የአቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲ በአወዛጋቢ ቦታዎች ላይ የተሰጠው ውሳኔ ካልተስተካከለ በምርጫ እንደማይሳተፍ አስታወቀ

የስምረት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ
የምስሉ መግለጫ, የስምረት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአወዛጋቢ የምርጫ ክልሎች ላይ የሰጠው ውሳኔ የማይስተካከል ከሆነ በምርጫ እንደማይሳተፍ አስታወቀ።

በተመሳሳይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር እና ግጭትን የሚቀሰቅስ ነው በማለት በጽኑ ተቃውሞታል።

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ከሁለቱም ክልሎች ውጪ በሆነ ሁኔታ በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ተከትሎ ስምረት ፓርቲ የተቃውሞ ደብዳቤ ጽፏል።

በቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በአቶ ጌታቸው የሚመራው ስምረት ፓርቲ ተቃውሞውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳወቀበት ደብዳቤው ውሳኔውን "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነት" ሲል ተችቷል።

ፓርቲው በአቶ ጌታቸው በተፈረመው እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምርጫ ክልሎች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ዳግም እንዲታይ በጠየቀበት ደብዳቤ በአወዛጋቢ የምርጫ ክልሎች ላይ የተላለፈው ውሳኔ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚንድ፣ የተቋማትን ነጻነት የሚደፈጥጥ እና በደፈናው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነት" ነው ብሏል።

አክሎም ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ተቋሙ በሌለው ሕገ መንግሥታዊ ውክልና ላይ የተመሠረተ ነው በማለት "የፌደራል ሥርዓቱ በጠራራ ፀሐይ እየተገዘገዘ መሆኑን ያሳያል" ብሏል።

የወሰን ክርክር በሕጋዊ መንገድ መፍትሄ ሳያገኝ "ምርጫ በፌደራል መንግሥት ይፈጸም" ማለት የክልል አስተዳደርን "በጉልበት የመንጠቅ ሙከራ ነው" በማለት ቦርዱ ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ሳለ የፌደሬሽን ምክር ቤት "በፖለቲከ ፍላጎት ተገፋፍቶ በቦርዱ ሥራ ጣልቃ መግባት ነው" ሲል ወቅሷል።

ስረምት ፓርቲ ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫ ቦርድን "የፖለቲካ መጠቀሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የምርጫውን ተዓማኒነት አጠያያቂ" ያደርገዋል በማለት ስጋቱን ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እና የምርጫ ቦርድ ድርጊት "ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ነው" በማለት ውሳኔው "በሕግ ፊት ተቀባይነት የሌለው እና የማይጸና ነው" ብሏል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በውሳኔው ላይ ማስተካከያ የማያደርጉ ከሆነ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ "በምርጫ እና በሌሎች መሰል ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ እንደማይሳተፍ" በደብዳቤው አሳውቋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ "በምርጫ ቦርድ የተጠቀሱት አምስቱ ወረዳዎች የትግራይ ታሪካዊ እና ሕገመንግሥታዊ ግዛቶች ናቸው" በማለት ለድርድር የሚቀርቡ እንዳልሆኑ በመግለጽ ተቃውሞውን አሰምቷል።

የምርጫ ቦርድ መግለጫ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጻረር እና "በወረራ ለተያዙት ቦታዎች ሕጋዊ ሽፋን የሚሰጥ ነው" በማለት የተፈናቀሉ ሰዎች በስቃይ ላይ እያሉ ምርጫ ለማካሄድ መሞከር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚቃረን ነው ብሏል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወጣው መግለጫን "ፀረ ሕገመንግሥት፣ ፀረ ፕሪቶሪያ ስምምነት ነው" በማለት ግጭትን የሚቀሰቅስ መሆኑን በመግለጽ እንደሚቃወመው አስተዳደሩ አሳውቋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩ አምስት የምርጫ ክልሎች ጉዳይ እስኪፈታ ለብቻቸው ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።

እነዚህ በትግራይ እና በአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ የተነሳባቸው እና ከሁለቱም ክልሎች ውጭ ሆነው በራሳቸው ምርጫ እንዲደረግባቸው የተወሰኑት የሁመራ፣ የአዲረመፅ፣ የኮረም አፍላ፣ የጠለምት እና የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች ናቸው።

በእነዚህ አምስት የምርጫ ክልሎች የሚገኙ መራጮች ድምጻቸውን የሚሰጡት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎች ሲሆን፣ የክልል ምክር ቤት ምርጫው በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ መንግሥት ውሳኔ ከተፈታ በኋላ እንደሚካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ ነው ስምረት ፓርቲ የተቃውሞ ደብዳቤ የጻፈው።