ባለንበት ዘመን ወጣቶች ከአዛውንቶች በበለጠ በብቸኝነት የሚሰቃዩት ለምንድን ነው?

ብቻውን የተቀመጠ ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የ26 ዓመቱ አዳም ቤኬት በቀዝቃዛው የጥቅምት ወር አንድ ምሽት የሆነውን በሚገባ ያስታውሳል።

ጊዜው በአውሮፓውያኑ 2021 ነው። ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ብሪስቶል በሥራ ምክንያት ቢመጣም ጓደኛ ለማፍራት ግን ዳገት ሆኖበት ነበር።

"ሁሌም ብቻዬን አይደለሁም. . . ግን ባዳነት ይሰማኝ ነበር" ሲል ያስታውሳል።

የዚያን ዕለት ወደ ቤቱ እየሄደ የሃሎዊን በዓልን ለማክበር የተዘጋጁ ሰዎች በተለያዩ አልባሳት ደምቀው መንገዱን ሞልተውት ነበር።

"ወደ ጓደኞቻቸው ቤት የሚሄዱ፣ ቢራ ለመግዛት ወደ መደብር ጎራ የሚሉትን ሰዎች አልፌ ጉዞዬን ቀጠልኩ።"

"ሁሉም ግሮሰሪዎች ጢም ብለው ሞልተዋል። ልክ ከሌላ ዓለም እንደመጣሁ እና እኔ የዚህ አካል አንዳልሆንኩ ተሰማኝ።"

በዚያ ምሽት ብቸኛ የሆነው እርሱ ብቻ እንደሆነ ተሰምቶታል። ነገር ግን ይህ የእርሱ ስሜት የትውልዱ መገለጫ እየሆነ ነው።

ስለ ማኅበራዊ መገለል ሲወራ አብዛኛውን ጊዜ ትኩረቱ የሚሆነው አረጋውያን ላይ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጥናቶች በብሪታኒያ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አፍላ ወጣቶች ብቸኝነት እንደሚያጠቃቸው አሳይተዋል።

አዳም ቤኬት በእግሩ እየተንሸራሸረ (በስተቀኝ) አዳም ቤኬት ባይስክል እየጋለበ (በስተግራ)

የፎቶው ባለመብት, Adam Becket

የምስሉ መግለጫ, አዳም የሩጫ እና የብስክሌት ቡድኖችን ከተቀላቀለ በኋላ ብቸኝነቱ ቀለል እያለው መጥቷል

ባለፈው ወር ዩናይትድ ኪንግደም የብሔራዊ ስታትስቲክ ቢሮ ይፋ ያደረገው ጥናት ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 29 የሚሆን 33 በመቶ ብሪታንያዊያን ብቸኝነት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም ላይ የተሠሩ የተለያዩ ጥናቶችን በመፈተሽ ወጣቶች እና አዋቂዎች በከፍተኛ ደረጃ በብቸኝነት መጠቃታቸውን መናገራቸውን ይፋ አድርጓል።

መረጃው ውስብስብ ነው። በአንዳንድ አገራት በጣም በዕድሜ በገፉ ሰዎች ዘንድ ብቸኝነት እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ከ18 እስከ 30 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ወጣቶች ዘንድ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ተገኝቷል።

ተንታኞች እንደሚሉት በአብዛኞቹ ጥናቶች ውስጥ ወጣቶች በተለየ ብቸኝነት እንደሚያጠቃቸው ያሳያሉ።

"ከ18 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በጣም ብቸኛ ናቸው። ከዚያም አዛውንቶች ይከተላሉ" ይላሉ በሼፊልድ ሃላም ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ላይ ምርምር የሚያደርግ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሪያ ዊግፊልድ። "እየጨመረ የመጣ ችግር ነው።"

ግን ይህ ለምን ሆነ - እና መፍትሄ አለ?

