በአገራቸው ላይ አደገኛውን ስለላ ለዩክሬን የሚያካሂዱት ፀረ ፑቲን ሩሲያውያን

ስለላ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ሁለት ሩሲያውያን በምሥጢር ለዩክሬን የስለላ ተቋም ሲሠሩ እንደነበር ይናገራሉ። በሩሲያ የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማት እና ግለሰቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አንደኛውን ለዚህ ዘገባ ስንል ኢቫን ብለን እንጠራዋለን። በሩሲያ ላይ የተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ላይ መሳተፉን ይናገራል።

እነዚህ ጥቃቶች የተሰነዘሩት ከዩክሬን ነው። የቦምብ እና ሌሎችም ጦር መሣሪያ ማምረቻዎችን ዒላማ አድርገዋል።

ሩሲያ ላይ የሚፈጸሙ ምሥጢራዊ ጥቃቶችን በተመለከተ ለቢቢሲ ተናግሯል። በስደት ፖላንድ የሚኖረው እና ለዚህ ዘገባ ፎማ የምንለው ሩሲያዊም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥቷል።

ፖላንዳዊው ጋዜጠኛ ማርሲን ማሞን የኢቫን እና ፎማን ምስክርነት ወደ ዘጋቢ ፊልም ለውጧል።

ፎማ በሩሲያ የሚንቀሳቀሱ በጎ ፈቃደኞች መረብን ይመራል።

በጎ ፈቃደኞቹ ከፍተኛ የሩሲያ ባለሥልጣናትን ይከታተላሉ። እነዚህ ባለሥልጣናት የዩክሬን ስለላ ተቋም (ጂዩአር) ዒላማ ለማድረግ የሚከታተላቸው ናቸው።

ፎማ እንደሚለው በጎ ፈቃደኞቹ በቀጥታ ጥቃት ላይ አይሳተፉም። የትኞቹን ባለሥልጣናት እንደሚከታተሉም አልገለጸም።

አምና ሞስኮ ውስጥ ሌተናንት ጄነራል ፋኒል ሳርቫሮቭ ሲገደሉ ግን ፎማ የስለላ መረጃ ለዩክሬን ማቀበሉን ተናግሯል።

ከዚህ በፊትም ሩሲያ ውስጥ በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ የስለላ ባለሙያዎች እንዳሉ ይነገር ነበር።

አምና ሞስኮ ውስጥ ሌተናንት ጀነራል ፋኒል ሳርቫሮቭ ተገድለዋል
የምስሉ መግለጫ, አምና ሞስኮ ውስጥ ሌተናንት ጀነራል ፋኒል ሳርቫሮቭ ተገድለዋል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን እንደ ኢቫን ያሉ ሥራውን የሚያከናውኑ ሰዎችን ማግኘት ቀላል አይደለም።

የዩክሬን የስለላ ተቋም ኢቫን እና ፎማ ሠራተኞቹ መሆናቸውን አረጋግጧል።

የኢቫን የቅርብ አለቃ ምን ያህል እንደሚያምነው ሲጠየቅ "ከዚህ በኋላ እርግጠኛ መሆን አልችልም፤ የማምነው ራሴን ብቻ ነው" ብሏል።

የዩክሬን የስለላ ተቋም እንዲሁም ሠራተኞቹ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ይቆጠባሉ። በዚህ ምክንያትም ስለ እንቅስቃሴዎቻቸው አጠቃላይ ምሥል ማግኘት ይከብዳል።

ኢቫን እና ፎማ የሚጠቀሟቸው የስለላ መንገዶች የዩክሬን የስለላ ተቋምም የሚተገብራቸው ናቸው።

ዩክሬን የተቀናጀ የድሮን ጥቃት እንደምትፈጽም ከዚህ ቀደም አስታውቃለች። በሩሲያ ላይ ለምትፈጽማቸው ጥቃቶች ምሥጢራዊ ሰላዮችን እንደምታሰማራም አረጋግጣለች።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ሩሲያ ውስጥ የፖለቲካ ግድያዎች ተበራክተዋል።

