በኢትዮጵያ የተካሄደው እና አስር ባለሙያዎች የተሳተፉበት ተደራራቢ የልብ ቀዶ ሕክምና

ቀዶ ህክምናው ሲካሄድ

የፎቶው ባለመብት, DR. FEKADE

የምስሉ መግለጫ, ቀዶ ህክምናው ሲካሄድ

የልብ ቀዶ ህክምና ከፍ ያለ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ህክምና ሲሆን በተለይ ተደራራቢ ችግር ሲኖር ደግሞ ሥራው በእጅጉ የተወሳሰበ ስለሚሆን ከፍ ያለ ልምድና ቴክኖሎጂ ባላቸው አገራት ውስጥ እንዲካሄድ ይመከራል።

ሰኞ እሁድ 18/2013 ዓ.ም ከዚህ በፊት 'ኢትዮጵያ ውስጥ አልተደረገም' የተባለ እና ስድስት ሰዓታትን የፈጀ የልብ ቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።

አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ኤሎዚየር የልብ ህክምና ማዕከል ውስጥ በአንድ ጊዜ ሁለት የቀዶ ህክምናው የተደረገላቸው ግለሰብ የ55 ዓመት ጎልማሳ ናቸው።

በህመምተኛው ግለሰብ ልብ ላይ በአንድ ጊዜ የተሰራው ሁለት ቀዶ ህክምና ሲሆን፣ አንደኛው የልብ የደም ቧንቧዎች በሚዘጉበት ጊዜ የደም ቧንቧን ከሌላ የሰውነት ክፍል በመውሰድ የተዘጋው ቦታ ላይ በመተካት የተከናወነ የልብ የደም ስር ነቅሎ መትከል (ሲኤቢጂ) ነው።

ሌላኛው ደግሞ 'ኦርቲክ ቫልቭ' ወይም ደግሞ አንደኛው የግራ የልብ ክፍል በር ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ደም ከቀኝ የልብ ክፍል ወደ አኦርታ (Aorta) መውጣት ሲቸገር የልብ በር ቀዶ ህክምና (ቫልቭ) የሚባለው ነው።

በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተከናወነው ይህንን ስኬታማ የቀዶ ህክምና ካከናወኑት ሐኪሞች መካከል አንዱና በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል ውስጥ የሚሰሩት ዶ/ር ፈቃደ አግዋር ለቢቢሲ እንደተናገሩት "እነዚህን ሁለት ቀዶ ህክምናዎች እኚህ ግለሰብ ላይ በአንድ ጊዜ ተደርገዋል። ይህ በቀዶ ሕክምና ሙያ በጣም ትልቅ የሚባል ስኬት ነው። ቀዶ ህክምናው በአገራችን ባለሙያዎች ሲሰራ የመጀመሪያው ነው።"

ለስድስት ሰዓታት የተካሄደውን የቀዶ ህክምና ሂደት የመሩት ዶ/ር ፈቃደ እንደሚሉት አሁን በአንድ ህመምተኛ ላይ በአንድ ጊዜ የተከናወነው ቀዶ ህክምና በተናጠል ከሚሰራው ውስብስብና አስቸጋሪ ነው።

በዚህ ሂደት ሁለቱን ቀዶ ህክምናዎች በአንድ ልብ ላይ ሲሰራ የልብንና የሳንባን ሥራ ተክቶ የሚሰራው ማሽን አገልግሎቱን አብቅቶ ወደተፈጥሯዊው ሂደት ሲመለስ እንዴት ይሆናል? የሚለው ዋነኛው አሳሳቢ ጉዳይ ሲሆን ባለሙያዎቹም አስፈላጊውን ጥንቃቄና ክትትል አድርገዋል።

ይህ ተደራራቢ ቀዶ ህክምና አደጋን የሚያስከትል በመሆኑ እያንዳንዱን ለውጥ ባለሙያዎቹ በቅርበት ሲከታተሉት ነበር።

"ከኦፕራሲዮን ስንወጣ ሐዘን ይዘን ልንወጣ እንችላለን። የማይነሳ ልብ ሊሆን ይችላል። በ24 ሰዓት ውስጥ ማንኛውም አደገኛ ነገር ሊከሰት ይችላል። ይህንን ሁሉ ነገር ከአዕምሯችን ጓዳ ውስጥ አድርገን ነበር የሰራው። ነገር ግን ሁሉም ነገሮች አልተከሰቱም" ብለዋል ዶ/ር ፈቃደ።

ከመነሻው ቀዶ ህክምናው እስከ ሰባት ሰዓት የሚደርስ ጊዜን ሊወስድ ይችላል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም በስድስት ሰዓታት ውስጥ በስኬት መጠናቀቁ ተነግሯል።