የመለያየት ጣጣ

ባለሙያዎች ዘመናዊውን ዓለም ይኮንናሉ።

በርካታ ዕድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ወጣቶች በዙሪያቸው ስላሉ ሰዎች በበቂ ሳያውቁ አብረው ይኖራሉ።

ወዳጆቻቸውን የሚያናግሩትም ቢሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው።

በእርግጥ ሁሉም ነገር ድቅድቅ ጨለማ አይደለም። ኢንተርኔት ምስጋና ይግባውና ጓደኞቻቸውን ከመላው ዓለም ማግኘት ይችላሉ።

ነገር ግን በአጠቃላይ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ እንደ ፍሬንድስ ባሉ ተከታታይ ድራማዎች ውስጥ የሚታየው የሃያ ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያለው ጓደኝነት ያበበት ሕይወት ምሥል አስቸኳይ እርማት ያስፈልገዋል።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ዝነኛ የነበረው 'ፍሬንድስ' የተሰኘው ሲትኮም ላይ ዕድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ማኅበራዊ ሕይወታቸው የዳበረ መሆኑን ይታያል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች፣ ኃላፊዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች ግን 20ዎቹ የዕድሜ ክልል በዋናነት የብቸኝነት ዘመን ነው ይላሉ።

ከፍሬንድስ ፊልም የተወሰደ

የፎቶው ባለመብት, NBC Universal via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እአአ በ1990ዎቹ ዝነኛ የነበረው 'ፍሬንድስ' የተሰኘው ሲትኮም ላይ ዕድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ማኅበራዊ ሕይወታቸው የዳበረ መሆኑን ይታያል።

"የወጣትነት ዘመን ሀሳብ እና ጭንቀት የሌለበት አድርገን እናቀርበዋለን፤ ነገር ግን በሰዎች ሕይወት ውስጥ መከራ የሞላበት ወቅት ነው" ይላሉ በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ዊዝባወርድ።

ወጣትነት መረጋጋት የራቀው ጊዜ ነው። ከቤተሰብ ተለይቶ የራስን ኑሮ ለመጀመር የሚታሰብበት፣ ጓደኞች በየፊናቸው ለራሳቸው የሚማስኑበት፣ የቤተሰብ ትስስር እየላላ የሚመጣበት ወቅት ነው።

ይህ የሽግግር ወቅት ለአንዳንዶች ወደ ብቸኝነት የሚመራ ይሆናል።

"ዋናው ችግር መለያየት ነው። የምታውቁት ሰው ሁሉ በየፊናው ይሮጣል" የሚሉት ደግሞ የሥነ ልቡና ባለሙያዋ ዶ/ር ሜግ ጄይ ናት።

ብቻ የመቅዘፍ አባዜ

በዚህ ዘመን ደግሞ ዘመን ያመጣው ሌላ ችግሩን የሚያባብስ ጉዳይ አለ።

በበርካታ ዓለም ሰዎች አግብተው ለመውለድ ይዘገያሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም ሰዎች የሚያገቡበት አማካኝ ዕድሜ 31 ሆኗል።

ይህ ዕድሜ ግን በአውሮፓውያኑ 1970 ለወንዶች 23 ለሴቶች ደግሞ 21 ነበር።

ወጣቶች ስሜትን ለመግለጽ እና ለማካፈል የበለጠ የሚደገፉት ጓደኞቻቸውን ነው። ይህንን የሚያደርግ ጓደኛ በአጠገብ ሲጠፋ ደግሞ የብቸኝነት ጉም ይከብባቸዋል።

ፕሮፌሰር ዊዝቦርድ የማኅበረሰብ እየተራራቀ መምጣትንም በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። በበለጸጉ አገራት በቤተክርስቲያናት፣ በማኅበረሰብ ቡድኖች ወይንም በንግድ ማኅበራት ውስጥ ያለ ተሳትፎ ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ወዲህ እጅጉን ተመናምኗል።

ይህ ብቻ መቅዘፍ ይባላል። ማኅበራዊ ሕይወትን ከመሻት ይልቅ ብቸኛ ሆኖ በተዘጋ ቤት ማሳለፍ እና ከራስ ጋር የመሆን ፍላጎት ነው።

ፕሮፌሰር ዊዝቦርድ የልጅነት ቤቱን ጥሎ ብቻውን ለመኖር የሚወስን ወጣት በፍጥነት ማኅበራዊ ትስስሩ የላላበት ኅብረተሰብ ውስጥ ሲወድቅ ብቸኝነት በሻካራ እጆቹ ይቀበለዋል ይላሉ።

"ብቸኝነት በሚያጠቃው ማኅበረሰብ ውስጥ ነው የምንኖረው። ብቸኝነት አንዳችን ለሌላችን ያለን አሳቢነት እና ተቆርቋሪነት መጥፋቱ ማሳያ እንደሆነ አስባለሁ"

ስልካቸውን እየነካኩ ሰልፍ የያዙ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዩኬ ወጣቶች በአማካኝ በየቀኑ 6ሰዓት ከ20 ደቂቃ በኦንላይን ላይ ያሳልፋሉ

