አገራት ኒውክሌር መታጠቅ ይችላሉ? ያላቸው አገራትስ መሳሪያው እንዴት ሊኖራቸው ቻለ?

ኒውክሌር ቦምቦች ፍናዳታ በጂሮሺማ እና ናጋሳኪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ በጃፓን ከተሞች ላይ ኒውክሌር ቦምቦችን ጥላለች። በግራ በኩል ያለው በሂሮሺማ፣ በቀኝ በኩል ደግሞ በናጋሳኪ ላይ የተጣሉት ቦምቦች በፈነዱበት ጊዜ

ዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያውን የኒውክሌር ቦምብ ካፈነዳች ከሰማንያ ዓመታት በኋላ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር የመካከለኛው ምሥራቅን ወደ ግጭት ቀጣና እየቀየረው ነው።

እስራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ በሰኔ ወር የኒውክሌር ተቋሞቿን ማጥቃታቸውን ተከትሎ የኢራን ፕሬዝዳንት አገራቸው የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም ከሆነ ከዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ያላትን የትብብር ግንኙነት የሚያቋርጥ ሕግ ሰኔ መጨረሻ ላይ ፈርመዋል።

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትገነባ ለመከላከል ጥቃቶቹ አስፈላጊ ነበሩ ሲሉ እስራኤል እና አሜሪካ እየተናገሩ ነው። ጥቃቶቹ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሱ እና ጥፋቱ በቀጣናው ምን ሊያስከትሉ እንደሚችል እስካሁን ግልጽ አልሆነም።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ55 ዓመታት በፊት በሥራ ላይ የዋለው እና የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታን ለመገደብ የተዘጋጀው ስምምነት ላይ ያለው ተጽዕኖም አልታወቀም።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ዘጠኝ አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላቸው ይታወቃል። እንዴት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሊታጠቁ ቻሉ? ሌሎች አገራትስ መሣሪያውን ማግኘት ከፈለጉ ይህንን ማሳካት ይችላሉ? [ተያያዥ ዘገባ በቪዲዮ እዚህ ያገኛሉ]

የሂሮሺማ ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጃፓን ሂሮሺማ (ፎቶ) እና በናጋሳኪ ከተሞች ላይ በአሜሪካ የተጣሉት የኒውክሌር ቦምቦች እስካሁን በጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉ ቦምቦች ናቸው

የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ያላቸው እነማን ናቸው?

አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ እስራኤል እና ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላቸው ይታወቃል። እስራኤል ግን ይህንን በይፋ እስካሁን አላረጋገጠችም።

ዩናይትድ ስቴትስ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የማንሃተን ፕሮጀክት አካል በማድረግ መሳሪያውን በድብቅ ካዘጋጀች በኋላ የመጀመሪያዋ የኒውክሌር መሣሪያ ባለቤት ሆናለች።

ዩናይትድ ስቴትስ መሳሪያውን እአአ በ1945 ተጠቅማበታለች። በዚህም በጃፓን ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ ከባድ እልቂት እና ውድመት ደርሷል። ጃፓን በወቅቱ ከናዚ ጀርመን እና ከጣሊያን ጋር ኅብረት ፈጥራ በጦርነቱ ውስጥ ስትሳተፍ ነበር።

በጥቃቱ በትንሹ 200 ሺህ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ይገመታል። ይህም በግጭት ውስጥ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ የዋለበት ብቸኛው አጋጣሚም ሆኗል።

የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ፓትሪሺያ ሉዊስ አጋጣሚው "የኑክሌር ጦር መሳሪያ እሽቅድድም የተጀመረበት ነው" ብለዋል።

ሌሎች አገራት በተለይም ሶቪዬት ኅብረት የራሷን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድትሠራ ገፋፍቷታል። ዓላማው ደግሞ ራስን ከጥቃትን ለመከላከል እና በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ኃይልን ማሳየት ነው።

ቀጥሎስ ምን ተፈጠረ?

