ልጆችዎ የልብ ችግር እንዳለባቸው በምን ሊያውቁ ይችላሉ? 5 ምልክቶች ልብ ይበሉ!

አዳጊ ታካሚ ሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, BSIP

የልብ ሕመም ልብ ይሰብራል፤ ለታማሚም ላስታማሚም። ለልጅም ለወላጅም። አይበለውና ልጅዎ የልብ ቀዶ ህክምና ቢያሻውስ?

ፈተና ነው። አንደኛ በአገራችን ሁለት ሆስፒታል እንኳ የለም።

ለሕጻናት የልብ ቀዶ ህክምና የሚሰጥ ተጨማሪ ሆስፒታል የለም። እሱው ነው። አንድ ነው። የግልም የመንግሥትም።

ጥቁር አንበሳ ግቢ ውስጥ የሚገኘው የሕጻናት የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል። አንድ ለእናቱ!

ለ110 ሚሊዮን ሕዝብ ይኸው ነው ያለው። ለማመን ይቸግራል።

"ተመስገን ነው! እሱ መኖሩም አንድ ነገር ነው" ሊሉ ይችላሉ።

ሌላ መጥፎ ነገር አለ።

ወደ 8 ሺህ ገደማ ሕጻናት ቀዶ ህክምና ለማድረግ በታላቅ ጉጉት ወረፋ ይዘዋል። እዚሁ ማዕከል! ከዚህ በላይ ምን ልብ የሚሰብር ነገር አለ?

አንድ ሕጻን መዳን እየቻለ በወረፋ መርዘም ሲሞት ምንኛ ሕመም ነው? ምንኛ ጸጸት ነው?

"ይብላኝ ለእናቱ!" ተብሎ አይታለፍ ነገር። አሁን አሁን፣ ሐኪሞችም ሕመሙ ጠልቆ እየተሰማቸው ነው።

ለዚህም ነው ዶ/ር ሔለን በፍቃዱ፣ "ለኛ ለሐኪሞችም ነገሩ ልብ የሚሰብር እየሆነ ነው" የሚሉት።

ዶ/ር ሔለን በፍቃዱን በኢትዮያ የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል፣ የጽኑ ሕሙማን ከፍተኛ የልብ ስፔሻሊስት ናቸው።

"መከላከል ላይ ብንሠራ ሳይሻል አይቀርም" ሲሉ ይመክራሉ። ምን ማለታቸው ይሆን?

የልብ ሕመም ያለበት ልጅ ምልክት ያሳያል?

አዎ ያሳያል!

እርግጥ ነው የሕጻናት የልብ ሕመም በሁለት ይከፈላል። በተፈጥሮ የሚመጣ የሕጻናት የልብ ሕመም አለ።

ካደጉ በኋላ የሚከሰት የልብ ሕመምም አለ። ምልክቶቹም ለየቅል ሊሆኑ ይችላሉ።

የመጀመሪያውን እንመልከት።

በእኛ አገር ጥቂት እናቶች ካልሆኑ የእርግዝና ወቅት ክትትል አያደርጉም። ቢያደርጉም መሠረታዊ የሚባለውን ብቻ ነው።

ስለዚህ የሚወለደው ጨቅላ የልብ ሕመም ይኑርበት፣ አይኑርበት አይታወቅም።

ታዲያ መቼ ነው የሚታወቀው?

