በግሪክ የተገኘው ምሥጢራዊ የባሕር ድሮን እየተመረመረ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Lefkadatika Nea
በግሪክ የታየው ምሥጢራዊ ሰው አልባ የባሕር ድሮን ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የአገሪቱ መከላከያ አስታወቀ።
ምንነቱ በውል ያልታወቀው ድሮን የታየው በአዮኒያን ባሕር አቅራቢያ ነው። ድሮኑን የተመለከቱት ዓሣ አስጋሪዎች መሆናቸውም ተገልጿል።
ላፍካዳ በተባለ ደሴት አቅራቢያ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ድሮኑን እንዳገኙ ለባሕር ጥበቃ ኃይሎች አስታውቀዋል።
የግሪክ መከላከያ ሚኒስቴር ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ድሮኑ ፈንጂዎችን የጫነ ሲሆን ሞተሩ እየተንቀሳቀሰ ሳለ ነው የተደረሰበት።
ድሮኑ የዩክሬን ወይም ከዩክሬን ጦርነት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግሪክ እና የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴሮችን ጠይቋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ምሥሎች የጀልባ ጠባቂዎች ረዥሙን ድሮን ወደ ባሕር ዳርቻ ሲወስዱ ያሳያል።
የባሕር ላይ ድሮኑ ከየት እንደተነሳ የሚጠቁም ጽሑፍ በላዩ ላይ አይታይም።
የድሮኑ ጥቅም ምን እንደሆነ እና እንዴት ግሪክ እንደደረሰ በወታደራዊ ባለሙያዎች ይፈተሻል። ግሪክ የደረሰው ምናልባትም በቴክኒክ ብልሽት ወይም ከተቆጣጣሪው አካል ጋር የግንኙነት መስመር በመቋረጡ ሊሆን ይችላል።
ሩሲያ የምዕራባውያንን ማዕቀብ በማለፍ ነዳጅ ለማዘዋወር የምትጠቀምበትን ድብቅ ነዳጅ ጫኝ መርከብ (shadow fleet) ዒላማ ያደረገ ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል።
የግሪክ ታ ና ጋዜጣ እንደዘገበው፤ ድሮኑ የዩክሬንን ድሮን (MAGURA V5) የሚመስል ነው። ይህ ግን በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።
የዩክሬን ድሮኖች የባሕር ላይ የጦር መሣሪያን የለወጡ መሆናቸው ይነገርላቸዋል። የሩሲያን ተዋጊ መርከቦች እና ታንከሮች በባሕር ላይ ዒላማ በማድረግ ይታወቃሉ።
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2025 በጥቁር ባሕር ሲጓዙ የነበሩ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሁለት የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ ታንከሮችን መምታቷን ዩክሬን ይፋ አድርጋለች።
ያለፈው ሚያዝያ ላይ በሊቢያ እና ማልታ መካከል በሜድትራኒያን ባሕር ላይ እየተጓዘ የነበረ የተፈጥሮ ነዳጅ የጫነ ታንከር ላይ ዩክሬን ጥቃት መፈጸሟን ሩሲያ ገልጻለች። የዩክሬን ጦር ለዚህ ክስ ምላሽ አልሰጠም።