ስልኮቻችን የሚያመጡት አሉታዊ ስሜት

በዚህ ዓመት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት ውስጥ ያሉ ብሪታኒያዊያን በቀን ለስድስት ሰዓት ከ20 ደቂቃ በኦንላየን ላይ ያሳልፋሉ።

አንዳንዶች እንደ ኢንስታግራም እና ስናፕቻት ያሉ መተግበሪያዎች ሰዎች በአካል ከመነጋገር ይልቅ በኦንላይን ላይ እንዲያወሩ ስለሚያበረታቱ ለብቸኝነት ስሜት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለው ያስቡ ይሆናል። ነገር ግን መረጃው ይህንን በግልጽ አይደግፍም።

አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት በእርግጥ እውነት የሆነው ነገር፣ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ቀደም ሲል የነበረውን የብቸኝነት ስሜቶች የሚያጎሉ መሆናቸው ነው።

ዶ/ር ጄይ ይህንን "የማወዳደር እና የተስፋ መቁረጥ" ምክንያት ብላ ትጠራዋለች።

"እያንዳንዱ ሰው የቅርብ ጓደኞች ያሉት ይመስላል እና ሁሉም በዱባይ ከአውሮፕላን ላይ እየዘለሉ እየተዝናኑ ነው ብለን እናስባለን። 'የእኔ ችግር ምንድን ነው? ቅዳሜ እና እሁድን ማንንም አላየሁም' እንላለን።"

ሌላው ጉዳይ ብቸኝነት ላይ የሚደረጉ ጥናቶች ለራስ ማድላት ያላቸው ይመስላል።

ስለ ብቸኝነት የተደረጉ ጥናቶች በአብዛኛው የተመሠረቱት ግለሰቡ በሚሰጠው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው።

ይህም ማለት ሰዎች ብቸኝነት ይሰማቸው እንደሆን ተጠይቀው የሰጡት መልስ ነው የጥናቱ ግብዓት የሆነው።

ፕሮፌሰር ዌይዝቦርድ ደግሞ የአእምሮ ጤና እና ሕክምና ቋንቋን የበለጠ አቀላጥፈው የሚናገሩ ወጣቶች ከአረጋውያን ይልቅ ራሳቸውን በዳሰሳ ጥናቶች ውስጥ 'ብቸኛ ነኝ' ብለው የመግለጽ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ይላሉ።

የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, The Great Friendship Project

የምስሉ መግለጫ, በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰባስበው የእግር ገዞ የሚያድርጉ ወጣቶች

ለራስ አድልቶ መረጃ መስጠት የእንቆቅልሹን አንድ "ክፍል" ሊያብራራ ይችላል ብለው ያስባሉ። ግን በእርግጠኝነት ሁሉም ላይሆን ይችላል።

በእርግጥ በወጣቶች እና በአዋቂዎች መካከል የሚታየው ከፍተኛ የብቸኝነት ደረጃ እውነተኛ ክስተት እንጂ የቁጥር ቅዠት አይደለም።

ዶ/ር ጄይ የመጪውን ጊዜ ስትመለከት ተስፋ ይታያታል። ዕድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ እንደነበረው በቤታቸው ብቻቸውን ተቀምጠው የሚሠሩበት ጊዜ አብቅቷል።

በርካታ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው በቢሮ ውስጥ ረዥም ጊዜ እንዲያሳልፉ እያበረታቱ ነው።

ዶ/ር ጄይ በተጨማሪ ስም እና ዝና ያላቸው ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እያመጣ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ መረዳታቸውን ተመልክታለች።

በእርግጥ ወጣቶች ከማኅበራዊ ሚዲያ ለመራቅ ፍላጎት እያሳዩ ባይሆንም ተስፋው ግን ይታያታል።

አክላም "ማኅበራዊ ሚዲያ ጠልነት በርክቶ ማየት እፈልጋለሁ። ችግሩ በኪሳችን ውስጥ መሆኑ ነው" ብላለች።

ለአንዳንዶች ድመት ማሳደግ ብቸኝነትን ሲያባርር ለሌሎች ደግሞ በጋራ ወጣ ብሎ ሳይክል መጋለብ፣ ተራራ መውጣት፣ የእግር ጉዞ ማድረግ ብቸኝነትን ለማባረር መፍትሄ ሆኗል።