በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ይቀሰቀስ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, EBC
በሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሹ ጦርነት ካበቃ ከሦስት ዓመት በኋላ ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚለው ፍራቻ በርካቶች ትግራይን ለቅቀው እንዲወጡ እያደረገ ነው።
በመቀለ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች "የአውሮፕላን ቲኬት መግዛት የቻሉ በአውሮፕላን፤ ያልቻሉ በአውቶቡስ" ክልሉን ለቅቀው በመውጣት ወደ አዲስ አበባ እየሄዱ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
የክልሉ ዋሪዎች የሸቀጣ ሸቀጥ እቃዎችን እየገዙ ማከማቸት በመጀመራቸው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ይናገራል።
በክልሉ የሚገኙ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ስላጋጠማቸው አንድ ሰው በቀን ማውጣት የሚችለው 2000 ብር ብቻ እንዲሆን ማድረጋቸውን ነዋሪዎች ጨምረው ገልጸዋል።
ለሁለት ዓመት የቆየው ጦርነት ክፉኛ በጎዳት ትግራይ ክልል የሚገኙ ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ስላለባቸው በርከት ያለ ቁጥር ያለው ገንዘብ ለማስተላለፍ የሚፈልጉ ሰዎች ተጨማሪ ክፍያ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱ ምን ገጠመው?
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት 600 ሺህ ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ገልጾ ነበር።
የአፍሪካ ኅብረት ከሦስት ዓመት በፊት ሁለቱን ወገኖች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ወደ ሰላም እንዲመጡ ካሸማገለ ወዲህ በክልሉ የተኩስ ድምጽ መሰማት አቁሟል።
ይህንንም ተከትሎ በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ መደበኛ ሕይወትም ቀጥሏል።
ይኹን እንጂ በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ ሁለት አካላት በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ላይ ባለመካተታቸው ወዲያው ፍርሃት እና ስጋት ቦታውን ተረክቧል።
በአንድ ተሰልፈው ህወሓትን የተዋጉት ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ሆድ እና ጀርባ ሆነዋል።
የአማራ ኃይሎችም በምዕራብ ትግራይ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበትን እና ምርታማ የሆነ አካባቢ ተቆጣጥረው በመያዛቸው አሁንም የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ከፈረመ በኋላ ከቀድሞ አጋሩ ከኤርትራ እና ከአማራ ታጣቂዎች ጋር ጠብ ውስጥ ገብቷል።
አገሪቱ በሰኔ ወር ወደ ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና እያለች ባለችበት ሰዓት መንግሥት በአማራ ኃይሎች የተያዙት አካባቢዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ መፍትሄ ባለመስጠቱ ከህወሓት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል።
ይህ በሁለቱ የፕሪቶሪያ ተፈራራሚዎች መካከል አለመተማመንን ያስከከተለ ሲሆን፣ የሰላም ስምምነቱም በፍጥነት አደጋ ውስጥ እንድዲወድቅ አድርጎታል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ነገሮች እንዴት ሊባባሱ ቻሉ?
በሰሜን ኢትዮጵያ የወታደሮች መሰባሰብ እየተካሄደ መሆኑን የሚገልጹ ዘገባዎች መሰማት ጀምረዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን ሁኔታ "በጣም ተለዋዋጭ" ሲል ገልጾታል።
በጥር ወር መጨረሻ ላይ በአማራ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ለመመለስ ያደረጉትን ሙከራ ተከትሎ ከአገሪቱ መከላከያ ጋር ለአጭር ጊዜ ግጭት ተከስቶ ነበር።
የድሮን ጥቃቶች በክልሉ ወስጥ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን፣ ወደ ትግራይ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎችም ለአንድ ሳምንት ያህል ተቋርጠው ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ኤርትራ የትግራይ ኃይሎችን ትደግፋለች ስትል የምትከስ ሲሆን፣ ኤርትራ ግን ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች።
በጥቅምት ወር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ በጻፈው ደብዳቤ ኤርትራ "በህወሓት ውስጥ ካሉ አክራሪዎች" ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን "ጦርነት ለመግጠም" እየሠራች ነው ሲል ከስሷል።
ባለፈው ሳምንት የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በትግራይ ላይ ጦርነት "እያንዣበበ" መሆኑን እና "ሕዝቡም...የሚቃጣበትን ጥቃት በመቋቋም ኅልውናውን ለማስጠበቅ ራሱን የመከላከል ግዴታ እንዳለበት" ተናግረዋል።
የህወሓት ቅሬታ ምንድን ነው?
ህወሓት ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ ያጣቸው አወዛጋቢ ስፍራዎች እንዲመለሱለት ይፈልጋል።
በግጭቱ ወቅት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመላው ትግራይ ውስጥ በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ይኖራሉ። ላለፉት አምስት ዓመታት እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ አልቻሉም።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ በሆኑ ቦታዎች "ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው" በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን ተከትሎ በትግራይ ፖለቲከኞች ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሯል።
በጦርነቱ ወቅት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ እውቅና የሌለው ሲሆን፣ ይህም እንዲመለስለት ይፈልጋል።
በክልሉ ሌላ ጦርነት ቢቀሰቀስ ምን ይሆናል?
በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት የጣላቸው ጠባሳዎች እና ጉዳቶች አሁንም በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ናቸው።
በጦርነቱ የተጎዱ እና ውድመት የደረሰባቸው መሠረተ ልማቶች አልተጠገኑም፤ እንዲሁም የክልሉ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ አላገገመም።
ስር የሰደደ የሥራ አጥነት የክልሉን ወጣቶች ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ የተሻሉ ዕድሎችን ለመፈለግ አደገኛ የሆኑ የስደት መንገዶችን እንዲሞክሩ እያስገደዳቸው ነው።
በኢትዮጵያ እና በትግራይ ኃይሎች ወይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ የትግራይ ክልልን እንደገና የሚያወድም ይሆናል።
ከዚህም ባሻገር ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሊያቃውስ ይችላል።
የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ሱዳን በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ የሆነውን የሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።
መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ሚካኤል ወልደማርያም ለቢቢሲ "በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ትግራይን እና ሌሎች የኢትዮጵያን ታጣቂዎች የሚያካትት ማንኛውም ጦርነት ከሱዳን ጋር የመገናኘት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ሁለቱ ግጭቶች ይዋሃዳሉ" ብለዋል።
ሌላ ግጭትን ለመከላከል ምን ማድረግ ይቻላል?
በአውሮፓውያኑ 2022 የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ወደ ሰላም ጠረጴዛ እንዲመጡ ያደረገው በተለይም ከአሜሪካ የሚመጣ የዲፕሎማሲ ጫና ነበር።
የባሕረ ሰላጤው አገራት አሁን በአካባቢው የበለጠ ተሳትፎ እያደረጉ ስለሆነ ከእነሱ የሚመጣ ጫና ሌላው ሊኖር የሚችልን አስከፊ ግጭትን ሊያስቀር የሚችል መንገድ ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአዲስ አበባ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ ተቀናቃኛዋ ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ከአሥመራ ጋር የቅርብ ወዳጅ መሆኗ ይታሰባል።
ይኹን እንጂ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ሚካኤል ብሩህ ተስፋ አይታያቸውም።
በዚህ ጊዜ "የአፍሪካ ኅብረት የሚፈለገው አቅም የለውም" ሲል የአሜሪካ ትኩረት በሌላ ቦታ ላይ በመሆኑ እና የባሕረ ሰላጤው አገራትም መከፋፈላቸውን ገልጸዋል።















