"የማንቂያ ደወል" – በኢትዮጵያ "በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ" ያለው መድኃኒትን የሚቋቋም የወባ በሽታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግዛቸው ማንደፍሮ፣ በአማራ ክልል ከጎንደር ከተማ 42 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ማክሰኝት ከተማ የጤና ጣቢያ ኃላፊ ነው። በዚህ ወይና ደጋማ አካባቢ የወባ በሽታ መከሰት ያልተለመደ ነገር አይደለም።
ለግዛቸው ሊዋጥለት ያልቻለው ግን በአብዛኛዎቹ የወባ ታካሚዎች ላይ የሚመለከተውን ተመሳሳይ ሁኔታ ነው። በወባ በሽታ መያዛቸው የተረጋገጠ "አብዛኛዎቹ" የአካባቢው ነዋሪዎች የሚሰጣቸው 'ኳርተም' የተባለው መድኃኒት ከበሽታው እያዳናቸው አይደለም።
በንግድ ስሙ 'ኳርተም' ተብሎ የሚጠራው ይህ መድኃኒት፣ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ለሚከሰተው 'ፕላስሞዲየም ፋልሲፓረም' የተባለ የወባ በሽታ በዋንኛነት የሚሰጥ መድኃኒት ነው።
መድኃኒቱን ከወሰዱም በኋላ ተመሳሳይ የወባ ሕመም ምልክቶች የሚታይባቸው ታካሚዎች ብዛት ችላ የሚባል እንዳልሆነ ግዛቸው ይናገራል።
"ያንን [መድኃኒት] ወስደው 'ለውጥ አጣን' ነው የሚሉኝ። እንደገናም ተመልሰው ወዲያውኑ በሁለተኛው ቀን የመምጣት ሁኔታዎች አሉ። መድኃኒቱን ጨርሰው ከሦስት ቀናት በኋላ የሚመጡ አሉ፤ ለውጥ የለውም በሚል" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Gondar zuria communication
ለስድስት ዓመታት በአካባቢው በጤና ባለሙያነት የሠራው ግዛቸው እንደሚያስረዳው ይህ ሁኔታ በድንገት የተፈጠረ አይደለም። ባለፉት ዓመታት ውስጥ ዋነኛውን የወባ መድኃኒት ወስደው የማይሻላቸው ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ያስረዳል።
ግዛቸው እና ባልደረቦቹ በቀጣይነት የሚከተሉት አማራጭ ታካሚዎቹን ከፍ ያለ ሕክምና ወደሚያገኙበት የጤና ተቋም በመላክ፣ በሆስፒታሎች ደረጃ የሚሰጠውን 'አርቴሱኔት' የተባለ መድኃኒት እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
"አርቴሱኔቱን ገና የመጀመሪያውን ዶዝ እንደወሰዱ ይነቃሉ። ደህና ለውጥ ያሳያሉ፤ ወዲያውም በሁለት ቀን ውስጥ ድነው በእግራቸው የሚሄዱበት አጋጣሚ ነው ያለው" ሲል ያስተዋለውን ልዩነት ይጠቅሳል።
ምንም እንኳ ታካሚዎቹ 'አርቴሱኔት' ወስደው ለውጥ ቢታይባቸው፣ በዋነኛነት ለወባ በሽታ እንዲውል የተቀመጠው መድኃኒትን ወስደው "አለመዳናቸው" ያሳስበዋል።
"ሰው ታክሞ 'ለውጥ የለኝም፤ በቃ ሕመሙ እንደቀጠለ ነው' ሲል እኛንም ከሰውየው በላይ ያመናል" ይላል።
"እንዴት? [መድኃኒቱን] ከወሰደ ለምን አይሻለውም ነበር? የሚል ሌላ ጥርጣሬ ውስጥም እያስገባን ያለበት ሂደት ነው ያለው" ሲልም የላብራቶሪ ምርመራ ውጤት ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ እንደሚያደርጋቸው ይናገራል።
የማክሰኝት ጤና ጣቢያ ባለሙያዎችን ያሳሰበው ይህ ሁኔታ ትክክለኛነት በቅርቡ በወጣ አንድ ጥናት ተረጋግጧል።
በሐምሌ መጨረሻ በታዋቂው የሳይንስ ጆርናል 'ኔቸር' ላይ የታተመው ጥናት በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሚከሰተው የወባ በሽታ ዓይነት ላይ የመድኃኒት ብግርና አዝማሚያ መታየቱን በመግለፅ የሚያስጠነቅቅ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'የመድኃኒት ብግርና' ተዋሲያን እንዲያጠፋቸው የተዘጋጀ መድኃኒትን መቋቋም ሲጀምሩ የሚፈጠር ሁኔታ ነው።
በስምንት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ላይ የተደረገው ይህ ጥናት የተመራው በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ነው።
