የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር አምስቱ ተሿሚዎች ማን ናቸው?

(ከግራ ወደ ቀኝ) ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ፣ ብ/ጄ ገብረ እግዚአብሔር በየነ፣ አሰፋ አብርሃ፣ ⁠ዶ/ር ሺሻይ አማረ እና ረዳኢ ኃለፎም
የምስሉ መግለጫ, (ከግራ ወደ ቀኝ) ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ፣ ብ/ጄ ገብረ እግዚአብሔር በየነ፣ አሰፋ አብርሃ፣ ⁠ዶ/ር ሺሻይ አማረ እና ረዳኢ ኃለፎም
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

በትግራይ ጦርነት ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ የክልሉን በርካታ አካባቢዎች የተቆጣጠረው የፌደራል መንግሥት፣ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይን የሚመራ ባለአደራ አስተዳደር መቋቋሙን አርብ ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።

"የህወሓት አመራር ለአራተኛ ጊዜ የጀመረው አውዳሚ ጦርነት ለአራተኛ ጊዜ በህወሓት ሽንፈት ተጠናቋል" ያለው የፌደራል መንግሥት፣ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በክልሉ ምርጫ የማድረግ እቅድ እንዳለውም አስታውቋል።

እስከዚያው ድረስ ክልሉን እንዲመራ የተሰየመው ባለአደራ አስተዳደር፣ "የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች የማቅረብ እና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን" የማመቻቸት ኃላፊነት ተጥሎበታል።

በትግራይ ክልል የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር፣ የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ መዘርጋት እንዲሁም የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደየቀያቸው መመለስ የሚሉትም ከኃላፊነቶቹ መካከል ናቸው።

"በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ" የሚቆየው ይህ አስተዳደር "ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ" እንደሚንቀሳቀስ እንዲሁም "ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ" እንደማይሠራ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባለአደራ አስተዳደሩን እንዲመሩ ለስድስት ግለሰቦች ሹመቶችን ሰጥተዋል። አምስቱ ግለሰቦች የተለያዩ ዘርፎች ዋና አስፈጻሚዎች ሲሆኑ አንዱ ደግሞ የመቀለ ከተማ ከንቲባ ሆነዋል።

ቢቢሲ ስለ ስድስቱ ተሾሚዎች ማንነት የሚከተለውን አጠናቅሯል።

አሰፋ አብርሃ

አሰፋ አብርሃ

የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት አሰፋ አብርሃ የታዋቂው ፖለቲከኛ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ስዬ አብርሃ ወንድም ናቸው። የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ድርድር ወቅትም ህወሓትን ከወከሉ ተደራዳሪዎች አንዱ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በወታደራዊው ደርግ ዘመነ መንግሥት በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ሲመራ የነበረውን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለመክፈት በወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው።

ከ1986 እስከ እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር የነበረውን የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በኃላፊነት መርተዋል። በዚህ ኃላፊነታቸው ወቅት በመንግሥት ሥር የነበሩ ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ የተዛወሩበትን ሂደት መርተዋል።

በድኅረ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በህወሓት ውስጥ ከተፈጠረው መከፋፈል በኋላ አራቱ ወንድማማቾች ስዬ፣ አሰፋ፣ ምህረተአብ እና ፍሰሐ አብርሃ በሙስና ወንጀል ታስረው ነበር። ስዬ ለሰባት ዓመታት በእስር ከቆዩ በኋላ በ2000 ዓ.ም. ተለቅቀዋል።

አሰፋ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸው ዲግሪያቸውን ያገኙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው ሲቲ ኤንድ ጂርጅ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ደግሞ በኢንጂነሪንግ ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪ ይዘዋል።