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ሁለት ዓመት ሳይሞላው ቀዝቃዛው ጦርነት ተጀመረ። በዩናይትድ ስቴትስ እና በሶቪዬት ኅብረት እና በሁለቱም ወገን አጋሮች መካከል የተደረገው ዓለም አቀፍ የበላይነት ፉክክር ከ40 ዓመታት በላይ የፈጀ እና አንዳንዴም ወደ ኒውክሌር ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋትን የፈጠረ ነበር።

ሶቪዬት ኅብረት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአውቶሚክ ቦምብ ለመሥራት ሙከራ ጀምራ በ1949 ተሳክቶላታል። ይህም የአሜሪካንን ብቸኛ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤትነት የገታ ነበር። ከዚህ በኋላ ሁለቱም አገራት የበለጠ አውዳሚ የሆነ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት ጥረታቸውን ቀጠሉ።

በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ውስጥ ደግሞ ተጨማሪ ሦስት አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን በቁ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከአሜሪካ ጋር በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልማት ትብብር የነበራት ዩናይትድ ኪንግደም እአአ በ1952 ሦስተኛዋ አገር ሆነች። ፈረንሳይ በ1960 እና ቻይና ደግሞ በ1964 መሣሪያወን ታጠቁ።

ሌሎች አገራትስ የኒውክሌር ጦር መሳሪያውን መቼ ታጠቁ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እአአ በ1960ዎቹ አምስቱ የኒውክሌር ባለቤቶች ማለትም ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሶቭዬት ኅብረት፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ቻይና መሳሪያቸውን አጠናከሩ። የኒውክሌር መሳሪያ የታጠቁ አገራት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋትም እያደገ መጣ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህንን ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መስፋፋትን ለመከላከል፣ የታጠቁት ደግሞ እንዲፈቱ ለማበረታታት እና የኒውክሌር ኃይልን በሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም የተነደፈውን ስምምነት (ኤንፒቲን) አስተዋወቀ።

ስምምነቱ እአአ በ1970 ሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም ሁሉም አገራት አልፈረሙትም፤ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች መስፋፋትም አልተገታም።

ሕንድ በ1974 ፓኪስታን ደግሞ በ1998 የኒውክሌር ኃይል ባለቤት ለመሆን በቁ። ሁለቱም አገራት ስምምነቱን አልፈረሙም። ለዚህ ደግሞ አንደኛው ምክንያት እርስ በርስ ባላቸው ቁርሾ ምክንያት በተፈጠረው ስጋት ነበር።

እስራኤልም ስምምነቱን አልፈረመችም።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ስምምነቱን ላለመፈረም በምክንያትነት የሚጠቅሱት ቀጠናዊ ስጋቶችን እና ውጥረቶችን እንዲሁም ደግሞ ከበርካታ ጎረቤቶቿ ጋር ያላት ቅራኔን ነው። ስለዚህም እስራኤል ከኒውክሌር ጋር በተያያዘ አሻሚ ፖሊሲን ስለምትከተል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላት አታምንም በተመሳሳይም አትክድም።

ሰሜን ኮሪያ ስምምነቱን የፈረመችው እአአ በ2003 ነበር። ሆኖም አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን አድርገዋል በማለት ከስምምነቱ ወጥታ በ2006 ሙከራ በማድረግ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት ሆነች።

እአአ በ2011 የተመሠረተችው ደቡብ ሱዳን ብቻ ስምምነቱ ያልፈረመች ብቸኛዋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገር ነች።

አይዘንአወር ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ1953 (እአአ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ድዋይት አይዘንአወር ኒውክሌርን ለሰላማዊ አገልግሎት ማዋልን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ሃሳብ አቀረቡ

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ናት?

በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው የሌስተር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሩ ፉተር "እስከምናውቀው ድረስ ኢራን የኒውክለር ቦምብ ባለቤት አልሆነችም" ብለዋል። "በቴክኒክም ሆነ በቴክኖሎጂ ረገድ ግን ያን ማድረግ የማይችሉበት ምክንያት የለም" ሲሉ አክለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነትን የፈረመችው ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ሰላማዊ እንደሆነ እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመሥራት እንደማትፈለግ ደጋግማ አስታውቃለች።

ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ የሆነው ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከ1980ዎቹ መገባደጃ ጀምሮ እስከ 2003 ድረስ ኢራን "ከኒውክሌር ቦምብ ልማት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተግባራትን" ስታከናውን እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ አግኝቷል።

ይህ "ፕሮጀክት አማድ" የተባለው የኒውክልር ግንባታ በ2003 እንዲቋረጥ ተደርጓል።

እአአ በ2015 ኢራን በኒውክሌር ግንባታዋ ላይ የተጣሉ ገደቦችን ተቀብላ ከስድስት የዓለም ኃያላን አገራት ጋር ስምምነት ላይ ደረሰች። በዚህም ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቁጥጥር እንዲያደርግ ፈቅዳለች። በምትኩም ኢኮኖሚዋን ያንኮታኮተው ማዕቀብ እንዲነሳ ተደረገ።

