አሰቃቂ ምስሎችን የሚያዩ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የፌስቡክ ሠራተኞች ብሶት

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቀድሞው የፌስቡክ የይዘት ተቆጣጣሪ (content moderator) ሥራው የአእምሮ ጤንነቱ ላይ ስላመጣው ጫና ለቢቢሲ ይናገራል።

ሰዎችን ራሳቸውን ሲያጠፉ ከሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ጀምሮ በጣም አሰቃቂ የሚባሉ ይዘቶችን ይቆጣጠራ። እኒህ ይዘቶች የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ጋር እንዳይደርሱ ይጥራል።

ግለሰቡ ኬንያ መዲና ናይሮቢ መቀመጫውን ባደረገ አንድ የቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ የሚሠራ ነው።

ፌስቡክ አፍሪካ ውስጥ በጣም አስከፊ እና አሰቃቂ የሚባሉ ይዘቶችን እየተቆጣጠረ አይደለም የሚል ወቀሳ በተደጋጋሚ እያስተደናገደ ይገኛል።

እሱ “ማሽን መሰል” ሲል በሚጠራው የናይሮቢ ቢሮ ካለው ኮምፒውተር ፊት ቁጭ ብሎ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አሰቃቂ ይዘት እንዳይመለከቱ ይቆጣጠራል።

ነገር ግን እነዚህ ይዘቶች እሱ ላይ ከሚያደርሱት ተፅዕኖ የሚጠብቀው የለም።

“ስለ ወሲብ ያለኝ ግንዛቤ አሁን ትርጉም አልባ ሆኗል” ይላል።

“ሰዎች ከእንስሳት፣ ከሕፃናት፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲብ ሲፈፅሙ እናያለን። ይህም በጣም ብዙ ጊዜ ይገጥመናል። ሁሉም የምር የሆኑ ናቸው” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

ነገር ግን ከሁሉ በላይ የአእምሮ ጤናውን የጎዳው ሰዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ አሊያም የገዛ አካላቸውን ሲጎዱ የሚያሳዩ ምስሎችን ሲመለከት ነው።

“ዓይኖቼን ስጨፍን ቲኬቱን አየዋለሁ” ይላል።

ቲኬት ማለት የይዘት ተቆጣጣሪዎች ለአንድ የፌስቡክ ልጥፍ የሚሰጡት ስያሜ ነው።

ኬንያ የሚገኙ የፌስቡክ ይዘት ተቆጣጣሪዎች አብዛኞቹ ወጣት ሴት እና ወንዶች ከኢትዮጵያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሩዋንዳ፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች የአህጉሪቱ አገራት የመጡ ናቸው።

የይዘት ተቆጣጣሪዎቹ በአስር ቋንቋዎች ፌስቡክ ላይ የሚለጠፉ አሰቃቂ እና አስከፊ የሚባሉ ይዘቶችን ይቆጣጠራሉ።

የሚያሰራቸው ተቋም ሳማ ይባላል። መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ አድርጎ በኬንያ ቀጣናዊ ቢሮ ያለው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ድርጅት ነው።

ራሱን በፈረንጆቹ ጥቅምት 2021 ሜታ ሲል የሰየመው ፌስቡክ አፍሪካ ውስጥ ላለው የይዘት ቁጥጥር ይህን ድርጅት ቢቀጥርም እርምጃው ገንዘብ ከመቆጠብ አንፃር ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።

ስክሪን ፊት የተቀመተ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንዲት ሠራተኛ ከተቀጠረች በኋላ ሥልጠና ሲሰጣት ካየቻቸው መካከል በማኅበራዊ ሚዲያው መድረክ ላይ ከኢትዮጵያ የተለጠፈን አንድ ይዘትን አትዘነጋውም።

“አስታውሳለሁ ሁሉም የሚጀምረው ከሥልጠና ነው። ሥልጠናው ላይ ሰዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ እንድንመለከት እንደረጋለን። እነዚህን ሰዎች አልረሳቸውም። መቼም ቢሆን የምረሳው አይመስለኝም” ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ደግሞ በጣም ብዙ አሰቃቂ ምስሎች እናያለን። ሰዎች በሕይወት እያሉ ሲቃጠሉ፣ የጅምላ ግድያ እና የተለያዩ ጥቃቶች እናያለን።”

“አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ሲቀሰቀሱ እና ሲጋጋሉ እናያለን። ሁሉም ነገር ተመዝግቦ ይቀመጣል። እዚህ ቁጭ ብለን ጦርነቱን ያየን ያህል ነው። ምንም የሚያመልጠን ነገር የለም” ትላለች።

ቢቢሲ ያናገራቸው የድርጅቱ ሠራተኞች ምሬት እና የደቡብ አፍሪካ ዜጋ የሆነው የድርጅቱን ምስጢር ያሾለከው ዳንዔል ሞታውንግ ያቀረበው ክስ ተመሳሳይነት አላቸው።

ደቡብ አፍሪካዊው ዳንዔል ሳማ የተሰኘውን ድርጅት ኬንያ ውስጥ ፍርድ ቤት አቁሞታል።

“መጀመሪያ ለሳማ መሥራት ስጀምር እኔ እና የሥራ አጋሮቼ ሰዎች ሲታረዱ፣ ሕፃናት ሲደፈሩ፣ ሲገደሉ አሊያም ጥቃት ሲደርስባቸው የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ቪድዮዎችን እናያለን ብዬ አልጠበቅኩም ነበር” ይላል ዳንዔል።

“ፎቶዎቹ አስከፊ መሆናቸው ሳያንስ ሰዎች ሲቀሉ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ተመልክቻለሁ” ሲል ለችሎቱ እንደተናገረ የፍርድ ቤት መዛግብት ያሳያሉ።

ዳንዔል “ያለአግባብ ከሥራ ተባርሪያለሁ” ከሚል ክስ አንስቶ እሱ እና የሥራ ባልደረቦቹ “የሕይወት ዘመን የአእምሮ ጉዳት ደርሶብናል” የሚል ክስ ነው ያቀረበው።

እሱ እንደሚለው በሥራው አማካይ የጭንቀት ተጠቂ እንደሆነ አልፎም ፒቲኤስዲ የተሰኘው የአእምሮ በሽታ እንዳጋጠመው ተናግሮ ሕይወቴ ተበላሽቷል ይላል።

“እንዴት አድርጌ ወደ ተሻለ ሕይወት መመለስ እንዳለብኝ አላውቅም።”

የሜታ እና የሳማ ጠበቃዎች የዳንዔል ክስ ውድቅ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ በዳንዔል ክስ ላይ ውሳኔ እስካሁን አልሰጠም።

በፈረንጆቹ 2020 አሜሪካዊያን የይዘት ተቆጣጣሪዎች ፌስቡክ ለአእምሮ ጤና መረበሽ ዳርጎናል ሲሉ ከሰው ድርጅቱ 52 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል መወሰኑ አይዘነጋም።

ኬንያ የሚገኘው የፌስቡክ አጋር የሆነው ሳማ ሠራተኛ ለቢቢሲ እንደምትናገረው ድርጅቱ “የአእምሮ ጤና ጥበቃ” የሚል ፕሮግራም ቢኖረውም ከሚደርስባቸው ጫና አንፃር በቂ አይደለም።

“በየቀኑ ነው መሰል ይዘት የምናየው። ቤት ስንገባ የምንረሳው ጉዳይ አይደለም። ትዝ ይለናል። በሕልማችን ይመጣል። ስለዓለም ያለን አተያይ ይቀየራል። ምክንያቱም ሥራ ላይ ቀኑን ሙሉ የምናየው መጥፎ ነገር ነው” ትላለች።

ቢቢሲ ይህን ቅሬታ በተለመከተ ከሜታ አስተያየት ቢጠይቅም “በሳሙዔል ክስ ምክንያት” አስተያየት መስጠት አንችልም የሚል ምላሽ ነው ያገኘው።

ሳማ በበኩሉ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ፌስቡክ እና ሳማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ነገር ግን ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ ታይም የተሰኘው የአሜሪካ መጽሔት ተመሳሳይ ቅሬታ ያላቸውን ሠራተኞች አስመልክቶ ለሠራው ዘገባ “ሐሰት እና አሳሳች” የሚል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