አሰፋ አብርሃ
የምስሉ መግለጫ, አሰፋ አብርሃ

ከእስር ከተፈቱ በኋላ 'ራህዳን ኢንጂነሪንግ ኤን ሰፕላይ' እንዲሁም 'ወለባ ቢዝነስ ኤንድ ኮንሰልታንሲ ሰርቪስ' የተባሉ የግል ተቋማትን መርተዋል። 'ኩሽ ኤንድ ኪ ኮንሰልታንሲ' በተባለ ድርጅት አማካኝነትም ለደቡብ ሱዳን መንግሥት በአማካሪነት ሠርተዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እና ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥም በአማካሪነት እንዳገለገሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ2013 ዓ.ም. የትግራይ ጦርነት ከተነሳ በኋላ በውጭ አገራት "በዲፕሎማሲ ሥራ" ላይ ተሰማርተው የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱን ለመቋጨት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተደረገው ድርድር ወቅትም ህወሓትን ከወከሉ ግለሰቦች አንዱ ነበሩ።

ከስምምነቱ በኋላ በተመሠረተው እና በጌታቸው ረዳ ይመራ በነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በአማካሪነት አገልግለዋል። በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ መካከል ክፍፍል በተፈጠረበት ወቅት ከአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጎን ነበሩ።

ከህወሓት ጋር የተለያዩ ፖለቲከኞች፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ በአዲስ አበባ ያቋቋሙት "የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት" አባል ከነበሩ ፖለቲከኞች አንዱ አሰፋ ናቸው።

በኃይል ሥልጣን የተቆጣጠረውን በህወሓት የሚመራ አስተዳደር ለመጣል ሲንቀሳቀስ የነበረ ይህ ምክር ቤት፣ የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር መቋቋሙ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ከአሁን በኋላ "በተቋቋመበት አደረጃጀት" እንደማይቀጥል በይፋ አስታውቋል።

ብ/ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥሩ)

ብ/ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ

በመስከረም አጋማሽ በተቀሰቀሰው ውጊያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የተዋጋው ብቻውን አይደለም። ከትግራይ ኃይሎች በተለዩ ወታደራዊ አዛዦች የሚመራው 'የትግራይ ሠላም ኃይል' የተባለው ታጣቂ ቡድን ከፌደራል መንግሥት ጎን ተሰልፏል።

የዚህ ታጣቂ ቡድን ዋነኛ መሥራች አሁን በባለአደራ አስተዳደሩ ውስጥ የፀጥታ እና ሰላም ዋና አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ብርጋዴር ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ናቸው።

ወዲ አንጥሩ በሚል ቅፅል ስማቸው ይበልጥ የሚታወቁት ብ/ጄነራል ገብረእግዚአብሔር ህወሓት ከደርግ መንግሥት ጋር ሲያደርግ የነበረውን የትጥቅ ትግል የተቀላቀሉት በ1974 ዓ.ም. መሆኑን ይናገራሉ። ኢህአዴግ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች አገልግለዋል።

የብርጌድ መሪ እንዲሁም የክፍለ ጦር አዛዥ ሆነው ሠርተዋል። የትግራይ ጦርነት ከመቀስቀሱ ጥቂት ወራት ድረስም ዋና መቀመጫውን ኩሓ ላይ ባደረገው እና ለጦርነቱ መጀመር ቀጥተኛ ምክንያት የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ ነበሩ።

ጦርነቱ ከመነሳቱ ወራት አስቀድሞ ከመከላከያ ሠራዊት በጡረታ የተሰናበቱት ብ/ጄነራል ገብረእግዚአብሔር፣ ግጭት ሲነሳ ከትግራይ ኃይሎች ጎን ተሰልፈዋል። ከጦርነቱ ጅማሮ አንስቶ ከትግራይ ኃይሎች ጎን ከነበሩ ወታደራዊ አዛዦች አንዱ እንደሆኑም ይናገራሉ።

በትግራይ ኃይሎች ውስጥ በነበራቸው ቆይታ የኮር እንዲሁም አርሚ መሪ መሆን አገልግለዋል። ወዲ አንጥሩ ሲመሩት የነበረው 'አርሚ 50' ተጠቃሽ ከሆኑ የትግራይ ኃይሎች ወታራዊ አሃዶች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። ይህንን 'አርሚ' ማደራጀታቸውን ይገልጻሉ።