ዩክሬን ለተፈጸሙት ጥቃቶች በይፋ ኃላፊነት አትወስድም። ነገር ግን የዩክሬን የስለላ ተቋም ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት በሌተናንት ጄነራል ፋኒል ሳርቫሮቭ ግድያ ውስጥ እጃቸው አለበት።

የሩሲያው ወታደራዊ ባለሥልጣንደ የተገደሉት ታኅሣሥ 2025 ላይ ነበር።

ምን ያህል ሩሲያውያን ለዩክሬን እንደሚሠሩ በትክክል አይታወቅም። ፎማ እንደሚለው ከሆነ ግን ቁጥራቸው ከ300 እስከ 500 ሊደርስ ይችላል።

በእርግጥ ይህንን አሐዝ ለማረጋገጥ ቀላል አይደለም።

ኢቫን እና ፎማ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ይነቅፋሉ። የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አገዛዝም ያወግዛሉ።

የጦርነቱ ውጤት የፑቲንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደሚወስን ያምናሉ።

"አሁን ላይ የፑቲን አስተዳደር በጦርነቱ ከተሸነፈ የሚወድቅ ይመስለኛል። እኛም ይሄንን ለማፋጠን እንሠራለን" ይላል ኢቫን።

ኢቫን ለፖላንዳዊው ጋዜጠኛ ማርሲን ማሞን እንደነገረው፤ ወታደራዊ ተቋማትን መሰለል እና ሩሲያ ላይ የድሮን ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ድሮኑ የሚደበቅበትን ቦታ መፈለግ የሥራው አካል ነው።

"እነዚህ ድሮኖች ኃይለኛ መሣሪያ ናቸው። አንድ ጊዜ ሲተኮሱ የሚያደርሱት ውድመት በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ከፍተኛ ገንዘብ ያስወጣል" ይላል።

ኢቫን በሩሲያ አየር ኃይል አቅራቢያ ተቀጣጣይ ሲደብቅ የሚያሳይ ቪድዮ ለዘጋቢ ፊልም ሠሪው ጋዜጠኛ ልኳል።

ድርጊቱን ሲፈጽም ቢያዝ በአገር መክዳት ተከስሶ ለአሥርት ዓመታት እስራት ይፈረድበታል።

የፎማ ኃላፊነት ከዚህ የተለየ ነው። በሩሲያ በጎ ፈቃደኞችን ያሠለጥናል።

ስለላ እንዲደረግበት የተመረጠ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣንን እንዴት መከታተል እንደሚቻል ትምህርት ሲሰጥ ዘጋቢ ፊልም ሠሪው ጋዜጠኛ ተመልክቷል።

"ከእኔ ወይም ከሥራ ባልደረባዬ የሚሰጥህ ሰነድ የምትከታተለውን ሰው ማንነት ይገልጻል። የምትከታተለው ሰው ምሥል፣ ዕድሜ እና ሌሎችም ግላዊ መረጃዎችን የያዘ ሰነድ ነው። መኪና ካለው ስለ መኪናውም መረጃ ይሰጥሀል። ይሄንን ግለሰብ ስትከታተል ስልክህን ይዘህ መሄድ የለብህም" ሲል ያስረዳል።

ሩሲያውያን በምሥጢር ለዩክሬን የስለላ ተቋም ይሠራሉ
የምስሉ መግለጫ, ሩሲያውያን በምሥጢር ለዩክሬን የስለላ ተቋም ይሠራሉ

ፎማ አንድ ወቅት ላይ በሩሲያ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል ነበር። ውስጥ አዋቂ በመሆኑም በርካታ መረጃዎች አከማችቷል።

