የግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎች ስደተኞችን ወደ ባሕር በመጣል ለሞት እንደዳረጉ የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ

የግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎች በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ በርካታ ስደተኞችን ለህልፈት መዳረጋቸውን እማኞች ተናገሩ፣ ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ ደግሞ ሆን ብለው ወደ ባሕር ወርውረዋል ተብሏል።
ዘጠኙ ሰዎች ከግሪክ ግዛት እንዲወጡ ከተገደዱ እና ግሪክ ደሴቶች ከደረሱ በኋላ እንዲመለሱ ተደርገው ሕይወታቸው ካለፉ ከ40 በላይ ሰዎች መካከል እንደሚገኙበት ቢቢሲ አረጋግጧል።
የግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎች ሁሉንም ውንጀላዎች በጥብቅ አስተባብለው የምርመራ ውጤቱን ውድቅ አድርገውታል።
ቢቢሲ 12 ሰዎች የግሪክ የጠረፍ ጥበቃ ጀልባ ላይ ከተጫኑ በኋላ ወደ ሌላ ታንኳ ሲጫኑ የሚያሳይ ምሥልን ለቀድሞ የግሪክ የጠረፍ ጠባቂ መኮንን ካሳየ በኋላ ማይክራፎኑ በርቶ ሳለ “በግልጽ ሕገ-ወጥ” እና “ዓለም አቀፍ ወንጀል” ነው ሲል ተቀርጿል።
የግሪክ መንግሥት ለዓመታት ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ቱርክ ይመልሳል የሚል ክስ ተደጋግሞ ቀርቦበታል። አብዛኞቹ መነሻቸው ቱርክ ቢሆንም በግዳጅ መመለሱ ግን የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው።
የግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎች በወሰዱት እርምጃ የሰው ሕይወት ማለፉን የሚገልጹ ክስተቶችን ቢቢሲ ያሰላው ለመጀመሪያው ጊዜ ነው።
እአአ ከግንቦት 2020-23 ጀምሮ የነበሩ 15 ክስተቶች ተተንትነዋል። በዚህ ወቅት 43 ሰዎችን ሞተዋል። ቢቢሲ በዋናነት የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና የቱርክ የባሕር ጠባቂዎችን እንደመነሻ የመረጃ ምንጭ ተጠቅሟል።
እንደእነዚህ ያሉትን ጉዳዮች ማረጋገጥ በጣም ከባድ ነው። ብዙ ጊዜ ምስክሮች ይጠፋሉ አልያም ለመናገር ይፈራሉ። በአራቱ ጉዳዮች ላይ ግን ከዐይን እማኛች ጉዳዩን ለማረጋገጥ ተችሏል።

ከክስተቶቹ በአምስቱ ስደተኞች በግሪክ ባለሥልጣናት በቀጥታ ወደ ባሕር መወርወራቸውን ተናግረዋል። በአራቱ ደግሞ ግሪክ ደሴቶች እንዴት እንደደረሱ እና እንደታደኑ አብራርተዋል። በሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ደግሞ ስደተኞች በሞተር አልባ ጅልባዎች ላይ ተጭነው ነበር። አንዳንዶቹ ተንፍሰዋል ወይም ተበስተዋል።
መስከረም 2021 ሳሞስ ደሴት ከደረሰ በኋላ በግሪክ ባለሥልጣናት ታድኖ እንደነበር የሚናገር አንድ ካሜሩናዊ በጣም አሳዛኝ ታሪኮችን ለቢቢሲ አጋርቷል።
እንደሌሎቹ ሁሉ እሱም ግሪክ ላይ እንደ ጥገኝነት ጠያቂ ለመመዝገብ ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል።
“በጭንቀት በመርከብ ስጓዝ ፖሊሶች ከኋላ መጡ። ጥቁር ልብስ የለበሱ ሁለት ፖሊሶች እና ሌሎች ሦስት ሲቪል የለበሱ ሰዎች ነበሩ። ጭንብል አጥልቀው ነበር። ዐይናቸው ብቻ ነው የሚታየው” ይላል።
እሱ እና ከካሜሮን እና ከአይቮሪ ኮስት የመጡ ሁለት ሰዎች ወደ ግሪክ የባሕር ዳርቻ ጠባቂ ጀልባ ተጫኑ። አስፈሪ የሆነው ታሪክ እዚህ ጋር ይጀምራል።
“[በሌላኛው] ካሜሮናዊ ጀመሩ። ወደ ውሃ ጣሉት። አይቮሪ ኮስታዊው ‘አድነኝ፣ መሞት አልፈልግም’ አለኝ… እጁ ብቻ ከውሃ በላይ ነበር።”
“ቀስ ብሎ እጁም ገባ። እናም ውሃው ዋጠው።”
ቃለ መጠይቁን ለቢቢሲ የሰጠው ይህ ግለሰብ በጠባቂዎቹ መደብደቡን ተናግሯል።
“ቡጢዎች ጭንቅላቴ ላይ ይዘንቡ ጀመር። እንስሳ እየመቱ ነበር የሚመስለው” ብሏል። ከዚያም እሱንም ወደ ውሃው ውስጥ እንደወረወሩት ይናገራል። ወደ ባሕር ዳርቻ ዋኝቶ ለመድረስ ቻለ። የሲዲ ኪዬታ እና የዲዲየር ማርሻል ኩአሙ ናና አስከሬኖች ደግሞ በቱርክ የባሕር ዳርቻ ላይ ተገኙ።
