የኢራን የኒውክሌር ግንባታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ዕውን አሁንም ስጋት ነው?

የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራምን የሚያሳይ ግዙፍ ፖስተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዳግም ዐይን ውስጥ ገብቷል። ዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶቿን እና መርከቦቿን ወደ ቀጠናው አስጠግታለች።

አሜሪካ ቴህራን ከስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ ጥቃት ለመፈጸም ተሰናድታ እየጠበቀች ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአውሮፓውያኑ የካቲት 19 "ተጨባጭ ስምምነት" ላይ መድረስ ካልተቻለ "መጥፎ ነገር ይከሰታል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

"የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራቸው አይችልም፤ በጣም ቀላል ጉዳይ ነው. . . የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ካላቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ሊኖር አይችልም" ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

ኢራን ግን የኒውክሌር ቦምብ እንዲኖራት እንደማትፈልግ በተደጋጋሚ ተናግራለች። ነገር ግን በርካታ አገራት እንዲሁም የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት የኢራንን ቃል አምነው መቀመጥ አይፈልጉም።

የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው?

በእስራኤል እና በኢራን መካከል ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ለአስራ ሁለት ቀናት ጦርነት ከተካሄደ በኋላ የኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም ያለበት ደረጃ በግልጽ አይታወቅም።

ዩናይትድ ስቴትስ ጦርነቱን ለአጭር ጊዜ ተቀላቅላ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የአየር ድብደባ ፈጽማለች።

ጥቃቱ የደረሰባቸው ተቋማት በኢስፋሃን የሚገኘው የኒውክሌር የምርምር ተቋም፣ በናታንዝ እና ፎርዶ የሚገኙት ዩራኒየም ለማበልጸግ የሚያገለግሉ ማዕከሎች ናቸው።

ከጥቃቱ በኋላ ትራም ተቋማቱ "ከጥቅም ውጭ ሆነዋል" ሲሉ ተናግረዋል። ከሳምንት በኋላ ግን የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ በተቋማቱ ላይ የደረሰው ጥቃት ከባድ ቢሆንም "ሙሉ በሙሉ" አለመውደማቸውን በመግለጽ በወራት ውስጥ ማበልጸግ ሊጀመሩ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የኢራን የኒውክሌር ማዕከላትን የሚያሳይ ካርታ

የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋጣጣሪ ኤጀንሲ እስራኤል ባለፈው ዓመት ሰኔ 13 ጥቃት ስትፈጽም ኢራን 440 ኪሎ ግራም የበለፀገ እና ጥራት ደረጃው 60 በመቶ የሆነ ዩራኒየም ክምችት ነበራት ብሏል።

ይህም የጦር መሣሪያ ለማምረት ጥቂት ብቻ የቀረው ማለት ነው።

ግሮሲ በጥቅምት ወር ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት ይህ መጠን፣ የበለጠ ከበለፀገ ለ10 የኒውክሌር ቦምቦች በቂ ይሆናል።

በኅዳር ወር የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለ ዘ ኢኮኖሚስት እንደተናገሩት ዩራኒየም ማበልጸጉ "አሁን ቆሟል" ብለዋል።

ባለፈው ወር ለፎክስ ኒውስ ደግሞ "አዎ፣ ተቋማቱን፣ ማሽኖቹን አወድማችሁታል…ግን ቴክኖሎጂው ሊደበደብ አይችልም፤ እናም ቁርጠኝነታችንም ሊደበደብ አይችልም" ብለዋል።

ግሮሲ በጥር ወር ለሮይተርስ እንደተናገሩት፣ የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ በኢራን ውስጥ በቦምብ ጥቃት ያልደረሰባቸውን 13 የኒውክሌር ጣቢያዎችን መመልከት ችሏል። ነገር ግን ሦስቱን ቁልፍ ቦታዎች መመርመር አልቻለም።

ኤጀንሲው ለመጨረሻ ጊዜ የኢራንን ከፍተኛ የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት ከፈተሸ ሰባት ወራት ሆኖታል ብለዋል።

በተለይም የክምችቱ ቦታ እና ሁኔታ እንዲሁም የማበልጸጊያ ተቋማት ሁኔታ ላይ እርግጠኛ አይደለም።

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ በተደጋጋሚ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት እንደማይፈቀድ ይናገራሉ

እዚህ እንዴት ደረስን?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢራን መንግሥት የኒውክሌር ዓላማ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል።

አገሪቱ የፈረመችው ስምምነት የሚፈቅደው የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሕክምና፣ ለግብርና እና ለኢነርጂ አገልግሎት ብቻ መጠቀም ሲሆን፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን መታጠቅን ይከለክላል።

