

ጄሰን ቀዶ ሕክምናውን እንደሚወስድ ከመወሰኑ በፊት፣ ለአንድ ዓመት ያህል ምን አማራጮች እንዳሉት ሲመለከት ቆይቷል።

ጄሰን የመረጠው በ"ሃያሉሮኒክ አሲድ" (hyaluronic acid) የሚሰጠው የብልት ማወፈሪያ ሙሌት ነው። ምንም እንኳ ለብልቱ የሚሰጠውን ቅርፅ ባይወደውም፣ "በጊዜ ሂደት ሟሙቶ ስለሚጠፋ" እንደመረጠው ያስረዳል።

ሕክምናውን ለመውሰድ ወሰነው፣ የወንዶች የውበት መስፈርቶች በመለወጣቸው መሆኑን ይናገራል። "ራሳቸውን መጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ሴቶች ብቻ አይደሉም፤ ወንዶችም ራሳቸውን መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል" ይላል።

"ማኅበረሰቡ እየተለወጠ ነው። መገናኛ ብዙኃን ሁሉንም ነገር የሚስሉበት መንገድ በዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው ይመስለኛል፤ አሁን ላይ ፍጹም የሆነ [ሰውነት] ያለው ሰው ምሥል ሳትመለከት የትም መሄድ አትችል" በማለት ያስረዳል።

የብልት ማሳደጊያ ሕክምና የሚሰጡ ክሊኒኮች ድረ ገጾች ላይ "በብልትዎ መጠን ያፍራሉ?" የሚሉ ዓይነት ማስታወቂያዎች ይታያሉ። ይህ ዓይነቱ ጥያቄ ሰዎች ሕክምናውን እንዲወስዱ ሊያሳስባቸው ይችላል።

በቀዶ ሕክምናም ሆነ ያለ ቀዶ ጥገና ብልትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ አማራጮች አሉ። ብልት ላይ የሚወጉ ንጥረ ነገሮችም ይለያያሉ።

በብዛት የተለመደው መንገድ 'ሃያሉሮኒክ አሲድ' የተባለውን የጄል መሰል (የሚዝለገለግ) ንጥረ ነገር ብልት ውስጥ መውጋት ነው። ይህ ንጥረ ነገር ከንፈርን ለማተለቅ በሚሰጠው ሕክምናም ጥቅም ላይ ይውላል።

ሃያሉሮኒክ አሲድ በተፈጥሮ ሰውነት ውስጥ የሚገኝ የስኳር ሞለኪውል ነው። ውሃ ይዞ ስለሚቆይም "የእርጥበት ማግኔት" በመባል ይታወቃል።

ዶ/ር ጃቬድ ሁሴን

የፎቶው ባለመብት, BBC/James Gallagher

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ጃቬድ ሁሴን የብልት ሙሌትን ጨምሮ የተለያዩ የኮስሜቲክ ሕክምናዎችን ይሰጣሉ

ዶ/ር ጃቬድ ሁሴን በፕሬስትዊች ላለፈው አንድ ዓመት በዩናይትድ ኪንግደም ግሬተር ማንተስተር ውስጥ በሚገኘው ክሊኒካቸው የብልት ማወፈሪያ ሙሌት ሕክምና ሲሰጡ ቆይተዋል።

ሕክምና ያጠኑት ዶ/ር ሁሴን፣ ወደዚህ ዓይነቱ የኮስሞቲክስ ሕክምና ከመዛወራቸው በፊት በሐኪምነት ሠርተዋል። የብልት ሙሌትን የሚሰጥ ሰው በሕክምና የተመረቀ መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ የለም።

የሕክምና ባለሙያው እንደሚናገሩት ይህን አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በ20ዎቹ አጋማሽ እስከ 72 ዓመት ድረስ፤ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችን እንዳከሙ ይገልጻሉ።

የሕክምና ሂደቱ የሚጀምረው ስለ ታካሚው የጤና ሁኔታ፣ ለምን ይህንን ሕክምና እንደፈለገ፣ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚጠብቅ እንዲሁም ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ በመመካከር ነው።

ሕክምናው በሚሰጥበት ዕለት፣ የግለሰቡ ብልት የላይኛው ክፍል እና በሁለቱ ጎኖቹ ላይ ሃያሉሮኒክ አሲድ ሦስት ጊዜ ይወጋል። መርፌው ከብልቱ መጀመሪያ አንስቶ፣ ሙሉ ዘንጉ ድረስ ይገባል።