የግሪክ ባለሥልጣናት ተደራራቢ የግድያ ክስ እንዲከፍቱ የተረፉት ሰዎች ጠበቆች እየጠየቁ ነው።
ሰኔ 2023 ላይ ከመጠን በላይ የጫነች ጀልባ ከግሪክ የጠረፍ ጠባቂ ጀልባ ፊት ለፊት ይገለብጣል። ከ600 በላይ ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት በአደጋው ይሞታሉ። ለመሆኑ ተጠያቂው ማነው? ጥፋቱ የጠረፍ ጠባቂዎቹ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Fayad Mulla
የሶማሊያ ተወላጅ የሆነ ግለሰብ እአአ በ2021 ቺዮስ ደሴት ላይ በግሪክ ጦር ተይዞ ለግሪክ የጠረፍ ጠባቂ ተላልፎ የተሰጠበተን መንገድ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የጠረፍ ጠባቂው ወደ ውሃው ከመጣላቸው በፊት እጆቹን ከኋላ እንዳሰሩትተናግሯል።
“እጄን አስረው ውሃው መሐል ላይ ወረወሩኝ። እንድሞት ፈልገው ነበር” ብሏል።
እጁን ከእስር ከመፍታቱ በፊት በጀርባው በመንሳፈፍ መትረፍ መቻሉን ተናግሯል። ከእሱ ጋር ከነበሩት ውስጥ ሦስቱ ሞተዋል። ግለሰቡ ምድር ላይ ሲደርስ የቱርክ የጠረፍ ጠባቂዎች አገኙት።
መስከረም 2022 ላይ 85 ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በግሪክ ሮድስ ደሴት አቅራቢያ ችግር አጋጠማት።
ከሶሪያ የመጣው ሞሐመድ የግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎችን እርዳታ ለማግኘት ሞክረው እንደነበር ይገልጻል። ጠባቂዎቹ ናቸው በጀልባ ጭነው ወደ ቱርክ የውሃ ክልል የመለሷቸው። ሞሐመድ እና ቤተሰቡ የተሳፈሩበት አነስተኛ ጀልባ በትክክል አይሠራም ይላል።
“ወዲያው መስጠም ጀመርን። እነሱም እያዩን ነበር… ሁላችንም ስንጮህ ሰሙ። ሆኖም ትተውን ሄዱ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
“መጀመሪያ የሞተው የአጎቴ ልጅ ነው…ከዚያ በኋላ አንድ በአንድ መሞት ጀመሩ። አንድ በአንድ አጎቴም ጠፋ። ጠዋት ላይ ሰባት ወይም ስምንት ልጆች ሞተዋል።”
“ልጆቼ እስከ ጠዋት ድረስ አልሞቱም... ልክ የጠረፍ ጠባቂዎች ከመድረሳቸው በፊት ነው የሞቱት።”
የግሪክ ሕግ ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞች በሙሉ ጥያቄያቸውን በተለያዩ ደሴቶች በሚገኙ የምዝገባ ማዕከላት እንዲያቀርቡ ይፈቅዳል።
በኮንሶሊዴትድ ሬስኪው ግሩፕ አማካኝነት ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች ግን ወደ እነዚህ ማዕከላት ከመድረሳቸው በፊት መያዛቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ሰዎች የሚሠሩት በድብቅ ሲሆን ዩኒፎርም የሌላቸው እና ብዙ ጊዜም ጭምብል አጥልቀው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ በአውሮፓ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከግሪክ ወደ ቱርክ በሕገ ወጥ መንገድ እንዲመለሱ ተደርገው ጥገኝነት የመጠየቅ መብታቸውን ተነፍገዋል ብለዋል። ይህም ከዓለም አቀፍ እና ከአውሮፓ ኅብረት ሕጎች የተቃረነ ነው።
ኦስትሪያዊው አክቲቪስት ፋያድ ሙላ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ በግሪኳ ሌስቦስ ደሴት ላይ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ምን ያህል በምሥጢራዊነት እንደሚከናወኑ በራሱ እንደደረሰበት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጥቆማ አግኝቶ ስደተኞች በግዳጅ ተመለሱ ወደተባለበት ቦታ በመንዳት ላይ እያለ ጭንብል ባጠለቀ ሰው እንዲቆም ተደረገ። በኋላ ላይ ግለሰቡ ለፖሊስ እንደሚሠራ ታወቀ። ፖሊስ በመኪናው የተገጠመው ካሜራ ላይ ያለውን ምሥል ለመሰረዝ ከመሞከር ባለፈ የፖሊስ መኮንንን መቃወም የሚል ክስ ሊመሠርትበት ሞክሯል።
ምንም እርምጃ ግን አልተወሰደበትም።

ሙላ ከሁለት ወራት በኋላ በተመሳሳይ ቦታ ላይ በግዳጅ ስደተኞችን ሲመልሱ ቀርጾ በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ወጥቷል።
ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ ምንም ምልክት ከሌለው መኪና ላይ ወደ ትንሽ ጀልባ ተጫኑ።
ከዚያም ከባሕር ዳርቻው በርቀት ላይ ወደሚገኝ የግሪክ የጠረፍ ጠባቂ መርከብ ተወሰዱ። ቀጥሎም በአየር ወደሚነፋ ጀልባ ተዘዋወሩ።
በኋላም በቱርክ የጠረፍ ጠባቂዎች ሕይወታቸው ሊተርፍ ቻለ።
ቢቢሲ ያረጋገጠውን ምሥል ለቀድሞው የግሪክ የጠረፍ ጠባቂ የልዩ ዘመቻ ኃላፊ ለነበረው ለዲሚትሪስ ባልታኮስ አሳይቷል።
ቀደም ሲል የግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎች ሕገወጥ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ይገደዳሉ የሚለውን ቢክድም፤ በቃለ መጠይቁ ወቅት ቀረጻው ስለሚያሳየው ለመገመት ፈቃደኛ አልሆነም። ቃለ መጠይቁ ለእረፍት ሲቋረጥ በግሪክ ቋንቋ ከሌላ ግለሰብ ጋር ሲነጋገር ተሰማ።
“እኔ ብዙ አልነገርኳቸውም አይደል? በጣም ግልጽ ነው አይደል። ይህ የኒውክሌር ፊዚክስ አይደለም። ለምን በጠራራ ፀሐይ እንዳደረጉት አላውቅም... ግልጽ ነው ... ሕገወጥ ነው። ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው” ሲል ተደምጧል።
የግሪክ የባሕር ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢንሱላር ፖሊሲ ምሥሉ በአገሪቱ ገለልተኛ በሆነው የብሔራዊ ትራንስፓረንሲ ባለሥልጣን እየተጣራ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መቀመጫዋን በሳሞስ ደሴት ያደረገች እና ቢቢሲ ያነጋገራት መርማሪ ጋዜጠኛ በበኩሏ ከግሪክ ልዩ ኃይል አባል ጋር በቲንደር [የፍቅር ጓደኛ ማፈላለጊያ መተግበሪያ ነው] ማውራት እንደጀመረች ትናገራለች።
“የጦር መርከብ” ብሎ ከገለጸው ቦታ ሲደውልላት ደግሞ ሮሚ ቫን ባርሰን ስለሥራው እና የስደተኛ ጀልባ ሲያዩ ምን እንደሚፈጠር ጠየቀችው።
“እንደገና ወደ ኋላ እንመልሳቸዋል” ሲል መለሰ። እንደዚህ ዓይነት ትዕዛዞች “ከሚኒስትሩ” የመጡ ናቸው። ጀልባ ማቆም ካልቻሉ እንደሚቀጡም ገለጸ።
ግሪክ ስደተኞችን “መመለስ” ላይ እንደማትሳተፍ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ለብዙ ስደተኞች ግሪክ ወደ አውሮፓ መግቢያ በር ናት። ባለፈው ዓመት 263 ሺህ 48 የባሕር ስደተኞች አውሮፓ ሲደርሱ ግሪክ 41,561 (16 በመቶ) ግሪክ ተቀብላለች።
ቱርክ በ2016 ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ወደ ግሪክ የሚሻገሩ ስደተኞችን ለማስቆም ስምምነት ተፈራርማ የነበረ ቢሆንም በ2020 ግን ይህንን ማስፈጸም እንደማትችል አስታውቃለች።
ቢቢሲ ምርመራውን ለግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎች አሳይቷል። አባላቱ “በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት፣ በኃላፊነት ስሜት እና የሰው ሕይወት እና መሠረታዊ መብቶችን በማክበር ያለመታከት እየሠሩ ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
“ከ2015 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ የሄለኒክ የጠረፍ ጥበቃ አባላት በ6161 አጋጣሚዎች 250 ሺህ 834 ስደተኞችን መታደግ መቻሉ ሊሰመርበት ይገባል። የዚህ የተከበረ ተልዕኮ እንከን የለሽ አፈጻጸም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ አዎንታዊ እውቅና አግኝቷል” ሲልም አክሏል።
የግሪክ የጠረፍ ጠባቂዎች ለአስር ዓመታት ያህል በሜዲትራኒያን ባሕር በስደተኞች መርከብ ላይ በነበራቸው ሚና ምክንያት ወቀሳ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
ባለፈው ሰኔ ወር አድሪያና የተባለች ጀልባ ለግሪክ በተከለለ የነፍስ አድን ቦታ ሰጥማ ከ600 በላይ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተግምቷል።
የግሪክ ባለሥልጣናት ጀልባዋ ችግር እንዳልነበረባት እና ወደ ጣሊያ በሠላም በመጓዝ ላይ ነበረች ብለዋል። በዚህ ምክንያትም የጠረፍ ጠባቂዎች ለማዳን አልሞከሩም ሲል አክሏል።