ዋና መሥሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ የሆነው ይህ ተቋም "ምርምሮችን የማካሄድ" እና "የሕክምና ምርምር ውጤቶች ላይ ተመርኩዞ የፖሊሲ ምክረ ሀሳብ" የማቅረብ ኃላፊነት በሕግ የተጣለበት ነው።
በጥናቱ የተሳተፉት ከ40 በላይ ተመራማሪዎች ከ2012 እስከ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከ605 ታካሚዎች ናሙና በመውሰድ፣ በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ላይ የመድኃኒት ብግርና ስለመኖሩ ምርምር አድርገዋል።
የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ዶ/ር ፍፁም ግርማ የጥናቱን ውጤት "የማንቂያ ደወል" በማለት ይገልጹታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ ወባን ለማከም በዋንኛነት ጥቅም ላይ የዋለው 'ኳርተም' መድኃኒትን የሚቋቋም የዘረመል ለውጥ "በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ" መሆኑን ጥናቱ አስፍሯል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ምርመራ ከተደረገባቸው ናሙናዎች ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት መድኃኒት ለመቋቋም የሚያስችል የዘረመል ለውጥ ታይቶባቸዋል።
ማክሰኝት ከተማ በሚገኝበት የአማራ ክልል ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ደግሞ ይህ ቁጥር 50 በመቶ ገደማ ደርሶ ተገኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, abiy ahmed ali
የወባ መድኃኒት ብግርና እንዴት ይፈጠራል?
ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለው 'ኳርተም' በውስጡ ሁለት መድኃኒቶችን የያዘ ነው። ሁለት መድኃኒቶች በአንድ ላይ የተዘጋጁት የወባ ተዋስያንን መድኃኒቱን የመቋቋም አቅም ለመግታት እንደሆነ በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪው ዶ/ር ፍፁም ይናገራሉ።
ሁለቱ መድኃኒቶች የሚሠሩበት መንገድ የተለያየ መሆኑን የሚጠቅሱን ዶ/ር ፍፁም፤ አሠራራቸው "በጣም ስለሚለያይ ፓራሳይቱ ግራ ይጋባል" ሲሉ በቀላል አማርኛ ያስረዳሉ።
'አርቲሚሲኒን' የሚባለው የመድኃኒቱ የመጀመሪያ ክፍል፣ በፍጥነት የሚሠራ ሲሆን፣ ታማሚው በተሰጠው በሦስት ሰዓት ተኩል ውስጥ ግማሽ የሚሆኑትን ተዋሲያን ማጥፋት ይችላል። ይህ የመድኃኒቱ ክፍል ሰውነት ውስጥ የሚቆየው ለትንሽ ጊዜ ነው።
'ሉሜፋንትሪን' የሚባለው ሁለተኛው ክፍል በአንጻሩ ሰውነት ውስጥ ይቆያል። ዋና ተግባሩ "የተቀሩትን ተዋሲያን ለቃቅሞ መግደል" እንደሆነ ዶ/ር ፍፁም ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ መድኃኒት መሰጠት ከተጀመረ በኋላ ወባን ለመከላከል የተወሰዱ መጠነ ሰፊ እርምጃዎች በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ጥሩ ውጤት እንዲታይበት አድርገዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት በወባ በሽታ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር በ40 በመቶ ለመቀነስ አስቀምጦት የነበረውን ዕቅድ "ካሳኩ በጣም ጥቂት አገራት" አንዷ ኢትዮጵያ እንደነበረች ዶ/ር ፍፁም ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያ በዓመታት ጥረት ያገኘችው ይህ ስኬት ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ ወደ ኋላ የሚመልስ ተግዳሮት አጋጥሞት ታይቷል።
