የሕንድ ግዛት ጠጪ እና ከልክ በላይ ውፍረት ያላቸውን ፖሊሶች ከሥራ ልታሰናብት ነው

እጁ ብቻ የሚታይ መጠጥ የሚቀዳ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሕንድ አንድ ግዛት በሆነችው አሳም የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ የሆኑ እንዲሁም ከልክ በላይ የወፈሩ የፖሊስ አባላት ከሥራቸው ሊሰናበቱ ነው።

የግዛቲቱ ባለሥልጣናት እንዳሉት በተለይ የአልኮል መጠጥ ችግር አለባቸው የተባሉ 300 የሚደርሱ የፖሊስ መኮንኖች በፈቃዳቸው ሥራቸውን እንዲለቁ እየተጠየቁ ነው።

የግዛቲቱ ዋና አስተዳዳሪ ሂማንታ ቢስዋ ሳርማ እንደተናገሩት፣ በተጠቀሱት የፖሊስ ሠራዊቱ አባላት ዘንድ ያለው የአልኮል ሱሰኝነት ችግር ጤናቸው ላይ እክል እየፈጠረ በመሆኑ ከዕድሜያቸው ቀድመው ጡረታ እንዲወጡ ተጠይቀዋል።

አስተዳዳሪው ጨምረውም ከአልኮል መጠጥ ሱሰኞች የፖሊስ አባላት በተጨማሪ፣ ከልክ በላይ ውፍረት ያላቸው ፖሊሶች እንዲሁም፣ የሙስና ክስ ያለባቸው የፖሊስ መኮንኖችም በፈቃዳቸው ከሥራቸው እንዲሰናበቱ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል።

የግዛቲቱ አስተዳደር በተለያዩ ምክንያቶች በተገቢው ሁኔታ የፖሊስ ሥራቸውን ለማከናወን የማይችሉ አባላትን የማሰናበት ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ ዋና አስተዳዳሪው “ዋጋ የላቸውም” ያሏቸውን የፖሊስ አባላትን የሚያስወግድ እርምጃ እንደሚወስዱ ካሳወቁ በኋላ ነው።

በመጠጥ ሱስ፣ በከፍተኛ ውፍረት እና በሙስና የሚታወቁ አባላትን ከፖሊስ ሠራዊቱ ከተሰናበቱ በኋላ፣ የግዛቲቱ የፖሊስ አዛዦች የአባሎቻቸውን ሥነ ምግባር ከመከታተል ባሻገር፣ ሸንቃጣ እና ለሥራው ብቁ መሆናቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው አስተዳዳሪው አዘዋል።

የአልኮል ሱሰኝነት ከልክ ያለፈ ውፍረትን ጨምሮ ለተለያዩ ጤና ችግርች እና ለሙስና በር እንደሚከፍት የሚታመን ሲሆን፣ የግዛቲቱ አስተዳደርም እነዚህን ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ ለማስተካከል እየሰራ ነው።

በሕንድ ውስጥ የአልኮል ሱሰኝነት የተስፋፋ ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሠረት በሕንድ ካሉ ወንዶች መካከል አንድ ሦስተኛው አልኮል የሚጠጡ ሲሆን፣ ከሁሉም ሕንዳውያን መካከል ከ14 በመቶው የሚበልጡ እድሜያቸው ከ10 አስከ 75 ዓመት የሚሆኑት አልኮል ይጠጣሉ።

በዓለም ጤና ድርጅት ግምት መሠረት ደግሞ 11 በመቶ የሚሆኑ ሕንዳውያን ጠጪዎች ናቸው። ይህም ከአጠቃላዩ የምድራችን አማካይ የጠጪዎች አሃዝ ከሆነው 16 ከመቶ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው ተብሏል።