ይሁን እንጂ፣ በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የተደረገ ለአስር ዓመታት የዘለቀ ምርመራ ኢራን ከ1980ዎቹ መጨረሻ እስከ 2003 ድረስ "ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ ከመሥራት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተግባራትን" እንዳከናወነች አረጋግጧል።

የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያመለክተው ይህ ፕሮጀክት አማድ በመባል የሚታወቀው ፕሮግራም ከዚያ በኋላ ተቋርጧል። ሆኖም ግን በ2009 የምዕራባውያን የስለላ ተቋማት የፎርዶን ተቋም መገንባት ማወቅ ችለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2015 የኤጀንሲው ሪፖርት እንዳመለከተው "ከ2009 በኋላ በኢራን ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ከመገንባት ጋር የተያያዙ ተጨባጭነት ያላቸው እንቅስቃሴዎች አልታዩም " ብሏል።

እንዲሁም በ2015 ኢራን ከስድስት የዓለም ኃያላን መንግሥታት ጋር ስምምነት ተፈራረመች። በዚህም ምክንያት የማዕቀብ እፎይታ ለማግኘት በምትኩ የኒውክሌር እንቅስቃሴዎቿ ላይ ጥብቅ ገደብ ለማድረግ ተስማምታለች።

ስምምነቱ ለኒውክሌር ኃይል ምርት ተስማሚ የሆነውን 3.67 በመቶ ማበልጸግ እና በፎርዶ ላይ ያለውን ማበልጸግ በተጠናከረ ክትትል ማቆም የሚሉ ይገኙበታል።

ነገር ግን በ2018 ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት የምታደርገውን ጥረት ማስቆም አልቻለም በሚል ከስምምነቱ በመውጣት ማዕቀብ እንደገና ጥለዋል።

ኢራን የስምምነቱን ገደብ በመጣስ ዩራኒየምን ወደ 60 በመቶ በማበልጸግ፣ ዩራኒየም ለማበልጸግ የሚያግዙ የተራቀቁ መሣሪያዎችን በመጠቀም እንዲሁም የፎርዶ ማበልጸጊያን እንደገና ሥራ በማስጀመር ምላሽ ሰጥታለች።

ሰኔ 12/2025 የኤጀንሲው የቦርድ አመራሮች ኢራን ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባችውን ስምምነት መጣሷን በይፋ አስታውቋል። በማግስቱ እስራኤል የአየር ድብደባ ጀመረች።

የኢራን ባንዲራ እና የኢራን የበላይ መሪ አሊ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እአአ በ2015 የማዕቀብ እፎይታ ለማግኘት የኒውክሌር እንቅስቃሴያቸውን ለመገደብ ተስማምተው ነበረ

ኢራን በኒውክሌር ተቋማቷ አሁን ምን እያደረገች ነው?

የሳተላይት ምሥሎች በቅርብ ወራት ውስጥ በናታንዝ እና በኢስፋሃን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ አንዳንድ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያሳያሉ።

በኢስፋሃን ወደ ዋሻው ሕንፃ የሚወስዱ ሁሉም መግቢያዎች አሁን የተዘጉ ይመስላሉ፤ ምሥሎቹን የተመለከተው መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ደኅንነት ተቋም (አይኤስአይኤስ) አዲስ ጣሪያ ተገንብቷል ሲል ገልጿል።

ምሥሎቹ በናታንዝ በሚገኘው ተቋም ላይም ጣሪያ መገንባቱን ያሳያሉ።

በአይኤስአይኤስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተነተኑት የቅርብ ጊዜ የሳተላይት ምሥሎች ኢራን የኮላንግ ጋዝ ላ ተራራ የተባለ የመሬት ውስጥ የሚገኝ ተቋምን እያጠናከረች መሆኑን ያሳያሉ።

በተጨማሪም ፒካአክሴ ተራራ በመባል የሚታወቀው ቦታ በእስራኤል ወይም በአሜሪካ አየር ኃይል ጥቃት አልደረሰበትም። ይህ ተቋም ከናታንዝ የኒውክሌር ተቋም በስተደቡብ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

በኢራን የኒውክሌር ማዕከላት የተካሄደ ግንባታ የሚያሳዩ የሳተላይት ምሥሎች

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ ይፈጅባታል?

