ዓለም አቀፍ የወባ ቀን፡ በኢትዮጵያ መድኃኒት የሚቋቋም የወባ በሽታ ያሰጋ ይሆን?

የወባ ትንኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መድኃኒት የተላመደ የወባ ፓራሳይት በእስያ ታይላንድና ካምቦዲያ ድንበር አቅራብያ እንዲሁም በአፍሪካ ደግሞ በሩዋንዳ መገኘቱ ይፋ ተደርጓል።

ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ በሽታውን ለመቆጣጠር የተለያዩ ፕሮግራሞችን ዘርግታ እየሰራች ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ መድኃኒቱን የተለማመደ ወባ ስለመኖሩ የሚያመለክት መረጃ የለም።

በጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የወባ ማጥፋት ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ መብርሃቶም ኃይለ በኢትዮጵያ መድኃኒቱን የተለማመደ የወባ በሽታ አለመከሰቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የወባ መድኃኒቶች ፍቱንነት ላይ በየሁለት ዓመቱ ጥናት እንደሚደረግ የገለጹት አስተባባሪው፣ በዚህም መሠረት የመድኃኒት 'ብግርነት' ወይንም መድኃኒቱን የሚቋቋም የወባ ዝርያ በኢትዮጵያ አለመኖሩን ተናግረዋል።

በአርማወር ሃንሰን የምርምር ተቋም ወባ ላይ ጥናት የሚያደርጉት ዶ/ር ፍፁም ግርማ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን የወባ መድኃኒቶች ውጤታማነት ላይ ጥናት በየጊዜው እንደሚሰራ አመልክተው፤ እስካሁን ድረስ መድኃኒቱን የተለማመደ የወባ ዝርያ ስለመከሰቱ ምንም ዓይነት መረጃ አልተገኘም ይላሉ።

ነገር ግን መድኃኒቱን የሚቋቋም ፓራሳይት መኖር አለመኖሩን ለመለየት የተሻለ የመመርመሪያ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በፈረንጆች አቆጣጣር ከ2000 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት መቀነስ አሳይቶ ቆይቷል።

ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ለውጦች ቢመዘገቡም እ.አ.አ ከ2015 ወዲህ ግን ወደፊትም ወደ ኋላም እየሄድን አይደለም ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት በ2019 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በዓለም ላይ የወባ ስርጭትን እየቀነሱ ከሄዱ አራት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች።

የወባ ትንኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወባ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ አጠቃላይ የወባ ስርጭት የሚከሰተው የዝናብ ወራቱን ተከትሎ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ድረስ ባሉት ወራት ውስጥ እንደሆነ አቶ መብርሃቶም ኃይለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የበልግ ዝናብን ተከትሎም በሚያዚያ እና በግንቦት ወራት በተወሰነ መልኩ ወረርሽኙ ጭማሪ እንደሚያሳይ አክለው ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወባ በወረርሽኝ መልክ የመከሰት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የለም ያሉት ኃላፊው፤ ይህንን ለማድረግ የተቻለውም የስርጭት ወቅቶችን ታሳቢ ያደረገ የመከላከል እና የመቆጣጠር እንዲሁም ወባን ማስወገድ የሚያስችል ስትራቴጂዎች ተነድፈው ላለፉት 15 ዓመታት በመሰራቱ እንደሆነ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከአስር ዓመት በፊት በዓመት እስከ 5 ሚሊዮን በወባ የተያዙ ህሙማን ሪፖርት ይደረግ እንደነበር ገልፀው፤ በ2011 ዓ ም ደግሞ ከ1 ሚሊየን በታች የወባ ህሙማን ቁጥር ሪፖርት መደረጉን ያስታውሳሉ።

በ2012 ዓ.ም ረዥም የዝናብ ወቅት እና ጎርፍ ከመኖር ጋር ተያይዞ ቁጥሩ በተወሰነ መልኩ ጨምሮ የነበረ በሆንም በ2013 ዓ.ም ቁጥሩ መቀነሱን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጣር ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም አሁን ግን ወባን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር 52 በመቶው ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖር አቶ መብርሃቶም ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው ክልልች ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል መሆናቸውን አመልክተው፤ በሌሎች ክልሎች ግን የዝናብ ወቅትን ተከትሎ የመጨመር እና የመቀነስ ሁኔታ እንደሚታይ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ፕላስሞዲየም ፋልሲፓረም እና ፕላስሞዲየም ቫይቫክስ የሚባሉ ሁለት ዓይነት የወባ ፓራሳይቶች ይገኛሉ።

ስለ ወባ ምን ማወቅ አለብዎት?

  • አራት ከተለያዩ ፕላስሞድየም በሚባሉ የፓራሳይት ዓይነቶች የሚተላለፍ ከባድና ሞትን የሚያስከትል በሽታ ነው።
  • አራቱ ፓራሳይቶች፡ ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም፣ ፕላስሞድየም ማላሪዬ፣ ፕላስሞድየም ኦቫሌ እና ፕላስሞድየም ቫይቫክስ ናቸው።
  • ሰዎች በፓራሳይቶቹ በተያዙ ወባ አስተላላፊ እንስት ቢምቢዎች ከተነከሱ ወባ ይያዛሉ።
  • በሽታውን መከላከልም ሆነ ማዳን ይቻላል።