ኮምፒውተሩ ላይ ወታደራዊ ዒላማዎችን እንዴት እንደሚያደራጅ ይናገራል።

"ይሄ የመረጃ ቋት ነው። መጋዘን እና ወታደራዊ መቀመጫ የት እንዳለ ማየት ይቻላል። ጄነራሎች የት እንደሚኖሩ እና ዩክሬን ላይ የቦምብ ጥቃት የሚያደርሱ ፓይለቶቸ የት እንደሚኖሩ ማየት ይቻላል። ሥርዓቱ እንዲንኮታኮት መጀመሪያ ላይ ሥርዓቱ እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ ያስፈልጋል። ሥርዓቱን መረዳት ክፍተቱን ለማግኘት ይረዳል" ይላል።

በስለላ መረቡ ውስጥ ወደ 30 ሰዎች እንዳሉት እና በዩክሬን፣ በሩሲያ እንዲሁም በአውሮፓም እንደሚሠሩ ይናገራል።

ከሩሲያ ውጭ ያለው ቡድን ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን ዲጂታል እንቅስቃሴ በተመለከተ መረጃ የመስጠት እና የመከታተል ኃላፊነትን ይወጣል።

የዩክሬን የስለላ ተቋም ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን መከታተልን እንደሚያበረታታ ፎማ ይናገራል።

ፎማ የሚመራው ቡድን ክትትል የሚደረግባቸው ሰዎች ወታደራዊ ወንጀል የፈጸሙ ስለመሆናቸው ያጣራል።

"እኛም የሚሰጠንን መረጃ እናጣራለን። ሥራውን ለማከናወን የምንወስነው ከዚህ በኋላ ነው" ይላል።

"ለፑቲን እና ለሩሲያ ብለው ዩክሬን ላይ ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ዋጋ መክፈል እንዳለባቸው እንዲያውቁ እፈልጋለሁ። መፍራት አለባቸው" ሲልም ፎማ ይናገራል።

ፎማ ኃላፊነቱ ለዩክሬናውያን የስለላ መረጃ ማቀበል ብቻ እንደሆነ ይናገራል። ፖለቲካዊ ግድያ ግን እንደማይፈጽሙ ገልጿል።

ሌተናንት ጄነራል ፋኒል ሳርቫሮቭ ከተገደሉ በኋላ "እሱን መከታተል ከባድ ጥረት ይጠይቅ ነበር። የሚኖረው ከውሽማው ወይም ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ነበር። በየጊዜው መንገዱን እና የዕለት ውሎ ዕቅዱን ስለሚቀያይር ለመከታተል ያስቸግራል" ሲል ተናግሯል።

ፎማ ፖለቲካዊ ግድያው ከመፈጸሙ በፊት እና በኋላም ዘጋቢ ፊልም ለሠራው ጋዜጠኛ ወይም ለቢቢሲ የስለላ ዕቅዱን አልተናገረም።

ፎማ በዩክሬን እና በሩሲያ ካሉት የስለላ ባልደረቦቹ ጋር ከተነጋገረ በኋላ፤ ኢቫን የሩሲያ ግዙፉ የድሮን አምራች ፋብሪካ 'ላቡጋ' ላይ ጥቃት ለማድረስ እያቀደ እንደነበር አውቋል።

በዚህ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉ ተገልጿል።

ኢቫን እንደሚለው ሁሌም ቢሆን ንጹኃን እንዳይሞቱ ጥንቃቄ ይደረጋል። የሚያከናውናቸው ኦፕሬሽኖች እሱንም አደጋ ውስጥ ይከቱታል።

"አንድ ጊዜ መኪናዬ ለፍተሻ እንዲቆም ተደረገ። በጣም አደገኛ ክስተት ነበር። ቤት ውስጥ የሠራሁትን ተቀጣጣይ ፈንጂ ይዤ ነበር። ነገር ግን አልተያዝኩም" ይላል።

ሥራው እንዳይጋለጥ ለማድረግ መከተል ያለበት ግልጽ አሠራር የለም።

ኢቫን በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማንነት አያውቅም። ፎማም ተመሳሳይ አሠራር ይከተላል።