ይህ እጅግ ከፍ ያለ ጥንቃቄን የሚፈልገው ተደራራቢ የልብ ቀዶ ህክምና ሂደት ሲከናወን ውጥረት የተሞላበት ቢሆንም ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

"ምንም አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አልተፈጠረም ነበር። ጮክ ብለን እንኳን የተነጋገርንበት ጊዜ እንኳ አልነበረም። በስድስት ሰዓቱ ውስጥ በተቻለን አቅም ተረጋገግተን የአስቴር ዘፈንን እየሰማን ነበር የሰራነው" ብለዋል ዶ/ር ፈቃደ።

ዶ/ር ፈቃደ አግዋር

የፎቶው ባለመብት, DR. FEKADE

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ፈቃደ አግዋር

የልብ ቀዶ ህክምና በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ህክምና መከናወን ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት ብቻ ነው የተቆጠሩት። ከዚያ ውጪ ልብ ቀዶ ህክምና ይከናወን የነበረው ከውጪ አገር በሚመጡ ባለሙያዎች በተመላላሽነት፣ ለአጭር ጊዜ ነበር።

የልብ ቀዶ ህክምና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሲከናወንባቸው በቆዩት አራት ዓመታት ውስጥ፣ አሁን በአንድ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ በአንድ የልብ ታማሚ ላይ የተደረገው ቀዶ ህክምና ተደርጎ አይታወቅም።

ነገር ግን ሁለቱንም ቀዶ ህክምናዎች በተናጠል ሲከናወኑ መቆየታቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ፈቃደ፣ ሁለቱንም አንድ ላይ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ልምዱ ስላልነበረና ውስብስብ በመሆኑ ሳይደረግ መቆየቱን ይናገራሉ።

ስለዚህም እንዲህ አይነቱ ተደራራቢ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎችም የነበራቸው አማራጭ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ወደ ውጪ አገር ሂዶ መታከም ነበር። ለዚህም ከ50 ሺህ ዶላር በላይ መክፈልን ይጠይቃል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ተደራራቢ የልብ ችግር ሲያጋጥማቸው ህክምና ለማግኘት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ወደ ሕንድ፣ ቱርክና ታይላንድ ይሄዳሉ።

ዶ/ር ፈቃደ እንደሚሉት በስኬት የተከናወነው ቀዶ ህክምና ለዘርፉ ታላቅ ዕመርታ ነው "የመጀመሪያው የቀዶ ህክምና ፈተናዎች ይኖሩታል። ነገር ግን አንድ ጊዜ በስኬት ከተከናወነ ለቀጣይ ህክምና መንገዱ ይከፈታል" በማለት ሰዎች ህክምናውን ለማግኘት ወደ ውጭ አገር መሄድ አይጠበቅባቸውም ብለዋል።

የልብ ህመም በኢትዮጵያ

ከአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ ተላላፊ ካልሆኑ የጤና ዕክሎች መካከል የሚጠቀሱት የልብ ህመሞች እየተስፋፉ መሆናቸው ይነገራል። በተለይ ከፍ ያለ ሙያ፣ ጥንቃቄና ወጪን የሚጠይቁት የልብ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በኢትዮጵያም የተለያዩ የልብ ችግሮች የሚያጋጥማቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ፈቃደ፣ በስፋት የሚያጋጥመው ዋነኛው የልብ ቫልቭ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ።

የልብ በሮች መጥበብ ወይም ወደ ኋላ ማፍሰስ ደግሞ ሌላኛው እክል ነው።

በተጨማሪም "የልብ የደም ቧንቧዎች መደፈን በአሁኑ ወቅት እየበዛ የመጣ ነው" ሲሉ ያክላሉ። "ከደም ግፊት እና ከስኳር ህመም ጋር ተያይዞ የሚመጣ የልብ የደም ስሮች መዘጋት ወይም ደግሞ 'ኮሮናሪ አርተሪ ዲዚዝ' የምንለው በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ይገኛል።"

የተሳካው ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ታካሚ ላይ ሁለት ተደራራቢ የልብ ችግሮች በአንድ ላይ በመከሰታቸው ችግሩን የተወሳሰበ በማድረግ ታማሚውን ለከፍተኛ ችግር እንዳጋለጣቸው ዶ/ር ፈቃደ ይናገራሉ።

