"በጡቴ በጣም እሸማቀቅ ነበር" - ትልቅ ጡት ጤናን ይጎዳል?

ትልቅ ጡት ያላት ሴት

የፎቶው ባለመብት, BBC/Getty Images

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

"ስራመድ ጀርባዬ ይጎብጥ ነበር። ትልቅ ጡት እንዳለኝ እንዳይታወቅ ከትከሻዬ ጎበጥ ብዬ እሄዳለሁ። ትልቁ ጡቴ በጣም ያሳፍረኝ ነበር" ትላለች ራቄል።

አርጀንቲናዊቷ ራቄል የጡቷን መጠን ለመቀነስ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።

አሁን 52 ዓመቷ ነው። ቀዶ ሕክምናው "ቀድሞ ያልነበረኝን ነጻነት ሰጥቶኛል" ትላለች።

በአብዛኛው የዓለም ክፍል ትልቅ ጡት እንደ ውበት ይቆጠራል። ነገር ግን የሴቶች ጤና እና አኗኗር ላይ ጫና ያሳድራል።

ከትልቅ ጡት ጋር በተያያዘ ከሚጠቀሱ እክሎች ውስጥ ከፍተኛ የጀርባ ሕመም፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት አቋም መዛባት፣ የአካል መደንዘዝ፣ እንቅልፍ ማጣት እና የአእምሮ ጤና ቀውስ ይገኙበታል።

ለውበት የሚደረግ ቀዶ ሕክምናን የሚከታተለው ዓለም አቀፍ ማኅበር እንደሚለው፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ብቻ 652 ሺህ 676 የጡት ቅነሳ ቀዶ ሕክምናዎች ተከናውነዋል።

ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና ቁጥር የተመዘገበው በብራዚል ሲሆን 115 ሺህ 647 ቀዶ ሕክምና ተካሂዷል።በቀጣይም በአሜሪካ 67 ሺህ 478፣ በፈረንሳይ 38 ሺህ780፣ በጀርመን 32 ሺህ 068፣ በቱርክ 25 ሺህ 334 እና በሕንድ 22 ሺህ 400 በዝርዝሩ ተካተዋል።

አርጀንቲናዊቷ ራቄል የጡቷን መጠን ለመቀነስ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።

የፎቶው ባለመብት, Raquel

የምስሉ መግለጫ, አርጀንቲናዊቷ ራቄል የጡቷን መጠን ለመቀነስ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።

ራቄል በትልቅ ጡቷ ምክንያት ከታዳጊነቷ ጀምሮ በጀርባ ሕመም ትሰቃይ እንደነበር ትናገራለች።

አርጀንቲና ውስጥ ትልቅ ጡት እንደ ውበት መገለጫ ይቆጠራል።

"ብዙ ሴቶች ዕድለኛ ነሽ ይሉኝ ነበር። ዕድለኛ አልነበርኩም። በጣም ነው የተሰቃየሁት። ወጣት ሳለሁም እናት ከሆንኩ በኋላም ተሰቃይቻለሁ" ትላለች።

ጡቷን ለመደበቅ ከትከሻዋ ጎብጣ ትራመድ ስለነበር አሁንም ድረስ ጀርባዋን ያማታል።

ራቄል ዮጋ፣ ፒላቲስ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትወዳለች። የጡቷ ትልቅ መሆን ግን ሰውነቷን እንዳሻት እንዳታንቀሳቅስ አግዷታል።

የእንግሊዝ የውበት ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኖራ ኑገንት እንደሚናገሩት፤ የጡት ቅነሳ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሴቶች እንደልባቸው ሰውነታቸውን ለማንቀሳቀስ የሚቸገሩ ናቸው።

ጡቷን ለመደበቅ ከትከሻዋ ጎብጣ ትራመድ ስለነበር አሁንም ድረስ ጀርባዋን ያማታል።

የፎቶው ባለመብት, Raquel

የምስሉ መግለጫ, ራቄል ጡቷን ለመደበቅ ከትከሻዋ ጎብጣ ትራመድ ስለነበር አሁንም ድረስ ጀርባዋን ያማታል።

"ትልቅ ጡት ይከብዳል። ስለዚህ ሰውነትን ወደፊት ይጎትታል። ጀርባ እና አንገት ላይ ሕመም የሚፈጠረውም ለዚህ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሠራም ምቾት ይነሳል። ጡትን መደገፍ የሚችል የጡት ማስያዣ ለማግኘትም ያስቸግራል" ሲሉ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

ራቄል ጡቷን ለመደገፍ ሁለት ወይም ሦስት የጡት ማስያዣ ማድረግ ያስፈልጋት ነበር። በጡቷ መጠን የተዘጋጀ የጡት ማስያዣ ለመግዛት የምታወጣው ወጪ ቀላል እንዳልሆነ ትናገራለች።

ዶ/ር ኖራ ኑገንት እንደሚናገሩት፤ የጡት ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው ሴቶች ከሰውነታቸው ውስጥ ከ500 ግራም እስከ 800 ግራም ያስወግዳሉ።

