ካናዳውያን በሳምንት የሚጠጡትን የአልኮል መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ተመከሩ

የፎቶው ባለመብት, PAUL CHIASSON
ካናዳ ዜጎቿ በሳምንት የሚጠጡትን የአልኮል መጠጥ መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ከጤና ስጋት እራሳቸውን እንዲታደጉ መከረች።
መጠጥን በተመለከተ ለጤና ዋነኛ ጠቃሚ ውሳኔ መሆን ያለበት ከአልኮል ነጻ የሆነ ሕይወት ብቻ ነው ሲሉ የካናዳ ባለሙያዎች መክረዋል።
ነገር ግን ሰዎች መጠጣት ካለባቸው በሳምንት ሁለት ብርጭቆ ብቻ መጎንጨት በጤና ላይ የሚከሰትን ስጋት ዝቅ ያደርገዋል የሚለውን መመሪያ የካናዳ መንግሥት ደግፎታል።
ይህ ምክር ከአስር ዓመት በፊት መንግሥት ካስቀመጠው ገደብ በጣም በጣም ዝቅ ያለ ነው።
ቀደም ሲል አንድ ወንድ በሳምንት ቢበዛ አስራ አምስት ብርጭቆ ሴት ደግሞ አስከ 10 ብርጭቆ የሚደርስ አልኮል መጠጣታቸው ችግር የለውም ተብሎ ነበር።
የካናዳ የጤና መሥሪያ ቤት በገንዘብ የደገፈው አዲስ ሪፖርት እንዳለው መጠጥ አምራቾች በምርታቸው ላይ የጤና ማስጠንቀቂያዎችን መለጠፍ ግዴታ እንዲያደርጉ ይጠይቃል።
የካናዳ ግዛት በሆነችው ኦንታሪዩ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም ውስጥ ሳይንቲስት የሆኑት እና አዲሱ የአልኮል መጠጥ መመሪያን ካዘጋጁት መካከል አንዱ የሆኑነት ዶክተር ኤሪን ሆቢን “የዚህ መመሪያ ዋነኛ ዓላማ አልኮል በየትኛውም መጠን ለጤና ጥሩ እንዳልሆነ ማሳወቅ ነው” ብለዋል።
ጨምረውም “መጠጣት ግድ ከሆነ ግን በዝቅተኛ መጠን መጎንጨት የተሻለ ነው” ሲሉ አክለዋል።
በካናዳ ከዕጽ አጠቃቀምና ሱሰኝነት ጋር በተያያዘ በሚሰራው ማዕከል ይፋ የሆነው እና ወደ 90 ገጾች ያሉት ሪፖርት ቀደም ብሎ ዝቅተኛ የአልኮል መጠን የሚባለውን ትርጓሜ ፈትሿል።
ማዕከሉ ባወጣው ሪፖርት መሰረት 5 በመቶ የአልኮል መጠን ያላቸው ወይም 12 በመቶ የአልኮል መጠን ያለው ወይን የጡት እና የአንጀት ካንሰርን ጨምሮ ጎጂ ውጤቶችን እንደሚያስከትል አመልክቷል።
ምን አልባት ይህ ዜና በግርድፉ 80 በመቶ መጠጥ ለሚጎነጩት የካናዳ አዋቂዎች አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል።
“አዲሱ መመሪያ ትንሽ ሊያስደንግጥ ይችላል” የሚሉት ዶክትር ሆቢን “ሦስት መደበኛ መጠጦችን በየሳምንቱ መጎንጨት ለጭንቅላት እና ለአንግት ካንሰር የመጋለጥ ዕድል በ15 በመቶ ከፍ እንደሚያደርግና የመጠጡ መጠን በጨመረ ቁጥር የመጋለጥ ዕድሉም ከፍ እያለ እንደሚድ መስማት አዲስ መረጃ ይመስለኛል” ሲሉ አክለዋል።
ጨምረውም “አብዛኛው ካናዳዊ ሦስት መደበኛ መጠጦችን [ወደ 4.8 በመቶ የአልኮል መጠን ያላቸው እና 285 ሚሊ ሊትር የሚይዙ ሦስት ቢራ ብለን ልንይዘው እንችላልን] በሳምንት መጠጣት ብዙ አልኮል እንደመጠጣት አድርጎ አይቆጥረውም” ብለዋል።
እናም አዲሱ መመሪያ ቀደም ሲል በግርድፉ በቀን ሁለት የአልኮል መጠጦችን መጎንጨትን ዝቅተኛ አድርጎ ይቆጥረው ነበር። ሆኖም ይህ ምክረ ሀሳብ በሳምነት ሁለት ወደሚል መቀየሩ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የጤና እና ሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ጃኮብ ሼሊ “የተሰበሰበው መረጃ እስካሁን ስንለካበት የነበረውን መንገድ እና ምንነትን ቀይሯል” ብለዋል።