በ55 ዓመቱ ጎልማሳ ላይ በተደራራቢነት ያጋጠሙት የልብ ችግሮች በተለያዩ ሰዎች ላይ በተናጠል መከሰታቸው የተለመደ መሆኑን ሕክምና ባለሙያው ያስረዳሉ። ነገር ግን ሁለቱም አንድ ታካሚ ላይ በተደራራቢነት መከሰታቸው አልፎ አልፎ የሚያጋጥ ነው ሲሉም አክለዋል።

ቀዶ ህክምናው ካካሄዱት ባለሙያዎች መካከል

የፎቶው ባለመብት, DR. FEKADE

የምስሉ መግለጫ, ቀዶ ህክምናው ካካሄዱት ባለሙያዎች መካከል

ታካሚውና ቤተሰባቸው

ታማሚው ወደ ህክምና ሲመጡ የገጠማቸው የልብ ችግር አንድ ብቻ እንደሆነ ነበር ያሰቡት። ነገር ግን ሐኪሞቹ ሰፋ ያለ ምርመራ ሲያደርጉ ሌላ ተደራቢ ችግር መኖሩ ተረዱ።

ያለውን ሁኔታ የተገነዘቡት የታማሚው ቤተሰቦቹ ሁለቱንም ችግሮች በአንድ ጊዜ በቀዶ ህክምና ማስተካከል እንደሚያስፈልግ በተነገራቸው ጊዜ "እውነታውን ተቀብለው እምነታቸውን በእኛ ላይ ጣሉ" ይላሉ ዶ/ር ፈቃደ።

ቀዶ ህክምናው ከቀኑ 8 ሰዓት ተጀምሮ ማታ ሁለት ሰዓት ላይ ተጠናቀቀ። ታካሚውም ከኦፕራሲዮኑ ከወጡ በኋላ በ4 ሰዓት ውስጥ መንቃት ቻሉ።

"ሲቀጥልም ሰውነታቸው ሙሉ በሙሉ እንደሚሰራ ካረጋገጥን በኋላ ማሽኑን ከሰውነታቸው መንቀል ችለናል። በሚቀጥለው 24 ሰዓት ውስጥም ያስገባናቸውን ጎማዎች ሙሉ በሙሉ በማስወጣት ከአልጋ እንዲወጡ ተደረገ" ይላሉ ዶ/ር ፈቃደ።

"ሁሉም ነገር የተሳካ ነበር። ታካሚውም ያስገባንላቸው ሁሉም ጎማዎች ወጥተውላቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመሳሳቅ እና ለመጨዋወት በቁ" በማለት የቀዶ ህክምናውን ስኬት በደስታ ይገልጹታል።

ባለሙያዎች እንደሚሉእት ደረት ተከፍቶ የልብ ቀዶ ህክምና ከተደረገ በኋላ አጥንት እስኪገጥም ድረስ 12 ሳምንት ይፈልጋል። ታካሚው በሰባት ቀናት ውስጥ ከሆስፒታል እንደሚወጡና ምናልባት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው ይመለሳሉ።

የመጨረሻው ስኬት

ይህ የልብ የቀዶ ጥገና በርካታ ሙያተኞች የተሳተፉበት ተግባር ነበር። የልብ ቀዶ ህክምና ሐኪም፣ የልብ ቀዶ ህክምና አጋዥ፣ ሰመመን ሰጪ ሐኪሞች፣ የልብና የሳንባን ሥራ ተክቶ የሚሰራውን ማሽን የሚያንቀሳቅሱ ባለሞያዎች እና ሌሎችም በቡድኑ ውስጥ የተካተቱ ናቸው። በአጠቃላይ ከ10 በላይ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ተሳትፈውበታል።

በዚህ በአገሪቱ ውስጥ ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው በተባለው የተሳካ ተደራራቢ የልብ ቀዶ ህክምና የተሳተፉት ባለሙያዎች ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ታካሚያቸው በደህና ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

በዚህም ታካሚውን ከቀዶ ህክምና ጠረጴዛ ላይ አስነስተው የልብ ምታቸውን፣ የልብ የደም ግፊት መጠናቸውን፣ የሽንት በበቂ ሁኔታ መምጣትን፣ የልብ የኤሌክትሪካዊ ተግባርን፣ የሳንባ የኦክስጂን አቀባበል እና የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት መወሰን ነበር።

"በሚገርም ሁኔታ እኚህ የመጀመሪያ ታካሚያችን የልባቸውን ሥራ የሚያግዝ ምንም አይነት መድኃኒት አላስፈለጋቸውም" የሚሉት ዶ/ር ፈቃደ "ስለዚህ በተመለከትነው ውጤት ስለተደሰትን አንድ ላይ ተቃቅፈን ፎቶ ተነሳን።"