ነገር ግን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2018 በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ስምምነቱን ውድቅ አደረጉት። ምክንያት ያሉት ደግሞ ስምምነቱ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትሠራ የፈየደው ነገር የለም በማለት ነው። በዚህ ሳያበቁ ማዕቀቡን መልሰው ጣሉባት። ኢራንም የተቆጣጣሪ ተቋሙን ገደቦችን በተደጋጋሚ በመጣስ በተለይም ከዩራኒየም ማበልፀግ ጋር በተያያዘ ምላሽ መስጠቷን ቀጠለች።

በዚህ ዓመት ሰኔ ወር መጀመሪያ ደግሞ የ35 አገራት የቦርድ አባላትን ያካተተው የተቆጣጣሪ ቡድን፤ ኢራን በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የስምምነት ግዴታዋን ጥሳለች ሲል አስታወቀ።

በቀጣዩ ቀን እስራኤል በኢራን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ተከታታይ ጥቃት ፈጸመች። በኋላም አጋሯ ዩናይትድ ስቴትስ ጥቃቱን ተቀላቀለች። ዋሽንግተን በፎርዶ የሚገኘውን ጨምሮ ሦስት የኢራንን የኒውክሌር ማዕከላት ናቸው ያላቻቸውን አጠቃች።

ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቀዝቃዘው ጦርነት ወቅት የኒውክሌር ጦርነት ሊያስከትል ይችላል ተብሎ የተሰጋበትን የኩባ የሚሳዔል ቀውስን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በዋይት ሐውስ መግለጫ ሲሰጡ

ለመሆኑ እስራኤልስ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ሆናለች?

እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗን በይፋ አረጋግጣ አታውቅም። ነገር ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ እንደያዘች ይታመናል።

እአአ በ1986 እስራኤላዊው የኒውክሌር ባለሙያ መርዶኻይ ቫኑኑ እስራኤል ቀደም ሲል ከሚታሰበው ብዙ እና እጅግ የተራቀቀ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራም እንዳላት ለእንግሊዙ ሰንዴይ ታይምስ ጋዜጣ መረጃውን አሾልኮ ሰጠ።

በዚህ ምክንያትም በእስራኤል ሰላዮች ከአውሮፓ ታፍኖ ወደ እስራኤል ከተወሰደ በኋላ ለ18 ዓመታት ታስሮ በ2004 ተፈትቷል።

ስቶክሆልም ኢንተርናሽና ፒስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት (ኤስአይፒአርአይ) እንደተባለው የጥናት ተቋም ከሆነ እስራኤል የጦር መሳሪያዎቿን እያዘመነች ነው።

እስራኤል እአአ በ2024 "የኒውክሌር አቅም ካላቸው ባለስቲክ ሚሳዔሎች ጋር ሊዛመድ የሚችል የሚሳኤል ሥርዓት" ሙከራ አድርጋለች። በተጨማሪም ዲሞና በሚባለው ስፍራ ያላትን የፕሉቶኒየም ማምረቻ ቴክኖሎጂዋን እያዘመነች ይመስላል ሲል ኤስአይፒአርአይ ዘግቧል።

እስራኤል ኒውክሌር እንዳላት በስፋት የሚታመን ሲሆን፣ በቀጣናው ያሉ ተቀናቃኞቿ አውዳሚው የጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳይሆኑ ለመከላከል በተደጋጋሚ ወታደራዊ እርምጃዎችን ወስዳለች።

በቅርቡ ኢራን ላይ ከፈጸመችው ጥቃት በተጨማሪም እአአ በ1981 በኢራቅ የሚገኘውን የኒውክሌር ጣቢያ እና በሶሪያ ደግሞ የኒውክሌር ጣቢያ እንደሆነ የሚጠረጠረውን ቦታ በ2007 በቦምብ ደብድባለች።

ሞርዴኻይ ቫኑኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤላዊው የኒውክሌር ቴክኒሻን ሞርዴኻይ ቫኑኑ እጅግ ምሥጢራዊ የነበረውን የእስራኤልን የኒውክሌር ፕሮግራም ካጋለጠ በኋላ ለ18 ዓመታት ታስረወል

የትኞቹ አገራት የኒውክሌር መርሃ ግብራቸውን ለማቆም ወሰኑ?

