በልጅነቱ ሕይወቱን ካተረፈለት ዶክተር ጋር አየር ማረፊያ ውስጥ የተገናኘው ኢትዮጵያዊ ሐኪም ታሪክ

መስፍን ዶላር እና ጂም ካውተን
የምስሉ መግለጫ, መስፍን እና ጂም
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

መስፍን ዶላር የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ናቸው።

ተወልደው ያደጉት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ነው። 11 ዓመት ሲሞላቸው ነበር በጠና የታመሙት።

የአካባቢው ዶክተሮች ሊረዷቸው አልቻሉም። ለተሻለ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ተወሰዱ።

የበጎ አድራጎት ድርጅት ወደ አሜሪካ ለሕክምና እንዲሄዱ አመቻቸላቸው።

በ15 ዓመታቸው ወደ አትላንታ ግዛት አቀኑ። ዶ/ር ጂም ካውተን በተባሉ አሜሪካዊ ሐኪም ሁለት ሕይወታቸውን ያዳኑ የልብ ቀዶ ሕክምናዎች ተደረገላቸው።

"የምሞት መስሎኝ ነር። ዶ/ር ጂም ካውተን ሕይወቴን ማዳን ቻለ" ይላሉ መስፍን።

የመጀመሪያው ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ውስብስብ የጤና እክል ስለገጠማቸው ሁለተኛ ቀዶ ሕክምና እዚያው አሜሪካ ውስጥ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር።

"እንደምሞት አስብ ነበር። ግን ዶ/ር ሪክ ሆትስ ያንን መቀበል አልፈለገም። በድጋሚ በተደረገልኝ ቀዶ ሕክምና ጂም ሕይወቴን ለሁለተኛ ጊዜ አዳነው" ሲሉ ያስታውሳሉ።

ከቢቢሲ 'ሀፒ ፖድ' ፖድካስት ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ጂም የሰዎችን ሕይወት ማዳን የነፍስ ጥሪያቸው እንደሆነ ያምናሉ።

"ወደ ዓለም የመጣሁት የልብ ቀዶ ሕክምና እያደረግኩ የሰዎችን ነፍስ ለማዳን እንደሆነ የተገነዘብኩት በሙያ ሕይወቴ እኩሌታ ላይ ነው" ሲሉ ይገልጹታል።

ከሁለተኛ ቀዶ ሕክምና በኋላ ጂም ለመስፍን ልብ ሜካኒካል ቫልቭ ገጥመዋል። ይህም አንዳንዴ ድምጽ ያወጣ ነበር።

"ልጁ ይሄንን ድምጽ ይሰማዋል። እንዴት ነው የማስረዳው? ምን ላድርግ?" ብለው ማሰብ ጀመሩ።

እናም ለታዳጊው መስፍን ሰዓት ሰጧቸው። "ልጆች ከልቡ ቫለቭ ስለሚወጣው ድምጽ ሲጠይቁት የሰዓቱ ነው እንዲል ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

መስፍን ከሕክምናቸው በኋላ እዚያው አሜሪካ ቀሩ። ዕድሜያቸው ሲጨምር፤ በቀዶ ሕክምና ወቅት የታካሚዎችን እስትንፋስ የሚከታተለው መሣሪያ ባለሙያ (cardiac perfusionist) ለመሆን ወሰኑ።

ለውሳኔያቸው መነሻ የሆናቸው በታዳጊነታቸው የተደረገላቸው እና ሕይወታቸውን የታደገው የልብ ቀዶ ሕክምና እንደሆነ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የልብ ቀዶ ሕክምናው ሕይወታቸውን ካተረፈው 25 ዓመታት ተቆጥረዋል።

መስፍን አሁን ሕይወታቸውን ካዳኑት የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ጂም ካውተን ጋር አብረው ሆነው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በቅተዋል።

"ቀዶ ሕክምና የሚደረግበት አልጋ ላይ ሆኜ አውቃለሁ። ታማሚ መሆን ምን ማለት እንደሆነ አውቃለሁ። ፍርሃቱን አውቀዋለሁ" ይላሉ።

በሙያቸው ታማሚዎችን መርዳት እንደሚችሉ በማመን ነው ሕክምናን የተቀላቀሉት።

የልብ ቀዶ ሕክምና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የበጎ አድራጎት ድርጅት ታዳጊ ሳሉ ወደ አሜሪካ ሄደው እንዲታከሙ ዕድሉን አመቻችቶላቸዋል።

እሳቸውም የሕይወትን ዑደት ተከትለው 'ኸርት አታክ ኢትዮጵያ' በተባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ሆነዋል።

መስፍን ወደ 'ኸርት አታክ ኢትዮጵያ' ሲሄዱ ጂም እዚያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ አላወቁም ነበር።

