ብቸኝነት በቀን 15 ሲጋራ የማጨስ ያህል ለጤና አደገኛ መሆኑ ተገለጸ

አንዲት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን አገሪቱ በወረርሽኝ ደረጃ ሊታይ የሚታይችል ጉልህ የብቸኝነት ችግር በዜጎቿ መካከል እየገጠማት መሆኑን አስጠነቀቁ።

የአሜሪካ ዋነኛ የጤና ባለሥለጣን የሆኑት ቪቬክ ሙርቲ እንዳሳሰቡት ብቸኝነት በቀን 15 ሲጋራ የማጨስ ያህል ለጤና አደገኛ ውጤት አለው።

የጤና ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረጉት የጤና ምክር መሠረት እራሳቸውን ከማኅበረሰብ በመነጠል ብቸኝነትን የሚመርጡ ሰዎች ከልክ እንዳለፈ ውፍረት ወይም እንደ አደንዛዥ ዕጽ ሁሉ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

ባለሙያው ባወጡት ማሳሰቢያ ላይ እንዳመለከቱት በተለያየ ሙያ እና የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ከሁሉም አሜሪካውያን መካከል ግማሽ የሚሆኑት የብቸኝነት ችግር እንደሚገጥማቸው ይታሰባል።

ይህንንም ችግር ለመቋቋም የሚያስችል በዜጎች መካከል ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጎለብት አገር አቀፍ ዕቅድን የጤና ባለሥልጣኑ ቪቬክ ሙርቲ ይፋ አድርገዋል።

ብቸኝነት የስኳር እና የልብ ህመምን፣ እንቅልፍ ማጣትን እና ከእድሜ ጋር የሚከሰትን የአእምሮ መዳከምን ጨምሮ በሌሎች የጤና ችግሮችን ምክንያት ከተገቢው ጊዜ ቀደም ብሎ ለሚከሰት ሞት መጨመር በ30 በመቶ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።

በተጨማሪም ብቸኝነት እና ከማኅበራዊ ትስስር መነጠል በትምህርት እና በሥራ ቦታ የሚገኝን ውጤት ዝቅተኛ ሊያደርገው እንደሚችል አሁን ይፋ የተደረገው የጤና ምክር አመልክቷል።

ይህ ብቸኛ የመሆን ችግር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተከስቶ የነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ፣ በርካታ ሰዎች ከተለያዩ ሰዎች ጋር የነበራቸውን የትስስር መጠን በመቀነስ ችግሩን አባብሶታል ተብሏል።

በማሳሰቢያው ላይ የተጠቀሰ አንድ ሪፖርት እንዳሳየው በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ በጥናቱ የተሳተፉት ሰዎችን የማኅበራዊ ግንኙነት በ16 በመቶ ቀንሷል።

ይህንን በሕዝቡ ውስጥ ስር እየሰደደ ያለውን የብቸኝነት ችግር ለመከላከል እና የባህል እና የፖሊሲ መፍትሄ ለማግኘት “በአገራችን ያለው ማኅበራዊ ትስስር መልሶ እንዲጠናከር የጋራ ጥረት ማድረግ” ያስፈልጋል ሲሉ ቪቬክ ሙርቲ ጥሪ አድርገዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥም የጤና ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች መረጃ እና ድጋፍ በመስጠት የሚሳተፉበት እንዲሁም አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት ዘዴ ተዘጋጅቷል።

ይህ የጤና ችግር ጉዳይ የጆ ባይደን አስተዳደር በአሜሪካ ውስጥ ያለውን የአእምሮ ጤና ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ የሚደረገው ሰፊ ጥረት አካል መሆኑን የዋት ሐውስ ፕሬስ ኃላፊ ካሪን ጂን ፒየር ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

በአውሮፓውያን አቆጣጠር ሰኞ ዕለት የጀመረው የግንቦት ወር በአሜሪካ ውስጥ የአእምሮ ጤና ግንዛቤን የማስፋፊያ ወር ነው።