በጽንስ ክትትል ጊዜ ሕጻኑ ማህፀን ውስጥ ሳለ የሚከወን የአልትራሳውን ዘዴ አለ። የልብ ችግር እንዳለ በዚያ ይታወቃል።

ይህ ግን ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ተደራሽ አይደለም። ስለዚህ ልጃቸው ከልብ ችግር ጋር እንደተወለደ አያውቁም።

ልጁ ከተወለደ በኋላ ግን አንዳንድ ጥርጣሬዎች ይኖራሉ። "የሚከተሉትን ልብ በሉ"፣ ይላሉ ዶ/ር ሔለን።

  • 1ኛ. ጡት አጠባባቸው ከተቀየረ

ልጆች ከተወለዱ ጀምሮ የጡት አጠባባቸው ከተቀየረ መጠርጠር አይከፋም።

  • 2. ትንፋሻቸው ከተቆራረጠ

ጡት በሚጠቡ ጊዜ ለምሳሌ ትንፋሻቸው ቁርጥ-ቁርጥ ካለ፤ በዚህም የተነሳ ጡት መጥባት ከተቸገሩ አንድ ምልክት ሊሆን ይችላል።

  • 3ኛ. ከንፈራቸው ከጠቆረ

ከተወለዱ ከ3 ሳምንት እስከ 6 ወር ሊሆን ይችላል፣ ብቻ የከንፈራቸው ቀለም ወደ ጥቁር ወይም ሰማያዊ ከተቀየረ ሌላ ምልክት ሊሆን ይችላል።

  • 4ኛ. ዕድገታቸው ሲወሰን/ሲገታ

አንዳንድ ልጆች ከዕድሜ እኩዮቻቸው ወይም ለዕድሜያቸው ሊኖራቸው ከሚገባው ክብደት ያነሰ ኪሎ ቢኖራቸው ለምን ብሎ መጠየቅ መልካም ነው።

ከእነዚህ አንዱ ወይም ሁለትና ሦስት ምልክቶች ከታዩ የልብ አልትራሳውንድ ተሠርቶ ችግራቸው ሊታወቅላቸው ይችላል።

ብዙዎቹ የልብ ችግሮች ደግሞ ከሳንባ ምች ጋር ተቀራራቢ ምልክት ያሳያሉ። መፍትሔው መታየት ነው።

ሐኪሞች በቀዶ ህክምና ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በውጭ አገራት የሕጻናት የልብ ችግር ቶሎ ይታወቃል። ለምን?

ምክንያቱም የሕክምና መሣሪዎች በአንጻራዊ ተሟልተው ስላሉ። በዚህም የተነሳ ቅድመ ወሊድ ላይ ክትትል ስለሚያደርጉ።

እኛ ጋር ሲሆን ግን የልብ ችግር የሚታወቀው በኋላ ነው። ዘግይቶ ነው።

ወላጅ አንዳች ምልክት አስተውሎ ደንግጦ ወደ ጤና ጣቢያ ሲኬድ ነው። በአጋጣሚ ነው የሚታወቀው።

አቅሙም፣ ባለሙያውም መሣሪያዎችም እንደልብ ስለሌሉ፤ ቅድመ ወሊድ ክትትል ላይ እኛ አገር ብዙውን ጊዜ መሠረታዊ ነገሮች ብቻ ናቸው የሚታዩት።

ደግሞም አንዳንድ ምልክቶች ከሳምባ ምች ጋር መሳ-ለ-መሳ ናቸው። ስለዚህ ሁሉም ምልክቶች የልብ ችግር እንዳለ ያመላክታሉ ማለት አይደለም። አይደናገጡ!

ሆኖም ጡት የሚጠቡ ሕጻናት በደንብ ሳይጠቡና ሳይጠግቡ አሁንም አሁንም ትንፋሻቸው ከተቆራረጠ መጠርጠር አይከፋም።

የሕጻናት ከንፈር ወደ ጥቁር ወይም ሰማያዊ ከተቀየረ፤ ጥፍራቸው ቀለሙን ከቀየረ፣ በሚተኙበት ጊዜ አተነፋፈሳቸው ቶሎ ቶሎ ከሆነ፣ ወላጅ መጠራጠር ቢጀመር አይከፋም።

ምክንያቱም ጨቅላ ሕጻናትን ሲደክማቸው ጠይቀን ልንረዳ ስለማንችል፤ ባለሙያ እንዲያያቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

ቶንሲል በልጆች ላይ የልብ ሕመም ያመጣል እንዴ?