ከ2012 ዓ.ም. አንስቶ በአምስት ዓመታት ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ሚሊዮን የማይሞላ የነበረው የወባ ታማሚዎች ቁጥር 10 ሚሊዮን ገደማ ደርሶ ተስተውሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መንግሥት ከ2017 ዓ.ም. ወዲህ በወሰዳቸው እርምጃዎች ምክንያት ግን ይህ ቁጥር በ54 በመቶ መቀነሱን ተመራማሪው ገልጸዋል።
ዶ/ር ፍፁም፣ መድኃኒት ማዘጋጀትን ጨምሮ ወባን ለማጥፋት የሚደረጉ ጥረቶች በሕይወት ያለን ነገር ለማጥፋት የሚወሰዱ እርምጃዎች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። "ያ ሕይወት ያለው ነገር መጥፋት አይፈልግም። ስለዚህ [ህልውናውን የሚያስቀጥልበት] መንገድ ያዘጋጃል፤ ይህ ዘዴ የመድኃኒት ብግርና (drug resistance) ይባላል" በማለት ያብራራሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ሁለት መድኃኒቶችን በውስጡ የያዘው ኳርተም በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ብግርና አያጋጥመውም። በቅድሚያ የሚፈጠረው 'ከፊል ብግርና' የወባ ተዋሲያኑን በፍጥነት ለማጥፋት የሚውለው የመድኃኒቱ የመጀመሪያ ክፍልን የመሥራት አቅም ያስተጓጉላል።
መድኃኒቱን በከፊል በተለማመዱ የወባ ዝርያዎች የተያዙ ታካሚዎች የሚወስዱት መድኃኒት "በሦስት ቀናት ውስጥ ሁሉንም ተዋሲያን ጠራርጎ በማስወገድ አቅሙ አነስተኛ" እንደሚሆን የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።
ዶ/ር ፍፁም፣ "በዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ መሠረት የመጀመሪያው አርቲሚሲኒን መድኃኒት ችግር ውስጥ ገባ፣ ከሸፈ ማለት ማስጠንቀቂያ ነው። ሁለተኛውም መድኃኒት ተግዳሮቱ አይቀርለትም ማለት ነው" ይላሉ።
ኤርትራ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ከፊል የመድኃኒት ብግርና ተረጋግጧል። ኢትዮጵያ እና ሱዳንን ጨምሮ በሌሎች አራት የአፍሪካ አገራት ውስጥ ደግሞ ተከስቷል ተብሎ እንደሚጠረጠር የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያን ምን ያህል ያሰጋል?
ዋነኛውን የወባ መድኃኒት ከተሰጣቸው በኋላ "ለውጥ የለንም" የሚሉ ታካሚዎች የተደጋገሙበት የማክሰኝት ጤና ጣቢያ ኃላፊው ግዛቸው፣ "እኛ አሁን ኳርተም [መድኃኒት] ፈውስ እየሰጠ እንዳልሆነ ነው ያየነው" ሲል ስጋቱን ይገልጻል።
ግዛቸው በአካባቢው በጤና ባለሙያነት መሥራት ከጀመረበት 2012 ዓ.ም. አንስቶ ምልክቶች እንደነበሩ ይናገራል። "ያን ጊዜ ጀምሮ የሆነ በቃ የሚታዩ ነገሮች ነበሩ፤ እንደ አሁን እየተባባሰ ባይመጣም...ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው የመጣው" ይላል።
"እኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጤና ጣቢያዎች ላይም እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገሮች አሉ" ይላል ስፋቱን ሲያስረዳ።
"'ሌላ ጤና ጣቢያ [መድኃኒት] ወስደን ነበረ፤ ለውጥ አጣን' ብለው የባለሙያው ወይም የአገልግሎቱ ችግር እየመሰላቸው እንደገና መልሰው ወደ እኛ የሚመጡ አሉ" በማለትም ማሳያ ይጠቅሳል።
ግዛቸው እና ባልደረቦቹ ይህንን ጉዳይ ስብሰባዎች ላይ ቢያነሱትም በጥናት "ተጨባጭ" ነገር አለማግኘታቸውን ያነሳል።
ጥናት ከተደረገባቸው አካባቢዎች መካከል ማክሰኝት የሚገኝበትን ጎንደር ዙሪያ ወረዳን በመድኃኒት ብግርና ምልክቶች በቀዳሚነት ያስቀመጠው የእነ ዶ/ር ፍፁም ምርምር የጤና ባለሙያዎቹን ስጋት ያረጋገጠ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Wolayta Zone Health Department