"ሰዎች በቡድን ተሰብስበው መረጃ ሲለዋወጡ ኢንተርኔት ላይ ጥለው የሚያልፉት አሻራ ይኖራቸዋል። ይሄ ማለት በቀላሉ አጠቃላይ ቡድኑ በቁጥጥር ሥር ሊውል ወይም ሊከስም ይችላል ማለት ነው" ሲል ያስረዳል።

ኢቫን እንደሚለው ይሄንን ሥራ የሚያከናውኑ ጥቂት ሰዎች ሩሲያ ውስጥ ይገኛሉ። አብዛኞቹ ግን በርዕዮተ ዓለም ልዩነት ከአገር እንደወጡ ወይም ለእስራት እንደተዳረጉም ይገልጻል።

ፖላንዳዊው ጋዜጠኛ ማርሲን ማሞን
የምስሉ መግለጫ, ፖላንዳዊው ጋዜጠኛ ማርሲን ማሞን

በሩሲያ የስለላ ሥራ ከሚያከናውኑ የአገሪቱ ዜጎች መካከል ገንዘብ የሚከፈላቸው ይገኙበታል።

ኢቫን እንደሚለው ግን ሥራውን የሚያከናውነው በርዕዮተ ዓለም አቋሙ ምክንያት ነው። የተቃዋሚ ፖለቲከኞች አባልም ነበር።

ኢቫን በሩሲያ ባለሥልጣናት የቅርብ ክትትል እንደሚደረግበት ይገመታል። ወደ ሩሲያ በነጻነት እየገባ መውጣቱ ጥያቄ የሚያስነሳውም ለዚህ ነው።

ዘጋቢ ፊልም ከሠራው ጋዜጠኛ ጋር የተነጋገሩት በጆርጂያ በረሃ ነው። ዩክሬናውያን እንዴት ኢቫንን እንደሚያምኑት ጋዜጠኛው ሲጠይቀው "ዩክሬን ሄደን እውነት ወይም ውሸት መናገራችንን ለማወቅ ምርመራ ይደረግልናል" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

በዩክሬን የስለላ ተቋም የሚሠራው የኢቫን የቅርብ አለቃ እንደሚለው፤ ኢቫን በድብቅ ለሩሲያ እየሰለለ ሊሆን እንደሚችል መጠራጠሩ አልቀረም።

ኢቫን በፈቃዱ ወይም ተገድዶ ለሩሲያ ሊሠራ ይችላል ብሎ ማመኑ እንዳለ ሆኖ ኢቫን ለዩክሬን የስለላ ተቋም እንደሚሠራ ይናገራል።

ኢቫን ሩሲያ በነጻነት ገብቶ መውጣቱ አጠራጣሪ እንዳልሆነ ፎማ ይናገራል።

"የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ብዙ ክፍተቶች አሉ። እነዚህን ማወቅ ይረዳል። አንዳንዴ ዕድለኛ መሆንም ይረዳል። በአይብ መካከል የሚሽሎከሎክ አይጥ ማለት ነው" ይላል።

ኢቫን ለሩሲያ የስለላ ተቋም የሚሠራ ቢሆን ኖሮ ከዩክሬን ስለተቃጡ ጥቃቶች ለሞስኮ መረጃ ይሰጥ ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩክሬን ድሮኖች ጥቃት ሲፈጽሙ ለጋዜጠኛው መረጃ ሰጥቶ ነበር።

በሩሲያ ስትራቴጂክ የቦምብ እና ሌሎችም ጦር መሣሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎች ጥቃት እንደሚፈጸም ከመግለጽ ውጪ የትኞቹ ተቋማት ዒላማ እንደተደረጉ እና ጥቃቱ መቼ እንደሚደርስ አልተናገረም።

"ሁሌም ፍርሃት አለኝ። ሁሉም ቦታ ስሄድ ፍርሃት ይከተለኛል። ምንም ባላደርግም እፈራለሁ። ሩሲያ ውስጥ መሆኔን አትርሳ" ሲል ለጋዜጠኛው ተናግሯል።

ሥራው ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ አለው።

"ፑቲን ለዘለዓለም አይኖርም" ይላል።