"ስንተያይ ሁለታችንም ተገረምን። የሕይወት ዑደት እንዴት አስደናቂ እንደሆነ በዚያ ቅጽበት አስተዋልን። ምንም ጊዜ ሳይወስድብን እንደቀደመው ጊዜ ሆንን" ይላሉ መስፍን።

ጂም እስከ ዛሬ ድረስ መስፍንን ያስታውሳሉ። 25 ዓመታት ቢያልፉም ታካሚያቸውን አልረሱም።

"በጣም ቆራጥ እና ደስ የሚል ልጅ ነበር። እሱን ለመውደድ ቀላል ነው" ሲሉ ታዳጊውን መስፍን ያስታውሳሉ።

መስፍን እና ጂም አንድ የሚያደርጋቸው የሕይወት መስመራቸው ነው። ሁለቱም የሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ይፈልጋሉ።

"ድሮ ካቆምንበት ቦታ ነው አሁን የጀመርነው። ድሮ ታካሚው ነበርኩ። አሁን ግን አብረን ነፍስ እያተፍን ነው" ይላሉ።

ጂም እና መስፍን ከ400 በላይ ሰዎችን ከሞት አድነዋል። የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችንም ያሠለጥናሉ።

ጂም በመስፍን ከፍተኛ ኩራት ይሰማቸዋል።

"መስፍንን አደንቀዋለሁ። እረፍት ከማይሰጠው ሥራው እና ሕይወቱ ጊዜ ቀንሶ ወደ አገር ቤት በመመለስ ውለታውን እየከፈለ ነው። ባደረገው ነገር ሁሉ በጣም ነው የምኮራበት" ይላሉ።

የመስፍን ሕልም ከጂም ጋር መሥራት ነበር።

"ሕልሜ እውን ሆኗል። በአንድ ወቅት ለእኔ ቀዶ ሕክምና ካደረገልኝ ሐኪም ጋር አብሬ እየሠራሁ ነው። አብረን ሆነን ሌሎችን መርዳት መቻላችን ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነው" ሲሉ ስሜታቸውን ይገልጻሉ።

አሁን ግንኙነታቸው የታካሚ እና የሐኪም አይደለም።

"አራተኛ አባቴ ይለኛል። በዚህም ክብር ይሰማኛል" ሲሉ ጂም ይናገራሉ።

መስፍን ደግሞ "አብረን መሥራት በመቻላችን ዕድለኛ ነን። ስሜቴ ከምስጋናም በላይ ነው" ይላሉ።

መስፍን እና ጂም በጋራ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ወቅት በጋራ የሰዎችን ሕይወት በማዳን ጉዞ ውስጥ መሆናቸው የሚፈጥርላቸውን ደስታ ገልጸዋል።

መስፍን "ሕይወቴ የዳነው በእነሱ ነው። የሚሰማኝ ከምስጋናም በላይ ነው። የልጆች አባት የሆንኩት እና ሥራ የምሠራውም በሐኪሞቹ አማካኝነት ነው" ብለዋል።

ይሄንን ሙገሳ የሰሙት ጂምም መስፍን እንደሚያኮሯቸው ይናገራሉ።

ጂም አሁን ጡረታ ቢወጡም ለ36 ዓመታት የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል።

"ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የልብ ቀዶ ሕክምና አድርጌያለሁ" ይላሉ። ሰዎችን የማዳን የነፍስ ጥሪያቸውን እንዳሳኩ ያምናሉ።

"መስፍን ሁለት ስኬታማ ቀዶ ሕክምናዎች ተደርገውለታል። በዚህም ደስተኛ ነኝ" ይላሉ።

ሁለቱ የሕክምና ባለሙያዎች አራት ጊዜ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥተዋል።

ጂም በመጀመሪያው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጉዞ መስፍንን አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ሲመለከቱ ለማመን ተቸግረው ነበር።

ከ25 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ተገናኝተው ሕይወት የማዳን ተልዕኳቸውን በጋራ እየተወጡ እንደሆነ ጂም እና መስፍን ይናገራሉ።

መስፍን እና ጂም የሰዎችን ሕይወት አብረው ማዳናቸው ልዩ ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ።

"መስፍን መኖሩ በጣም ልዩ ያደርገዋል። በጣም ውድ ጓደኛዬ ነው" ሲሉ ጂም ይገልጹታል።

መስፍንም "ሕልሜ ዕውን ሆኗል" በማለት ይናገራሉ።

"ለአንድ ሰው ልጅ ተስፋ መስጠት ትልቅ ዋጋ አለው። እኔም በአንድ ወቅት እንደነሱ ዓይነት የልብ ቀዶ ሕክምና እንደተደረገልኝ ለሕሙማን እነግራቸዋል። ያ ደግሞ ሰላም ይሰጣቸዋል፤ ተስፋም ይሆናቸዋል" ሲሉ ይገልጻሉ።