አዎ!

እንዲያውም ብዙዎቹ ቀዶ ህክምናዎች የሚደረጉት በዚህ ችግር ታመው በሚመጡ ልጆች ላይ ነው።

"ብዙዎቻችን…" ይላሉ ዶ/ር ሔለን፣ "..በቶንሲል እየታመምን ነው ያደግነው። ነገር ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ቤተሰብ በአግባቡ ሕክምና ሳይወስደን ቀርቶ ይሆናል። አንዳንድ ወላጆች ደግሞ ነገሩ ሲደጋገም በባሕል ሕክምና ሊያልፉት ይችላሉ።"

ይህ አደጋ አለው።

ቶንሲል በአግባቡ ካልታከመ ምን ይሆናል?

የልብ ጠባሳ ይፈጠራል። በዚህን ጊዜ ከውልደት በኋላ የሚከሰተው የልብ በሽታ ይፈጠራል።

በብዛት ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 15 ዓመት አዳጊዎች ቶንሲልን በአግባቡ ካልታከሙ የልብ ጠባሳ ሊፈጠርባቸው የሚችለው ለዚህ ነው።

የሚገርመው በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ሕጻናት በዚህ የልብ ጠባሳ ምክንያት ለልብ ቀዶ ህክምና መዳረጋቸው ነው።

የሕጻናት የልብ ቀዶ ህክምና ለምን ተወደደ?

ዶ/ር ሔለን ሲያስረዱ የልብ ሕክምና በየትኛው ዓለም በአንጻራዊነት ውድ ነው። የተራቀቀ ግብአትን ይፈልጋል። ይህም የሚሆነው ከሕክምናው ባሕሪ የተነሳ ነው።

መድኃኒቶቹ ውድ ናቸው። የሕክምና ግብአቶች ውድ ናቸው። የጽኑ ሕሙማን ክፍል ውድ ነው። የቀዶ ህክምና መከወኛ እልፍኝና ቁሳቁሶቹ ውድ ናቸው።

ባለሙያም ቢሆን ብዙ የለም። እነዚህ ተደማምረው ሕክምናውን የማይቀመስ ያደርጉታል።

ውጭ አገር ለመታከም ምን ያህል ዶላር ያስወጣናል?

አይበለውና አንድ ሕጻን የልብ ቀዶ ህክምና ቢያስፈልገው አገር ውስጥ ያለው ተቋም አንድ ብቻ ነው ብለናል። እዚያ ያለው ወረፋ ደግሞ ለጉድ ነው።

አንዳንድ ጊዜ "ወረፋ ደርሷችኋል፣ ኑ" ተብለው የሚደወልላቸው ቤተሰቦች፣ 'ውይ ልጄ እኮ አረፈ!' ብለው በጥልቅ ሐዘን ውስጥ የሚዘፈቁ ያጋጥማሉ።

ከልጅ ሞት በላይ ምን ይቆጫል?

የአንዳንድ ሕጻናት የቀዶ ህክምና ዓይነቱ ደግሞ ጊዜ የማይሰጥ ይሆናል።

ሐኪሞች በቀዶ ህክምና ላይ

የሆነስ ሆኖ ውጭ አገር ወስዶ ለማሳከም ምን ያህል ገንዘብ ይፈልግ ይሆን?

ዶ/ር ሔለን ይህ በብዙ ሁኔታዎች የሚወሰን በመሆኑ ወጥ ዋጋ መስጠት ያስቸግራል ይላሉ።

ለምሳሌ ሕክምናው የሚሰጥበት አገር፣ የሆስፒታሉ ሁኔታ፣ የቀዶ ህክምናው ዓይነት፣ የታማሚው ልጅ የሆስፒታል ቆይታ፣ ከሕክምናው በኋላ የሚፈጠር ውስብስብ የድኅረ ቀዶ ህክምና ሁኔታ ወዘተ ዋጋውን ሊወስኑ ይችላሉ።