እንደብራዚል፣ ስዊድን እና ስዊትዘርላንድ ያሉ አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን ሥራ ከጀመሩት በኋላ ፕሮግራሞቻቸውን በፈቃደኝነት ወይም በሌሎች ጫና ምክንያት አቋርጠዋል።

ደቡብ አፍሪካ ደግሞ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን በተሳካ ሁኔታ ከገነባች በኋላ መሳሪያውን በማውደም የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ያቆመች ብቸኛዋ አገር ነች።

"ይህ በኒውክሌር ዘመን ውስጥ እንደ አንድ ጥሩ ጉልህ ምልክት ተደርጎ ይታያል። አገሪቱ የራሷን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የገነባች እና በኋላም ለማቆም የወሰነች አገር ሆናለች" ብለዋል ፉተር።

የአፓርታይድ አገዛዝ ማብቃት፣ የአካባቢያዊ ግጭቶች መቀነስ እና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ለውጦችን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ለውሳኔው አስተዋጽኦ አድርገዋል።

እአአ በ1991 ከሶቪዬት ኅብረት መፈራረስ በኋላ፣ ነፃ የወጡ ዩክሬን፣ ቤላሩስ እና ካዛኪስታን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመውረስ ቢችሉም በኋላ ላይ አስረክበዋል።

እአአ በ1994 በተደረሰው የቡዳፔስት ውል መሠረት ዩክሬን ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ከሩሲያ የደኅንነት ዋስትና ለማግኘት በሚል የጦር መሳሪያውን አስረክባለች።

ነገር ግን ከአስር ዓመታት በላይ በሩሲያ ወረራ ተፈጽሞባት ጦርነት ውስጥ የገባችው ዩክሬን መሳሪያዋን በማስረከቧ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ስንት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች አሉ?

መንግሥታት ስለኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቻቸው ሙሉ ዝርዝር መረጃ ስለማይሰጡ፣ እያንዳንዱ አገር ምን ያህል መሳሪያ እንዳለው በትክክል ማወቅ አስቸጋሪ ነው።

ነገር ግን እንደ ኤስአይፒአርአይ ከሆነ፣ የመሳሪያው ባለቤቶች በጥር ወር 2025 በድምሩ 12 ሺህ 241 የኒውክሌር አረር አላቸው። ሩሲያ እና አሜሪካ 90 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት ናቸው።

ምንም እንኳን ያረጁ ማሳሪያዎችን በማስወገድ አዳዲሶችን ከመገንባት አንጻር ብልጫ ቢኖረውም ይህ አካሄድ ግን "በሚቀጥሉት ዓመታት" ሊቀለበስ ይችላል ሲል ተቋሙ አስታውቋል።

ኪም ጆንግ ኢል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪም ጆንግ ኢል መሪ በነበሩበት በ2006 (እአአ) ሰሜን ኮሪያ የተሳካ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ አደረገች

ሌሎች አገራትስ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መሥራት ይችሉ ይሆን?

በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ የሚደረገው ጫና ሌሎች አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመሥራት በሚኖራቸው ዕቅድ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች።

በሰኔ ወር እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብርን "በአስር ዓመታት" ወደ ኋላ መመለሱን አስታውቀዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን የአሜሪካ ጥቃቶች የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር እስከ ሁለት ዓመት ወደ ኋላ መልሶታል ብሏል።

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ከሆነች ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በተለይም ሳዑዲ አረቢያ ለማልማት ልትነሳሳ ትችላለች ሲሉ ፉተር ተናግረዋል።

"እኔ እንደማስበው ከሆነ ሳዑዲ አረቢያ በአሁኑ ጊዜ የኒውክሌር ባለቤት እንደማትፈልግ ግልጽ ነው። ነገር ግን ኒውክሌር የታጠቀች ኢራን ከተፈጠረች ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ይለውጠዋል።"

ኢራን ከስምነቱ መውጣቷ "ከፍተኛ ስጋት" አለው ይላሉ ዶ/ር ሉዊስ። ይህ ደግሞ ሌሎች አገራትም የመውጣት ዕድላቸውን ይጨምራል። ይህ ለስምምነቱ ሞት እንኳን ባይሆን ከፍተኛ "ጉዳት" ይሆናል።

ዶ/ር ሉዊስ እንደሚሉት፣ ሌሎች አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመሥራት ቢወስኑ እንኳን ብዙ ማለፍ ያለባቸው ተግዳሮቶች አሉባቸው። በተለይም የበለፀገ ዩራኒየም ወይም ለጦር መሳሪያ ደረጃ የበቃ ፕሉቶኒየም ያስፈልጋቸው። ሁለቱም ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ናቸው።

በፋይናንስ ረገድም ያለውን ተጽዕኖ ያነሳሉ።

"በተለይም በምሥጢር ከተሠራ ውድ እና ዓመታትን የሚጠይቅ ነው። ይህ ግን ከበለጸጉት አገራት ባሻገር ያሉ መሳሪያውን ከመገንባት አላስቆመም። እንደ ሰሜን ኮሪያ እና ፓኪስታን ያሉ አገራት አሳክተውታል።"