የሕክምና መሣሪያዎች

የፎቶው ባለመብት, BBC/James Gallagher

የምስሉ መግለጫ, የብልት ሙሌት ሕክምናን ለማከናወን መርፌን ጨምሮ የተለያዩ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ

ከዚያም ብልቱ የተመጣጠነ ቅርፅ እንዲኖረው 'ማሳጅ' ይደረጋል፤ ታካሚው ወደ ቤቱም ከተመለሰ በኋላ ይህንን ማረድግ መቀጠል ይኖርበታል።

ዶ/ር ሀሰን እንደሚያስረዱት 3,500 ፓውንድ የሚደርስ ወጪ የሚጠይቀውን ይህንን ሕክምና የወሰዱ ወንዶች፣ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ የብልታቸው ውፍረት ከ10 እስከ 20 በመቶ ይጨምራል።

ሕክምናው ግን አደጋ ሊያስከትል ይችላል። እንደ ማበጥ፣ መቁሰል፣ እኩል ያልሆነ ሙሌት ያሉ አነስተኛ ጉዳቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እንደ ኢንፌክሽን ያሉ ከፍተኛ አደጋዎችም የማጋጠም ዕድል አላቸው። ይህ ዓይነቱ የጎንዮሽ ውጤት በሁሉም ዓይነት የሙሌት ሕክምናዎች ላይ ሊያጋጥም የሚችል ነው።

ከዚህም ባስ ሲል ግን፣ ለብልት መቆም የሚያስፈልጉትን አስፈላጊ የሆኑ አካላት እና ደም ስሮች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል።

የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ስጋታቸውን እየገለጹበት ያለውን ይህንን ሕክምና መስጠት ምቾት ይኖረው እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ሁሴን፣ የተወሰኑ ሰዎች ለምን ስጋት እንደሚገባቸው "ሙሉ በሙሉ እንደሚረዱ" ይናገራሉ።

"ያ ፍራቻ ከትክክለኛ ቦታ የሚመጣ ነው፤ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ማስረጃዎቹ እየጨመሩ ነው፤ ውጤቶችንም እያገኘን ነው" ብለዋል። ሕክምናው ለወንዶች የሚያስገኘው "ጥቅም" እንዳለም አክለዋል።

ነገሮች ወዳልተፈለቀ አቅጣጫ የሚሄዱ ከሆነ ሙሌቱን በፍጥነት ማሟሟትን ጨምሮ "ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚሆን የድርጊት ዕቅድ" እንዳላቸው ይናገራሉ። "ደስ የሚለው፣ ይህንን ዕቅድ መተግበር አስፈልጎን አያውቀወም" ይላሉ። ቢቢሲ ይህንን አስተያየታቸውን በራሱ ማረገገጥ አልቻለም።

በሌላ ቦታ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ "እጅግ የተበላሸበት" አንድ ታካሚ ምክር ፈልጎ መጥቶ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ጥቅም ላይ የዋለው የተሳሳተ የሙሌት ዓይነት እንደነበር ዶ/ር ሁሴን ይናገራሉ። ሕክምናው ብልት ውስጥ የሚገኙትን ደም ስሮች በመጉዳቱ እና ቆዳው እየሞተ ስለነበር፣ "የብልቱ ዘንግ መጥቆር መጀመሩን" ይናገራሉ። ግለሰቡ በቀጥታ ወደ ድንገተኛ ሕክምና ክፍል ተልኳል።

ፕሮፌሰር ቫይባቭ ሞድጊል

የፎቶው ባለመብት, BBC/James Gallagher

የምስሉ መግለጫ, ፕሮፌሰር ቫይባቭ ሞድጊል፣ የተደረገላቸው የብልት ማሳደጊያ ሕክምና የተበላሸባቸውን ወንዶች አክመዋል

በዩናይትድ ኪንግደም የአንድሮሎጂ እና አማካሪ የዩሮሎጂ ቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር ቫይባቭ ሞድጊል፣ በሕክምናው የተበላሸባቸው ወንዶችን አክመዋል። "ይህ በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ለታካሚው እጅግ አስከፊ ሊሆን ይችላል" ይላሉ።

"የቆዳው ህዋስ በመሞቱ እንጅ የጠቆረ እና እየተላጠ" ለነበረ ወንድ ሕክምና መስጠታቸውንም ያስታውሳሉ። "ወንዶች 'ምርጥ ይሆናል' ብለው በማሰብ ይሄዳሉ፤ ነገር ግን ሲሄዱ ከነበረው የበለጠ ደስታ አጥተው ሊመለሱ ይችላሉ" በማለት ያስጠነቅቃሉ።