የትግራይ ሰላም ኃይል አባላት መሬት ላየ ተቀምጠው

ወዲ አንጥሩ እንደሚያስረዱት፣ ከትግራይ ኃይሎች የተለዩት በህወሓት እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል የተፈጠረው ክፍፍል በወታደራዊ አዛዦች ዘንድም ሲንጸባረቅ ነው። በጥር 2017 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት "ኮር እና ከኮር በላይ" ያሉ የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ አዛዦች ጌታቸው ረዳ ከኃላፊነት እንዲነሱ ውሳኔ ካስተላለፈው ህወሓት ጎን እንደሚቆሚ አስታውቀው ነበር።

ይህ ውሳኔ አቋማቸውን ያስቀየራቸው ወሳኝ ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ወዲ አንጥሩን ጨምሮ ከ10 በላይ ወታደራዊ አመራሮች ይህንን ተከትሎ ከትግራይ ኃይሎች ተለይተዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወዲ አንጥሩ ከትግራይ ኃይሎች ከተለዩ ሌሎች አመራሮች እና ወታደሮች ጋር በመሆን 'ሓራ መሬት' በሚል ሲጠራ የነበረውን ታጣቂ ቡድን አቋቁመዋል።

መጀመሪያ ከትግራይ ጋር አዋሳኝ በሆነው አፋር ክልል ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረው ይህ ቡድን በኋላ በደቡባዊ እና ምዕራባዊ የክልሉ ስፍራዎች ይዞታውን አስፋፍቷል።

ኋላ ላይ "የትግራይ የሰላም ኃይል" የሚል ስያሜ የያዘው ይህ ቡድን በአምስት ግንባሮች እንደሚንቀሳቀስ ይገልጻል። በአሁኑ ውጊያም ከፌደራል መንግሥት ጎን ተሰልፎ ከትግራይ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ነው።

የታጣቂ ቡድኑ ዋና አዛዥ የሆኑት ብ/ጄነራል ገብረእግዚአብሔርም በትግራይ የባለአደራ አስተዳደር ውስጥ የፀጥታ እና ሰላም ዘርፍን በዋና አስፈጻሚነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተሹመዋል።

⁠ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ

ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ

የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚነት ሹመት የተሰጣቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ በፖለቲካዊ ተሳትፎ እምብዛም የሚታወቁ አይደሉም።

አብዛኛው የሥራ ዘመናቸውን በምሁርነት ያሳለፉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፖለቲካው መድረክ የመጡት የትግራይ ጦርነት ከተነሳ በኋላ 2013 ዓ.ም. በተቋቋመው እና በዶ/ር ሙሉ ነጋ ይመራ በነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር አማካኝነት ነው።

የፌደራል መንግሥት በዚያው ዓመት ሰኔ ላይ ትግራይን ለቅቆ እስከሚወጣ ድረስ ሽረ እና አከባቢውን የሚያጠቃልለው የሰሜን ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ። ይህንን ኃላፊነት ከያዙ በኋላም ገዢው ብልፅግና ፓርቲን በመቀላቀል ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወቅቱ የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከፌደራል መንግሥት ጋር ከትግራይ ከወጡ በኋላ ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ወደ ከ2014 እስከ 2016 ዓ.ም. ወደ መምህርነት ተመልሰው ቆይተዋል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ በሙያቸው የፊዚክስ ምሁር ሲሆኑ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ለስልኮች አገልግሎት ላይ እንደሚውለው 'ሊትየም አዮን ባትሪ' ባሉ ጉዳዮች ላይ ምርምር በሚደረግበት 'አድቫንስድ ማቴሪያል ሪሰርች' ላይ ይሠራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና አምስቱ የባለአደራ አስተዳደር ተሿሚዎች
የምስሉ መግለጫ, የባለአደራ አስተዳደሩ "ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት ማድረግ" እንዳለበት ፌደራል መንግሥት አስታውቋል

በፊዚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በ1994 ዓ.ም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከዚያው ዩኒቨርሲቲ በ'ሶሊድ ስቴት ፊዚክስ' ሠርተዋል። 'አድቫንስድ ማቴሪያል ሪሰርች' ላይ ያተኮረውን ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት ደግሞ በሕንድ ከሚገኘው አንድራ ዩኒቨርሲቲ ነው።

ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ መሥራች አባላት አንዱ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ወደ መንግሥት አስተዳደር እስከሚመጡበት ጊዜ ድረስም በዚያው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በኮሌጅ ዲንነት እንዲሁም በመምህርነት ሲሠሩ ነበር።

ከጀመሪያው ጊዜያዊ አስተዳደር በኋላም እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያስተምሩ ቆይተዋል። ቀጥሎም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ በኃላፊነት ሠርተዋል።

"አሁን ደግሞ ወቅቱ ደርሶ መንግሥት ወደ ትግራይ ሲመለስ በተደረገልኝ ጥሪ ሕዝቤን ለማገልገል በተሰጠኝ ተልዕኮ ተሰማርቻለሁ" ሲሉ በባለአደራ አስተዳደሩ ውስጥ ስለተሰጣቸው የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚነት ሹመት ተናግረዋል።

ረዳኢ ኃለፎም

ረዳኢ ኃለፎም

የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ ኃላፊነትን የያዙት ረዳኢ ኃለፎም፣ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ የፖለቲካ አመራር ናቸው። በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅትም ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተሰልፈው ነበር።

የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ በጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዜያዊ አስተደዳር ሲቋቋም የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤትን በኃላፊነት መርተዋል።

ከሁለት ዓመቱ ጦርነት አስቀድሞም በዚሁ ኃላፊነት ላይ የሠሩ ሲሆን የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪም ነበሩ።

ከህወሓት ጋር በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት ከፕሬዝዳንቱ ጌታቸው ረዳ ጋር ወደ አዲስ አበባ ከሸሹት የጊዜያዊ አስተደዳሩ በአመራሮች አንዱ ናቸው።

ከህወሓት የተለዩት እነዚህ አመራሮች ባቋቋሙት ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ምሥረታ ውስጥ ሚና ነበራቸው።

ዶ/ር ሺሻይ አማረ

ዶ/ር ሺሻይ አማረ

በፌደራል መንግሥት የመቀለ ከተማ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ሺሻይ አማረም በተመሳሳይ ስምረት ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ አላቸው። የፓርቲው ምክር ቤት አባል እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የተወለዱባትን ከተማ በከንቲባነት እንዲመሩ የተመረጡት ዶ/ር ሺሻይ የትምህርት መስካቸው ኢንጂነሪንግ ነው። በ2000 ዓ.ም. ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። በማኑፋክቸሪንግ ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪ የያዙት ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው።

ከሕንዱ 'ኢንዲያን ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ዴልሂ' በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በመቀለ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ዶ/ር ሺሻይ፣ በ2015 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮን መርተዋል።

በ2018 ዓ.ም. መጨረሻ በስምረት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና በኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ፣ የፓርቲው አመራር ላይ ቅሬታ ካቀረቡ የምክር ቤት አባላት አንዱ ዶ/ር ሺሻይ መሆናቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኮሚሽኑን በመደገፍ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታ ያቀረቡት ዶ/ር ሲሻይን ጨምሮ ሰባት የምክር ቤት አባላት፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከፓርቲውን የሥነ ምግባር ደንብ እና ከምርጫ ሕጉ ውጪ ተንቀሳቅሷል የሚል ክስ አቅርበዋል። የፓርቲው ማናቸውም ስብሰባዎች እና ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲታገዱ ጠይቀው ነበር።