ጥናቱ "ሰፊ የሆነ የበርካታ መድኃኒቶች ብግርና ማስረጃ" መገኘቱን አስፍሯል። በአሁኑ ሰዓት "በዋነኛነት ጥቅም ላይ በሚውሉ ሕክምናዎች ላይ [የተጋረጠው] ሥጋት እየጨመረ" መምጣቱንም በአሳሳቢ ጉዳይነት ይጠቅሳል።
በዓለም የጤና ድርጅት መሠረት ከፊል የወባ መድኃኒት ብግርና መከሰቱን ከሚያመለክቱ የወባ ተዋስያን ዘረመል ለውጦች ውስጥ ሁለቱ በጥናቱ መገኘታቸውን ዶ/ር ፍፁም ተናግረዋል።
የጥናት ቡድን መሪው፣ "ይህ ነገር ማንቂያ ደወል ነው" ይላሉ። አሁን የታየው ምልክት የመድኃኒቱ የመጀመሪያ ክፍል አቅሙ እየተሸረሸረ መሆኑን እንደሚጠቁም የሚያስረዱት ዶ/ር ፍፁም፣ "ለውጥ ካላደረግን ሙሉ በሙሉ የሆነ የመድኃኒት ብግርና በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ይችላል" በማለት ያስጠነቅቃሉ።
በሰዎች እንቅስቃሴ ምክንያት መድኃኒቱን የተለማመዱት የወባ ዝርያዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሊሠራጩ እንደሚችሉም አንስተዋል።
ተመራማሪው የሚያቀርቡት አንዱ የመፍትሔ ሃሳብ በወባ ተህዋስያኑ እየተለመደ ያለውን መድኃኒት "ለጊዜው አውጥቶ፣ በአዲስ መቀየር" እና ከጊዜ በኋላ "መልሶ ማምጣት" የሚል ነው።
"ለምሳሌ ሩዋንዳ ላይ ሦስት መድኃኒቶችን መረጡ እና አገራቸውን በሦስት ከፈሉት። ከዚያ ሦስቱን መድኃኒቶች በየዓመቱ፣ በየሁለት ዓመቱ ይለዋውጧቸዋል፤ ተዋስያኑ አንዱን እንዳይለማመደው ማለት ነው" ሲሉም የምሥራቅ አፍሪካዊቷን አገር ተሞክሮ ጠቅሰዋል።
ለውጥ መች ይመጣል?
በኢትዮጵያ የታየው ይህ የመድኃኒት መለማመድ "ይበልጥ እየተስፋፋ" የሚቀጥል ከሆነ በዋነኛነት ጥቅም ላይ የሚውለው የኳርተም መድኃኒትን "ብቃት ሊሸረሸር እንደሚችል" አጥኚዎቹ ጠቅሰዋል። ለዚህም ሲባል "ጊዜውን የጠበቀ ፖሊሲ እና የቁጥጥር እርምጃ" መወሰድ እንዳለበት ይገልጻሉ።
ቢቢሲ ይህንን የጥናት ግኝት በተመለከተ ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ሕብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተያየት ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም። ይሁን እንጂ የፀረ ወባ መድኃኒቶችን ብግርና የጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤቶቹ ክትትል የሚያደረግበት ጉዳይ እንደሆነ የተቋማቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የጤና ሚኒስቴር "የምርምር ክንፍ" መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር ፍፁም፣ ግኝቶቹን በተመለከተ "ቀጣይነት ያለው ግንኙነት" መኖሩን አስረድተዋል።
ይህም ቢሆን ግን ተመራማሪው የምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲ ውሳኔ ለመቀየር ጊዜ የመውሰዳቸው ነገር ያሳስባቸዋል። "ሂደቱ ጊዜ የሚወስድ ነው። አንዳንዴ እያወቅነውም ለውጦቹ ይቀድሙናል" ይላሉ።
"ምክንያቱም አዲስ መድኃኒት ስናመጣ አዲሱ መድኃኒት ውድ ነው። አቅርቦቱ ራሱ ላይኖር ይችላል፣ በቂ ላይሆን ይችላል" የሚሉት ዶ/ር ፍፁም፤ ከኢትዮጵያ ስፋት እና ሕዝብ ብዛት አንጻር አዲስ ፕሮግራም መተግበር "በጣም ውስብስብ" እንደሚሆን ያስረዳሉ።
የአሁኑ መድኃኒት በኢትዮጵያ መሰጠት ከመጀመሩ አስቀድሞ የነበረው መድኃኒት "ብግርና እንደተፈጠረበት ታውቆ ፖሊሲ ከመለወጡ በፊት፣ በጣም በአሳዛኝ ሁኔታ ከታማሚዎቹ ውስጥ 78 በመቶው መድኃኒቱን የሚወስዱት አይድኑም ነበር። የሞት ምጣኔው በጣም ጨምሮ ነበር" በማለት አብራርተዋል።
ዶ/ር ፍፁም፣ ከጥናት ውጤቶች በመነሳት ወደ ውሳኔ የሚደረስበት ሂደት መፋጠን እንዳለበት አሳስበዋል።
"ለውጥ ካላደረግን ችግሩ አይቀርም። በቃ ይመጣል… ጂኦግራፊውም፣ ጥንካሬውም ሊሰፋ ይችላል" በማለት አስጠንቅቀዋል።