ትክክለኛ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው አሌክስ፣ ሌላ ዓይነት የብልት ማሳደጊያ ሕክምና ለማግኘት ወደ ጀርመን ተጉዞ ነበር።

ብልቱ ረጅም መስሎ እንዲታይ፣ ብልቱን ከዳሌ አጥንት ጋር የሚያያይዘው ጅማት እንዲቆረጥ የሚያደርግ ቀዶ ሕክምና አድርጓል። በተጨማሪም የሰውነቱ ውስጥ ያለው ስብ ተሰብስቦ፣ ብልቱ ውስጥ ተወግቷል።

ሕክምናው ከተደረገ በኋላ ከሰመመን ሲነቃ፣ የማይቋቋመው ሕመም እንዳጋጠመው ያስታውሳል።

"ከፍተኛ ቁስለት አጋጥሞኛል፤ የእግሮቼ የላይኛው ክፍል በሙሉ ወደ ቢጫነት ተቀይሮ ነበር። ከአንድ ወር በላይ በትክክል መራመድ አልችልም ነበር" ይላል።

ኋላ ላይ አሌክስ ወደ ፕሮፌሰር ቫይባቭ ሞድጊል ክሊኒክ ሄዶ ሕክምና ተሰጥቶታል። "ብዙ ሰዎች ያንን ዓይነት ዕድል አያገኙም፤ እኔ ዕድል ቀናኝ" በማለት ይናገራል።

አሌክስ እንደሚናገረው ቀድሞውንም ቢሆን የብልቱ መጠን "ትንሽ አልነበረም"። ነገር ግን የማኅበረሰቡ እሳቤ እንዲሁም የወሲብ ፊልም መመልከቱ ከዚህ የበለጠ ትልቅ ብልት መኖር "ወንድነትን" እንደሚያጎናጽፍ አንዳሳመኑት ያስረዳል።

ቦክሰር ያደረገ ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ብልትን ለማወፈር የሚደረግ ሙሌት በረጅም ጊዜ ስለሚኖረው ጉዳት የሚያሳይ በቂ መረጃ የለም

የብልት ማሳደጊያ ሕክምናዎችን ብዛት የሚያሳይ ይፋዊ መረጃ ባይኖርም፣ በኦንላይን 'ትሬንዶች'፣ ማስታወቂያዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያ ምክንያት ሕክምናውን የሚወስዱ ሰዎች "ቁጥር እየጨመረ መሆኑን" ፕሮፌሰር ሞድጊል ይናገራሉ።

ይህ ሁኔታ፣ የብሪታንያ የዩሮሎጂካል ሐኪሞች ማኅበር ሕክምናውን በተመለከተ አዲስ ምክረ ሀሳቦችን እንዲያወጣ አድርጎታል።

ፕሮፌሰር ሞድጊል፣ የሕክምና ሂደቱን በተመለከተ ያሉት "መረጃዎች እጅግ አነስተኛ ስለሆኑ፤ በቅርቡ ባወጣነው መመሪያ [ታካሚዎች እነዚህን] ሕክምናዎች እንዲወስዱ የሚመክር ምክረ ሀሳብ ማቅረብ እንደማንችል ይገልጻል" ብለዋል።

3,750 ወንዶች የተሳተፉባቸው 36 ጥናቶች ላይ ግምገማ ቢካሄድም አሁንም ሕክምናው "የደኅንነት ሁኔታ" እስካሁን ግልጽ እንዳልሆነ መመሪያው ይገልጻል። በቂ መረጃ ካልተገኘባቸው ጉዳዮች አንዱ የሚሰጠው ሙሌት በረጅም ጊዜ ሂደት ብልት ላይ ምን ይፈጥራል የሚለው ነው።

ከንፈርን ለማተለቅ እንደሚደረገው የሙሌት ሕክምና ሁሉ፣ ሂደቱን ብልት ላይ ለማከናወን የተለየ ብቃት አያስፈልግም የሚለውም ሌላኛው ስጋት የጫረ ጉዳይ ነው።

ሕክምናውን ሙሉ በሙሉ ማገድ "ምናልባት እጅግ የከፋ" እርምጃ ሊሆን እንደሚሆን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሞድጊል፣ ይህ ሕክምና የሚቀጥል ከሆነ ግን ዘርፉ "ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው" ይገልጻሉ።

ወንዶች ጥቅሙን እና አደጋውን አውቀው ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ፣ የብልት ማወፈሪያ ሕክምና የተከናወኑባቸው ጊዜያት እንዲሁም የረጅም ጊዜ መረጃዎችን በብሔራዊ ደረጃ መመዝገብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።