መሰረት መብራቴ፡ ለ60 ህጻናት የልብ ህክምና የሚውል 6 ሚሊዮን ብር ያሰባሰበች የበጎ ፍቃድ አምባሳደር

መሰረት መብራቴ

የፎቶው ባለመብት, Meseret Mebrate

የልብ ማዕከል በኢትዮጵያ በተለያየ ስያሜና መዋቅር ከ30 ዓመታት በላይ ቀዶ ህክምናን ጨምሮ የተለያዩ የልብ ህክምናዎችን እየሰጠ ይገኛል። ሆኖም ማዕከሉ በተዳጋጋሚ አንድ መሰረታዊ ችግር እንዳለበት ይገልጻል - የአላቂ እቃዎች እጥረት።

በዚህ እጥረት ምክንያት ከ7 ሺህ በላይ የልብ ችግር ያለባቸው ህጻናት ለዓመታት ወረፋ ይጠብቃሉ። አንዳንዶቹም ወረፋው ሳይደርሳቸው ህይወታቸው ያልፋል።

ማዕከሉ የተለያዩ አካላት ይህንን ችግር እንዲረዱለት ብሎም እንዲረዱት ከሦስት ዓመት በፊት በአምባሳደርነት አርቲስት መሰረት መብራቴን ሰይሞ፣ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ገቢ እስከማሰባሰብ የዘለቀ እንቅስቃሴ አያደረገች ነው።

መሰረት በቅርቡ በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር 126 ሺህ ዶላር አሰባስባ ገቢ አድርጋለች። ቢቢሲ ከአርቲስቷ ጋር በልብ ህክምና ማዕከል ውስጥ ስላላት ያልትን ሚና በተመለከተ ቆይታ አድርጓል።

መስመር

ቢቢሲ፡ ለመነሻ እንዲሆነን ከፊልምና መሰል የጥበብ ራዎች የራቅሽው በምን ምክንያት እንደሆነ ንገሪን?

መሰረት፡ እርግጥ ነው አሁን ላይ ትንሽ ከመድረኩ ጠፋ ብያለሁ። በጣም ትልቅ የሆነ ነገር ላይ ተጠምጄ ነው ማለት ነው። ማኅበረሰብን፣ ወገንን ማገልገል ከምንም ነገር በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አጀንዳ እንደመሆኑ መጠን የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ጊዜዬን እዚያ ላይ ነው የማሳልፈው። ግን ደግሞ ማስታወቂያ ድርጀት ስላለኝ ማስታወቂያዎችንና አጫጭር ዶክመንተሪዎችን እየሰራሁ ነው።

በፊት እንደነበረኝ እንቅስቃሴ ፊልሞችና ትያትሮች ላይ የለሁም። ለእሱም ብዙ ተግዳሮቶችም አሉ - አሁን ላይ የማልጠቅሳቸ። ምናልባት ወደፊት ጊዜው ሲደርስ የምናገራቸው።

በተጨማሪ ደግሞ አንዲት ሴት ከላይ በሚታይ ውበትና አለባበስ ብቻ ሳይሆን ጥንካሬዋን፣ ብርታቷን፣ ጉብዝናዋን ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች እንዲሰሩ ከመፈለግ አንጻር የሚጻፉ ስከሪብቶች ላይ ሴቶች የሚሳሉበት መንገድን አለመውደድ አለ። ሌሎችም ተግዳሮቶች አሉ።

ቢቢሲ፡ ከልብ ማዕከል በተጨማሪ የምትሳተፊባቸው የጎ አድራጎት ድርጅቶች ወይም እንቅስቃሴዎች አሉ?

መሰረት፡ ይሄ ነገር ከድሮ ጀምሮ ነፍሴ ውስጥ ያለ ነገር ነው። በምድር ላይ በምክንያት መጥተናል። በምክንያት ተፈጥረናል። ካለ ምክንያት ወደዚህ ምድር የመጣ የለም ብዬ አምናለሁ። ትልቁ ነገር አንዳንችን ለሌላችን መትረፍ፣ ትርጉ ያለውን ሥራ ጥሎ ማለፍ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ነው ብዬ ስለማምን ለለሌሎች መድረስ በሌሎች ደስታ መደሰት አብሮኝ ያለ ነው።

ከድሮም ጀምሮ አገልግሎት ውስጥ አለሁ። በተለያየ መንገድ በሴቶች፣ በህጻናት፣ ጎዳና ልጆች ላይ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ተቋማት ጋር በበጎ ፍቃድ አምባሳደርነት አገልግያለሁ።

በዋነኝነት አሁን ላይ ጎልቶ የወጣው የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል የበጎ ፍቃድ አምባሳደርነቴ ቢሆንም፣ አገሬ እኔን በምትፈልግበት ቦታ ሁሉ ለሰው ልጅ በጎ ከሚያስቡ ተቋማት ጋር ሁሉ አብሬ አገለግላለሁ።

ቢቢሲ፡ የልብ ህሙማን ማዕከሉን በተለይ ለማገዝ የመጥሽበት ምክንያት ምንድን ነው?

