ብቸኛ ስለነበርኩ 38ሺህ ሴቶች ያሉበት የራሴን ማኅበረሰብ ፈጠርኩ

ሎቬና ሼኖይ

በ2022 መጀመሪያ ላይ ነበር፣ በለንደን ሌላ ጨለማ ቀን። ሎቪና ሼኖይ በማታውቀው እና አንዳንዴም በአስደናቂ ሁኔታ ውስጥ እየሄደች ለከተማዋ አዲስ ነበረች።

የ39 ዓመቷ ሎቪና ለቢቢሲ ስትናገር "ሕንድ፣ ቤተሰቦች አሉ፣ የትምህርት ቤት እና የኮሌጅ ጓደኞች አሉህ፣ ድጋፍ ብትፈልግ ሰው አለ በጥቅሉ የምቾት ዞን ውስጥ ነበርክ" ትላለች።

"ነገር ግን ወደ አዲስ አገር ስትመጣ በድንገት ትቀራለህ። ብቻህን ትሆናለህ"

ባብዛኛው ውጭ አገር በሚኖሩ የሕንድ ማኅበረሰብ ተከባ በዱባይ አስር ዓመታትን አሳልፋለች፤ ከዚያ በፊት ደግሞ በትውልድ ከተማዋ ሙምባይ ትኖር ነበር።

የትዳር አጋሯ አዲስ ሥራ በማግኘቱ ወደ ለንደን መሄድ አስደሳች ነበር። ነገር ግን 9 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሚኖሩባት ከተማ ውስጥ ብትሆንም፣ ባይተዋር ነበረች።

ሎቪና ሴት ጓደኞች እንዲኖሯት ትመኝ ነበር። ከባለቤቷ እና ከሁለት ልጆቿ ጋር ባላት ኑሮ ደስተኛ ብትሆንም ነፍስያዋ የጎደለ ነገር እንዳላት ይነግራት ነበር።

'የራሴን ጎሳ አገኘሁ'

ሎቬና ከሌሎች ሴቶች ጋር ፎቶ እየተነሳች

ሎቪና "ወደ ለንደን በሄድኩ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ፀሀይ 10 ሰዓት አካባቢ መጥለቅ እንደምትጀምር ተረዳሁ" ስትል ትቀልዳለች። "ብቸኝነት እና ድባቴ ውስጥ እገባለሁ ብዬ ሰግቼ ነበር። ምንም ጓደኛ አልነበረኝም"

እናም በግል የፌስቡክ ገጿ ላይ "ሰላም ሎቬና እባላለሁ፤ ከሙምባይ ነኝ፤ ወደ እዚህ [ለንደን] ከመምጣቴ በፊት በዱባይ ለአስር ዓመታት ኑሬያለሁ፤ አንድ ሲኒ ቡና አብሮኝ መጠጣት የሚፈልግ አለ?" የሚል አንድ መልዕክት አስተላለፈች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይግረምሽ ሲላት፣ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሴቶች ከእርሷ ጋር ለመገናኘት እንደሚፈልጉ መለሱ።

በፍጥነት ቦታ ጠቆመች እና ከ30 በላይ ሴቶች ከእርሷ ጋር 'አንድ ሲኒ ቡና ለመጠጣት' መምጣታቸውን ስታይ ተገረመች።

"በጣም ደንግጬ ነበር። አዲስ አገር ነው ያለሁት እና 30 የማላውቃቸው ሴቶች ከእኔ ጋር ቡና ለመጠጣት ጥረት አድርገዋል" ትላለች። "የራሴን ጎሳ አገኘሁ ስል አሰብኩ"

ሎቪና በዩናይትድ ኪንግደም ትልቁ የስደተኞች ቡድን አካል ናት።

እ.ኤ.አ. በ2021-22 በዩኬ የሕዝብ ቆጠራ መሰረት፣ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከሚገኙት የውጭ ተወላጆች መካከል 32 በመቶው የሚገመተው ከአምስት አገራት ማለትም ከፖላንድ፣ ፓኪስታን፣ ሮማኒያ፣ አየርላንድ እና ሕንድ የመጡ ናቸው።

በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ስደተኞች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሕንዳውያን ሲሆኑ በአገሪቱ የሚገኙት 965,000 ሕንዳውያን 9በመቶ የውጭ አገር ተወላጆችን ይወክላሉ።

ያንን የመጀመሪያ የቡና መሰባሰብ ተከትሎ ሎቪና የሕንድ ሴቶች በለንደን እና ዩኬ (IWLUK) የሚል የፌስቡክ ቡድን እአአ በመጋቢት 2022 ጀምራለች።

ብዙም ሳይቆይ መሠረታቸውን በተለያየ ቦታዎች ያደረጉ በርካታ የዋትስአፕ ቡድኖችን ጀምራለች።

ከሦስት ዓመታት በኋላ በፌስቡክ ቡድኑ ከ38,000 በላይ አባላት ሲሆኑ 15,000 ሴቶች ደግሞ የዋትስአፕ ቡድኑ አባል ናቸው።

ሎቪና እና የቡድኑ ሌሎች ሦስት አስተዳዳሪዎች፣ ፕራብሊን ሩፕራ⁠፣ ዲሻ ራዋት እና ኒሺ ጊል፣ በአዲስ አገር ውስጥ ስደተኞች ሴቶች ያጋጠሟቸውን በርካታ ፈተናዎች ተገንዝበው ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

'የሕንድ ሴቶች በለንደን እና ዩኬ'ን የመሠረቱት በተለያዩ የማኅበራዊ እና የንግድ ትስስር ዝግጅቶች በኤግዚቢሽኑ እና በዩናይትድ ኪንግደም በተወለዱ ሕንዳውያን ሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል ነው ይላሉ።

አኑ ቻንድራሴካር

'አዲስ ነገር ለመጀመር በራስ መተማመን'

ማኅበረሰቡ የእግር ጉዞዎችን፣ ቁምሳዎች (ብራንች)፣ ቦሊውድ ጭብጥ ያላቸውን ፓርቲዎች፣ የእናቶች ስብሰባዎችን እና የስራ ትስስር ዝግጅቶችን ጨምሮ በየወሩ ብዙ ስብሰባዎችን ያደራጃል።

ተነሳሽነቱ ጓደኝነታቸውን ከማሳደጉ ባለፈ ሙያዊ እድገታቸውን በማሳለጥ ስራ ፈጣሪዎች እንዲገናኙ አስችሏል ይላሉ።

የቡድኑ አባል አኑ ቻንድራሴካር ከ20 ዓመታት በላይ በኮርፖሬት አካባቢ ከሰራች በኋላ ማኅበረሰቡ በ2025 የግል የሙያ ስልጠና ስራዋን እንድትጀምር በራስ መተማመን እንደሰጣት ተናግራለች።

"ሴቶቹ በእርግጠኝነት የራሴን ስራ እንድጀምር በራስ መተማመን ሰጥተውኛል" ትላለች።

ኅብረተሰቡ ከሙያ እና ማኅበራዊ እድገት ባለፈ ለከባድ የግል ተግዳሮቶች ሴቶች ትርጉም ያለው ድጋፍ አድርጓል።

በአንድ አጋጣሚ አንዲት ሴት ስሟ ሳይገለጽ በፌስቡክ ቡድኑ ውስጥ ባለቤቷ ከቤቷ እንዳባረራት ገለጸች።

ኒሺ መልዕክቱን አይታ በፍጥነት ከሴትየዋ ጋር ተገናኘች። ድጋፍ እና የምትቆይበት አስተማማኝ ቦታ አዘጋጅታለች።

ኒሺ "ቡድኑ የመጀመሪያዋ ማረፊያዋ ነበር። ስደተኛ ሴት እንደመሆኗ መጠን ወደ ብሔራዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለመቅረብ ዕውቀት አልነበራትም። ግን ስለ ቡድናችን ታውቃለች" ትላለች።