አዲሱ የካናዳ የአልኮል መጠጦች መመሪያ ከበርካታ የምዕራባውያን አገራት የተለየ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 አውስትራሊያ ባሰተመችው ብሔራዊ መመሪያ 10 መደበኛ መጠጦችን በሳምንት መውሰድን ትምክራለች። ፈረንሳይም ተመሳሳይ መመሪያ አላት።
አሜሪካም በቀን ወንዶች ከሁለት ሴቶች ደግሞ ከአንድ የዘለለ መጠጥ እንዳይጎነጩ የምታሳስብ ሲሆን፣ ዩናይትድ ኪንግደምም እንዲሁ፣ በሳምንት ከስድስት ብርጭቆ የዘለለ ቢራ ወይም ወይን መጠጣትን አትመክርም።
የካናዳ ሳይንቲስቶች መጠጥን ፍጽሞ አትጡ ብለው የመከሩ የመጀመሪያዎቹ አይደሉም። እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 የኔዝርላንድስ ጤና መማክርት የአልኮል መጠጥ ፍጽሞ አትጠጡ ግድ ከሆነ በቀን ከአንድ መደበኛ መጠጥ አትዝለሉ የሚል ምክረ ሃሳብ ይፋ አድርገው ነበር።
ሆኖም ለመጠጥ ፍቅር ያላቸው ካናዳውያን ይህ አዲስ ምክረ ሀሳብ የለመዱትን የአልኮል መጠጥ እንዲቀንሱ ስለማድረጉ ማንም እርግጠኛ አይደለም።
በዓለም አቀፍ የሱስ ዳሰሳ ጥናት መሠረት ካናዳ ከአንድ እስከ አስር ባለው ደረጃ ባትቀመጥም “የስካር ዝርዝር” በሚለው ከአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በመቀጠል 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጣለች።
“በካናዳ አልኮል የባህላችን ትልቅ አካል ነው። እንደ መደበኛ ነገር ነው የሚቆጠረው። በማኅበረሰቡ ዘንድም ትልቅ ተቀባይነት አለው” የሚሉት ሳይንቲስቷ ዶክተር ሆቢን “በልደት፣ በሠረግ ወይም ስፖርታዊ ጨዋታዎች እየተመለከቱ መጠጣት የተለመደ” መሆኑን ይናገራሉ።
በካናዳ ከዕጽ አጠቃቀም እና ሱሰኝነት ጋር በተያያዘ በሚሰራው ማዕከል ውስጥ የሚሰሩ ሳይንቲስቶች ሲጋራዎች ላይ እንደሚደረገው ሁሉ በአልኮል መጠጦች ላይ የሚያስከትሉት የጤና ጉዳት ማሸጊያዎች ላይ እንዲሰፍር አስገዳጅ ማድረግ ጠቃሚ እና ቀዳሚ እርምጃ ነው ይላሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 በካናዳዋ ዩኮን ከተማ የተደረገ ሳይንሳዊ ሙከራን የሚጠቅሱት ዶክትር ሆቢን፣ በዚያ ጊዜ በመጠጥ መሸጫ ሱቅ ውስጥ መጠጥ ያለውን የጤና ጉዳት የሚያሳይ ማስጠንቀቂያ መለጠፉን ያስታውሳሉ።
ያም ማስጠንቀቂያ አልኮል በነፍስ ወከፍ የሚሸጥበትን መጠን ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር በ7 በመቶ እንደቀነሰው ጠቁመዋል።
በካናዳ በብሔራዊ ደረጃ ይህንን አይነት ማስጠንቀቂ አስገዳጅ ለማድረግ ግን ከካናዳ የጤና መሥሪያ ቤት ድጋፍን ይፍልጋል።
መሥሪያ ቤቱ በካናዳ የዕጽ አጠቃቀም እና ሱሰኝነት ላይ የሚያተኩረው ማዕከለል ስላቀረበው ምክረ ሃሳብ ምስጋናውን አቀርቧል። አክሎም የአልኮል ጉዳይ “አሳሳቢ እና የተወሳሰበ የሕብረተሰብ ጤና እና ደኅንነት ጉዳይ ነው” ሲል ለቢቢሲ በሰጠው መግጫ ጠቁሟል።
ሆኖም በመጠጦች ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ ማድረግን በተመለከተ አስተያየት አልሰጠም።