መሰረት፡ የመጀመሪያው የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርጎ የመረጠኝ ቦርዱ ነው [የልብ ማዕከል ኢትዮጵያ ቦርድ] ግን ከማዕከሉ ጋር የነበረኝ ቁርኝት ረዘም ያለ ነው። ለምሳሌ አንድ ብር ለአንድ ወገን የሚል እንቅስቃሴ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተሳትፎ ነበረኝ።

ብዙም ጠልቄ የማዕከሉን ችግር የማወቅ አጋጣሚ ባይኖረኝም አገልግሎቱ ላይ ግን ነበርኩኝ። ከሦስት ዓመት በፊት ነው ቦርዱ አጽድቆ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ሁኚ የሚል ጥሪ የደረሰኝ - እኔም በደስታ ወገኔን አገለግላለሁ ብዬ የጀመረኩት ነው።

ያለኝን ተሳትፎ ብርቱ እንዲሆን ያደረገኝ ነገር ማዕከሉን በቅርበት ማወቄ፣ የህጻናቱና የወላጆቻቸውን ስቃይ እና ሰቀቀን ስመለከት እዚያው ቦታ ላይ ቆሜ ነው በእግዚያብሔርም በሰው ፊት ቃል የገባሁት። ስለዚህም በምችለው ሁሉ፣ ፈጣሪ በሰጠኝ ጊዜ፣ ጉልበትና ተሰጥኦ ሁሉ ማድረግ የምችለውን ሁሉ ለማገዝ ቃል ገባሁ።

በዙሪያችን ብዙ ችግሮች አሉ፣ ልንሸፍናቸው የሚገቡ ብዙ ጉድለቶች ስላሉ ሁላችንም የራሳችንን ጠጠር መጣል ይገባናል ብዬ አምናለሁ። ሁሉንም ጋር ደርሰን መቅረፍ ባንችልም በአቅማችን ልንደርስ የምንችለው የቱ ጋ ነው? ድምጻችን ሊሰማ የሚችለው እስከምን ድረስ ነው? ብለን ማገልገል ከቻልን የእያንዳንዳችን ጠጠር ሲደመር ብዙ ታሪክ ሊቀየር ይችላል።

መሰረት መብራቴ

የፎቶው ባለመብት, Meseret Mebrate

ቢቢሲ፡ አምባሳደር በሆንሽባቸው ስት ዓመታት ያለሽን እውቅና እና ተወዳጅነት በመጠቀም ማዕከሉን እዴ እያገዝሽ ነው?

መሰረት፡ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብሮችን በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር በመሆን ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችሉ መርሃ ግብሮችን እየዘረጋን የገቢ ማሰባሰቢያ ተግባራትን እንዲሁም ስለልብ ህክምና ማዕከሉ በሰዉ ዘንድ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር ጥረት አድርገናል።

ቢቢሲ፡ ስለልብ ማዕከሉ የተለያዩ አካላት አልተረዱለትም ብለሽ የምታስቢው ችግር ምንድን ነው? አንቺ ልትሞይው የምትፈልጊው ክፍተት የትኛው ነው?

መሰረት፡ ማዕከሉ ከተመሰረ ከ30 ዓመት በላይ ሆኖታል። በዶ/ር በላይ አበጋዝ እና በጥቂት ቅን ግለሰቦች ነው የተመሰረተው። እንግዲህ በዚህ ማዕከል በርካቶች እድል አግኘተው ምናልባትም እስካሁን ድረስ ከ9 ሺህ 500 በላይ ታካሚዎች እድል አገኝተዋል።

ማዕከሉ ከመመስረቱ በፊት ውጪ አገር ሄዶ የመታከም እድሉን ለማግኘት ወረፋ መጠበቅ በራሱ ትልቅ እንግልት ነበር። ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ የማዕከሉ መመስረት ትልቅ የምሥራች የሆነው።

ነገር ግን የልብ ማዕከሉ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ ብርቱ ባለሙያዎች እያሉት ከልብ ህክምና ጋር በተገናኛ የአላቂ እቃዎች እጥረት ግን ዋነኛ ማነቆ ሆኖ እንደልብ ሥራዎች እንዳይሰሩ፣ በጣሙን የሚፈለገውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ እንዳይሰጥ ትልቅ ችግር እየሆነ ነው።

እንግዲህ ያንን ክፍተት ለመሙላት ነው ገቢ ማስባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በመንደፍ በቋሚነት ማዕከሉ የሚረዳበትን ነገር በመፍጠር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ሆኜ ያለሁት።

የማዕከሉ ትልቁ ችግር የአላቂ እቃዎች እጥረት ነው። እሱን ለመግዛት እንደገና ውጪ አገር ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር በቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር በቋሚነት እነዚህ የመርጃ መሳሪያዎች እንዲገኙ የሚቻልበትንም ሁኔታ ማመቻቸትም ጭምር ነው።

ቢቢሲ፡ እስኪ አሜሪካ ስለነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብር ደግሞ ንግሪን። እንዴት ነበር ገቢው የተሰባሰበው? ምን ያህል ውጤታማ ነበር?