በ2022 ከስድስት ወር ሴት ልጇ ጋር ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የተዛወረችው ሌላዋ ከማኀበረሰቡ ቡድኑ እውቀት በቀጥታ የምትጠቀመው ፕሪያ ማሃጃን ትባላለች። በዩናይትድ ኪንግደም ሱፐርማርኬት ውስጥ ሳለች ባልተጠበቀ ሁኔታ ራሷን ተውጣ አገኘች።

ፕሪያ በዚህ ሱፐርማርኬት ውስጥ "በጣም ብዙ ዓይነት ወተት አይቻለሁ። አረንጓዴ ነበር። ሰማያዊ ነበር " ትላለች።

"እኔ ከመጣሁበት ሕንድ የላም እና የጎሽ ወተት ነው ያለን። ምንም ልዩነት የለውም፤ ከፍተኛ ስብ ያለው ዝቅተኛ ስብ ያለው የሚል። በጣም ግራ ተጋባሁ"።

እናም ቡድኑን ጠየቀች እና ምክር ሰጡ።

ፕሪያ ጥያቄዎቿን ወደ ጎግል መላክ ትችል ነበር። ነገር ግን ሌሎች የሕንድ ሴቶችን ቡድን ለመጠየቅ የበለጠ እንደተመቻት ተናግራለች።

"ቡድኑ በሕይወቴ የሰዎችን ሚና ተወጥቷል" ትላለች ፕሪያ። "እናትን በአንድ ሰው ውስጥ አገኘሁ ፣ በአንድ ሰው ውስጥ አያት ፣ በአንድ ሰው ውስጥ ጓደኛ አገኘሁ ።"

ቡድኑ ለምን ወንዶችን አያካትትም የሚለውን ጨምሮ አንዳንድ ትችቶች ይቀርቡበታል።

ሎቪና ይህንን ኃላፊነት ውስዳ በለንደን እና በዩኬ ውስጥ የሕንድ ፕሮፌሽናልስ የተባለ ሁለተኛ ደረጃ የፌስቡክ ቡድን ፈጠረች ይህም ሁሉንም ጾታ ያካተተ ነው። ቡድኑ ከ53,000 በላይ አባላት አሉት።

"በተለይ ለሕንድ ሴቶች ቡድን ፈጠርኩ እንጂ ሁሉም ሴቶች አይደሉም፣ ምክንያቱም የተለየ እውቀት ያለኝ በሕንድ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደ ዲዋሉ ስላሉት የባህል በዓላት ነው" ትላለች ሎቪና።

"ከሕንድ ሴቶች ጋር ይበልጥ እዛመዳለሁ። ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የባህል ዳራ ላላቸው ሴቶች ማኅበረሰብ እንዴት እንደምመራ አውቃለሁ።"

የሎቪና ቡድን ብቸኝነት በአካል እና በአእምሮ ጤና ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ለመቅረፍ የመፍትሄ አካል ሊሆን ይችላል፣ ይህ ጉዳይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴን ካቆመ በኋላ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎችን እየጎዳ ያለ ይመስላል።

በዓለም ዙሪያ ከአምስት ሰዎች አንዱ ማህበራዊ መገለል ሊያጋጥመው እንደሚችል ተነግሯል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለ 2026 ግኝቶችን ለማሰባሰብ በማኅበራዊ ግንኙነት ላይ ልዩ ኮሚሽን ያቋቋመ ሲሆን የአሜሪካ የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ኃላፊ ብቸኝነትን እንደ ማኅበረሰብ ጤና ቅድሚያ እንዲሰጠው በይፋ አሳስበዋል ።

ሎቪና "እኛ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ላሉ ህንዳውያን ሴቶች እንደ የሩቅ ቅርብ ከቤት ርቀን ቤት ነን " ትላለች። ይህ ለእኛ ትልቁ የድጋፍ ስርዓት ነው ብዬ አስባለሁ"