"ሆኖም ግን አሁን ባለው አማካይ የገበያ ዋጋ፣ ታማሚው ልጅ አንድ ሳምንት ብቻ የሚቆይ ቢሆን ብለን አስበን ብናሰላው እስከ 6 ሺህ ዶላር በትንሹ ሊያስፈልግ ይችላል።"

ይህ ወጪ ታዲያ በጣም ቀላል ለሚባለው የቀዶ ህክምና ዓይነት በጣም ርካሽ ዋጋ አላቸው በሚባሉ አገራት ለማከናወን የሚብቃቃ አማካይና ግምታዊ ዋጋ ነው።

ነገር ግን ይህ በብዙ ምክንያቶች አሳሳች ተመን ሊሆን እንደሚችል ግምት ውስጥ እንድናስገባ ያሳስቡናል፣ ዶ/ር ሔለን።

ለምሳሌ ብዙ የልብ ቀዶ ህክምናዎች ከሦስት ሳምንት እስከ ወራት የህክምና ቆይታን ሊፈልጉም ይችላሉ።

የታካሚና የአስታማሚ የአየር ጉዞ ወጪ፣ የሆቴል እንዲሁም የምግብና ተያያዥ ወጪዎች፣ ከህክምና በኋላ የሚኖር ቆይታና በቀዶ ህክምናው ወቅት ሊፈጠር የሚችል ውስብስብ አጋጣሚ ይህን ዋጋ በብዙ እጥፍ ሊያንሩት ይችላሉ።

ታማሚና አስታማሚ ከአገር ሲወጡ የሚፈጠር የሥነ ልቦና ምስቅልቅልና እንግልትም ሌላው በዋጋ የማይተመኑ ወጪዎች ናቸው።

ሕጻናት በምን ያህል ፍጥነት ቀዶ ህክምና ሊሠራላቸው ይገባል?

ዶ/ር ሔለን እንደሚያስረዱት ከሆነ ይህ ውሳኔ በሐኪሞች ብቻ የሚወሰን ነው። ብዙ ሁኔታዎችም ከግምት ሊገቡ ይችላሉ።

አንዳንድ ጊዜ ወዲያውኑ ቀዶ ጥገና የሚፈልግ የልብ ህክምና አለ። አንዳንድ ሕጻናት ደግሞ ሆን ተብሎ ለቀዶ ህክምና ዓመታት እንዲጠብቁ ይፈለጋል።

ለምን?

በተለያዩ የሕክምና ዝርዝር ምክንያቶች።

ለምሳሌ ገና በ8 ወራቸው ችግሩ እንዳለባቸው እየታወቀ፣ ነገር ግን በተለያዩ የህክምና ዝርዝር ጉዳዮች የተነሳ እንዲዘገዩ የሚደረጉ ሕጻናት አሉ። ለምን?

ለምሳሌ ሰውነታቸው እንዲጠና። ክብደትም እንዲጨምሩ።

አንዳንድ ሕጻናት ሦስትና አራት ዓመት እስኪሞላቸው በመድኃኒት ብቻ እንዲቆዩ ሊደረጉ ይችላሉ። ይህ የህክምና ውሳኔ ነው።

"ሁሉም ቀዶ ህክምና አስቸኳይ አይደለም። ሁሉም ቀዶ ህክምና ደግሞ ዘግይቶ አይሠራም" ይላሉ ዶ/ር ሔለን።

የሕጻናት ልብ ቀዶ ህክምና ሐኪሞች ጭንቅ ምን ይመስላል? የወላጆችስ?