መሰረት፡ እንግዲህ አሜሪካ ከወር በፊት የነበረውን ጉዞ ስንነድፍ በተለይ ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ ያሰብናቸው ትላልቅ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች እንዳናከናውን እንቅፋት ሆኖ፣ እኔም የአቅሜን ያክል በመሮጥ ህጻናቱን እንዳልደግፍ እንቅፋት ሆኗል በሚል እረፍት የሚነሳኝ ጉዳይ ነበር።

በቅርቡ በአሜሪካ የኢትዮጵያን ቀን በሚከበርበት ጊዜ ተሳታፊ ሆነን ለምን በውጪ አገራት ከሚገኙ ወገኖቻችን ጋር በመገናኘት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ለማድረግ ከአዘጋጆቹ ጋር ተነጋገርን። እዚያ በሚኖረው ቆይታም 100 ሺህ ዶላር እናሰባስባለን የሚል እቅድ ነበረን።

መጀመሪያ ሲያትል ከዚያም ሚኒሶታ ቀጥሎ ደግሞ በአትላንታ የገቢ ማሰባሰቢ መረሃ ግብሮች አካሄድን። ዋሽንግተን ዲሲ የተዘጋጀ ነገር ስላልነበረ እዚያው ከሄድኩ በኋላ ነው ከእህት ወንድሞች አገልጋዮች ጋር በመመካከር የእራት ፕርግራም አዘጋጀን ጨረታዎችን በማካሄድ የተሳካ ጥሩ የሚባል መርሃ ግብር ተካሄደ። ከዚያም በኋላ ሳንዲዬጎ ላይም እንደዚሁ ተመሳሳይ ፕሮግራም አዘጋጀን።

ገንዘብ ማሰባሰብ ሂደቱን በተመለከተ በየከተማው የሚያግዙኝ በቅንነት የሚግዙኝ ኢትዮጵያውያን ወንድሞች ነበሩ። የተሰበሰበው ገንዘብም ማዕከሉ ለዚሁ ዓላማ ብሎ በአዋሽ ባንክ ወደከፈተው የዶላር አካውንት ነበር የምናስገባው።

ስንጀምር 100 ሺህ ዶላር እንሰበስባለን ብለን ነበር የተነሳነው። እንግዲህ እግዚያብሔር አግዞኝ በብዙ ቅን ደጋግ ኢትዮጵያውያን ብርታት ወደ 126 ሺህ ዶላር አካባቢ መሰብሰብ ተችሏል። ይህም በኢትዮጵያ ወደ 6 ሚሊዮን ብር ማለት ነው። አንድ ህጻን ለማሳከም 100 ሺህ ብር ያስፈልጋል ስለዚህ የ60 ህጻናት የተሰበሩ ልቦች ይጠገናሉ። የ60 ህጻናት ቤተሰብ እንባ ይታበሳል።

ቢቢሲ፡ በልብ ማዕከል የበጎ ፍቃድ አምባሳደርነትሽ ቀጣዩ ተግባርሽ ምንድነው?

መሰረት፡ እኛ ይዘን የተነሳ ነው አንድን ህጻን ማከምና ማዳን አገርን ማዳን ነው በሚል እምነት ነው። እንግዲህ በእግዚያብሔር ቸርነት 60 ህጻናት ይህንን እድል ያገኛሉ ማለት ነው። ሆኖም አሁንም ድረስ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህጻናት ወረፋ እየጠበቁ ነው።

ይህ የህጻናቱ ቁጥር ደግሞ በየቀኑ ቁጥሩ የሚጨምር በመሆኑ ችግር ለመቅረፍ እንደዚህ በአለፍ ገደም ብቻ የሚሰራ የገቢ ማሰባሰቢያ ብቻ የትም አያደርስም።

ስለዚህ በቋሚነት በውጪ አገራት ከሚገኙ የልብ ሆስፒታሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በቋሚነት ማዕከሉ እንዲደገፍና ችግሮቹ እንዲቀረፉ ማድረግ የሚቻልበት መስመርም መዘርጋትም ያስፈልጋል።

የተሰበሩ ልቦች ተጠግነው፣ ያለቀሱ ዓይኖች ታብሰው የእናቶችን የእልልታና የምስጋና ድምጽ መስማት እንዲሁም ህጻናት ለምስጋና ሲመጡ ማየትን ያህል በሥጋም ሆነ በመንፈስም የሚያስደስት ነገር አለ ብዬ አላምንም። ስለዚህ በየትኛውም በኩል ማዕከሉን ማገልገል ነው አላማዬ፤ ይህም ሰዎች ሲደሰቱ እንዳይ ስለሚያደርገኝ ለእኔ በረከቴ ነው ብዬ ነው የማምነው።