"ከአጠቃላይ የሰውነት ክብደት አንጻር ግዙፍ ባይሆንም እንኳን፤በአንድ የሰውነት ክፍል ሲከማች ትልቅ ነው" ይላሉ።

ራቄል ከአጠቃላይ ጡቷ 2.5 ኪሎ የሚመዝነውን አስወግዳለች።

"ከቀዶ ሕክምናው በኋላ እቃ ለማንሳት ሳጎነብስ የተሰማኝን ቅለት አልረሳውም። በጣም ነጻነት ተሰማኝ" ትላለች።

የባዮሜካኒክስ ባለሙያዋ ፕ/ር ጆአና ዋክፊልድ-ስከር ለስፖርተኞች ምቹ የሆነ የጡት ማስያዣ ለማዘጋጀት ጥናት ያደርጋሉ።

የፎቶው ባለመብት, UEFA/UEFA via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የባዮሜካኒክስ ባለሙያዋ ፕሮፌሰር ጆአና ዋክፊልድ-ስከር ለስፖርተኞች ምቹ የሆነ የጡት ማስያዣ ለማዘጋጀት ጥናት ያደርጋሉ።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የባዮሜካኒክስ ባለሙያዋ ፕ/ር ጆአና ዋክፊልድ-ስከር ጡታቸውን እያመማቸው ስለተቸገሩ ወደ ሕክምና ከሄዱ በኋላ ለጡታቸው ምቹ እና ተስማሚ የሆነ የጡት ማስያዣ እንዲያደርጉ ተመክረዋል።

"ጥሩ የጡት ማስያዣ ስፈልግ ያወቅኩት ስለ ጡት ማስያዣ ጥቅም እና እንዴት አገልግሎት እንደሚሰጠን እንደማናውቅ ነው" ይላሉ።

የጡት ማስያዣ ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ የውበት መገለጫነቱ አመዝኖ ይታያል።

"ያለው ጠቀሜታ አለመታወቁ በጣም የሚያሳዝን ነው" ሲሉ ፕ/ር ጆአና ይናገራሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፖርትስማውዝ የጡት ጤና ላይ ያተኮረ ማኅበር መስርተዋል።

ጡትን በተገቢው መንገድ የማይደግፍ ወይም የማይዝ የጡት ማስያዣ ያለውን አራት ዋና ዋና ጉዳቶች ለይተዋል።

አንደኛው ጉዳት ከቆዳ እስከ ሕዋሳት የሚደርስ ሕመም ነው። ምቹ ያልሆነ የጡት ማስያዣ አተነፋፈስንም ይጎዳል።

በልብ ምቶች መካከል ያለው ጊዜ ላይ ከሚያሳድረው ጫና ባሻገር አጠቃላይ የሰውነት እንቅስቃሴ ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል።

"ትልቅ ጡት ያላቸው ሴቶች ጡታቸው ከፍ እና ዝቅ ሲል አተነፋፈሳቸውን ያውከዋል። ትንፋሽ የሚወስዱበት መንገድ ላይ ከሚያሳድረው ጫና በተጨማሪ ሲራመዱም ሰውነታቸው ላይ ተጽዕኖ አለው" በማለት ያስረዳሉ።

ለዓመታት በተሠራ ጥናት መሠረት ጡት የሚንቀሳቀስበትን መንገድ ለማወቅ ችለዋል።

የጡት ሕመምን ለመቀነስ ቁልፍ የሆነው የሰውነት እንቅስቃሴን ፍጥነት መቀነስ እንጂ አጠቃላይ እንቅስቃሴን መቀነስ እንዳልሆነ ጥናታቸው ይጠቁማል።

የጥናት ቡድኑ የእንግሊዝ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድንን እንዲሁም ጎልፍ ተጫዋቾችን ያማክራል። ለስፖርተኞች ምቹ የሆነ የጡት ማስያዣ ለማዘጋጀትም ጥናት ያደርጋሉ።

"እንደ ኤፍኤ እና ወርልድ ራግቢ ያሉ የስፖርት ተቋማትን እናማክራለን። ሴት አትሌቶች ጤናማ ሕይወት እንዲኖራቸው ድጋፍ ማድረግ የተጀመረው ባለፉት አምስት ዓመታት ነው። ለውጥ ማየት መጀመራችን አበረታች ነው" ይላሉ የባዮሜካኒክስ ባለሙያዋ ፕ/ር ጆአና።

ራቄል የጡት መጠን ለመቀነስ ቀዶ ሕክምና በማድረጓ ብዙዎች እንደተቿት ትናገራለች።

"ቀዶ ሕክምናውን ያደረግኩት በሕመም ምክንያት ሳይሆን ለውበት ስል እንደሆነ ነው ሰዎች የሚገምቱት" ትላለች።

የጡት ቀዶ ሕክምና ስታደርግ አንዲት ሴት "የሆድ ቀዶ ሕክምናም አድርጊ" እንዳለቻት ታስታውሳለች።

ራቄል ምንም እንኳን ሰዎች ቢተቿትም ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ መወሰኗ አይጸጽታትም።

"አሁን በማረጥ ውስጥ እያለፍኩ እንደመሆኑ ትልቅ ጡት ቢኖረኝ ምን እንደማደርግ አላውቅም ነበር። ከሰውነቴ ጋር መታገል አልፈልግም" ትላለች።

የእንግሊዝ የውበት ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኖራ እንደሚናገሩት፤ የጡት ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉ ሴቶች መበራከት ለጤናቸው ቅድሚያ እየሰጡ መምጣታቸውን ያመለክታል።

"ቀዶ ሕክምናው ሰውነትን የማስተካከል ሳይሆን የጤና ነው" ሲሉ ገልጸውታል።