ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ ለወሲባዊ ብዝበዛ እንደሚዳረጉ የተመድ ሪፖርት አሳየ

የፎቶው ባለመብት, UNICEF
ወደ አውሮፓ አገራት ለመድረስ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የበርካታ አገራት ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ ለመደፈር፣ ለግዳጅ የወሲብ ንግድ፣ ለግዳጅ ሠራተኝነት እና ስቅይት እንደሚዳረጉ የተባበሩት መንግሥታት አዲስ ሪፖርት አሳየ።
ስደተኞቹ ላይ የሚደርሰው "ርህራሄ የለሽ እና ስልታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት" የሚፈጸመው፤ "ብዙውን ጊዜ ከሊቢያ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት" ባላቸው የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረቦች አማካኝነት እንደሆነም ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት እና የሊቢያ የድጋፍ ተልዕኮ ትናንት የካቲት 10/2018 ዓ. ም. በጋራ ያወጡት ሪፖርት፤ ሊቢያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን ስቃይ ዘርዝሯል።
ከጥር 2016 ዓ. ም. እስከ ታኅሣሥ 2018 ዓ. ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው ሪፖርት ሲዘጋጅ ከ16 የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ደቡብ እስያ አገራት የተወጣጡ 100 ገደማ ፍልሰተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል።
ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ስደተኞች መካከል የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ዜጎች ይገኙበታል።
ወደ አውሮፓ አገራት መሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች ዋነኛ መተላለፊያ በሆነችው ሊቢያ ውስጥ "በፍልሰተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ ስልታዊ እንዲሁም ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች ያለ ምንም ተጠያቂነት" እንደቀጠለ ሪፖርቱ ያስረዳል።
ሪፖርቱ እንደሚገልጸው፤ ሊቢያ የሚደርሱ ፍልሰተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች፤ ብዙውን ጊዜ መሣሪያ ተደቅኖባቸው "በኃይል ይያዛሉ፣ ይታፈናሉ እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው እንዲለዩ" ይደረጋሉ። ይህ ከሆነም በኋላ ወደ "ይፋዊ፣ ይፋዊ ያልሆኑ እና ሕገ ወጥ የእስር ተቋማት" እንደሚወሰዱ ዘርዝሯል።
በማጎሪያ ማዕከላቱ ውስጥ "ለረዥም ጊዜ ይታሰራሉ፤ በሚደረስባቸው ስቅይት እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ምክንያትም ለመፈታት ገንዘብ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ" ይላል።
"ብዙውን ጊዜ ከመንግሥት አካላት ጋር ግንኙነት ያላቸው" ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ስደተኞቹ የሚገኙበትን "ተጋላጭ ሁኔታ በመጥቀም ለማትረፍ" እንደሚንቀሳቀሱም ሪፖርቱ ያስረዳል።
የሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች፤ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ስደተኞቹን "ለግዳጅ የወሲብ ንግድ፣ የግዳጅ ሠራተኝነት እና የቤት ውስጥ ባርነት" እንደሚዳርጓቸው ተጠቅሰዋል።
ሌሎች ፆታን መሠረት ያደረጉ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ ስቅይት እንዲሁም ብዝበዛ እንደሚፈጸምባቸውም ሪፖርቱ ያመለክታል።
ከሦስት ዓመት እስር በኋላ 'አል ሹዌሪፍ' ከተባለው የማጎሪያ ካምፕ ነጻ መውጣቱን የተናገረ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ ማቆያው ውስጥ ሕጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙ መግለጹ ተጠቅሷል።
በሪፖርቱ ዝግጅት ወቅት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ዕድሜያቸው ከ17 እስከ 43 የሆኑ 45 ሴቶችን እና ሕጻናት ሴቶች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል።
ሁሉም ሴቶች በሥራ ቦታቸው ወይም በሰዎች ዝውውር ማዕከላት ውስጥ "እንደ መደፈር፣ የመድፈር ሙከራን እና ወሲባዊ ብዝበዛ ያሉ ፆታዊ ጥቃቶች" እንደተፈጸሙባቸው መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, IOM
በታኅሣሥ 2016 ዓ. ም. 'አል-ኩፍራ' በተባለ ሥፍራ በሚገኝ የአዘዋዋሪዎች ማዕከል ውስጥ የነበረች አንዲት ወጣት ኢትዮጵያዊት፤ "በበርካታ ጥቃት ፈጻሚዎች በተደጋጋሚ በመደፈሯ እርግዝና፤ ኋላም የፅንስ መቋረጥ" እንዳጋጠማት ተገልጿል።
የደረሰባት ጥቃት ቀዶ ሕክምና የሚሻ እንደነበረም ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል። ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው፤ ከአራት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያዊቷ ስትታከም ከነበረበት ክሊኒክ በፖሊስ ተይዛ በቂ ምግብ ወይም ሕክምና ወደሌለበት የእስር ማዕከል ተወስዳለች።
ሌላ የ19 ዓመት ወጣት ኢትዮጵያዊት ደግሞ "ድብደባን፣ ረሃብን እና መድፈርን ጨምሮ አስከፊ ግፎች" ተፈጽመውባት ለእርግዝና ከተዳረገች በኋላ "የሕክምና እርዳታ ተከልክላ" ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ሕይወቷ እንዳለፈ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
ሪፖርቱ፤ ባለፈው ጥር አንዲት ኢትዮጵያዊት "ስትሰቃይ እና ፆታዊ ጥቃት ሲፈጸምባት" የሚያሳይ ቪዲዮ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቅቆ እንደነበረም ይጠቅሳል። በቪዲዮው ላይ ቤተሰቦቿ ማስፈቻ ገንዘብ እንዲከፍሉላት ስትማጸን የምትታየው ኢትዮጵያዊት፤ 6,000 ዶላር ተከፍሎ እንደተለቀቀች ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ተርክ፤ "የትኞቹም ቃላት" በስደተኞቹ ላይ የሚፈጸመውን "ማለቂያ የሌለው" ግፍ ለመግለጽ እንደማይበቁ ተናግረዋል።
የሊቢያ የድጋፍ ተልዕኮ ተወካይ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሃና ቴትህ በበኩላቸው፤ ሊቢያ ውስጥ የሚገኙት የማጎሪያ ማዕከላት "የከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈልፈያ ሆነዋል" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ሪፖርቱ፤ የሊቢያ ባለሥልጣናት ኢ-መደበኛ እና በመደበኛ የእስር ማዕከላት ውስጥ በዘፈቀደ የታሰሩ ሰዎችን በሙሉ በአስቸኳይ እንዲለቅቅ ጠይቋል። የሊቢያ የፀጥታ አካላት ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ ሰዎች ላይ የሚፈጽሙትን "አደገኛ የመጥለፍ ድርጊት" እንዲያቆሙም አሳስቧል።
ሁሉንም የዘመናዊ ባርነት ዓይነቶች፣ የግዳጅ ሠራተኝነት እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቆም እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች ተጠያቂነትን ማስፈን አስፈላጊ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥቷል።















