ልብ የረሳው አውሮፕላን

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ውስጥ ከሲያትል ወደ ዳላስ ይጓዝ የነበረ አውሮፕላን ለህመምተኞች ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረስ የነበረበትን ልብ ረስቶ በመሄዱ ከሰአታት በኋላ እንዲመለስ ተገዷል።

የአውሮፕላኑ ባለቤት የሆነው 'ሳውዝዌስት' አየር መንገድ እንዳስታወቀው የልብ ንቅለ ተከላ ለሚደረግላቸው ሰዎች በሆስፒታል ማስተካከያ ሊሰራለት የነበረው የሰው ልብ መረሳቱ አስገርሞታል።

ልቡን ሲጠባበቁ የነበሩ የህክምና ባለሙዎች ሁኔታው አላምር ሲላቸው አውሮፕላኑ ዳላስ ለመድረስ ግማሽ ያህል ርቀት ሲቀረው ወደኋላ እንዲመለስ አስገድደውታል።

እስካሁን ልቡ ለማን ሊሰጥ እንደሆነ አልተወሰነም ተብሏል።

በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ ደንበኞችም ዋና አብራሪው ሁኔታውን ሲያስረዳቸው በጣም መደንገጣቸውንና በጭንቀት ሲተባበሩ እንደነበረ አየር መንገዱ አስታውቋል።

አንዳንዶቹ እንዳውም ስልኮቻቸውን በመጠቀም የሰው ልብ በማቀዝቀዣ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ መቆየት እንደሚችል ሲያጣሩ ነበር ተብሏል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የሰው ልጅ ልብ በማቆያ ውስጥ ከአራት እስከ ስድስት ሰአት መቆየት ይችላል።

ከሶስት ሰአታት በረራ በኋላ ወደተነሳበት አየር ማረፊያ እንዲመለስ የተገደደው አውሮፕላን፤ ውስጥ ተሳፋሪ የነበረ የህክምና ባለሙያ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው ክስተቱ ከባለሙያዎች የማይጠበቅ ቸልተኝነት ነው ብሏል።

ምንም እንኳን አውሮፕላኑ በታሰበለት ሰአት ልቡን ማስረከብ ባይችልም፤ ከስድስት ሰአታት በኋላ ልቡ ሟቾች ከመሞታቸው በፊት የለገሷቸው የሰውነት አካላት ወደ ሚጠራቀምበት ሆስፒታል መወሰዱ ተገልጿል።