የጦር መሣሪያ ለማምረት የሚያስችል የበለፀገ ዩራኒየም ማምረት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ከመገንባት ጋር ተመሳሳይ አይደለም። ይህንን ለማድረግ ተጨማሪ የቴክኒክ እርምጃዎችን ይፈልጋል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የአሜሪካ የመከላከያ መረጃ ኤጀንሲ (ዲአይኤ) ያደረገው ግምገማ እንዳመለከተው የእስራኤል እና የአሜሪካ ጥቃቶች ከመፈጸማቸው በፊት ኢራን በወቅቱ "ምናልባት ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ" የመጀመሪያውን የኒውክሌር መሣሪያ ለማምረት የሚያስችላት በቂ የጥራት ደረጃ ያለው ዩራኒየም ማምረት ችላለች።

ይሁን እንጂ ኢራን የበለፀገውን ዩራኒየም የጦር መሣሪያ የማምረት አቅም ለመፍጠር እየሞከረች ነው በሚል የሚቀርቡት ግምገማዎች ይለያያሉ።

የዲአይኤ ግምገማም "ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን እያመረተች እንዳልሆነች ጥርጥር የለውም፤ ነገር ግን ኢራን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከፈለገች ለማምረት የሚያስችሏትን ተግባራትን አከናውናለች።"

ይሁን እንጂ የእስራኤል ጦር ሰኔ ወር ላይ "የኢራን መንግሥት ለኒውክሌር ቦምብ የሚሆኑ የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት የሚያደርገው ጥረትን" የሚያሳዩ "ተጨባጭ እርምጃዎች" ማድረጉን የሚያሳይ መረጃ መሰብሰቡን አስታውቋል።

"ኢራን እስከ 2003 ድረስ የጦር መሣሪያ ዲዛይን ላይ የተወሰነ አቅም አዳብራ ነበር" ይላሉ ገለልተኛ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ፓትሪሺያ ሌዊስ።

ይኹን እንጂ "የ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት ከፈረሰ እና አዲስ ስምምነት ለማድረግ የተደረጉ ውይይቶች ያለውጤት ካበቁ በኋላ፣ ኢራን…የጦር መሣሪያ መሥራት አቅሟን እንደገና ለማዳበር እንደወሰነች ተናግራለች" ብለዋል።

ግሮሲ የካቲት 18 የፈረንሳዩ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢኤፍ1፣ ኤጀንሲው ኢራን የጦር መሣሪያ ለማምረት እየሞከረች መሆኑን ምልክቶች አይቶ እንደሆነ ሲጠይቃቸው "አላየም" ብለዋል።

በአሜሪካም ሆነ በኢራን በኩል "ስምምነት ላይ ለመድረስ" ፈቃደኛ መሆናቸውን ማየታቸውን አክለው ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ ኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዓለም አቀፉ ኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ኤጀንሲው ከቅርብ ወራት ወዲህ የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም መመልከት አለመቻሉን ተናግረዋል

የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለምን አሳሳቢ ሆነ?

የምዕራባውያን መሪዎች ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንድትታጠቅ መፍቀድ የለባትም የሚለውን እምነታቸውን ለረጅም ጊዜ ሲገልፁ ቆይተዋል።

ትራምፕ በግንቦት 2025 አንድ የኒውክሌር መሣሪያ ከታጠቀች "ዓለም ትጠፋለች" ብለዋል። በ2024 የምርጫ ዘመቻ ወቅት የኢራን የኒውክሌር ባለቤትነት ከተረጋገጠ "ሙሉ በሙሉ የተለየ ዓለም…ሙሉ በሙሉ የተለየ ድርድር" ማለት እንደሆነ እና እስራኤል "ትጠፋለች" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ኒውክሌር የታጠቀች ኢራን "በአካባቢው መረጋጋት ላይ ትልቁ ስጋት ትሆናለች" ሲሉ ገልጸውታል።

በዩኬ የሚገኘው የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት (ሩሲ) የመካከለኛው ምሥራቅ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኤች ኤ ሄሊየር "የቀጠናውን ውጥረትን ይጨምራል፤ በተለይም ለእስራኤል እና ለዩናይትድ ስቴትስ የሚፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ያወሳስበዋል" ይላሉ።

አንዳንድ ተንታኞች የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቅ በቀጠናው ላይ ሊያፈረጥማት ይችላል፤ ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያጠናክር እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የጦር መሣሪያ ውድድርን ሊያነሳሳ እንደሚችል ይከራከራሉ።

እስራኤል ምንም እንኳ በይፋ ባታምንም ወይንም ባትክድም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳላት ይታወቃል።

ሄሊየር ይህ ማለት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቃ "ዕውን የሚሆን ከሆነ"፤ "ወዲያውኑ ፍጥጫ ውስጥ ከመግባት ይልቅ የጋራ መከላከያ ይሆናል" ማለት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

አብዛኞቹ የቀጠናው አገራት "የእስራኤልን ኃይል፣ እንደ መላምታዊ የኢራን ቦምብ ሳይሆን፣ እንደ አሁናዊ እና አደፍራሽ የፀጥታ ስጋት አድርገው ይመለከቱታል" ብለዋል።

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቅ ትልቁ አደጋ "በግጭት ወቅት የሚኖር የስሌት ስህተት ነው" ብለዋል።