"ይሄ ከጥያቄዎች ሁሉ ከባዱ ጥያቄ ነው" ይላሉ ዶ/ር ሔለን።

"ስለ ልብ ሕመም ሙያዊ ማብራሪያ መስጠት ይቻላል። ልጁ የታመመበትን የወላጅ ስሜት ግን ማብራራት አይቻልም።"

እንኳንስ ወራትና ዓመታትን ጠብቂ የተባለች እናት ይቅርና፣ ዕድሉን አግኝቶ ቀዶ ህክምና ሊሠራለት የሚገባ ሕጻን፣ በወላጆቹ ዘንድ ያለው ጭንቅ ቃላት የለውም።

ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ከማደንዘዣ ነቅተው የሚነሱ እንኳ አይመስላቸውም። እናትን ማሰብ ነው እንግዲህ። ልጄን ነገ አገኘዋለሁ ወይ? ልጄ ይነቃል ወይ? ጭንቀቷ ጥልቅ ነው።

ለዚህም ነው ዶ/ር ሔለን፣ "ይህን እኔ በቃላት መግለጽ ይከብደኛል" በማለት ጥያቄውን ማለፍ የሚፈልጉት።

ሐኪሞችስ? ነገሩ ይጨንቃቸዋል ወይንስ ይለመዳል?

ለሐኪም ትልቁ ጭንቀት፣ "የወላጆችን እንባና የልጆችን ስቃይ ማየት ነው" ይላሉ ዶክተሯ።

ከሕክምናው ጫና ባልተናነሰ የሥነ ልቡናው ጫናው ያስጨንቃል።

"በዚያው ልክ ደግሞ…" ይላሉ ዶ/ር ሔለን፣ "…አንድን ሕጻን ይዘን ገብተን፣ ቀዶ ህክምና አድርገንለት ሲሳካ፣ ከጽኑ ሕሙማን ክፍል ወጥቶ ሲቦርቅ ስናይ ያ ድካማችን ሁሉ ይረሳል፤ የልብ ስብራቱን ሁሉ እንረሳዋለን" ይላሉ።።

ታዲያ ምን ተሻለ? ምን እናድርግ?

መከላከል ላይ መሰረት ያደረገ ህክምና ለእኛ አገር ተመራጩ መንገድ ነው ባይ ናቸው ዶ/ር ሔለን።

ለምሳሌ ቶንሲል እንዴት መታከም እንዳለበት በስፋት ግንዛቤ መስጠት ብቻውን የዛሬ 15 ዓመት ሊመጡ የሚችሉ የልብ ቀዶ ህክምናን የሚሹ ሕጻናትን ቁጥር በብዙ እጥፍ ይቀንሳል።

ለዚህም ነው ለእኛ የሚያዋጣው መከላከል ላይ መሥራት ነው የሚሉት።

ዶ/ር ሔለን ስለ ብቸኛው የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል የወፊት ዕጣ ፈንታም ያሳስባቸዋል።

"የተባበሩ እጆች ከሌሉ ተቋሙን ልናጣ እንችላለን። ተቋም ማጣት ስንል ሕንጻው ይኖራል፤ አገልግሎቱ ግን እየቀነሰ ይሄዳል ማለቴ ነው" ይላሉ።

13 ዓመት የደፈነው ይህ ተቋም አቅሙ የዕድሜውን ያህል ጎልብቷል? በሌላ የአገሪቱ ክፍልስ ቅርንጫፍ ከፍቷል?

ለነዚህ ጥያቄዎች መልሱ አሉታዊ ነው። ለምን?

"ዋናው ምክንያት ትኩረት ማጣቱ ነው። የጉዳዩ አሳሳቢነት የሚረዳው የደረሰበት ቤተሰብ ብቻ መሆኑ ነው ችግሩ።"

ዶ/ር ሔለን "ያለንንም እንዳናጣ ነው ፍርሃቴ" የሚሉትም ለዚህ ነው።

ብዙ ሰው ችግሩ በልጁ እስኪደርስበት ድረስ ዝም ብሏል። ስለ ጎረቤት አገር የሚወራ ይመስለዋል። የልብን ችግር ልብ ማለትን ትቷል።

መቼስ ምን ማድረግ ይቻላል?