በወቅቱ ሳማ አክሎም “ለሠራተኞቼ የአእምሮ ጤና በጥልቀት አስባለሁ” የሚል ዘገባ ምላሽ አስነብቦ ነበር።

“በመጀመሪያ ሠራተኞች በሳምንት ከ37.4 ሰዓት በላይ እንዲሠሩ አንፈቅድም። በተጨማሪ ሠራተኞቻችን የአእምሮ ጤናቸው እንዲጠበቅ በማሰብ በቀን የአንድ ሰዓት ተኩል የጤና እና የምግብ እረፍት እንዲወስዱ እናደርጋለን። በሦስተኛ ደረጃ ሳምንቱን ሙሉ ቀንና ሌሊት ሠራተኞች በፈለጉ ጊዜ የምክር አገልግሎት እንሰጣለን” ሲል ሳማ በድረ-ገፁ ላይ ባወጣው ማስተባበያ አስታውቋል።

ዳንዔል በፍርድ ቤት መዝገቡ ላይ ምንም እንኳ የይዘት ቁጥጥር ለሜታ አስፈላጊ ቢሆንም ሥራውን ለሌላ ድርጅት አኮናትሯል ሲል ይከሳል።

ይህን ያደረገውም “በርካሽ ዋጋ የሰው ኃይል ለመሸመትና የሥነ አእምሮ ድጋፍ ዋጋን ለማስቀረት ነው” በማለት ይወቅሳል።

የዳንዔል ጠበቃዎች ኬንያ ካለው ቢሮ ተቀጥረው የሚሠሩ 240 ባለሙያዎች በደቡብ እና ምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የይዘት ቁጥጥር ሥራ ለመሥራት በቂ አይደሉም ይላሉ።

አልፎም በኬንያ ብቻ 10 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ያሰምራሉ።

“ገበያው ላይ ያሉትን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ደኅንነት እና የይዘት ተቆጣጣሪዎችን ጤና ለመጠበቅ ተጨማሪ ሠራተኞች መቀጠር አለባቸው” ይላሉ ጠበቃዎቹ።

ቢቢሲ ካናገራቸው የድርጅቱ ሠራተኞች መካከል አንዱ “የጤና ጥበቃ ፕሮግራም” ተብሎ የሚሰጠው መርሐ ግብር ምስጢር የማይጠበቅበት ነው ሲል ይኮንናል።

“ስላየኸው የፌስቡክ መልዕክት እና ስለተሰማህ ነገር ይጠይቁሃል። ለአማካሪህ የነገርከውን ነገር ከሥል ባልደረባህ መልሰህ ትሰመዋለህ” ይላል።

ቢቢሲ ያናገራቸው የሳማ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ክፍያ እጅግ አነስተኛ እንደሆነም ጨምረው ይናገራሉ።

“ሥራው አካላዊ ድካም እና አእምሯዊ ተፅዕኖ አለው። የሚከፈለን ክፍያ በፍፁም ከሥራው ጋር የሚመጣጠን አይደለም። ሁሉም ሰው በልቶ ስለማደር ይጨነቃል።”

ሳማ በድረ-ገፁ በሰጠው ምላሽ ሠራተኞቹ ተገቢውን ክፍያ እያገኙ አይደለም የሚባለው ሐሰት ነው ሲል ያስተባብላል።

“የይዘት ቁጥጥር ከበድ ያለ ሥራ ከመሆኑ አንፃር ከዝቅተኛው ክፍያ ሦስት እጥፍ፤ ከኬንያ አማካይ ክፍያ ሁለት እጥፍ የሆነ ገንዘብ እንከፍላለን” ይላል።

ሳማ የተሰኘው ድርጅት ከሜታ ጋር ያለው የሥራ ኮንትራክት በቅርቡ እንደሚያበቃ ታውቋል።

በምትኩ ማጆሬል የተሰኘ ድርጅት የይዘት ቁጥጥር ሥራውን እንደሚረከብ የተሰማ ሲሆን፣ ድርጅቱ ከሳማ በግማሽ ያነሰ ክፍያ የሚከፍል ነው።

የኬንያ ፍርድ ቤት በዳንዔል ሞታውንግ ጉዳይ ቀጣይ ቀጠሮ ለጥር 29/2015 ዓ.ም. ሰጥቷል።